የሽግግር ሂደት ጥያቄ በኢትዮጵያ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 1 2016ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያድረገው የኢትዮጵያ ምሁራንና ባለሙያዎች መድረክ፣ ከኢትዮጵያ ምሁራን ኔትወርክ ጋር በመተባበር 13ኛ ጉባኤውን አካሄዷል። ጉባኤው ያተኮረባቸው ነጥቦች ምንድን ናቸው በሚል፣ዶይቸ ቨለ ጥያቄ ያቀረበላቸው የመድረኩ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ የሚከተለውን መልሰዋል።
"የፖለቲካ ባህልና የሽግግር ብለን ነው ያልነው። የፖለቲካ ባህላችን ይሆን ወይ ይህን ችግር የሚፈጥረው የሚል ሲሆን የሽግግር ፈተናዎች ሁሉጊዜም ያለ ነው።ብዙ ህዝብ እያለቀብን ነው።ረሃብ ነው፣የኢኮኖሚ ድቀት ነው ብዙ ችግሮች ነው ያሉት። በእኛ መድረክ ፣13 መሆኑ ነው እንግዲህ አንድ ሰባቱ በላይ ስብሰባዎች የተካሄዱት። እኤአ አቆጣጠር ከ2018 ማለትም አዲሱ መንግሥት ከመጣ በኋላ ነው፤ ከስድስት ዓመት በፊት ነው።ብዙ ጊዜ ሽግግሮችን እንደገና እንደገና ይነሳሉ።የምናገኛቸውም ዕድሎች እየተበላሸ፣ ከችግር ወደ ችግር እየሄደ ስለሆነ ይህንን ጉዳይ እንደገና ማጤን አለብን የሚል የሽግግር ጉዳዮች ያስፈልጋሉ የሚለውን ለማጥናት የተሞከረ ነው።"
ፕሮፌሰር ሚንጋ እንደሚሉት፣በጉባዔው ላይ ለኢትዮጵያ ይሆናሉ የተባሉ፣ ሦስት የሽግግር ሂደት አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት ተካሄዶባቸዋል።
ለውይይት የቀረቡ የሽግግር ሂደት ሰነዶች
ከእነዚህም መኻከል አንዱ፣በአቶ ልደቱ አያሌው አቅራቢነት ውይይት የተካሄደበት ሁሉን አቀፍ የሽግግር ሂደት ሰነድ ነው።
ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው፣በቅርቡ ሃገሪቱን ከጥፋት የሚታደግ ያሉትን የሽግግር ሠነድ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።
የአቶ ልደቱ አያሌው አዲሱ ሰነድና የኢትዮጵያ ፖለቲካ
ሌሎች በጉባዔው ላይ የተነሱና ሽግግር ላይ ያተኮሩ አጀንዳዎችን በተመለከተ፣ የመድረኩ ሊቀመንበር ያስረዳሉ።
"ዜጋ ተኮር የሽግግር ፕላን ነው የነበረው።እሱ ዳጎስ ያለ ጽሑፍ ብዙ ጊዜ ኮንሰፕት ላይ የሚደረግ ስለሆነ፣እሱን በቀላሉ ሕዝብ እንዲረዳው በዐማርኛ ቀርቧል።ከእዛም በሚቀጥለው ላይ፣ሴቭ ኢትዮጵያ በሚል የኢትዮጵያን የሽግግር ቢሆነኝ፣ እንዲሆን ቢሆን እንደዛ ቢሆን የሚል ዕቅድ ነው የሚያቀርበው፤ሠፊ ውይይት ጥያቄና መልስ ተደርጎበታል።"
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል
በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ባህል ችግር እንዳለበት ጉባዔው በጥልቀት እንደመከረበትም ከፕሮፌሰር ሚንጋ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ መዋቅራዊ መዛቦቶች እና መፍትሔያቸው
" የፖለቲካ ባህላችን ችግር እንዳለው፣በደንብ የተቀመጠ ጉዳይ ነው።በተለይ ይኼ ተምሬያለሁ የሚለው ህዝብ ከስልጣን ጋር ያለው ቁርኝት ምን እንደሆነ፣ሃገሪቱን ወደፊት ማራመድ አለመቻሉ፣ምን ያህል ለእዛም በአብዛኛው ያለው እንደውም እንግዳ ሆነው ተናጋሪዎች የነበሩት፣ይህንን ነገር የተመለከቱት፣ ከስነ ምግባር፣ከይሉኝታ ከኡቡንቱ አንፃር ነው የሄዱት እና የፐብሊክ ሰርቪስ ስሜት አለመኖሩ፣ውሸት መብዛቱ በብዙ ቦታ ላይ ነተግሯል።
ጉባዔተኞቹ፣በኢትዮጵያ የሽግግር ሂደት ብሔራዊ አጀንዳ መሆን አለበት የሚል መግባባት ላይ መድረሳቸውን የመድረኩ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል።
"በሁለተኛ ደረጃ ያለው ምንድነው የሽግግር ጊዜ ግድ ነው አሁን።"
በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ምስረታ ጉዳይ፣በመንግስት ተቀባይነት ያለው ዐሳብ አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አዲስ አበባ ውስጥ በቅርቡ በተካሄደው፣ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን መክፈቻ ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣"በኢትዮጵያ ከእንግዲህ የሽግግር መንግስት እንደማይኖር፣ሃገሪቱ ውስጥ የሚኖረው በምርጫ የተመረጠ መንግስት ብቻ ነው።"ማለታቸው አይዘገጋም።
ታሪኩ ኃይሉ
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ