የሽብር ጥቃት በቱርኩ | ዓለም | DW | 29.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሽብር ጥቃት በቱርኩ

ጥቃት አንድራሾቹ በታክሲ ወደስፍራዉ ከተጓዙ በኋላ ሲነቃባቸዉ ራሳቸዉን ማንጎዳቸዉን የቱርክ ባለስልጣናት ይናገራሉ። ማንነታቸዉን ለማጣራትም የስለላ ካሜራዎች ያነሷቸዉን ፊልሞች ከመመርመር አንስቶ እማኞችን እየጠየቁ ነዉ።

ቱርክ ትናንት ማምሻዉን በኢስታምቡል አዉሮፕላን ማረፊያ ለደረሰዉ ጥቃት እራሱን የሶርያ እና ኢራቅ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራዉን ቡድን ተጠያቂ አደረገች። በትናንቱ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት የሞቱት ቁጥር 41 መድረሱን እና የተጎዱትም 239 መሆናቸዉን የከተማዋ ገዢ ቫሲፕ ሳህኒ አመልክተዋል። ከሟቾቹ መካከልም 13ቱ የሳዉድ አረቢያ፣ የኢራቅ እና ቱኒዚያን ጨምሮ የሌሎች የዉጪ ሃገራት ዜጎች መሆናቸዉ ተገልጿል። ጥቃቱ የደረሰዉ ትናንት ማምሻዉን በሶስት አጥፍቶ ጠፊዎች መሆኑ ቢገለጽም እስካሁን ለድርጊቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢናሊ ይልዲሪም ግን የፀጥታ ኃይላቸዉ የሚጠረጥረዉ አካል አለ ይላሉ።
«የፀጥታ ኃይሎቻችን ይህን የሽብር ጥቃት እራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ አካል እንደፈጸመዉ ይገምታሉ።»
ጥቃት አንድራሾቹ በታክሲ ወደስፍራዉ ከተጓዙ በኋላ ሲነቃባቸዉ ራሳቸዉን ማንጎዳቸዉን የቱርክ ባለስልጣናት ይናገራሉ። ማንነታቸዉን ለማጣራትም የስለላ ካሜራዎች ያነሷቸዉን ፊልሞች ከመመርመር አንስቶ እማኞችን እየጠየቁ ነዉ። በአካባቢዉ ትልቅ መሆኑ የሚነገርለት የኢስታንቡል «አታ-ቱርክ» አዉሮፕላን ማረፊያ ከጥቃቱ በኋላ ለበርካታ ሰዓታት ተዘግቶ ቢቆይም ዛሬ ንጋት ላይ ዳግም አዉሮፕላኖች ማረፍ እንደጀመሩ ዘገባዎች ያመለክታሉ። በደረሰዉ ተከታታይ ፍንዳታ እና ከፖሊስ ጋር በተካሄደዉ የተኩስ ልዉዉጥም የአዉሮፕላን ማረፊያዉ ሕንፃ ከዉጭም ከዉስጥም መጎዳቱ ተገልጿል። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በጥቃቱ ለተጎዱት ሐዘናቸዉን ገልጸዋል።
«ለሞቱት ቤተ ሰቦች እና ለተጎዱት ጥልቅ ሐዘኔን እገልጻለሁ፤ ለመላዉ የቱርክ ሕዝብም ሽብርተኝነትን በመዋጋቱ በኩል አንድ እንደሆንን እና እንደምንደጋገፍም መግለጽ እፈልጋለሁ።»
በዛሬዉ ዕለት ቱርክ ብሔራዊ ሀዘን አዉጃለች።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ