የሻርም ኤልሼኩ የአውሮጳ እና የአረብ ሊግ ጉባኤ | ዓለም | DW | 25.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሻርም ኤልሼኩ የአውሮጳ እና የአረብ ሊግ ጉባኤ

የአውሮጳ ኅብረት እና የአረብ ሊግ መሪዎች በቅርበት ተባብረው ለመሥራት ቃል ገቡ። የሁለቱ ማኅበራት አባል ሃገራት መሪዎች በባህር ዳርቻዋ የመዝናኛ ስፍራ በሻርም ኤልሼክ ግብጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄዴት ጉባኤ ፍጻሜ ባወጡት የጋራ መግለጫ በተለያዩ ዘርፎች ትብብር የሚያደርጉበት አዲስ ዘመን መጀመሩን ዛሬ ዐስታውቀዋል።

የአውሮጳ ኅብረት እና የአረብ ሊግ መሪዎች በቅርበት ተባብረው ለመሥራት ቃል ገቡ። የሁለቱ ማኅበራት አባል ሃገራት መሪዎች በባህር ዳርቻዋ የመዝናኛ ስፍራ በሻርም ኤልሼክ ግብጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄዴት ጉባኤ ፍጻሜ ባወጡት የጋራ መግለጫ በተለያዩ ዘርፎች ትብብር የሚያደርጉበት አዲስ ዘመን መጀመሩን ዛሬ ዐስታውቀዋል። ሁለቱ ወገኖች ወደፊት ቋሚ ጉባኤዎችን ለማካሄድም ተስማምተዋል። በዚሁ መሠረት ቀጣዩን ጉባኤያቸውን ከሦስት ዓመት በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2022 በቤልጂየም ብራሰልስ እንደሚያካሂዱ የጉባኤው አስተናጋጅ የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲስ ዛሬ በጉባኤው መዝጊያ ላይ ባሰሙት ንግግር ዐስታውቀዋል።

አልሲሲ በዚሁ ንግግራቸው ጉባኤው ያልተግባባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም የሚደነቅ ነው ብለዋል። በሁለት ቀናቱ ጉባኤ ላይ የተገኙት የጀርመን መራኂተ- መንግሥት አንጌላ ሜርክል የአረብ ሃገራት መሪዎች የሶሪያን የፖለቲካ ለውጥ ሂደት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል። ሁሉም ሶሪያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያስችላል ያሉት በሶሪያ አዲስ ሕገ-መንግሥት የማርቀቅ ሒደት እንዲፋጠን ግፊት እንዲያደርጉ እና የሶሪያን የወደፊት የፖለቲካ እጣ ፈንታ የሚያመላክት ሁሉን አካታች ምክክር እንዲጀመር እንዲጥሩም ጠይቀዋል። ከዚህ ሌላ ለሁለቱ ማኃበራት የጋራ ጥቅሞች ሲባል ዘርፈ ብዙ ትብብር ያሻልም ብለዋል።  «የአውሮጳ ኅብረት ህልውና በነዚህ የአረብ ሊግ አባል ሀገራት ህልውና ላይ የተመሰረተ ነው። ለዚህም ከፍልሰት፣ ከአውሮፕላን በረራ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ተሞክሮ አለን። እናም ለዚህ ነው ምንም እንኳን በጣም የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም (ጉባኤው) ዘርፈ ብዙ ትብብሮችን ማዳበር ዋነኛው ተልዕኮ የሆነው።» ፍልሰት፣ በአረብ ሃገራት የሚታየው አለመረጋጋት ፀጥታ እና ንግድ የሁለት ቀናቱ የአውሮጳ ህብረት እና የአረብ ሊግ ጉባኤ ያተኮረባቸው ጉዳዮች ነበሩ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ