የሽብር ጥቃት ዛቻን ተከትሎ የ«ፔጊዳ» ሠልፍ ተሰረዘ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 18.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የሽብር ጥቃት ዛቻን ተከትሎ የ«ፔጊዳ» ሠልፍ ተሰረዘ

ከጀርመን ከተሞች፤ እንደ ድሬስድን እስልምና እንዳይስፋፋ የሚታገል ከተማ የለም። ባለፉት የሰኞ ሳምንታት ድሬስድን ውስጥ እስልምና እንዳይስፋፋ የሚታገሉ የፔጊዳ ደጋፊዎች ድሬስድን ከተማ ሰልፍ ሲወጡ ሰንብተዋል። የነገው ሰልፍ ግን የሽብር ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል በሚል ፍራቻ ፖሊስ በከተማዋ ማንኛውም አይነት የአደባባይ ሠልፍ እንዳይደረግ አገደ።

ከጀርመን የፌዴራል እና የክፍለ ሃገር ባለሥልጣናት በተገኘው መረጃ መሠረት የሽብር ጥቃቱ ሊደርስ ይችላል የተባለው በተለይ «ፔጊዳ» በተሰኘው ቡድን ላይ ነው። የሽብር ጥቃቱን በተለይ «ፔጊዳ» አመራሮችን በመግደል ለመፈፀም አቅዷል የተባለው እራሱን «እስላማዊ መንግሥት» እያለ የሚጠራው ቡድን መሆኑም ተጠቅሷል። «በምዕራባውያን ሃገራት እስልምና እንዳይስፋፋ የሚታገሉ የአዉሮፓ አርበኞች» በምኅፃሩ «ፔጊዳ» በማለት እራሱን የሚጠራው ቡድን በነገው እለት ድሬስደን ውስጥ ሰፊ የተቃውሞ ሠልፍ ለማከናወን አቅዶ ነበር። ቡድኑ ቀደም ሲል በጠራው የተቃውሞ ሠልፍ 18 ሺህ በላይ ደጋፊዎቹ አደባባይ መውጣታቸው ይታወሳል። «ፔጊዳ» እስልምና በምዕራቡ ሃገራት እንዳይስፋፋ ከሚያደርገው ዘመቻ በተጨማሪ፥ ስደተኞችን የሚመለከተው ሕግም እጅግ ጠበቅ ያለ እንዲሆን የሚሟገት ቡድን መሆኑ ይታወቃል። «ፔጊዳ» ለነገ ባቀደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ 25,000 ሰዎች ሊሳተፉ ይችሉ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ