የሶርያው ጦርነትና የኃይል አሰላለፍ | ዓለም | DW | 30.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሶርያው ጦርነትና የኃይል አሰላለፍ

ሶርያ ከታመሰች አምስተኛ አመቷን አስቆጠረች። ባለፉት አራት አመታት አራት ባላንጣዎች ተፈጥረው አንዱ የሌላውን መጥፊያ ይፈልጋል። አራቱም ከውጭ አገራት ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ደጋፊዎቻቸውም እርስ በርስ አይግባቡም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:23
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:23 ደቂቃ

የሶርያው ጦርነትና የኃይል አሰላለፍ

ከአብዮቱም፤ የርስ በርስ ጦርነቱም ሆነ የእጅ አዙር ፍጥጫው በፊት የመጀመሪያዋን ጥይት በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የተኮሱት የፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ወታደሮች በመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም. ነበር። በሐምሌ የተወሰኑት ተቃዋሚዎች በፕሬዝዳንቱ የጸጥታ ኃይሎች ላይ መልሰው መተኮስ ጀመሩ። የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ወታደሮች እየከዱ የተቃውሞውን ጎራ መቀላቀል ጀምረውም ነበር። የፕሬዝዳንት በሺር አል አሳድ ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ነጻ የሶርያ ጦር ብለው መጥራት ሲጀምሩ ሶርያ ሙሉ በሙሉ ወደ የርስ በርስ ጦርነት ገባች። ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጽንፈኞች ተቀላቀሏቸው። በጎርጎሮሳዊው ጥር 2012 ዓ.ም. አል-ቃዒዳ ጃብሃት አል-ኑስራ የተሰኘ ክንፍ በሶርያ መሠረተ። በዚህ ወቅት የሶርያ ኩርዶች በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ጦር አንግበው የበሽር አል-አሳድን መንግሥት ይወጉም ነበር። የሶርያ ኩርዶች ዛሬም ድረስ መገንጠልን ያቀነቅናሉ። በዚህ ወቅት የሶርያ ትንቅንቅ ከአብዮት ወደ እጅ አዙር ጦርነት ያመራበት ወቅት ነው።

የእጅ አዙሩን ጦርነት በመቀላቀል የበሽር አል-አሳድ መንግስት ደጋፊ የሆነችው ኢራንን የቀደማት አልነበረም። በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም. መገባደጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢራን ወታደሮች አግራቸውን በሶርያ ምድር እንዳሳረፉ የምዕራባውያን የጸጥታ ተንታኞች ይናገራሉ። የሊባኖሱ ሒዝቦላህ በኢራን እየተደገፈ ሌላው ከበሽር አል-አሳድ መንግስት ጎን የቆመ ኃይል ነበር። ሳዑዲ አረቢያና ኳታርን ጨምሮ የባህረ ሰላጤዉ አገራት በተቃራኒው ኢራን በቀጣናው ልታሳድር የምትችለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብና የጦር መሳሪያ ለአማጽያኑ ይለግሱ ነበር። ሶርያ ላይ የተጠነሰሰው የሺዓ እና ሱኒ እስልምና ተከታይ አገራት ፍጥጫ በበረታበት የጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም. ዩናይትድ ስቴትስ ብቅ አለች። የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በማዕከላዊ የስለላ ተቋም በኩል አማጽያኑን ማስታጠቅና ማሰልጠን ያዙ። ያኔ ሶርያ ጉታ በተሰኘችው ከተማ ላይ የኬሜካል ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች የሚል ወቀሳ ቀርቦባት ምዕራባውያን አገራትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሺር አል-አሳድን አጥብቀው የሚኮንኑበት ወቅት ነበር።

በየካቲት 2014 ዓ.ም. መቀመጫውን በአብዛኛው በኢራቅ ያደረገውና ከአልቃዒዳ ተገንጥሎ የወጣው የዛሬው «እስላማዊ መንግስት» የተባለ ቡድን ብቅ አለ። በአቡ ባካር አል-ባግዳዲ የሚመራውና በጥብቅ እስላማዊ ሕግጋት የሚተዳደር ግዛት መስርቻለሁ የሚለው ጽንፈኛ ቡድን ቀዳሚ ዓላማ ሃይማኖታዊ ፍልስፍናውን በዓለም ሁሉ ማዳረስ እንደሆነ ይሰብካል። ቡድኑ ጋዜጠኞች፤መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች አንገት ሲቀላ አሊያም በጥይት ሲረሽን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በድረ-ገጽ በማሰራጨት ጨካኝነቱን ለዓለም አሳይቷል። ወጣት እንስቶች ለሽያጭ አቅርቧል። ታሪካዊ ቦታዎችን፤ የእምነት ተቋማትም አውድሟል። የመጀመሪያ ሰለባዎቹ ግዛቱን ባስፋፋበት ኢራቅና ሶርያ የሚገኙ ንጹሃን ናቸው። ራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ በሚጠራው ቡድን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ትዕዛዝ ያስተላለፉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ነበሩ።

ጽንፈኛ ቡድኑ ከቱኒዝያ፤ ሳዑዲ አረቢያ እና ሩሲያ ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ታጣቂዎች ይመለምላል። በሸሪዓ ሕግጋት የሚተዳደረው በእስላማዊ መንግስት መመሥረት ደስተኛ የሆኑ ድንበር አቋርጠው ባህር ተሻግረው ተቀላቅለውታል። የበሺር አል-አሳድን መውደቅ ከሚደግፉ የመካከለኛው ምሥራቅ ቱጃሮችከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ያገኛል የሚባለው ቡድን ከመሰሎቹ ሁሉ በሀብት የናጠጠ ነው። እንደ አሜሪካ ብሔራዊ ግምጃ ቤት መረጃ ከሆነ በጎሮጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. ብቻ 100 ሚሊዮን ዶላር ነበረው። ይህ ታጣቂዎች ለመልመል በምዕራባውያን ላይ ጥቃት ለመፈጸም አቅም ፈጥሮለታል።

በኢራቅና ሶርያ በሚገኙ የታጣቂ ቡድኑ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት የጀመረችው አሜሪካ ምዕራባውያንንም ለተመሳሳይ ግዳጅ አስተባብራለች። ጥምረቱ አውስትራሊያ፤ ካናዳ፤ ፈረንሳይ፤ ሞሮኮ፤ ኳታር፤ ሳዑዲ አረቢያ፤ ቱርክና ታላቋ ብሪታኒያን ጨምሮ 24 አገራትን ያካትታል። ይህ ጥምረት የበሺር አል-አሳድን፤ እስላማዊ መንግስትንና መሰል ጽንፈኛ ታጣቂዎችን ዒላማ ያደረገ ነው። በእስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ ላይ የተወሰዱት የኃይል እርምጃዎች ግን እስካሁን ፍሬ አፍርተው ሰላም አላወረዱም። አላን ፖስነር የፖለቲካ ተንታኝና ጸሐፊ ናቸው። በዶይቼ ቬለ ኳድሪጋ የውይይት መሰናዶ የተሳተፉት ፖስነር ጽንፈኛ ቡድኑ ለሚፈጽማቸው አሰቃቂ ወንጀሎች ግዳጁን በተገቢው መንገድ መምራት የተሳናቸው የምዕራቡ ዓለም ፖለቲከኞች ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ይተቻሉ።

«ተጠያቂነቱ ሊወድቅ የሚገባው በ አይኤስ ላይ የሚደረገውን ትግል በአግባቡ መምራት በተሳናቸው ባራክ ኦባማ ፊት ላይ ነው። ይህ ሁሉንም ምዕራባውያን መሪዎች ይመለከታል። ፍራንሷ ኦሎንድ ከዴቪድ ካሜሩን ተገቢውን ድጋፍ አላገኙም። ስለዚህ በተናጠል የሚወሰደው እርምጃ ፍሬ አላፈራም። ኦባማ ከፓሪሱ ጥቃት በፊት ዓላማቸው የአይ.ኤስ ታጣቂዎችን ባሉበት መግታት መሆኑን ተናግረው ነበር። ይህ ሙከራ የፓሪሱን ጥቃት ወልዷል። ስለዚህ ተጠያቂነቱ እርምጃ መውሰድ በተሳናቸው ሰዎች ላይ ይወድቃል።»

ሩሲያ በሶርያ ጦርነት የጦር አውሮፕላኖቿን ያዘመተች አገር ነች። ራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ የሚጠራው ቡድን በግብጽ የሲና በረሐ 224 ሰዎችን ጭኖ ለተከሰከሰው የመንገደኞች አውሮፕላኗ አደጋ መንስዔ እኔ ነኝ ማለቱ አይዘነጋም። ሩሲያ በጽንፈኛው ቡድን ላይ የምትወስደው እርምጃ ግን ለምዕራባውያኑ የሚጥም አልሆነም። ምዕራባውያኑ የሩሲያ የአየር ጥቃቶች በበሽር አል-አሳድ ተቃዋሚዎች ላይ ያነጣጠሩ እንደሆኑ ይከሳሉ። ኢቫን ራዲያኖቭ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ ናቸው።

«የሩሲያ ዓላማ አሁን የተፈጠረውን አለመረጋጋት ማቆምና ሶርያን ማረጋጋት ነው። ጉዳዩ የርስ በርስ ጦርነት ሲባል ይደመጣል። ነገር ግን እንደዛ አይደለም። የሶርያ መረጋጋት የቀጣናው መረጋጋት ጭምር ነው። ማንኛውም አገር ሊያስጠብቀው የሚፈልገው ጥቅም ይኖረዋል። ቅድሚያ የሚሰጠው ግን የሶርያ መረጋጋት ነው። አገሪቱን ለማረጋጋት የሚችለው አንድ ኃይል ብቻ ነው ያለው። እሱም ከ10 ሚሊዮን በላይ ሶርያውያን ድምጽ ያለው የፕሬዝዳንት በሺር አል አሳድ መንግስት ነው።»

የሩሲያ ፍላጎትም ይሁን በሶርያ የምትወስደው እርምጃ የምዕራቡን ፖለቲከኞች ፈጽሞ አያስማማም። ይህ ግን ተንታኞቻቸውንም ይጨምራል። አላን ፖስነር የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንንም ሆነ ኢቫን ራዲያኖቭ ሃሳብ አጥብቀው ይተቻሉ።

«እውነታው ሩሲያ አለመረጋጋት ውስጥ የገባችው በበሽር አል አሳድ ነው። በመጀመሪያ በአገራቸው የተነሱትን ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ጨፍጭፈዋል። ከሩሲያ የቀረበላቸውን የኬሚካል የጦር መሳሪያ በራሳቸው ህዝብ ላይ ተጠቅመዋል። በሽብር ላይ ዘመቻ የከፈቱ ለማስመሰል የአይኤስ ታጣቂዎችን ከእስር በመፍታት ለጽንፈኛው ቡድን መቋቋም አስተዋጽዖ አበርክተዋል። ይህንንም በሶርያ የጦር ሰፈራቸውን ለማስጠበቅ ከሚፈልጉት ሩሲያውያን ጋር እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

እርስ በርስ የሚጋጩ ፍላጎቶች ያሏቸው ባላንጣዎች ሶርያን የደም ምድር አድርገዋታል። ኢራን፤ ቱርክ፤ ሳዑዲ አረቢያ እና ኳታርን የመሳሰሉት የሙስሊም አገራት ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ከመሞከር ባለፈ በተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ፍላጎት ያላቸው አይመስልም። ራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ በሚጠራው ቡድን ላይ የተጀመረው ዘመቻ ሰፍቶ ሩሲያና ቱርክን እስከማፋጠጥ ደርሷል። የሩሲያ የጦር አውሮፕላን በቱርክ ተመቶ መውደቁን ተከትሎ የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሻክሯል። ጥቅማቸውን ለማስከበር በየጎጣቸው የቆሙት ልዕለ ኃያላን በሶርያ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር የፈቀዱ አይመስልም። የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዳንዔል ጌርላሽ ህዳር 26 በዶይቼ ቬለ ኳድሪጋ ውይይት ላይ ራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ በሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን ላይ የሚወሰደው እርምጃ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

«አይ.ኤስ. ራሱን ችሎ የተገነጠለ ችግር አለመሆኑን ልብ ልንል ይገባል ብዬ አምናለሁ። በወታደራዊ ኃይል ማሸነፍ እንደሚቻል እኔም እስማማለሁ። ሊደረግ የሚገባውም ከረጅም ጊዜ በፊት ነበር። ነገር ግን በአንድ ቦታ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ራሳቸውን የእስላማዊ መንግስት ህዋስ አድርገው የሚቆጥሩ ታጣቂ ቡድኖች በአፍሪቃ በሊቢያ እና በአፍጋኒስታን ይገኛሉ። ስለዚህ የምንታገለዉ ከአንድ ቡድን ጋር ሳይሆን ከአስተሳሰብ ጋር መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። መንግስታት ሲፈራርሱ እና የሚጠበቅባቸውን ሚና መጫወት ሲሳናቸው ማንኛውም አካል መጥቶ መንግሥት መሥርቻለሁ፤ ካሊፌት አለኝ ሊል ይችላል። እስላማዊ መንግስት ነኝ ባዩን እንደ መንግስት ስንወስደው ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። ይህ በእኔ አስተያየት ፈጽሞ ትክክል አይደለም።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ከአውሮጳ አገራትና ከሪፐብሊካን ተቀናቃኞቻቸው የቀረበላቸውን የእግረኛ ወታደር ዘመቻ ለመቀበል ለጊዜው ፈቃደኛ አይመስሉም። የጸጥታ ተንታኞች አሜሪካ በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ የገጠማት ውድቀት ዳግመኛ እንዲከሰት ፕሬዝዳንቱ ስጋት አላቸው ሲሉ ይደመጣሉ። በጽንፈኛ ቡድኑ ላይ የዘመተው ዓለም አቀፍ ትብብር በየዕለቱ በሶርያና ኢራቅ የሚገኙ ይዞታዎችን ይደበድባል። የፖለቲካ ተንታኟ ኡልሪክ ሄርማን የአየር ድብደባውን ፋይዳ ብቻ ሳይሆን በጥምረቱ ላይም ጥያቄ አላቸው።

«ዓለም አቀፍ ትብብር ጥሩ ነበር። ነገር ግን የለም። ሩሲያውያኑ ከምዕራቡ የተለየ ፍላጎት ያራምዳሉ። ጉዳዩ በምዕራቡና ሩሲያ መካከል ያለው ልዩነት ብቻ ሳይሆን በሶርያ ዙሪያ የሚገኙ አገራት ሚናም ታሳቢ መሆን አለበት። አሁን በሶርያ በሚፈጠረው ጉዳይ ላይ ትልቅ ተደማጭነት ያላቸው ቱርክ፤ ሳዑዲ አረቢያና ኢራን ናቸው። እንዳለመታደል ሆኖ ሶስቱም ተቃራኒ ፍላጎት ነው ያላቸው። ለሶርያ ይበጃል በሚባል የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ሲስማሙ ማየት አስቸጋሪ ነው።»

ራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን በፓሪስ ከፈጸመው አሰቃቂ ሽብር በኋላ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ዓለም አቀፍ ትብብር ፍለጋ ሲባዝኑ ተስተውለዋል። ፕሬዝዳንቱ ከዋሽንግተን እስከ ሞስኮ በርረው በተለያየ ጽንፍ የቆሙትን ሁለት መሪዎች ለማስተባበር ያደረጉት ጥረት ፍሬ እስካሁን አልታየም። የሶርያን ቀውስ ለመፍታት በቪየና የተጀመረው ውይይትም የተዘነጋ ይመስላል። ልዕለ ኃያላኑ የጋራ ጠላታችን ባሉት ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን ላይ ድል መቀዳጀት ለምን ተሳናቸው? የዳንዔል ጌርላሽ ሃሳብ የጉዳዩን ውስብስብነት ይጠቁማል።

«ይህ እስላማዊ መንግስት አደገኛ ስጋት ብቻ ሳይሆን ለተወሰኑ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጥቅምም ነው። እስላማዊ መንግስት ቱርክ ስታጠፋ ፍላጎቷ ምንድ ነው? ኢራንስ? ሳዑዲ አረቢያስ? እስላማዊ መንግስት በአሳድ መንግስት ላይ ስጋት አይደለም። እየተስፋፋ አይደለም። ለጊዜው ለቱርክና ለኢራን ስጋት አይደለም። ፈጽሞ ለሳዑዲ አረቢያ ችግር አልፈጠረም። እውነቱን ለመነጋገር እግረኛ ወታደር በመላክ እስላማዊ መንግስትን ለማጥፋት ማን ነው ፈቃደኛ?»

ምዕራባውያኑ የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሯሯጡ ሶርያውያን ለሞትና ስደት ተዳርገዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ መሠረት ከ10.4 ሚሊዮን ሶርያውያን 2.2 ሚሊዮኑ በቀውሱ ተጠቅተዋል። 6.5 ሚሊዮኑ በአገራቸው ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። ከአፍጋኒስታን፤ ኢራቅና ሶማሊያ ለሚመጡ ስደተኞች መጠለያ በመስጠት ትታወቅ የነበረችው አገር አሁን የስደተኛ ምንጭ ሆናለች። ምዕራባውያኑ ግን እየተኮሱ ነው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic