የሶዌቶ ሕዝባዊ ዓመፅ 40ኛ ዓመት | አፍሪቃ | DW | 18.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሶዌቶ ሕዝባዊ ዓመፅ 40ኛ ዓመት

በደቡብ አፍሪቃ ከጆሀንስበርግ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ጥቁሮቹ ደቡብ አፍሪቃውያን በሚኖሩበት ሶዌቶ ውስጥ ታሪካዊ የሕዝብ ዓመፅ ከተካሄደ ከትናንት በስቲያ፣ እጎአ ሰኔ 16፣ 2016 ዓም 40ኛ ዓመት ሆነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:32

ሶዌቶ

የውሁዳኑ ነጮች ዘረኛ መንግሥት እጎአ ሰኔ 16፣ 1976 ዓም በሶዌቶ ከተማ ተቃውሞ ሰልፍ በወጡ ተማሪዎች ላይ በመደዳ ተኩስ በመክፈት በግምት ከ170 የሚበልጡትን ገድለዋል። በሰበቡም በቀጠሉት ቀናት በተካሄደው ዓመፅ እና ግጭት ከ500 በላይ ሰላማዊ ሰዎች በፀጥታ አስከባሪዎች የኃይል ርምጃ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ተማሪዎቹ በዚያን ጊዜ አደባባይ የወጡት የአፓርታይድ መንግሥት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ውሁዳኑ ነጮች የሚናገሩት «አፍሪካንስ» ብቸኛው የትምህርት መስጫ ቋንቋ እንዲሆን ያወጣውን ደንብ በመቃወም ነበር። ወጣቶቹ በሕይወታቸው የከፈሉት መሥዋዕትነት የተሻለች ሶዌቶ እና ነፃ ደቡብ አፍሪቃ ለመፍጠር እንዳስቻለ ከሰኔ 16፣ 1976 ጭፍጨፋ የተረፉት ሁሉ ይናገራሉ።

Rassenunruhen in Südafrika nach Schüleraufstand in Soweto


ሰኔ 16፣ 1976 ዓም ረቡዕ ዕለት ጥዋት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ተማሪዎች ወላጆቻቸውን ያው እንደወትሮአቸው ተሰናብተው ነበር ወደ ትምህርት ቤታቸው የሄዱት። ተማሪዎቹ ይኸው ስንብት ለብዙዎቹ የመጨረሻው ስንብት እንደሚሆን አላወቁም ነበር። ትምህርት ቤት እንደደረሱም በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አበረታቺነት የአፓርታይድ፣ ማለትም፣ የውሁዳኑ የነጮች ዘረኛ መንግሥት በሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች በአፍሪካንስ ቋንቋ እንዲያስተምሩ ያሳለፈውን ውሳኔ በመቃወም ተማሪዎች በጠቅላላ አደባባይ ሰልፍ ወጡ። ይህንኑ ታሪካዊ የተቃውሞ ሰልፍ ከጠሩት የተማሪዎች መካከል አንዱ የነበረው መርፊ ሞሮብ በዚያን ዕለት ሰልፍ የወጡት በሺህ የሚቆጠሩት ተማሪዎች በጠቅላላ በሰላማዊ መንገድ ሊያስተላልፉት የፈለጉት አንድ ግልጽ መልዕክት እንደነበር ያስታውሳሉ።
« ጨቋኞች የራሳቸውን ቋንቋ በተጨቆነ ሕዝብ ላይ ለመጫን የሞከሩበት ድርጊት ጭቆናውን አባብሶታል፣ እና በዚህ አንፃር ርምጃ መውሰድ እንዳለብን ተሰማን። »
ይሁን እንጂ፣ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ በምዕራብ ኦርላንዶ ፣ ቪላካዚ መንገድ በደረሱበት ጊዜ የአፓርታይድ መንግሥት ፖሊሶች ተኩስ እንደከፈቱባቸው ይታወሳል። በፖሊስ ጥይት ተመቶ በማጣጣር ላይ የነበረውን የ13 ዓመቱን ተማሪ፣ ሄክቶር ፒተርሰንን ፎቶ ያነሳው በሰልፉ የተገኘው እና ፎቶግራፍ አንሺው ሳም ንዚማ፣ እንዴት አንድ ወጣት ነጭ ፖሊስ ከ600 የሚበልጡ ተማሪዎችን ሕይወት ያጠፋውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ያቆሰለውን ተኩስ እንደከፈተ ያስታውሳል።
« ሽጉጡን ወጣ አድርጎ የተሰበሰበው ሕዝብ ላይ መተኮስ ጀመረ። ፖሊስም እንዲተኩስ ትዕዛዝ ሰጠ። እና በዚያን ጊዜ ግርግር ተፈጠረ። ፖሊስ እንዳሻው ካለዒላማ መተኮስ ቀጠለ። አንድ ትንሽ ልጅ ሲወድቅ ተመለከትኩ። »
በ1976 ዓም የሕዝብ ዓመፅ ወቅት የ16 ዓመት ወጣታ የነበሩት ሴት ማዚቡኮ በዚያች ዕለት ፖሊስ በወሰደው ርምጃ እጅግ መደናገጣቸውን ገልጸዋል።
« ፖሊስ በኛ በተማሪዎች ላይ የፈፀመው የኃይል ርምጃ ያን ያህል ጠንካራ እና የሕፃናትን ሕይወት ያጠፋ ነው ብለን አልገመትንም ነበር። »
ከሶዌቶው ጭፍጨፋ በኋላ በመቶዎች የሚገመቱ ወጣቶች ከሀገሪቱን ሸሽተው በመሰደድ የ1994 ዓም ነፃነትን ያስገኘውን የብረት ትግል ጀምረዋል። ይሁንና፣ ልክ እንደ ማንኛውም ትግል ሁሉ የተማሪዎቹም ተቃውሞ በብዙ ቤተሰቦች ላይ የማይጠፋ ጠባሳ ትቶ ነው ያለፈው። አንትዋኔት ሲትሆል ሰኔ 16፣ 1976 ዓም የተገደለው የ13 ዓመቱ ሄክቶር ፒተርሰን እህት ናት።
« ከዚያ ወንድሜን ተመለከትኩ፣ ከ,አፉ ደም ይፈስ ነበር። ደነገጥኩ። እና ሰውየው ወንድሜን መኪና ውስጥ ሊያስገባ ሲል ፣ ውይ ሞቶዋል አለ። ያንን ስሰማ የማደርገው ጠፋኝ። ግራ በመጋባት ለቅሶየን ቀጠልኩ። »


በማጣጣር ላይ የነበረውን ሄክቶር እጆቹ ላይ አቅፎ ይዞ የነበረው ምቡይሳ ማክሁቡ የት እንደደረሰ የሄክቶር ቤተሰቦች እስከዛሬ ይጠይቃሉ። በሶዌቶ ታሪካዊ ቦታዎችን የሚያስጎበኘው ፖሎኮ ንታህኮ የሄክቶር ቤተሰብ ዛሬ ከአርባ ዓመት በኋላም ለምን ሀዘን ላይ እንደሆኑ ያስረዳል።
« ከደቡብ አፍሪቃ ሸሽቶ ወደ ቦትስዋና ሄደ። ከዚያ የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ ናይጀሪያ ተጓዘ። ከዚያ ወዲህ ግን የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ጠፍቶዋል። ምቡይሳ ማክሁቡ በሕይወት ይኑር አይኑር እስከዛሬ እየጠየቅን ነው። »

ብዙ የሶዌቶ ነዋሪዎች በ1976 ወጣቶችን ለሀገሪቱ ነፃነት ላበረከቱት ድርሻ አድናቆታቸውን ይገልጻሉ። ከአርባ ዓመት በፊት በሶዌቶ በተካሄደው የተማሪዎች ተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፈው ኡፓ ሞሎቶ ዛሬ የሰኔ 16፣ መታሰቢያ ድርጅት በሶዌቶ ያነቃቃው ፕሮዤ አስተባባሪ ነው። እንደ እርሱ አመለካከት፣ ተማሪዎቹ በ1976 ዓም በከፈሉት መሥዋዕትነት የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ሶዌቶ እና ደቡብ አፍሪቃ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
« እንደበፊቱ ነጮች እና ጥቁሮች ተለያይተው አይደለም የሚኖሩት። ሁላችንም አንድ ዓይነት መታወቂያ ነው ያለን። ዛሬ አስፋልት መንገዶች አሉን። ልጆች ሳለን፣ ትዝ ይለኛል፣ እግር ኳስ እንጫወት የነበረው አቧራ ላይ ነበር። »
የወጣቶቹ መስሥዋዕትነት በሀገሪቱ ለተገኘው የፖለቲካ ነፃነት ከፍተኛ ድርሻ ቢያበረክትም፣ በትምህርቱ ዘርፍ የሚፈለገው ውጤት ላይ ሙሉ በሙሉ አልተደረሰም፣ እርግጥ፣ ዘረኛው የትምህርት መዋቅር ፈራርሶዋል፣ ግን፣ ደቡብ አፍሪቃውያን ዛሬም ቢሆን፣ ከኤኮኖሚያዊ ነፃነት እጅግ ርቀው በመገኘታቸው፣ ከነጮቹ የሀገሪቱ ዜጎች ጋር በእኩል ደረጃ እንደማይገኙ ነው በጆሀንስበርግ ያሉት የፖለቲካ ተንታኝ ራልፍ ማቴጋ ያስረዱት።
« ምንም እንኳን ባሁኑ ጊዜ ጥቁሮች ደቡብ አፍሪቃውያንን በፈለጉበት የትምህርት ተቋም ገብተው ትምህርታቸውን ከመከታተል የሚያግዳቸው ሕግ ባይኖርም፣ የኤኮኖሚ አቅማቸው ይገድባቸዋል። በሌላ አነጋገር፣ ተማሪዎቹ ለትምህርቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ መክፈል የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኙት። »
ማቴጋ በነጮች እና በጥቁሮች ኤኮኖሚው ደረጃ ላይ የሚታየው ጉልሁ ልዩነት የሚያሳስባቸውን ደቡብ አፍሪቃውያን፣ የተማሪዎችን አስተያየት ጭምር በመጥቀስ እንዳስረዱት፣ ከተፈለገ የሶዌቶን ጭፍጨፋ በያመቱ በተለያየ ስነ ስርዓት ማሰብ ብቻውን ለውጥ ማምጣት አያስችልም።
« ሰዎች ብዙ መስራት አለብን እያሉ ነው። ለ1976 ዓም ወጣቶች የሚገባቸውን ክብር መስጠት የሚቻለው ትምህርትን ለሚፈልጉ ሁሉ ተደራሽ በማድረግ ነው። »


ተማሪዎች በሀገሪቱ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በሚታየው የነጮች ተፅዕኖ አንፃር ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ባካሄዱት ተቃውሞ ያነሱዋቸው ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን ተንታኙ ራልፍ ማቴጋ ገልጸዋል።ማቴጋ እንደሚሉት፣ የአፓርታይድ ስርዓት ከተገረሰሰ በኋላ በደቡብ አፍሪቃ ስልጣን ላይ የሚገኘው የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች እንቅስቃሴ፣ በምህፃሩ «ኤ ኤን ሲ» የሚመራው መንግሥት ባለፉት ሀያ ዓመታት ትምህርትን በሁሉም ደረጃ ለሁሉም ማዳረስ የሚያስችል መርሀግብር አላወጣም። « ለዚሁ ጥያቄ መንግሥት የሰጠው ምላሽ ትምህርታቸውን ለመከታተል ለሚፈልጉ ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በብድር መልክ መስጠት የተሰኘ ነው፣ ይሁን እንጂ፣ ብድር በመስጠት የአፓርታይድ ስርዓት ትቶት ያለፈውን ፣ ማለትም፣ ብዙኃኑን ከትምህርቱ ስርዓት ያገለለውን የተሳሳተ አሰራር ማረም አይቻልም። »

ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ በሶዌቶው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የተሳተፉትም ሳይቀሩ በዚህ ካለፈው ሀሙስ ወዲህ መከበር በያዘው 40ኛው የሶዌቶ ጭፍጨፋ መታሰቢያ ወቅት በተለይ ያጎሉት አንድ መልዕክት፣ ይላሉ ራልፍ ማቴጋ፣ የአሁኑ የደቡብ አፍሪቃ ወጣት ትውልድ በጠቅላላ ተጠቃሚ እንዲሆን በትምህርቱ ስርዓት ላይ የሚታየው እኩልነት የተጓደለበት አሰራር ሊስተካከል ይገባል የሚለውን ሀሳብ ነው።


ቱዞ ኩማሎ/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic