የሺናሻ የዘመን መለወጫ ″ጋሪ ዎሮ″ | ባህል | DW | 06.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የሺናሻ የዘመን መለወጫ "ጋሪ ዎሮ"

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚከበሩት ዓመታዊ በዓላት መካከል የሺናሻ ዘመን መለወጫ በዓል "ጋሪ ዎሮ" አንዱ ነው፡፡ በዓሉ በየዓመቱ በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ይከበራል፡፡ በዓሉን ለመታደም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ተሰባስበው በሀገር ሽማግለዎች ተመርቀው የተጣላ ታርቆ በአንድነት የሚያከበር በዓል ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:08

"ጋሪ ዎሮ" ለሺናሻ ማኅበረሰብ አዲስ ዓመት እሁድ ብሎ ይጀምራል


በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚከበሩት ዓመታዊ በዓላት መካከል የሺናሻ ዘመን መለወጫ በዓል "ጋሪ ዎሮ" አንዱ ነው፡፡ በዓሉ በየዓመቱ በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ይከበራል፡፡ በዓሉን ለመታደም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ተሰባስበው በሀገር ሽማግለዎች ተመርቀው የተጣላ ታርቆ በአንድነት የሚያከበር በዓል ነው፡፡ ለአዲሱ ዓመት እንኳን በሰላም አደረሰን” “አዲስ ዘመን የሰላምና የፍቅር ዘመን ይሁንለችችሁ እያሉ ይመርቃሉ፡፡"ጋሪ ዎሮ" በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው በዓል ሲሆን የዕርቅና የአንድነት በዓል በመባልም ይታወቃል፡፡

 ስፔናዊ ጸሐፊ ጆሀን ጉንዛለዝ ኑኔዝ ጋሪ ዎሮን የሺናሻ ባህላዊ የዕርቅ ሲል« ኖርዝ ኦፍ ዘ ብሉ ናይል» በሚል መጸሐፉ መዝግቦታል፡፡ 
በበዓሉ ዕለት የተለያዩ ማህበረሰቡ የሚገልጹ ባህላዊ ምግቦች ይቀርባሉ፡፡ እንደ ጹምባ ያሉ ባህላዊ ምግቦች ይዘወተራሉ፡፡ ዘንድሮም የጋሪ ዎሮ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን በአሶሳ ከተማ  የጋሪ ዎሮ በዓል ሲያከብሮ ያነጋገርናቸውን አቶ ለማ አልጋ እንደሚሉት በዓሉን ለማክበር የሚሳተፉ ሰዎች በዓሉ ከመድረሱ በፊት የተጣሉ ታርቀው፣ አልያም ደግሞ በበዓሉ ዕለት በብሔረሰቡ ወግ መሰረት ታርቀው ዕለቱን ያሳልፋሉ፡፡ በሺናሻ ማህበረሰብ ባህል ላይ ጥናት ያደረጉ የብሔረሰቦች ተወላጆች መረጃ መሰረት በዓሉ በተለያዩ ወረዳዎች ለሁለት ወር ያህል በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፤ መስከረም 17 እና 18 ደግሞ የዓመቱ በ"ጋሪ ጀባ"  ወይም ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት  በአደባባይ  በኅብረት የሚከበር ነው፡፡ አቶ አበበ አኖ  በኡስማኒያ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት የሦስተኛ ዲግሪአቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡  በሺናሻ ማህበረሰብ ባህል፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያ ሁኔታ ላይም ጥናት  አድርጓል፡፡ ጋሪ ዎሮን አስመልክቶም የበዓሉ አከባበር ለረጅም ዘመናት በተለያዩ አካባዎች  ሲከበር መቆየቱን እና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ  በዓሉን  በክልል ደረጃ እያከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የበዓሉ መከበር በቀጣይም ባህሉን ለማስተዋወቅ በሚደረገው ጥረት ምሁራንና የተለያየ የህበረሰተብ ክፍሎች የሚገናኙበት  ዕለት  በመሆኑ የብሔረሰቡን ባህል ጠብቆ ለማቆየትና ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡  ጋሪ ዎሮ ሲከበር በሁሉም የዕድሜ ክፍል ያሉ የብሔረሰቡ አባላቶች ይሳተፋሉ፡፡

በዕለቱ አዳዲስ  ለምግብነት የደረሱ የእህል ዓይነቶች በሙሉ በዚሁ በአንድነት በሚከበረው ቦታ ቀርበው በአባቶች ተመርቆ እንዲቀመሱ ተደርጎና የዘመን መለወጫ ምርቃቶች ተካሂደው ሁሉም የብሄረሰቡ አባላት ያለምንም ልዩነት በድምቀት ያከብሩታል፡፡ የበዓሉ  ይዘት ላይ ያተኮሩ ሶስት ዓይነት ዘፈኖች ይዘፈናሉ ይላሉ አቶ አበበ፡፡  ዘፈኖቹም ከሐምሌ ወር መጨረሻ  ጀምሮ እስከ በዓሉ ዋዜማ እንዲሁም  ከበዓሉ ዋዜማ  ጀምሮ እስከ በዓሉ ዕለት እና ከዓሉ በኋላ እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ ከወቅቶቹ ጋር የሚሄድ ባህላዊ ጭፈራን ያካተተ  ነው፡፡  "ጋሪ ዎሮ" ሲከበር በሀገር ሽማግለዎች ተመርቀው በተመረጠው  ስፍራ ብቻ በየዓመቱ ይከበራል ይላሉ የሺናሻ ህዝብ ታሪክ የሚል መጽሐፍ ደራሲ  የሆኑት አቶ አዲሱ አዳሜ፡፡  በበዓሉ ላይም  መስከረም 17 የደመራ  ሥነ- ሰርዓት የሚከናነወን ሲሆን ለመስቀል በዓል ከሚደረገው ደመራ የተለየ ነው ይላሉ አቶ አዲሱ፡፡ "ጋሪ ዎሮ"  በየዓመቱ በመስከረም ወር ሲከበር ከማንኛውም ሃይማኖት  ጋር የማይገናኝ እና የብሐረሰቡ ተወላጆች  በሚገኙበት አካባቢ ሁሉ ራሱን ችሎ የሚከበር መሆኑን አጥኝዎቹ ይናገራሉ፡፡ በብሔረሰቡ በአጠቃላይ ሁለት አይነት የበዓሉ አከባበር ያለው ሲሆን የመጀመሪያው መላ ማህበረሰቡ፣ በአንድ ላይ በመሰባሰብ በተመረጠው የ“ጋ-ሮ” ቦታ የሚከበር አከባበር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከበዓሉ በኋላም እስከ ሁለት ሳምንት በሚዘልቅ ጊዜ የብሔረሰቡ አባላት ዘመድ አዝማዳቸዉን በመጥራት በየቤታቸዉ በመሆን በድግስ የሚያከብሩት ክብረ በዓል ነው፡፡ 
የሺናሻ የዘመን መለወጫ በዓል ጋሪ ዎሮ ዘንድሮ በክልል ደረጃ ከመስከረም 16 ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ዝግቶች በአሶሳ ከተማ ተክብሯል፡፡ "ጋሪ ዎሮ" ለሺናሻ ማህበረሰብ አዲስ ዓመት እሁድ ብሎ የሚጀምርበት ዕለት ነው፡፡ ሙሉ ጥንቅርሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ። 

ነጋሳ ደሳለኝ 
አዜብ ታደሰ
 
 

Audios and videos on the topic