የሶቺ ኦሊምፒክ በሩሲያ | ዓለም | DW | 10.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሶቺ ኦሊምፒክ በሩሲያ

የኦሎምፒክ ውድድሮች ኣጀማመር፣ የታሪክ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት፣ ከ2700 ዓመታት በፊት ነበር፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ 776 ዓ ዓለም ገደማ መሆኑ ነው፣ በጥንታዊቷ ግሪክ፣ ኦሎምፒያ በምትባል ከተማ።

በ393 ዓም የሮማው ክርስትያናዊ ንጉስ፣ ቀዳማዊ ቴኦዶሲዎስ፣ የጥንታዊ ልማዶች ባህል ነው በሚል ደምስሶ ደብዛውን እስካጠፋው ድረስም ኦሎምፒክ በየአራት ዓመቱ እየተካሄደ ለ 1200 ዓመታት ያህል መዝለቁ ይተረክለታል። በግምት ከ 1500 ዓመታት በኃላ ግን ኣንድ ፒየር ዲ ኮውበርቲን የተባለ ወጣት ፈረንሳዊ የኦሎምፒክ ውድድሮችን ዳግም መልሶ ለማቆም ራዕይ ሰንቆ ተነሳ። በ1894 ዓ ም ተሳካለትና የዛሬውን ዓለም ዓቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴን መሰረተ። ይህም ለዘመናዊው ኦሎምፒክ አዲስ ምዕራፍ ከፈተና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክኒያት የተሰረዙ 3 የበጋ እና 2 የክረምት ኦሎምፒኮችን ሳይጨምር እስከ ኣሁን 22 የበጋ እና 21 የክረምት ኦሎምፒኮች በዓለም ዙሪያ በተለያዩ 40 ከተሞች ላይ ተካክዷል። የመጀመሪያው ዘመናዊ ኦሎምፒክ የተካሄደው በ1896 ዓም ሲሆን፤ እኣኣ መሆኑ ነው፤ ለኣንድ ምዕተ ዓመት ያህልም የክረምት እና የበጋ ኦሎምፒኮች በተመሳሳይ ዘመን ሲካሄዱ ቆይቷል። ከ 1992 ዓም ጀምሮ ግን የክረምት ኦሎምፒክ ከበጋው ኦሎምፒክ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ እንዲካሄድ ተወስኖ፤ ነገር ግን ሁለቱም በአራት ዓመት ኣንዴ እንዲካሄዱ ተደርገዋል።

የመጀመሪያውን ዘመናዊ ኦሎምፒክ ያስተናገደችው በ 1896 የግሪክዋ አቴንስ ከተማ ስትሆን ቀጣዩን በ1900 የፈረንሳይዋ ፓሪስ፣ በ 1904 እንደገና አቴንስ፤ በ 1908 የብሪታኒያዋ ሎንደን፣ የ 1912 ቱን የስዊድኗ ስቶኮልም እና ከስምንት ዓመት በኃላ 1920 የተካሄደውን ደግሞ የቡልጂየሟ አንቲዎርፐን ነበረች ያስተናገደችው።

የክረምት ኦሎምፒኮችን ለይቶ ለመቃኘት ያህልም፤

1ኛው የክረምት ኦሎምፒክ በ 1924 ፈረንሳይ ቻሞኒክስ፣

2ኛው በ 1928 ስዊዘርላንድ st ሞሪትዝ፣

3ኛው US አሜሪካ ሌክ ፕሌሲድ፤

4ኛው ጀርመን ጋርሚሽ ፖርተንክሪቸን፣

5ኛው ስዊዘርላንድ st ሞሪትዝ፣

6ኛው ኦስሎ ኖርዌይ፣

7ኛው ኢጣሊያ ኮርቲና ዲ አምፔዞ፣

8ኛው US አሜሪካ ስኩዋው ሸለቆ፣

9ኛው ኦስትሪያ ኣንስብሩክ እና

10ኛው ፈረንሳይ ግሬኖብል ላይ ነበር የተካሄዱት።

11ኛውጃፓን ሰፖሮ ከተማ፣

12ኛው ኦስትሪያ አንስብሩክ፣

13ኛው US አሜሪካ ሌክ ፕላሲድ፣

14ኛው በቀድሞዋ ይጎዝላቪያ ሳራዬቮ፣

15ኛው ከናዳ ካልጋሪ፤

16ኛው ፈረንሳይ ኦልበርት ቪሌ፣

17ኛው ኖርዌይ ሊለኃመር፣

18ኛው ጃፓን ነጋኖ እና

19ኛው US አሜሪካ ሳልት ሌክ ሲቲ ላይ እና፤

20ኛው በ 2006 ኢጣሊያ ቱረን ላይ ነበር የተካሄዱት።

21ኛው የክረምት ኦሎምፒክ በ 2010 ከናዳ ቫንኮቨር ላይ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፤

22ኛው ደግሞ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ በደቡባዊ ሩሲያ፣ ጥቁር ባህር ዳርቻ ላይ በተገነባው የሶቺ የኦሎምፒክ መንደር በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ከመግቢያችን ላይ እንደሰማችሁት የሶቺ ኦሎምፒክ በይፋ መከፈቱን ያበሰሩት የኣገሪቱ ፕሬዚደንት ሲሆኑ ዕድሉ ዘመናይዋ ሩሲያ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር በምታደርገው ግስጋሴ በሯን ለዓለም ህብረተሰብ ክፍት ማድረጉዋን የምታረጋግጥበት አጋጣሚ ነው ብሏል ፑቲን። እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ታዲያ ገና ከጅምሩ ማለት ይቻላል፤ ወቀሳና ነቀፌታም ግን ኣልተለያቸውም። የፑቲን መንግስት የሚከተለውን ፖሊሲ በመንቀፍ የUS አሜሪካው ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ የከናዳው ጠ/ሚ እና የፈረንሳዩ ፕሬዚደንትም በሶቺው ኦሎምፒክ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ሳይገኙ ቀርቷል። ከሰብዓዊ መብት ይዞታ አንጻር ሩሲያ በተለይም የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን በመከልከሏ በምዕራባዊያኑ ዘንድ ስትወነጀል ቆይታለች። በኦሎምፒኩ ዋዜማ በመርዝ በፈጀቻቸው ኣውደልዳይ ውሾች ጉዳይ ሳይቀር ስትኮነን ሰንብታለች። በተለይም የሲርኮዚያን ብሔራዊ ድርጅት የዛሬ 150 ዓመት ገደማ የሩሲያ ተስፋፊዎች በህዝባቸው ላይ ያፈጸሙትን የዘር ማጥፋት ወንጀል በማውሳት የሶቺ ኦሎምፒክ እንዲሰረዝ ጠይቐል። በ1864 ዓም በሲርኮዚያኑ መግለጫ መሰረት፣ የሩሲያ ወራሪዎች በነባሩ የሲርኮዚያን ህዝብ ላይ በከፈቱት ዘመቻ በትንሹ 1,5 ሚሊየን ገደማ ሲርኮዚያንን ፈጅቷል። የተቀሩት አካባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገዷል። እናም ይላል ድርጅቱ ኣውስትራሊያ በ2000፣ US አሜሪካ በ2002 እና ከናዳ በ2010 ዓም እንዳደረጉት ሁሉ ሩሲያም በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባታል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች በበኩላቸው ሩሲያ በሶቺ ያስገነባችው የኦሎምፒክ መንደር የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃን ያላገናዘበ በመሆኑ ኃላፊነት የጎደለው ነው ሲሉ ይሟገታሉ።

ዓለም ዓቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ግን ግንባታው ምንም ይሁን ምን በሶቺ ኦሎምፒክ ከዝግጅቱ ጀምሮ በመስተንግዶው ጭምር መርካቱን ኣስታውቐል። ጀርመናዊው የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚደንት ቶማስ ባህክ በመክፈቻው ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት ሩሲያ ምስጋና ይገባታል ሲሉ ኣሞካሽቷታል። የመንግስታት መሪዎች ኦሎምፒክን ለፖለቲካ ዓላማቸው መጠቀሚያ ከማድረግ እንዲቆጠቡም ባህክ ኣበክረው ኣሳስቧል።

ለሶቺው ኦሎምፒክ መንደር ግንባታ ቀድሞ የተያዘለት በጀት 12 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን በተለያዩ ምክኒያቶች ዋጋው በአራት እጥፍ ንሮ ከ 51 ቢሊየን ዶላር በላይ ማውጣቱን መንግስት ኣስታውቐል። እናም በኦሎምፒክ ታሪክ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ውድ ኦሎምፒክም ተብሏል። ሶቺ። ማየት ማመን ነውና ካዩት ለመስማት ቀድሞ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል የነበሩትን እና ኣሁን ደግሞ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የክብር እንግዳ ሆነው እዚያው ሶቺ የሚገኙትን አቶ ፍቅሩ ኪዳኔን በስልክ ኣግኝቼኣቸው ነበር።

ጸጥታን ኣስመልክቶ የአሜሪካው የስለላ ድርጅት CIA የሽብር ጥቃት ሊደርስ ይችላል ሲል ማስጠንቀቁ ባይቀርም የሶቺ ኦሎምፒክ በከፍተኛ ጥበቃ ስር መሆኑን ፕሬዚደንት ፑቲን በተደጋጋሚ ተናግሯል። በሰሜናው ካውካስ ግዛት የጸጥታ ጥናት ተቐም ተንታኝ የሆኑት ቫርቫራ ፓቾሜንኮ በበኩላቸው የCIA ን ስጋት ይጋራሉ።

ባለፈው ዓርብ በደማቅ ስነስርዓት በተከፈተው 22ኛው የሶቺ ኦሎምፒክ ከ87 ኣገራት የመጡ 2900 ስፖርተኞች በ98 የተለያዩ የውድድር ዓይነቶች ለወርቅ፣ ለብርና ለነኃስ ሜዳሊያ ይፋለማሉ። ጀርመንም 153 ስፖርተኞችን ወደዚያው ልካለች። የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አኃዱ ያለው በሆኪ (የበረዶ ሸርተቴ) የሩሲያዋ ዋና ተቀናቃኝ የUS አሜሪካ አትሌት ነው። የሶቺ ኦሎምፒክ የሚገባደደው በፊታችን የካቲት 16 ቀን ይሆናል።

ጃፈር ዓሊ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic