የሶጁ ዉጤት፤ ከስድድብ ወደ ድርድር | ዓለም | DW | 19.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሶጁ ዉጤት፤ ከስድድብ ወደ ድርድር

«ገበታ ከተነሳ በኋላ ወይኑ ጎረፈ።ሶጁ የተባለዉ የሰሜን ኮሪያ አልኮል መጠጥ ተደጋጋመ።» የነበሩ እንዳወሩት፤ ወጣቱ  መሪም  ፈገግታ ጨመሩ።አሉም «ሚሳዬን በተኮስን ቁጥር ሙን (የደቡብ ኮሪያዉ ፕሬዝደንት) የፀጥታ ምክር ቤታቸዉን ለመሰብሰብ በጠዋት ከእንቅልፋቸዉ ለመነሳት እየተገደዱ ነበር።»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:02

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት እና የሰሜን ኮርያ ግንኙነት

ኑኬሌር እንደ ታጠቀ  ጦር ኃይል ጠቅላይ አዛዦች ለመጠፋፋት ተዛዛቱ፤የዘመኑን ምርጥ ጦር መሳሪያ የታጠቀ ጦራቸዉን ሰሜን-ደቡብ አፋጠጡ።ዓለምን ግራ ቀኛ ለማሰለፍ አራወጡ። እንደ ግል ጠበኛ ባልተገሩ ቃላት ተሰዳደቡ። አስራ-አራት ወራቸዉ። የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት እና የሰሜን ኮሪያ መሪ። የመዛዛት፤ መፋጠጥ፤ መሰዳደባቸዉ ንረት ዓለምን በስጋት ቋያ ሲለበለብ እጅ ለእጅ ለመጨባበጥ ተስማሙ። ሠላም ለማታዉቀዉ ዓለም ሠላም ያወርዱ ይሆን?

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን የካቲት 21 1972 ቻይናን ለመጎብኘት ከያኔዋ ፔኪንግ ሲገቡ የአሜሪካ የጡት ልጅ የሚባሉትን የሶል እና የቶኪዮ መሪዎችንም፤ የሞስኮ ኮሚኒስቶችንም እኩል አስደንግጦ ነበር።

የለንደን፤ፓሪስ፤ ቦን ካፒታሊስቶችን ጉድ  ሲያሰኝ፤ኒክሰን በ1952 የፕሬዝደንት ድዋይት ዴቪድ አይዘንአወር ምክትል ፕሬዝደንት ሆነዉ የተመረጡት ኮሚንዝምን ለማጥፋት በመማል መገዘታቸዉ እንደነበር ባልዘነጉ አሜሪካዉያን ዘንድ ደግሞ «ቃል አባይ» እያሉ ዘለፉ፤ አወገዟቸዉም።

ኒክሰን ማኦ ዜዱንግን ቤጂንግ ድረስ ሔደዉ ማነጋገራቸዉ ግን ዩናይትድ ስቴትስ የዓለምን ልዕለ ኃይልነት ሥፍራ ጠቅልላ እንዳትይዝ እንቅፋት የሆነችባት የሞስኮን እና የቤጂንግን ዉስጣዊ ሽኩቻ ለማጋጋም ጠቅሟቸዋል።25 ዓመታት በራቸዉን ዘግተዉ እሩቅ-ለሩቅ የሚዋጉትን የቻይና እና የዩናይትድ ስቴትስን ጠብ ለማርገብ፤ የአሜሪካኖችን ጠላቶች ቁጥር ለመቀነስ ረድቷቸዋል።

እራሳቸዉ ኒክሰን እንዳሉት ደግሞ ጉብኝታቸዉ ለዓለም ሠላም ደሕንነት እጅግ ጠቃሚ ነበር።

                                      

«ባለፉት ሰወስት ዓመታት በተለያዩ ጊያዚያት እንዳስታቅሁት፤ የሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ እና 750 ሚሊዮን ሕዝቧ ካልተካፈሉበት፤  የተረጋጋ እና ዘላቂ ሠላም በዓለም ሊኖር አይችልም።ለዚሕም ነዉ በሁለቱ ሐገሮቻችን መካከል መደበኛ ግንኙነት ለመጀመር በየመስኩ የተለያዩ ጥረቶችን የጀመርኩት።»

ምዕራብ አዉሮጶች በጦር ኃይል የማይችሉ ወይም የሚፈሯቸዉን ኮሚንስቶችን በድርድርም፤ በምልጃ-በግብዣም እያባበሉ ማዳከምን እንደ ሥልት መከተል የጀመሩት ከኒክሰን-ማኦ ንግግር  በኋላ ነዉ ባዮች አሉ።

አንዳድ የፖለቲካ ተንታኞች የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ቪሊ ብራንድት ከ1963 ጀምሮ ሲያመነቱ የነበረዉን «የምሥራቅ መርሕ» Ostpolitik በግልፅ ገቢራዊ ማድረጋቸዉ፤ የሬጋን ጥሪ፤ የታቸር ጎርቫቾቭ ወዳጅነት፤ የሔልሙት ኮል የዉሕደት መርሕ ከኒክሰን የቤጂንግ ጉብኝት የተወለዱ እስከማለትም ይደርሳሉ።

የኒክሰን መልዕክት፤ የተቃዋሚዎቻቸዉ ወቀሳ፤ የተንታኞቹ አስተያየትም እዉነትም ሆነ ሐሰት ጉብኝቱ የረጅም ጊዜ የድብቅ እና የግልፅ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ዉጤት መሆኑ አያጠያይቅም።ሐምሌ 1971 የያኔዉ የኒክሰን የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ሔንሪ ኪሲንጀር በድብቅ ቤጂንግን ከጎበኙ በኋላ እንኳን የአሜሪካ ዲፕሎማቶች የኒክሰንን ጉቭኝት ለማመቻቸት ከቻይና አቻዎቻቸዉ ጋር ብዙ ጊዜ በድብቅ አልፎ አልፎ በግልፅ ተወያይተዋል።

ኒክሰን የቻይና መሪን ለማነጋገር በሥልጣን ላይ የሚገኝ የመጀመሪያዉ ፕሬዝደንት እንደሆኑ ሁሉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ የሰሜን ኮሪያ መሪን ለመናጋገር የመጀመሪያዉ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ይሆናሉ።ልዩነቱ የኒክሰን-ማኦ ዉይይት የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዉ ጥረት ፍሬ ሲሆን የትራምፕ-ኪም ድርድር የተካረረ ዛቻ ፍጥጫ፤ የተደጋጋሚ ማዕቀብ፤የተራ ስድብ፤ ያጭር ጊዜ አጋጣሚ ዉጤት መሆኑ ነዉ።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ከምረጡኝ ዘመቻቸዉ ጀምሮ ደጋግመዉ ከዛቱ ካስፈራሯቸዉ መንግሥታት አንዷ ሰሜን ኮሪያን ናት።ሥልጣን በያዙ በመንፈቁ ከረር አድርገዉ ደገሙት።

                               

«ሰሜን ኮሪያ ዩናይትድ ስቴትስን ማስፈራራቷን ብታቆም ይሻላታል።አለበለዚያ ዓለም ከዚሕ ቀደም አይቶት የማያዉቀዉ እቶን እና ቁጣ ይወርድባታል።እሱ (ኪም ጆንግ ኡን) ከተለመደዉ አልፎ በጣም እያሰጋ ነዉ።እና እንዳልኩት እቶን፤ ቁጣና እዉነቱን ለመናገር ዓለም አይቶት የማያዉቀዉ መዓት ይወርድባቸዋል።»

ነሐሴ 2017። የሰሜን ኮሪያ አፀፋ ሌላ ሚሳዬል ወይም የኑክሌር ቦምብ ሙከራ ነዉ።

                             

«ሁለተኛዉ የአሐጉር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳዬል (ICBM ሁሳንግ 14) የተሳካ ሙከራ ለሌቱን ተደርጓል።ሙከራዉ

በኮሪያ የሰራተኞች ፓርቲ ሊቀመንበር በኪም ጆንግ ኡን የበላይ ተቆጣጣሪነት ተደርጓል።ይሕ ሙከራ የአሜሪካ ፖሊሲ አዉጪዎች፤ በወረራ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ እና መርሐቸዉን እንዳሻቸዉ ገቢር ማድረግ እንደማይችሉ እና ዴሞክራቲክ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ኮሪያን መተናኮላቸዉን እንዲያቆሙ የሚያስገነዝብ ነዉ።»

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ከያዙ አስራ-አራት ወራቸዉ ነዉ።ትራምፕ ሰሜን በኮሪያን ባስፈራሩ፤ ወደ ደቡብ ኮሪያ ጦር ባዘመቱ ቁጥር የፒዮንግዮንግ ገዢዎች ሲችሉ የኑክሌር ቦምብ ሳይሆን የረጅም ርቀት ሚሳዬል ይሞክራሉ።ሰሜን ኮሪያ ባለፉት አስራ አራት ወራት ዉስጥ አስራ-ስድስት ጊዜ ሞክራለች።በወር ካንድ በላይ ማለት ነዉ።

ዛቻ ፉከራዉ ባለፈዉ መስከረም ወደ  ተራ ስድድብ ወርዶም ነበር።መወጋጋዘ፤ መዛዛት መሰዳደቡ በዩናይትድ ስቴትስ እና በደቡብ ኮሪያ ጦር የጋራ የዉጊያ ልምምድ በጋመበት መሐል የቀዝቃዛዉ ክረምት የኦሎምፒክ ዉድድር ፒዮንግቻንግ-ደቡብ ኮሪያ ዉስጥ ተጀመረ።ጦርነት ቢጀመር የመጀመሪያዉ የጥፋት ዱላ የሚያርፍባት ደቡብ ኮሪያም የጋመዉን ፍጥጫ በክረምቱ በረዶ ለማቀዝቀዝ ሳትፈልግ አልቀረችም።

አጋጣሚዉ የሰጠ ነዉ።የሰሜን ኮሪያዎችም  መልስ ከተጠበቀዉ በላይ ፈጣን እና ቀና ነበር።በስፖርቱ ዉድድር የሁለቱ ኮሪያዎች ስፖርተኞች እንደ አንድ ቡድን ባንድ ባንዲራ ለመሳተፍ ሲወስኑ የመጀመሪያዉ የተስፋ ጭላጭል  ታየ።የሰሜን ኮሪያዉ የሕዝባዊ ላዕላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ኪም ዮንግ ናም እና የኪም ጆንግ ኡን  እሕት ኪም ዮ ጆንግ ከስፖርተኞቹ ጋር ፒዮንግቻንግን በጎበኙበት ወቅት ከደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ጋር ያደረጉት ዉይይት ይዘት በዉል አልተነገረም።ይሁንና ሁለቱ ባለሥልጣናት በተለይም ሴትዮዋ የደቡብ ኮሪያዉ ፕሬዝደንት ሙን ጄ-ኢን ሰሜን ኮሪያን እንዲጎበኙ መጋበዛቸዉ ይፋ ነበር።

ግብዣዉ ሰላማዊ ድርድር እንዲደረግ አጥብቀዉ ለሚሹት ለሙን ጥሩ አጋጣሚ ነበር።አልሔዱም ግን ልዩ ረዳቶቻቸዉን ለማላክ ጊዜ አላጠፉም።ፒዮንግዮንግ የተጓዘዉ የደቡብ ኮሪያ የመልዕክተኞች ጓድ ከሰሜን ኮሪያዉ መሪ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ያደረገዉ ዉይይት በተለይ ከራት በኋላ ዘና፤ ቀለል፤ ያለ ነበር።

«ኪም ጆንግ ኡን በእራቱ ሲቀልዱ ነበር።» አሉ አንደኛዉ መልዕክተኛ።«ገበታ ከተነሳ በኋላ ወይኑ ጎረፈ።ሶጁ የተባለዉ የሰሜን ኮሪያ አልኮል መጠጥ ተደጋጋመ።» የነበሩ እንዳወሩት፤ ወጣቱ  መሪም

 ፈገግታ ጨመሩ።አሉም «ሚሳዬን በተኮስን ቁጥር ሙን (የደቡብ ኮሪያዉ ፕሬዝደንት) የፀጥታ ምክር ቤታቸዉን ለመሰብሰብ በጠዋት ከእንቅልፋቸዉ ለመነሳት እየተገደዱ ነበር።» ከእንግዲሕ ግን ሙን በጠዋት ከእንቅልፋቸዉ መነሳት አያስፈልጋቸዉም።ሚሳዬል ሙከራ አናደርግም።»

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደደንት የፀጥታ አማካሪ ቹንግ ኡይ-ዮንግ ከፒዮንግ ያንግ ያገኙትን ቃል ወደ ሶል ይዘዉ በረሩ።ብዙ አልቆዩም ዋሽግተን ገቡ።ፒዮንግዮንግ ላይ እንደዘበት የተገኘዉ ቃል ከዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ከዶናልድ ትራምፕ ጆሮ የደረሰዉም ሳይታሰብ ነዉ።ቹንግ የምዕራብ ክንፍ በሚባለዉ የዋይት ሐዉስ አንድ ክፍል ከሌሎች የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ሲነጋገሩ  ትራምፕ አዩአቸዉ።አስጠሯቸዉ።ቹንግ ያሉትን ትራምፕ ሰሙ።ዉጤት፤-

«የሰሜን ኮሪያዉ መሪ ኪም ጆንግ ኡን የኮሪያ ልሳነ ምድርን ከኑክሌር ጦር መሳሪያ የማፅዳት አቋም እንዳላቸዉ መግለፃቸዉን ለፕሬዝደንት ትራምፕ አስረድቻቸዋለሁ።ሰሜን ኮሪያ ከኑክሌር እና ከሚሳዬል ሙከራ እንደምትታቀብ ቃል ገብተዋል።የኮሪያ ሪፐብሊክ እና የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች የሚያደርጉት የተለመደ ወታደራዊ ልምምድ መቀጠሉን እንደሚረዱትም አስታዉቀዋል።ከፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር በተቻለ ፍጥነት ለመነጋገር እንደሚፈልጉም ገልፀዋል።ፕሬዝደንት ትራምፕ የተደረገላቸዉን ገለፃ አድንቀዉ ኑክሌርን ለዘላቂዉ ከአካባቢዉ ለማስወገድ በሚረዱ ሐሳቦች ላይ ለመነጋገር ኪም ጆንግ ኡንን በመጪዉ ግንቦት ለማግኘት  ፈቃደኛ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።»

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት የፀጥታ አማካሪ ቹንግ ኡይ-ዮንግ።በቃ።

ኪም ጆንግ ኡን ባንዴ፤ ብቻቸዉን መወሰናቸዉ ሲሰማ ምዕራባዉያን ተቺዎቻቸዉ «አምባ ገነን ስለሆኑ» አሏቸዉ።ትራምፕ ከ60 ዓመት የበለጠዉን ዕዉነት ለመለወጥ ባንዴ-እና ብቻቸዉን ሲወስኑ ግን ደጋፊዎቻቸዉ «ድርድር አዋቂ» አሏቸዉ።Deal Macker.

የኮሪያ ልሳነ ምድር ዉዝግብ ጃፓንን፤ ቻይናን እና ሩሲያን በቀጥታ ሌላዉን ዓለም በተዘዋዋሪ ይነካል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሜን ኮሪያን በተደጋጋሚ ማዕቀብ የቀጣዉም ለዓለም ታሰጋለች፤ የዓለም ሕግን ጥሳለች በሚል ነዉ።ትራምፕ እና ኪም በየፊናቸዉ ያሻቸዉን ሲወስኑ ግን ዓለም እንደባይተዋር ይመለከታል።አለያም የይድረስ ይድረሱ ድርድር ሲፈርስ እንደገና እንደመናጆ መንጋ ይጠራል። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ

 

 

 

Audios and videos on the topic