የሽትራዉስ ካን የፍርድ ሒደትና ተስፋቸዉ | ዓለም | DW | 04.07.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሽትራዉስ ካን የፍርድ ሒደትና ተስፋቸዉ

የሽትራዉስ ካን ቀጠይ ቀጠሮ ግን ከሁለት ሳምንት በላይ ይቀረዋል።የፓርቲዉ መሪዎች እጩዉን ዘግይተን የማስመዝገብ መብት አለን እያሉ ነዉ።ሰዉዬዉ ላሁኑ አንሰራርተዋል።ግን ከወደቁበት መነሳት እንደለመዱት ሁሉ ከተነሱበት መዉደቅንም ማወቃቸዉ መዘንጋት የለበትም።

default

ሽትራዉስ ካን-ግንቦት


04 07 11

እንደ ሐብታም ልጅ ኤኮል ናስዮናል ደ አድምንስትራሲዮን ከተሰኘዉ ምርጥ ዩኒቨርስቲ እንደሚገባ ወላጅ-ዘመዶቹ አልጠረጠሩም ነበር።ግን የመግቢያ ፈተናዉን ወደቀ።ምኞቱ ተቀጨ ሲባል እንዳባቱ በሕግ፣ እንደራሱ በኢኮኖሚስ ዶክተር ሆነ።ዶመኒክ ጋስቶን አንድሬ ሽትራዉስ ካሕን።በ2006 (ዘመኑ በሙሉ እጎአ ነዉ) ለፓርቲያቸዉ እጩ ፕሬዝዳትነት ተፎካክረዉ ተሸነፉ።ፖለቲካ በቃቸዉ በቁት ሲባል የአለም ገንዘብ ድርጅት የበላይ ሆኑ።ፕሬዝዳት ይሆናሉ ነበር የፈረንሳዮች እምነት።ግንቦት ላይ በነነ።ሥልጣን፥ ክብር፣ ተስፋቸዉም አለቀቀ-ደቀቀ ሲያሰኝ ዳግም አንሠራሩ። አርብ። የአርቡ ዉሳኔ መነሻ፣ የክሱ ሒደት ማጣቀሻ የሰዉዬዉ ጉዞ መድረሻን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

«ከመገናኛ ዘዴ ባልደረቦች አንዳቻችሁ፥ ተበዳይዋ ዶሞኒክ ሽትራዉስ ካሕንን ለመጣል የተሸረበ ሴራ አካል እንደሆነች ተናግራችኋል።ይሕ እዉነት አይደለም።»

የከሳሽ ጠበቃ ኬን ቶምፕሰን።ሰኔ ስድስት።ኒዮርክ። የቶምፕሰንን የመከራከሪያ ሐሳብ፥ ቃል፥ መረጃ፥ የተረጠሩ፥ ያልተቀበሉም ነበሩ።አሉም።በተለይ ፈረንሳዮች።ሰዉዬዉም ወድቆ መነሳት እንግዳቸዉ አይደለም። የዚያን ቀን ግን፥ ስልሳ ሁለት ዘመን ከተዉጣጡበት የሥልጣን፥ ሥም ዝና ክብር ተራራ ባፍታ ተፈጠፈጡ።ግንቦት አሥራ አራት።ኒዮርክ።ቅዳሜ ነዉ።ትልቁን ሰዉዬ ያሳፈረችዉ ታክሲ የሰዉ-መኪናዉን የጥድፊያ ግር ግር ባሕርን እየቀዘፈች ትከንፋለች።መድረሻ ኬኒዲ አዉሮፕላን ጣቢያ።

ስምንት ሰዓት ተጋምሷል።የበረራ ቁጥር ሃያ ሰወስት የፈረንሳይ አዉሮፕላን ወደ ፓሪስ ሊበር ሁለት ሰዓት ግድም ነዉ ቀረዉ።ታክሲዋ ከአዉሮፕላን ጣቢያ ለመድረስ አርባ ደቂያ ያሕል ያሻታል። ያሳፈረችዉ ሰዉዬ ግን የአዉሮፕላን ቲኬት ሻጮች፥-«ከአዉሮፕላኑ መነሻ ቢያንስ ሁለት ሠዓት ቀደም ብለዉ አዉሮፕላን ጣቢያ ይድረሱ» የሚባሉ ዓይነት አይደሉም።ከበቂ በላይ ጊዜ አላቸዉ።ቢሆንም ታክሲዋ ትምዘገዘጋለች።

የትልቁ ድርጅት ትልቅ ሐላፊ ያዉ እንደ ትልቅ ሰዉ ወግ ረጋ ደርበብ እንዳሉ ነዉ።የሚያስቡትን መገመት አይገድ ይሆናል፥ ማወቅ ግን በርግጥ አይቻልም። ከሁለት ሰዓት በፊት ከለቀቁት ትልቅ ሆቴል አድርገዉት ከሆነ ያደረጉትን ትንሽ ነገር በርግጥ ሊዘነጉት አይችሉም።እንደ አባት ከዉድ ልጃቸዉ፥ እንደ የወደፊት አማች ከዉድ ልጃቸዉ ዉድ ፍቅረኛ ጋር ያደረጉትን ጭዉዉት፣ እንደ ቱጃር ከዉድ ልጃቸዉ ጋር የተመገቡትን ዉድ ምሳ በሚያሰላስሉበት፥ ወይም እንደ ትልቅ ባለሥልጣን ከበርሊን-ፓሪስ ብራስልስ ትላልቆች ጋር የሚያደርጉትን ዉይይት በሚያዉጠነጥኑበት በዚያ ቅፅበት-የቅፅበት የትንሾች ምግባራቸዉን ማስታወሳቸዉ ግን አጠራጣሪ ነዉ።

ትንሽ የሚያረጋቸዉን ትንሽ ነገር ቀርቶ፥ ያን ትልቅ ሆቴል ማስታወሳቸዉን መገመት ይጠናል። ብቻ ዉድ የእጅ ቦርሳቸዉን ከፈቱት።ከብዙ ተንቀሳቃሽ ሥልኮቻቸዉ መሐል ትልቁ መስሪያ ቤታቸዉ የሰጣቸዉን አጡት።ብዙ ሚስጥ አለዉ።ደነገጡ።በሌላኛዉ ሥልካቸዉ ልጃቸዉ ጋ ደዉለዉ ምሳ ከበሉበት ምግቤት እንድትፈልገዉ ጠየቋት።

Freilassung von Dominique Strauss-Kahn in New York

ሽትራዉስ ካንና ባለቤታቸዉ- ባለፈዉ አርብ


ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ታክሲዋ አዉሮፕላን ጣቢያ ደረሰች።ስልኩ ግን አልተገኘም።ያኔ ትልቅ ሆቴላቸዉን አስታወሱ።ሆቴሉን ከለቀቁ ሁለት ሰዓት ተኩል ደፈነ።ሆቴሉን በጣሙን ላንድ አዳር ሰወስት ሺሕ ዶላር የከፈሉበትን ቁጥር 2806 ምቹ ክፍልን ምናልባትም እዚያ ክፍል ዉስጥ ከዚያች ጊኒያዊት የሠላሳ ሁለት አመት አልጋ አንጣፊ ጋር---ሁሉንም ሳያስቡት አልቀሩም።እዚያ ምቹ ክፍል ያደረጉ፥ የተናገሩ፥ ያለፉ-ያገደሙበት እየተብጠለጠለ፥ ትልቅ ስም ማዕረጋቸዉ እየወደቀ እንደሚነሳ የሚያዉቁበት ፍንጭ-ምክንያትም የለም።

ብቻ በጠፋ-ሥልካቸዉ ሰበብ ሆቴሉን አስታወሱት።ደወሉም።ትልቁ ሰዉዬ ያሉትን የሰማዉ የመርማሪዎች አለቃ ሥልኩን ላነሳዉ አስተናጋጅ ሹክ አለዉ። «ስልኩን እንዳገኘን አዉሮፕላን ጣቢያዉ ድርስ እንልክልዎታለን ጌታዬ።» አለ አስተናጋጁ-።በል የተባለዉን።

ሰአታቸዉን አዩ።ዘጠኝ ሠዓት ከአርባ።ሥልኩን ያቀብልዎታል የተባለዉ የሆቴል ሠራተኛ የለም። እንደገና ደወሉ።እንደገና ጠየቁ።«መንገድ ላይ ነዉ።»አስር-ሰዓት ከዜሮ ሰወስት።ለሰወስተኛ ጊዜ ደወሉ። አዲስ መልስ አላገኙም።አይናቸዉን ግን ወደ አዉሮፕላኑ ከሚያስገባዉ ቁጥር አራት በር እንደተከሉ ነዉ።አስር ሠዓት ከአርባ።ሁለት ሰዎች ወደ እሳቸዉ ሲጠጉ አዩ።
«ብዙ እናወራለን።ደግሞም እንጣደፋለን።»

አሉ የፈረንሳዩ የግብርና ሚንስትር ብሩኖ ሊ ማሪ በቀደም።ጥድፊያ ሩጪ በበዛበት ዓለም ያዉም ኒዮርክ የማይጣደፍ ማግኘት በርግጥ ሲበዛ ከባድ ነዉ።የዚያን ቀን አዉሮፕላኑ መነሳት ነበረበት።ግን አልተጣደፈም።የትልቅ መንገደኛዉን ትልቅ ጉዳይ ትቶ መነሳት አይችልም።እሳቸዉ ስልካቸዉ፥ ሁለቱ ሰዎች ደግሞ እሳቸዉ ለማግኘት ተጣድፈዋል።«ሥልኬን አመጣችሁልኝ።» ጠየቁ-ሰዉዬዉ-ሰዎቹን።

ሁለቱ የኒዮርክና የኒዉ ጀርሲ ፖሊስ መርማሪዎች ናቸዉ።ለሰዉዬዉ ጥያቄ ብዙም አልተጨነቁም። «ሚስተር ዶመኒክ ሽትራዉስ ካሕን ነዎት» ጠየቀ ከመርማሪዎቹ አንዱ።

«አዎ» መለሱ ሰዉዬዉ።«ክሱ እዉነት ይሆናል ብዬ አስቤ አላዉቅም።ምን ጊዜም ቢሆን ጥፋተኛ አንዳልሆኑ አምን ነበር።ለፕሬዝዳትነት መወዳደር ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።»


አሉ አንዱ ፈረንሳዊ ባለፈዉ አርብ።የዚያን ቀን ተራዉን ፈረንሳዊ አይደለም እሳቸዉንም ለመስማት የታገሰ የለም።እጃቸዉ ተጠፍሮ እስር ቤት ተወረወሩ።ሥልጣን፥ ማዕረግ፥ ክብር፥ዝናቸዉ ሁሉ ተደረመሰ።ባለፈዉ አርብ ግን ስድስት ሳምንት የነበረዉ ሁሉ እንዳልነበር ሆነ።እርግጥ ነዉ ሽትራዉስ ካሕን አስገድደዉ ደፍረዉኛል በማለት የከሰሰችዉ ጊኒያዊት ስደተኛ ጠበቃ ኬን ቶምፕሰን አርብም ሴትዮዋ ተገድዳ ተደፍራለች እንዳሉ ነዉ።

«ዶሞኒክ ሽትራዉስ ካሕን ያላቸዉ መከላከያ የወሲብ ግንኙነቱ በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነዉ የሚል ነዉ።ይሕ ዉሸት ነዉ።የሕክምና ማስረጃዉ፥የአሸራ ማስረጃዉ በሙሉ የተበዳይዋን አቤቱታ የሚደግፍ ነዉ።»

እስከ አርብ እንጂ አርብ ጠበቃዉን ያመናቸዉ የለም ወይም ካለ ጥቂት ነዉ።የሰላሳ ሁለት አመትዋ የአልጋ ክፍል ሠራተኛ ከአደዛዥ እፅ ነጋዴዎች ጋር ግንኙነት አላት፥ የስደተኝነት ማመልከቻዋ የተጭበረበረ ነዉ፥ ወይም ትክክለኛ የመኖሪያ ፍቃድም የላትም የሚለዉን የተከላካይ ጠበቆች መረጃ ፍርድ ቤቱ አርብ ተቀበለዉ።

ሽትራዉስ ካሕን ከተመሰረተባቸዉ ክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ አልወጡም።ግን ከቁም እስረኝነት ተለቀዋል።ለዋስትና ያስያዙት አንድ ሚሊዮን ዶላርና የአምስት ሚሊዮን የአክስዮን ሠነድ ተለቆላቸዋል።የሽትራዉስ ከሐን ጠበቆች መሪ ቤንጃሚን ብራፍማን በሚቀጥለዉ ቀጠሮ ክሱ በሙሉ መሠረዝ አለበት ባይ ናቸዉ።

«ባለፉት ስድስት ሳምንታት በነበረዉ በያንዳዱ የችሎት ሒደት በዚሕ ጉዳይ ላይ ከድምዳሜ ለመድረስ እንዳትጣደፉ እናንተንም አለምንም መጠየቃችንን ላስታዉስ እወዳለሁ።አሁን ቢያንስ ያን ለምን እንዳልን ትገነዘባላችሁ።ጉዳዩ እንደሚመስለዉ እንዳልሆነ ገና ከመጀመሪያዉ ጀምረን አምነን ነበር።እና የዛሬዉ ዉሳኔ ወደ በትክክለኛዉ አቅጣጫ አንድ ትልቅ እርምጃ ሲሆን፥ ቀጣዩ እርምጃ ክሱ ባጠቃላይ የሚሰረዝበት እንደሚሆን ፍፅም እናምናለን።»

ጠበቃ ብራፍማን የጥድፊያ ድምዳሜዉ እንዲቀር የመከሩት ለተጋለቢጦሹም እዉነት ነዉ።ከሳሽዋ የአደንዛዥ ዕፅ፥ የመኖሪያ ፍቃድ ወዘተ ችግር እንዳለባት ገና ከመነገሩ አንዳድ መገናኛ ዘዴዎች በሴተኛ አዳሪነት እንደምትሠራም እየዘገቡ ነዉ።ተከሳሹም በስምምነት አሉት እንጂ ከሴትዋ ጋር አንሶላ መጋፈፋቸዉን ወይም በትዳራቸዉ ላይ መማገጣቸዉን አልካዱም።

ደጋፊዎቻቸዉ ግን ከመጣደፍ አልታቀቡም።አንዳዶቹ እንደሚሉት ከክሱ ነፃ ይሁኑ እንጂ ተስማምተዉ ያደረጉት ነገር ለፕሬዝዳትነት ከመወዳደር፥ ፕሬዝዳት ከመሆንም የሚያግዳቸዉ የለም።ሽትራዉስ ካሕን ከፈለጉና ከተሰካላቸዉ የሚወክሉት የሶሻሊስቱ ፓርቲ ተቀናቃኝ የወግ አጥባቂዉ ፓርቲ አባልና የቀድሞዉ የፈረንሳይ ሚንስትርና ዤን ሊዊስ ቦርሎ እንኳን ሌላ አቋም የላቸዉም።«በቂ ጉልበት እና ፍላጎት ካለዉ በፈረንሳይ የዉስጥ ፖለቲካ እንዳይሳተፍ የሚያግደዉ ምን አለ? ሽትራዉስ ካሕን አለቀለት እያሉ እንደዚያ መናገር፥ መግለጣቸዉ በጣም ነዉ የሚገርመኝ።እስካሁን የለቀቀዉ ከዓለም ገንዘብ ድርጅት ሐላፊነቱ ነዉ።እኔ እስከማዉቀዉ ድረስ የሶሻሊስቱ ፓርቲ አባልነቱን አልቀቀም።»

ፈረንሳይ ከአስራ-አንድ ወራት በሕዋላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ታስተናግዳለች።ሽትራዉስ ካሕን እራሳቸዉን በእጩነት ለማቅረብ ከፈለጉ የሶሻሊስቱ ፓርቲ ከፍተኛ መሪዎች እንደማይቀናቀኗቸዉ አስታዉቀዋል። ይሁንና በሐገሪቱ የምርጫ ሕግ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለፕሬዝዳትነት የሚወዳደሩ እጩዎቻቸዉን እስከ መጪዉ ሐምሌ አስራ-ሰወስት ድረስ ማስመዝገብ አለባቸዉ።

የሽትራዉስ ካን ቀጠይ ቀጠሮ ግን ከሁለት ሳምንት በላይ ይቀረዋል።የፓርቲዉ መሪዎች እጩዉን ዘግይተን የማስመዝገብ መብት አለን እያሉ ነዉ።ሰዉዬዉ ላሁኑ አንሰራርተዋል።ግን ከወደቁበት መነሳት እንደለመዱት ሁሉ ከተነሱበት መዉደቅንም ማወቃቸዉ መዘንጋት የለበትም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ


Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች