የሽታይንማየር የኢትዮጵያ ጉብኝት ፋይዳ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 29.01.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የሽታይንማየር የኢትዮጵያ ጉብኝት ፋይዳ

ሽታይንማየር እንደተናገሩት ጀርመን የኢትዮጵያን ለውጥ ለመደገፍ ከፍተኛ ፍላጎት አላት። ብዙ ዓመታት ያስቆጠረው የጀርመን እና የኢትዮጵያ ግንኙነትም በአሁኑ ጊዜ ከቀድሞው ከፍ ወዳለ ደረጃ ተሸጋግሯል። እንደ ሽታይንማየር ትኩረቱን በልማት አጋርነት ላይ አድርጎ የቆየው የጀርመን እገዛ  አሁን ለውጡን ወደ መደገፍ ትብብር አድጓል።

የሽታይንማየር የኢትዮጵያ ጉብኝት ፋይዳ

የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የኢትዮጵያ ጉብኝት ዛሬም እንደቀጠለ ነው። ትናንት ከኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጋር በኢትዮጵያ እንዲሁም በጀርመን ግንኙነቶች እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተወያዩትት ሽታይንማየር የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለውጡን ወደ መደገፍ ትብብር ከፍ ማለቱን አስታውቀዋል። ጀርመን እና ኢትዮጵያ ከ110 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው። የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአጼ ሚኒልክ ዘመነ መንግሥት በጎርጎሮሳዊው 1906 ዓም ነው የተጀመረው ከዚያን ጊዜ አንስቶም ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች ግንኙነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። ወደ ኋላ መለስ ብለን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ስንመለከት በተለይ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በጎርጎሮሳዊው 1954 የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክን በመጎብኘት የመጀመሪያው መሪ መሆናቸው በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ታሪክ ትልቁን ስፍራ ይይዛል። በወቅቱ ጦርነት ላደቀቃት ጀርመን ያበረከቱት እርዳታም እንዲሁ የኢትዮጵያ ባለውለታነት ምስክር ሆኗል። ከዚያን ወዲህ በርካታ የጀርመን መሪዎች ኢትዮጵያን በተለያዩ ጊዜያት ጎብኝተዋል። ከመካከላቸው ፕሬዝዳንት ሀይንሪሽ ሉብከ በ1964 ሮማን ሄርዞግ በ1996 ኽርስት ኮለር በ2004 እንዲሁም ዮአሂም ጋውክ በ2013 በኢትዮጵያ ያካሄዷቸው ጉብኝቶች ይጠቀሳሉ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም ኢትዮጵያን በ2007 እና በ2016 ጎብኝተዋል። ካለፈው እሁድ አንስቶም የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር

በኢትዮጵያ ይፋ ጉብኝት እያካሄዱ ነው። ሽታይንማየር ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከዛሬ 4 ዓመት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅትም ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። የአሁኑ ከያኔው የሚለየው ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ላይ መሆኗ ነው። ለውጡ በልዩ ልዩ ፈተናዎች ውስጥ እንደሚገኝ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ላይ ሽታይንማየር ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ልዩ ትርጉም ተሰጥቶታል።  ወደ ኢትዮጵያ ከመሄዳቸው በፊት ሽታይንማየር ከዶቼቬለ የአማርኛው ክፍል ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያን አሁን መጎብኘታቸው ትክክለኛው ጊዜ  መሆኑን ተናግረው ነበር። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም፥   

« ፕሬዝደንት ሳሕለ ወርቅ ዘዉዴና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ሐገሪቱን እንድጎበኝ ሲጠይቁኝ ግብዣዉን ሳላመነታ የተቀበልኩትም ለዚሕ ነዉ። ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገዉን የለዉጥ ሒደት ከሩቅ ሆኖ ክብር መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ እኛ አዉሮጳውያንና ጀርመናዊያን፣ እዚያዉ ስፍራዉ ተገኝተን የዴሞክራሲያዊውን የለዉጥ ጉዞ ማበረታት ይገባናል ብዬ አምናለሁ። ለዚሕም ነዉ ኢትዮጵያን የምጎበኝበት ትክክለኛዉ ጊዜ አሁን ነዉ የምለዉ።»

የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም የፕሬዝዳንት ሽታይንማየር የኢትዮጵያ ጉብኝት በትክክለኛው ጊዜ የተካሄደ መሆኑን ትናንት ከርሳቸው ጋር በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከተነጋገሩ በኋላ  በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልጸው ነበር።

«ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን በጣም ወቅታዊም ነው። ምክንያቱም በኛ እምነት አንድ ሀገር ሁሉንተናዊ ለውጥ እያካሄደች ያለችበት ጊዜ ሀገሪቱን የመጎብኛው ትክክለኛው ጊዜ ነው። ፕሬዝዳንቱ እዚህ መገኘታቸው የአስተሳሰብ ለውጥ መኖሩን ያሳያል ይበልጥ የተጠናከረ ግንኙነት እንዲኖር በስፍራው መገኘት ያስፈልጋል። ሁሉም ነገር እስኪመቻች መጠበቅ የለበትም።»

ዶክተር ፀጋዮ ደግነህ በግዙፉ የጀርመን መኪና አምራች ኩባንያ ሜርሰዲስ ቤንዝ በፕሮጀክት አስተዳደር የሰሩ በአሁኑ ጊዜም በዚሁ ኩባንያ በብዝሀነት አስተዳደር ዘርፍ በመስራት ላይ የሚገኙ የምጣኔ ሀብት ምሁር ናቸው። በርሳቸው አስተያየት የሽታይንማየር የአሁኑ የኢትዮጵያ ጉብኝት ምክንያት ከብዙ አቅጣጫዎች ሊታይ የሚችል ነው።

ሽታይንማየር ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ እንደተናገሩት ጀርመን የኢትዮጵያን ለውጥ ለመደገፍ ከፍተኛ ፍላጎት አላት። ብዙ ዓመታት ያስቆጠረው የጀርመን እና የኢትዮጵያ ግንኙነትም እርሳቸው እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ ከቀድሞው ከፍ ወዳለ ደረጃ ተሸጋግሯል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንዳስረዱት እስካሁን ትኩረቱን በልማት አጋርነት ላይ አድርጎ የቆየው የጀርመን እገዛ አሁን ለውጡን ወደ መደገፍ ትብብር አድጓል።

«ዛሬ ከኢትዮጵያ ጋር የለውጥ ትብብር ነው የምናደርገው። ኢትዮጵያ ለውጡን ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማ ከሆነች፣ህዝቡም በለውጡ ከተስማማ በፍጥነትም ባይሆን ወደ ተረጋጋ እና የተሻለ የምጣኔ ሀብት ደረጃ ሊወስዳት ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ከድንበሯ ባሻገር ተጽእኖ የምታደርግ ሀገር ልትሆን ትችላለች። በምሥራቅ አፍሪቃ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባሻገር አርአያ ትሆናለች።ይህ ደግሞ አሁን ያለንን ግንኙነት ወደ በከፍተኛ ደረጃ ያድሰዋል። ለዚህም ነው በአዲሱ የኢትዮጵያ እና የፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክ ግንኙነት በፖለቲካው መስክም መዋዕለ ንዋይ የምናፈሰው።»

ሽታይንማየር በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅትም ሆነ ከዚያ በፊት በሰጡት መግለጫ አድናቆት ከቸሯቸው ጉዳዮች ውስጥ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር እርቅ ማውረድዋ እና በካቢኔዋም ለሴቶች እኩል ውክልና መስጠትዋ ይገኙበታል ።የኢትዮጵያን ለውጥ ለመደገፍ የጀርመንን ዝግጁነት የገለጹት ሽታይንማየር ወደ ኢትዮጵያ የሄዱት የግዙፍ የጀርመን ኩባንያዎችን የሥራ ሃላፊዎች አስከትለው ነው። ከመካከላቸው ትልቁ የመኪና አምራች የፎልክስቫገን ኩባንያ እና የዚመንስ የስራ ሃላፊዎች ይገኙበታል። በትናንትናው እለትም የፎክስቫገን ኩባንያ ከኢትዮጵያ ኢንቬስትመንት

ኮሚሽን ኮሚሽነር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። ይኽው ስምምነት ኩባንያው በኢትዮጵያ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለማቋቋም የሚያስችለው እንደሆነም ተነግሯል። ስምምነቱ ሌሎች የጀርመን ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ይረዳል ተብሏል። የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ ከሆነ ለኢትዮጵያ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ይላሉ ዶክተር ፀጋዬ። በርሳቸው እምነት ጀርመን ኢትዮጵያን ይበልጥ ልታግዝ የምትችልባቸው ሌሎች መስኮችም አሉ።

ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር ያላትን ግንኙነት በኢንቬስትመንት እና በሌሎችም መስኮች ለማጠናከር ትፈልጋለች። ጀርመን ፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑ የህግ ባለሞያ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ጀርመን በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ዘርፍም ለኢትዮጵያ ልታደርግ የምትችለው እገዛ ሊኖር እንደሚገባ ያሳስባሉ። በዚህ ረገድ በተለይ በኢትዮጵያ ትክክለኛ እና ፍትሀዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ድጋፎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ።

 ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር የተወያዩት ሽታይንማየር ለውጡን ወደ መደገፍ ትብብር ከፍ ብሏል ያሉትን የኢትዮጵያ እና የጀርመን ግንኙነት፣ ይበልጥ ለማጠናከር  እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።   

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ 

Audios and videos on the topic