የቀኝ ጽንፈኞች እንቅስቃሴ በጀርመን  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 25.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

 የቀኝ ጽንፈኞች እንቅስቃሴ በጀርመን 

በሉብከ ግድያ ተጠርጥሮ የተያዘው ሽቴፋን ኢ ለመርማሪዎች አዲስ ሰው አይደለም። ተጠርጣሪው ባለሥልጣናት ለዓመታት በቀኝ ጽንፈኛነት የሚያውቁት ግለሰብ ነው።በጎርጎሮሳዊው 1980 ዎቹ መጨረሻ ላይ ነው በቀኝ ጽንፈኝነት መንቀሳቀስ የጀመረው።የዛሬ 26 ዓመት ሄሰን በሚገኝ አንድ የተገን ጠያቂዎች መጠለያ ላይ የቦምብ ጥቃት አድርሶ ነበር።

በጀርመኑ በሄሰን ፌደራዊ ክፍለ ሀገር ውስጥ የሚገኘው ካስል የተባለው ከተማ ዋና አስተዳዳሪ ቫልተር ሉብከ የዛሬ 23 ቀን ነበር በቤታቸው የአትክልት ስፍራ በቅርብ ርቀት ተተኩሶባቸው ተገድለው የተገኙት።የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር CDU ፖለቲከኛ የ64 ዓመቱ ሉብከ የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የስደት ፖሊስ ደጋፊ ነበሩ።ሉብከ በተገደሉ በሁለተኛው ሳምንት አቃቤ ህግ በግድያው የጠረጠረውን ሽቴፋን ኢ የተባለ ግለሰብ መያዙን ካሳወቀ በኋላ በጀርመን የቀኝ ጽንፈኞች እንቅስቃሴ እያነጋገረ ነው።ተጠርጣሪው ጀርመን ውስጥ ከሚካሄዱ የቀኝ ጽንፈኞች እንቅስቃሴዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ተነግሯል።ጥርጣሪው እውነት ከሆነ ሉብከ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በቀኝ ጽንፈኛ የተገደሉ የመጀመሪያ ፖለቲከኛ ነው የሚሆኑት።የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኽርስት ዜሆፈር ግድያውን ለጀርመን ማንቂያ ጥሪ ሲሉ ገልጸው የቀን ክንፍ ጽንፈኝነት ህብረተሰቡ ትኩረት የሚሰጠው እና ከፍተኛ አደጋ መሆኑን ተናግረዋል።የCDU ሊቀመንበር አነግሬት ክራምፕ ካረንባወር ለሉብከ ግድያ ተጠያቂው አማራጭ ለጀርመን የተባለው ፓርቲ ድርጊት ነው ሲሉ ፓርቲውን ኮንነዋል። በክራምፕ ካረንባወር አባባል ግድያው በጀርመንኛው ምህጻር AFD ተብሎ የሚጠራው የዚህ ፓርቲ የጥላቻ እና አንዱን በአንዱ ላይ የማነሳሻ ንግግሮች ውጤት ነው።የጀርመን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግራዎቹ አረንጓዴዎቹ እና የነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲዎች፣ በጉዳዩ ላይ የፓርላማው የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚቴ ልዩ ስብሰባ እንዲካሂድ ጥሪ አቅርበዋል።በግድያው ላይ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምርመራ እያካሄደ ነው።ጌኦርግ ማስኮሎ ARD፣NDR፣WDR እና ዙድ ዶቸ ሳይቱንግ የተባሉት የጀርመን ትላላቅ የመገናኛ ዘዴዎች በጋራ የሚያካሂዷቸው የምርመራ ሥራዎች ሃላፊ ናቸው።በርሳቸው አስተያየት በግድያው ላይ የሚያካሄደው ምርመራ ከተጠርጣሪው ጥፋት በተጨማሪ ቀኝ ክንፍ ጽንፈኞች ከግድያው በስተጀርባ አሉ የሉም የሚለውን ጥያቄም ማጣራት ይኖርበታል።ከዚሁ ጋርም አንድምታው  በሪፐብሊኩ ላይ ሊፈጸም የሚችል ጥቃትን ያካትት አያካትም ሊመረመር ይገባል ያላሉ።የፖለቲከኛው ግድያም የአፍቃሪ ናዚዎች እንቅስቃሴ ምን ያህል እየተጠናከረ መሄዱን ያሳያልም ብለዋል።   

«ይህ ሁኔታው ምን ያህል በግልጽ ጽንፍ እንደያዘ የሚያሳይ ማስረጃ ነው እላለሁ።ለዚህም ብዙ ማሳያዎች አሉ።አደጋዎች እየጨመሩ ነው።በዓምደ መረብ የሚሰነዘሩ ዛቻዎች ተበራክተዋል።በኢንተርኔት የሚሰራጭ ጥላቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው።የቀኞች የኃይል ጥቃት እንዲሁ ጨምሯል።የፌደራል አቃቤ ህግ ጥርጣሬም ከጀርመን የቀኝ ክንፍ እንቅስቃሴ ጋር የተገናኘ ተጨማሪ ማስረጃ ነው»  
የምርመራ ጋዜጠኝነት የሚያካሂዱት ትላልቆቹ የጀርመን መገናና ብዙሀን ማህበር እንደዘገበው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የምስክሮችን ማስረጃዎች እየሰበሰበ ነው። በነዚህ ማስረጃዎች መሠረት አንዳንድ ወንጀለኞችም በግድያው እጅቸው አለበት።የጀርመኑ የግራዎቹ ፓርቲ የሀገር ውስጥ ፖሊሲ አዋቂ ማርቲና ሬነር እንደሚሉት ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በአፍቃሬ ናዚዎች የሚሰነዘሩ የግድያ ዛቻዎች እየጨመሩ ነው።እንደ ሬነር በህቡዕ ሲንቀሳቀስ በነበረው«ብሔራዊ ሶሻሊስት»በምህጻሩ NSU የተባለው ህዋስ ለ8 ዓመታት ጀርመን ውስጥ በ9 የውጭ ዜጎች እና በአንድ ፖሊስ ላይ የፈጸመው ግድያ ይፋ ከተደረገ በኋላ አደጋው ከመቀነስ ይልቅ ተባብሷል።ሬነር በቀኝ ጽንፈኝነት ላይ ማህበረሰቡም ሆነ ባለሥልጣናት የሰጡት ትኩረት አናሳ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።የግራዎቹ ፓርቲ ቃል አቀባይም በሆኑት በሬነር አስተያየት በሉብከ ግድያ «የአንድ ወንጀለኛ ተጠያቂነት ብቻ የሚያስኬድ አይሆንም።  
«አንድን ሰው ብቻ ወንጀለኛ የማድረጉ አስተሳሰብ ስህተት ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው።በተለይ ኹነቶቹን እና ጥቃቶቹን ጠለቅ ብለን ስንመለከት በጥቅምቱ ፌሽታ ወቅት የተፈጸመው

ግድያ፣በተከታታይ ለ10 ዓመታት በNSU የተፈጸሙ ግድያዎች፣በአፍቃሪ ናዚዎች ተኩሰው የሚፈጽሙት ግድያ የትም ይፈጸሙ የት ፣ሁሌም ከቀኝ ፖለቲካ መረብ ጋር የተገናኙ ናቸው።ሁልጊዜም የመሣሪያ ፣መረጃ የገንዘብ እና የመሳሰሉትን  ድጋፍ የሚሰጧቸው አሉ።ያም ሆኖ ባለሥልጣናት ስለነርሱ ሁል ጊዜ ይናገራሉ።በሉብከ ላይ የተፈጸመው ፖለቲካዊ ግድያ የተናጠልም ይሁን ጀርመን በተፈጸመ 9 የውጭ ዜጎች እና የአንድ ፖሊስ ግድያ ተጠያቂ የተባለው «ብሔራዊ ሶሻሊስት» በምህጻሩ NSU ጋር ግንኙነት ይኑረው የሚያሳስበው ነገር ጠቅላይ አቃቤ ህግ በግድያው የተሳተፈው ወገን ከሌሎች ጋር ግንኙነት የሌለው አንድ ህዋስ እንጂ ሰፊ መረብ አይደለም ማለቱ ነው። የኔ ፍርሃት የሉብከን ግድያ ጉዳይን በተመለከተም በአንድ ተጠርጣሪ ላይ ብቻ እንዳያተኩሩ ነው።የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አንድ ቡድን ብቻ እንጂ መረብ አይደለም ሲል ይከራከር ነበር።ይህ ደግሞ በርግጥ ተባባሪ ተጠርጣሪዎችን እና ከበስተጀርባ ያሉ ደጋፊዎችን ፍለጋውን እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል።» 
በሉብከ ግድያ ተጠርጥሮ የተያዘው ሽቴፋን ኢ ለመርማሪዎች አዲስ ሰው አይደለም። የጀርመን የህገ መንግሥት ጠባቂ እንደሚለው ተጠርጣሪው ባለሥልጣናት ለዓመታት በቀኝ ጽንፈኛነት የሚያውቁት ግለሰብ ነው።በጎርጎሮሳዊው 1980 ዎቹ መጨረሻ ላይ ነው በቀኝ ጽንፈኝነት መንቀሳቀስ የጀመረው።ሽቴፋን ኢ በጎርጎሮሳዊው 1993 የሀያ ዓመት ወጣት ሳለ በሄሰን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ውስጥ የሚገኝ አንድ የተገን ጠያቂዎች መጠለያ ላይ የቦምብ ጥቃት አድርሶ ነበር።ለዚህ ጥፋቱም ዋስ ሳይጠራ፣እንዳይንቀሳቀስ የሚገድብ ቅጣት ተጥሎበት ነበር።አሁን የ45 ዓመት

ጎልማሳ የሆነው ሽቴፋን ኢ በቅርቡ አካላዊ ጉዳት በመፈፀም፣በውጭ ዜጎች ጥላቻ ሰበብ ቤት በማቃጠል እና የጦር መሣሪያ ህግን በመጣስ ተቀጥቷል።እንደገናም «ኮምባት 18» በተባለው ነውጠኛ ቡድን እና በቀኝ ጽንፈኛው «የጀርመን ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ» በኩል ከቀኝ ጽንፈኞች ጋር ግንኙነት እንደነበረውም ተነግሯል።የአፍቃሪ ናዚዎች መረብ «ኮምባት 18»የትጥቅ ትግል እና ፕሮፓጋንዳ የሚያስተጋባ ቡድን ነው።የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዜሆፈር እንዳሉት ሽቴፋን ኢ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከባላስልጣናት ትኩረት ወጥቶ ነበር።ከዚያ ይልቅ ትኩረት የተሰጠው ሉብከ ከመገደላቸው በፊት ለስደተኞች በሚሰጡት ድጋፍ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የወረደባቸው ጠንካራ ጥቃት ነው።የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የጥላቻ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ የነበሩት የኢንተርኔት መድረኮች አስተናጋጆች ላሳዩት ወንጀለኛ ባህርይ ሊጠየቁ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።ብዙ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ኢንተርኔ በተለይም ማህበራዊ መገናና ዘዴዎች የቀኝ ጽንፈኞች መፈንጫ ሆነዋል።ጥላቻ፣እኩይ አስተሳሰብ ጽንፈኛ መፈክሮች እና የመሳሰሉት ቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን የሚከሰስባቸው ጉዳዮች ናቸው።የሄሰን ፌደራዊ ክፍለ ሀገር የፓርላማ አባል ሚሻኤል ብራንድ በቅርቡ በሰጡት ቃለ ምልልስ ለግድያው ተጠያቂዎቹ የፓርቲው አመራሮች ናቸው ብለዋል። 
«ይህ እንዲሆን ያደረገው፣በመጀመሪያ ደረጃ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተባባሰው በጥላቻ እና በጥላቻ ንግግር መሆኑ እውነት እንደሆነ በግልጽ ለመናገር እፈልጋለሁ።ይህም ደንበር

ከማይገድበው የሆከ እና ተባባሪዎቹ ጥላቻ አሁን ከሚፈጸመው ጥቃት እና ግድያ ጋር በቀጥታ ይገናኛል።ይህን ማየት የማይችል አይነ ስውር ነው።»
ብራንድ በቃለ ምልልሳቸው የጠቀሷቸው ሆከ «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ፖለቲከኛ ናቸው።መጤ ጠል የሆነውን የፓርቲያቸውን አቋም በተለያዩ አጋጣሚዎች በግልጽ በማራመድ ይታወቀቃሉ።ዮርግ ሞይተን እና አሌክሳንደር ጋውላንድ የተባሉ ሌሎች  የፓርቲው አመራሮች የሉብከ ግድያ እንዲጣራ እንዲሁም ወንጀለኞች እንዲቀጡ ቢጠይቁም ፓርቲያቸው ችግሩን በመባባስ የሚቀርብበትን ወቀሳ ማስቀረት አልቻሉም።በቀኝ አክራሪነት የሚከሰሱ ሰዎች ለድርጊታቸው በፍርድ ቤት እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡት የአማራጭ ለጀርመን ፓርቲ አመራሮችን ንግግር መሆኑን በየና የዴሞክራሲ እና የሲቪል ማህበረሰብ ጥናት ተቋም ሃላፊ ማትያስ ክዌንት ለዶቼቬለ ተናግረዋል። 
«ጥቃት የሚፈጽሙ ቀኝ ጽንፈኞች ፍርድ ቤት ቀርበው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ እና ታዋቂ ቀኝ ክንፎች ያሰሟቸውን ንግግሮች እየጠቀሱ የብዙሀኑን አመለካከት እንደሚተገብሩ የሚናገሩት በርግጠኝነት ስሜት መሆኑን እናውቃለን።ያ ማለት በነርሱ አስተሳሰብ የነርሱ እንቅስቃሴ ሌሎች ሰዎች የሚያስቡትን እና የህዝቦችንም ጥቅሞች ለማስጠበቅ የሚያካሂዱት ነው።ይህ ደግሞ «አማራጭ ለጀርመን» ጥቃት የሚፈጽሙ ወንጀለኞችን ተግባር ህጋዊ የማድረግ፣ምሥራቅ ጀርመን ያሉ የአፍቃሪ ናዚ ርዝራዦችን እንዲያንሰራሩ የሚያደርግ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እየታዘብን ነው።  
ፖለቲከኞች እና ተንታኞች ለሉብከ ግድያ የአማራጭ ለጀርመን ፖለቲከኞች የጥላቻ ንግግሮች እና መልዕክቶችን ተጠያቂ እያደረጉ ነው።ከሉብከ ግድያ በኋላ ስደተኞችን በመ,ርዳት የሚታወቁ አራት የተለያዩ የጀርመን ከተሞች ከንቲባዎች ከቀኝ አክራሪዎች የግድያ ዛቻዎች እንደደረሱዋቸው ተናግረዋል።ፖሊስ ግን ጉዳዩ ከሉብከ ግድያ ጋር መያያዝ አለመያያዙ ገና እየተጣራ ነው ብሏል። 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic