የሻኪሶ ነዋሪዎች ቁጣ ውጥረት ፈጥሯል | ኢትዮጵያ | DW | 01.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የሻኪሶ ነዋሪዎች ቁጣ ውጥረት ፈጥሯል

የሼክ መሐመድ አል-አሙዲ ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኩባንያ ወርቅ ከሚያመርትበት የማዕድን ማውጫ አቅራቢያ በምትገኘው ሻኪሶ ውጥረት ነግሷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ኩባንያው በለገደንቢ ወርቅ እንዲያመርት የሰጠው ፈቃድ መታደስ ቁጣ መቀስቀሱን የከተማዋ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:10

የሚድሮክ ኩባንያ ፈቃድ መታደስ በሻኪሶ ቁጣ ቀስቅሷል

ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ በሚወስደው መንገድ በምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ የምትገኘው የጊንጪ ከተማ ሚያዝያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ተቃውሞ አገርሽቶባታል። የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ የአይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በተቃውሞው የተሳተፉት አብዛኞቹ ተማሪዎች ናቸው። በጊንጪ የሚኖሩት ግለሰብ ተሳታፊዎቹ "ተቃውሞ እያሰሙ ከትምህርት ቤቱ አንስቶ እስከ ቴክኒክ እና ሙያ አካባቢ ድረስ ሰልፍ ወጥተው ነበር። ከ500 በላይ ይሆናሉ" ሲሉ የታዘቡትን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ስሜ አይጠቀስ ያሉት የከተማዋ ነዋሪ ምክንያቱ "ይኸ መንግሥት ይውረድ ነው። ጠቅላይ ምኒስትር ቢቀየርም ምንም የተለወጠ ነገር የለም። አዲስ ነገር አላየንም" ሲሉ አክለው ገልጸዋል። 

"ስሜቱ መጨረሻ ላይ ጥሩ አልነበረም። አጋጣሚ የኦሮሚያ ፖሊሶች አብረው ነበሩ። መጨረሻ ላይ የመከላከያ ወታደሮች መጡ። እነዛ ሲመጡ ትንሽ ግርግር ነገር ተፈጥሮ ነበር። ከዛም በተኗቸው። የታሰረ የለም" ያሉት የጊንጪው ነዋሪ የጸጥታ ኃይሎች ለተቃውሞ የወጡትን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መጠቀማቸውን ገልጸዋል። 

ትዊተር እና ፌስቡክን በመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጩ መረጃዎች የጊንጪው ሰልፍ የተደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚድሮክ ኩባንያ የሰጠውን የሥራ ፈቃድ በድጋሚ ማደሱን በመቃወም እንደሆነ አትተዋል። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ከና ደሜ በግል የትዊተር ገፁ "የሚድሮክ ፈቃድ በድጋሚ በመታደሱ ምክንያት ከአምቦ 25 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው ጊንጪ እንደገና ተቃውሞ ተቀሰቀሰ" የሚል መረጃ አስፍሯል።

ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ንብረትነቱ የሼክ መሐመድ አል-አሙዲ የሆነው ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ወርቅ ከሚያመርትበት ለገደምቢ አቅራቢያ የምትገኘው ሻኪሶ ውጥረት ነግሶባታል። የሚድሮክ ፈቃድን መታደስ "ሰው እየተቃወመ ነው ያለው" ይላሉ አንዲት የሻኪሶ ነዋሪ። የከተማዋ ነዋሪዎች በአደባባይ ሰልፍ ተቃውሟቸውን ለማሰማት ጠይቀው መከልከላቸውን የተናገሩ እኚሁ የአይን እማኝ በዛሬው ዕለት የጸጥታ አስከባሪዎች በብዛት በከተማዋ መታየታቸውንም አስረድተዋል። "ወታደሮች ከተማዋን ሞልተዋታል። ውጥረቱ ትንሽ ጨምሯል። እስካሁን ሰልፍ አልተወጣም። በከተማዋ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ግን ሰልፍ አለ" ሲሉም አክለዋል። 

ሌላ የሻኪሶ ነዋሪ ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ የጸጥታ ኃይሎች በከተማዋ ጥበቃ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ለሚድሮክ ኩባንያ የተሰጠው የወርቅ ማምረት ፈቃድ እንዳይታደስ ሲጠይቁ ረዥም ጊዜ እንዳስቆጠሩ የሚናገሩት ነዋሪው ከመንግሥት አጥጋቢ ምላሽ አለመገኘቱን አስረድተዋል።

የሼክ መሐመድ አል-አሙዲ ኩባንያ የሆነው ሚድሮክ ከኢትዮጵያ መንግሥት በገዛው የለገደምቢ ወርቅ ማምረቻ አሰራር ላይ ጥያቄ መነሳት ከጀመረ አስራ አንድ አመታት በላይ እንዳለፈ ጋዜጠኛ እና የፊልም ባለሙያው ይድነቃቸው ጋሻው ይናገራል። ይድነቃቸው ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል የጉጂ ዞን ውስጥ በምትገኘው ሻኪሶ ነው። ይድነቃቸው በአብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ለኩባንያው የተሰጠው የሥራ ፈቃድ ይታደሳል የሚል ግምት እንዳልነበር ይናገራል። በጋዜጠኛው እምነት መንግሥት ለአቤቱታቸው መፍትሔ ሳይበጅ ለተጨማሪ አስር አመታት ፈቃድ ማደሱ ነዋሪዎቹን ለቁጣ ዳርጓቸዋል።

"አሁን ውሉ ሲያልቅ መንግሥት ወይ የሚድሮክ ኢትዮጵያን አሰራር ይቀይረዋል። አለበለዚያ ደግሞ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ራሱ ተፈጥሮ ላይ የደረሱትን ጉዳቶች እንዲያስተካክል የራሱ አዲስ አሰራር ሊያቀርብ ይችላል። ወይም ደግሞ ሙሉ በሙሉ ኩባንያው ወጥቶ የማኅበረሰቡን የጤና ጉዳዮች የሚጠብቅ አዲስ ኩባንያ ይገባል ተብሎ ነበር ሲጠበቅ የነበረው" የሚለው ይድነቃቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ከኩባንያው ጋር በጉዳዩ ላይ በተደጋጋሚ ውይይቶች አድርገው ለውጥ ይጠብቁ እንደነበር አስረድተዋል። ጋዜጠኛው "በድብቅ እንደዚህ ሰው ሳያውቅ ሰውን ሳያማክሩ ነው ይኸ ፊርማ ተፈረመ የተባለው። ለሌላ 10 አመት አራዝመውላቸዋል" መባሉ በሕዝቡ ዘንድ ብስጭት ሳይፈጥር እንዳልቀረም አስረድቷል። 

የሚድሮክ ኢትዮጵያ ድረ-ገጽ እንደሚጠቁመው የመንግሥት ንብረት የነበረው ለገደንቢ ወርቅ ኢንተርፕራይዝ ለሼክ መሐመድ አል-አሙዲ ኩባንያ ከተሸጠ 21 አመታት ተቆጥረዋል። ኩባንያው የወርቅ ማምረት ሥራውን የጀመረው በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 1998 ዓ.ም. መሆኑንም ይኸው ድረ-ገጽ ያትታል። እንደ ድረ-ገፁ ሐተታ ከሆነ የለገደምቢ ወርቅ ማምረቻ ከኢትዮጵያ ግዙፉ ሲሆን በአመት 4.5 ቶን ወርቅ ይመረትበታል። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከዚህ ተፈጥሯዊ ሐብት የሚገባቸውን ጥቅም አላገኙም። የወርቅ ማምረቻው በሚጠቀመው ኪሚካል ሳቢያም በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ሲሉ ይከሳሉ።

"የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት ያስባል። ኩባንያው ለአካባቢው ማኅበረሰብ የተለያዩ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ይገነባል ተብሎ ይጠበቅም ነበር" የሚሉት የሻኪሶ ነዋሪ የሆነው ሁሉ ከተጠበቀው ተቃራኒ ሆኖባቸዋል። "የወንዞች በኬሚካል የመበከል ነገር አለ። አካል ጉዳተኛ የሆኑ ልጆች ይወለዳሉ። እንስሳትም ጭምር አካል ጉዳተኛ ሆነው የመወለድ ነገር አለ" ሲሉ የተፈጠረውን ያስረዳሉ። 

በአካባቢው በሚገኘው የማዕድን ሐብት ስሟ የሚነሳው የሻኪሶ ከተማ በዕድሜዋ አሮጌ ብትሆንም እጅግ እንደተጎሳቆለች ዛሬ ላይ መድረሷን ይድነቃቸው በቁጭት ይናገራል።ይድነቃቸው  "እስካሁን ድረስ አስፓልት እና ንፁሕ የመጠጥ ውሐ እንኳን የሌላት በጣም የምታሳዝን ከተማ" የሚላት ሻኪሶ "በቢሊዮን ዶላሮች" እንደሚታፈስባት ይናገራል።  እንደ ጋዜጠኛው ከሆነ በከተማው ኩባንያው ጭምር የሚገለገልበት መንገድ ተጀምሮ አልተጠናቀቀም። የአካባቢው አስተዳደርም የነዋሪውን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚችልበት ተሰሚነት አጥቷል።

ሚድሮክ ወርቅ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርም ሆነ ሚድሮክ ኢትዮጵያ በሚቀርቡባቸው ወቀሳዎች ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ያደረግንው ሙከራ አልተሳካም። ኩባንያው ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት "ለሻኪሶ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ት/ቤት፣ለገደምቢ ሻኪሶ ቴክኒክና ሙያ ተቋም፣የወረዳው የፍትህ ቢሮና፣የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት" እርዳታ ማድረጉን የሚጠቁም መረጃ በድረ-ገፁ ሰፍሯል።  

ሚድሮክ ለወርቅ ማምረቻ የተሰጠው ፈቃድ መታደሱን የሚገልፅ ደብዳቤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየተዘዋወረ ይገኛል። በቀድሞው የኢትዮጵያ የማዕድን፣ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ምኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ተፈርሞ የወጣ የተባለው ደብዳቤ ለኩባንያው ፈቃዱ መታደሱን የሚገልጽ ቢሆንም ዶይቼ ቬለ እውነተኛነቱን ማረጋገጥ አይችልም። የሚድሮክ ፈቃድ መታደሱ በግልባጭ የተነገረው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የውኃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቡሌ አበጋዝ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት የሚችለው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።  የኢትዮጵያ የማዕድን፣ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ በበኩላቸው ጉዞ ላይ በመሆናቸው በጉዳዩ ላይ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም ትምህርት ቤቶች ተዘግተው፤ ነዋሪው ሰልፍ ወጥቶ በኩባንያው ላይ የቀረቡ ጥያቄዎች በአካባቢው የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት እና የፌድራል ፖሊስ በወሰዷቸው እርምጃዎች መቆማቸውን ይድነቃቸው ያስታውሳል። ጥያቄው ዘላቂ መፍትሔ ካላገኘ በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ሳቢያ ወደ ከፋ ግጭት እንዳያመራ ያሰጋዋል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

 

 

 

Audios and videos on the topic