የሶሪያ ጦርነትና የተሻረው የድርድር ቃል | ዓለም | DW | 25.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሶሪያ ጦርነትና የተሻረው የድርድር ቃል

በብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መልዕክት የልብ ልብ የተሰማቸዉ አንካራ፥ ዶሐ፥ ካይሮና ቤይሩት የከተሙት የአማፂ ሐይላት መሪዎች ከሰወስት ሳምንት በፊት የገቡትን የድርድር ቃል ባለፈዉ ቅዳሜ ሻሩት።

default

ደማስቆ


የሶሪያ መንግሥት ዋነኛ ተቃዋሚ ማሕበር መሪ ሞአዝ አል ኻጢብ የገቡት የድርድር ቃል፣ የደማስቆ ገዢዎች ይሁንታ በቅድመ-ግዴታ ከመታጠራቸዉ እኩል፣ ካንጀት ካንገትነታቸዉ ያልለየ፥ ተስፋ ላለማጠት ከሚደረግ ተስፋ ያልዘለለ ነበር።የሶሪያ ተፋላሚዎች ቃል፣ ይሁንታቸዉን እንዳያጥፉ ከዋሽግተን፣ ብራስልስ፣ ከሞስኮ ቤጂንግ መንግሥታት፣ ከካይሮ፣ ኒዮርክ ማሕበራት የተሰማዉ ምክር፣ ማስጠንቀቂያ ግን የሩቅ፥ ግን የሠላም ተስፋ ፈንጣቂ መስሎ ነበር።ተቃዋሚዉ ማሕበር ባለፈዉ ቅዳሜ ከሌላ ቅድመ-ግዴታ ጋር ቃሉን ሲያጥፍ ግን የመሰዉ እንደመሰለ ቀረ።ሳይበራ የጠፋዉ ተስፋ ምንነት፥ የሶሪያ ዉድመት እስከየትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።


የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል ትናንት ሶሪያን በሚያዋስነዉ የቱርክ ግዛት የሠፈረዉን የጀርመን ጦር ሲጎበኙ ያስተላለፉት መዕልክት ድርብ ነዉ።የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የሆነችዉን ቱርክን ከሶሪያ ሊሰነዘር ከሚችል ጥቃት ለመከላከል ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል መትከሉ፥ ኔቶ፥ አባሉን ሊያጠቃ የሚችል ሐይልን በዋዛ እንደማይለፈዉ-ማሳየት አንድ፥ ደግሞ በተቃራኒዉ በሶሪያዉ ጦርነት የሚያልቀዉን ሕዝብ ለማዳን ብቸኛዉ የዓለም የጦር ተሻራኪ ድርጅት ሊያደርግ ከሚችለዉ ትንሹን ማድረጉን ጠቋሚ-ሁለት።

«በጣም አስፈላጊዉ ነገር፥ (በድንበሩ) የቱርክ ግዛት በኩል የሚኖሩ ሰዎች ቢያንስ (ጥቃትን) ለመከላከል እንደምንረዳቸዉ በግልፅ እንዲያዉቁት ማድረግ እና በሌለኛዉ የድንበሩ ማዶ፥ ግጭቱን ከሶሪያ ድንበር ለማሻገር ለሚፈልጉት ደግሞ የኔቶ ክልል (እንዲጠቃ) እንደማንፈቅድ የማያወላዳ መልዕክት ለማስተላለፍ ነዉ።»

Syrien Aleppo Februar 2013

እሌፖጀርመን፥ ዩናይትድ ስቴትስና ኔዘርላንድስ፥ ቱርክ ግዛት ያሠፈሩት የኔቶ ጦር የደገነዉ የፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል አፈሙዝ የማያወላዳዉን መልዕክት ለደማስቆ ገዢዎች በግልፅ ያስተላልፋል።ሁለተኛ ዓመቱን ባገባደደዉ ጦርነት የሚያልቀዉን ሶሪያዊ ለማዳን ግን ሐያሉ የጦር ተሻራኪ ድርጅት ያደረገዉ የለም።ካለም ሜርክል እንዳሉት በጣም ትንሹን ነዉ።

እርግጥ ነዉ የሐያሉ ብቸኛዉ የጦር ተሻራኪ ድርጅት ሐያል አባላት፥ ከአንካራ-ሪያድ፥ ከዶሐ ካይሮ ተከታዮቻቸዉ ጋር ሆነዉ፥ የሶሪያ መንግሥትን ለሚዋጉት ሐይላት ሁለንተናዊ ድጋፍ መስጠታቸዉን አላቋረጡም።ለሶሪያ ተቃዋሚዎች የተሰጠና የሚሰጠዉ፥ የፖለቲካ-ዲፕሎማሲ፥ የገንዘብ-ትጥቅ እርዳታ፥በደማስቆ መሪዎች ላይ የተጣለዉ ማዕቅብ፥ የሚሰነዘረዉ ማስፈራሪያም እንደተፈለገዉ ተቃዋሚዎችን ደማስቆ ቤተ-መንግሥት መዶል አልቻለም።

እንዲያዉም ደጋፍ-እርዳታ፥ ቅጣት-ዛቻዉ፥ ዋሽግተን-ብራስልሶችን፥ ከሞስኮ-ቤጂንጎች፥ ቀጠር-ሪያዶችን ከቴሕራ ጋር አናቁሮ ወትሮም ሠላም የማያዉቀዉን ድንፍን መካከለኛዉ ምሥራቅን እንዳያተራምስ ነዉ ያሁኑ ሥጋት።የአዉሮጳ ሕብረት የመካከለኛዉ ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ አንድርያስ ራይኒከ እንደሚሉት ደግሞ የሶሪያዉ ጦርነት ለሶሪያዎች ብቻ ሳይሆን ለመላዉ አካባቢዉ ታላቅ ድቀት መሆኑ እየታየ ነዉ።

Syrien Aleppo Februar 2013

እሌፖ

«በአሁኑ ጊዜ የሶሪያ ሁኔታ አሳሳቢ እና አሳዛኝ ነዉ።በደማስቆዉ ተቋም ላይ ተፈፀመዉ ጥቃት ደግሞ የሶሪያ የደሕንነት ሁኔታ በመካከለኛዉ ምሥራቅ መንግሥታት ላይ ከባድ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ መስካሪ ነዉ።የሶሪያ መርዛማ-ኬሚካሎች ይዞታ አሳሳቢ ነዉ።ከዚሕም በተጨማሪ ሶሪያ የሠፈሩት የፍልስጤም ስደተኞች ችግር አለ።ሶሪያ ዉስጥ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የፍልስጤም ስደተኞች ሠፍረዋል።የሚሔዱበት ሥለሌላቸዉ (ከርስ በርሱ ጦርነት ጦርነት) ገለልተኛ ሆነዉ ለመቆየት እየሞከሩ ነዉ።»

የዋሽግተን፥ ብራስልስ፥ የሞስኮ፥ ቤጂንግ ተፎካካሪዎች፥ የቴሕራን፥ የሪያድ፥ የአንካራ-ቀጠር ተቃራኒዎች ሐገር የተቀማዉን ፍልስጤማዊ ሲሆን ሐገር እንዲኖረዉ፥ ይሕ ቢቀር በየተሰደደበት በሠላም እንዲኖር ከመርዳት ይልቅ የሶሪያ ተፋላሚዎች እርስ በርስ እንዲቀጥሉ እያጃገኗቸዉ ነዉ።

የአረብ-አሜሪካ፥ የአዉሮጳ፥ እስያ ሐያል፥ ሐብታም መንግሥታት ለየታማኝ ተፋላሚዎች የሰጡና የሚሰጡት ድጋፍ የደማስቆ አምባገነኖችን ቢያስወግድ ኖሮ የጣልቃ ገብነቱ ጣጣ «ዕዳዉ ገለባ» ባሰኘ ነበር።ታሪካዊቱን፥ ጥንታዊቱን፥ ጠንካራዊቱን ሶሪያን የማዉደም፥አኩሪ ሐገር የነበረዉን ኩሩ ሕዝብን የመጨረሽ፥ የማዋራድ፥ ማሰደዱ ድቀት እንጂ ቀብፀ ተስፋ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ሁለተኛ ዓመቱን ባገባደደዉ ጦርነት ከሰሳባ ሺሕ በላይ ሕዝብ ፈጅቷል።አራት ሚሊዮን ያሕል አንድም ተሰዶ፥ አለያም ተፈናቅሎ የዕለት ጉርስ፥ የዓመት ልብስ፥ መጠለያ-ድንኳን ለማኝ ሆኗል።

አሌፖ፥ ደማስቆ፥ ዳራ፥ ሐማ ሌሎችም ዛሬም ቦምብ፥ ሚሳዬል እየተዘረባቸዉ፥ ከደም መስኖ ቁስለኛ ያጭዳሉ፥አስከሬን ይወቃሉ፥ የሐብት፥ ንብረት፥ የዉድ ቅርስ ድቃቂ ይከምራሉ።የሶሪያ መንግሥት ዋነኛ ተቃዋሚ የሶሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት መሪ ሞዓዝ አል-ኻጢብ የዛሬ ሠወስት ሳምንት ግድም ያሰሙት የድርድር ቃል ያ! ሕዝብ፥ ሐገር ቅርስ የሚያወድመዉን ጦርነት ለማስቆም ይረዳል የሚል ተስፋ ያኔ አላሳደረም ነበር።

Bashar al-Assad Rede TV Fernsehen Staats TV

አሰድያም ሆኖ የምዕራብ-አረቦቹ ሐያል-ሐብታም፥ ደጋፊዎቻቸዉ ፍቃድና ይሁንታን ሳይጠይቁ ኻጢብ «እጃቸዉ ከደም የፀዳ» ካሏቸዉ የደማስቆ መሪዎች ጋር ለመደራደር ባልጠየቁ ነበር።የኻጢብን የድርድር ጥያቄ የደማስቆ ገዢዎች እንዲቀበሉት ከንደን-ዋሽግተን፥ከአንካራ-ዶኸ የተሰማዉ ዛቻ አዘል-ማሳሰቢያ፥ ከሞስኮ የተነገረዉ ምክር ለበስ-ግፊት የጦርነቱ ግመት ሁሉንም በየፊናዉ እያተኮሰዉ መሆኑን ጠቋሚ፥ ለሶሪያዎች ደግሞ የሩቅ-ጭላንጭልም ቢሆን የሠላም ተስፋ ፈንጣቂ ነበር።

የኻጢብ ቅድመ-ግዴታ እንዲነሳ በመጠየቅ ድርድሩን ላለመቀበል ሲያንገራግሩ የነበሩት የደማስቆ ገዢዎች ከማስጠንቀቂያ፥ ምክሩ በሕዋላ ለመደራደር ፈቃደኝነታቸዉን አስታዉቀዋል።በዴንማርክ የደቡባዊ ዩኒቨርስቲ የሶሪያ ጉዳይ አጥኚ ኤሪክ ሞሐንስ እንደሚሉትም የድርድር ጥሪ፥ ይሁንታዉ ተፋላሚ ሐይላት ልዩነታቸዉን በጦርነት መፍታት እንደማይችሉ መገንዘባቸዉን ጠቋሚ ነዉ።

«ጥሪ፥ ይሁንታዉ በተቃዋሚዎቹ ወገን፥ የደማስቆ ሥርዓትን በወታደራዊ ዉጊያ ባጭር ጊዜ ማስወገድ እንደማይቻል መረዳታቸዉን አመልካች ነዉ።በሥርዓቱ በኩልም በዉጊያ አሸንፈዉ ሐገሪቱን ሙሉ በሙሉ መግዛት እንደማይችሉ የተረዱ የተወሰኑ ሐይላት መኖራቸዉን ጠቋሚ ነዉ ብዬ አምናለሁ።»

ከአረብ-ሊግ ዋና ፀሐፊ እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ፥ ለድርድር ጥሪ ይሁንታዉ ያላቸዉን ድጋፍ በሚያንቆረቁሩበት ባለፈዉ ሳምንት የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ብራስልስ-ቤልጂግ ዉስጥ ተሰብስበዉ ነበር።የስብሰባዉ ዋና ርዕስ ያዉ ሶሪያ ነበረች።

Ahmad Mouaz Al-Khatib Syrien Opposition Brüssel Treffen

ኻጢብ

ሕብረቱ በሶሪያ ላይ የጣለዉ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ ገደብ የፊታችን አርብ ያበቃል። የደማስቆን ገዢዎች በማዉገዝ፥ ተቃዋሚዎቻቸዉን በመደገፍ፥ የድርድሩን ሐሳብ በመቀበል አንድ የሆኑት የሕብረቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች የጦር መሳሪያዉ ማዕቀብ ይነሳ-አይነሳ በሚለዉ ሐሳብ ግን ሙሉ በሙሉ አልተግባቡም ነበር።

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቨለ የማዕቀቡ መነሳት የሶሪያዉን ጦርነት ያባብሰዋል ባይ ናቸዉ።«የጦር መሳሪያ ማዕቀቡን ማንሳት በሶሪያ የጦር መሳሪያ ሽቅድምድምን ያስከትላል።ይሕ ደግሞ የሶሪያዉን ዉጊያ አባብሶ በርካታ ሕዝብ ያልቃል።»

የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊሊያም ሔግ የጀርናዊዉ አቻቸዉን ሐሳብ አልተቀበሉትም። ሔግ እንደሚሉት የሶሪያ አማፂያን ተጨማሪ ትጥቅ እንዲያገኙ ማዕቀቡ ማዕቀቡ መሻሻል አለበት።

«(ለተቃዋሚዉ) ብሔራዊ ሕብረት ሠፊ ድጋፍ መስጠት እንችል ዘንድ፥ የጦር መሳሪያ ማዕቀቡ መሻሻል አለበት ብለን እናምናለን።ብሔራዊዉ ሕብረት የሶሪያ ሕዝብ ሕጋዊ ተወካይ ለመሆኑ እዉቅና ሰጥተናል።»

የሶሪያ አማፂያን፥ ምዕራቡ ዓለም በቀድሞዉ የሊቢያ መንግሥት ላይ የወሰደዉን ወታደራዊ እርምጃ በደማስቆ ገዢዎች ላይ እንዲደግመዉ በተደጋጋሚ ሲጎተጉቱ ነበር።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የሐይል እርምጃዉን እንዳያፀድቅ ሩሲያ ማከላከሏ ሰበብ፥ የምዕራባዉያኑ ሥጋት፥ ጣልቃ ከገቡ በአካባቢዉ ይደርሳል ተብሎ የሚታሰበዉ ጥፋት፥ ምክንያት ሆነዉ አማፂያኑ የሚሹትን የምዕራቡ ሐያል ዓለም መፈፀም አልቻለም።

የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ባለፈዉ ሳምንት ከብራስልስ ያስተላለፉት መልዕክት ግን የሶሪያ አማፂዎች ብዙ የተመኘቱን ቀጥታ ወታደራዊ ድብደባ ቢያጡ እንኳን፥ በይፋ የጦር መሳሪያ ለማግኘት እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጠ ብጤ ነበር።

በብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መልዕክት የልብ ልብ የተሰማቸዉ አንካራ፥ ዶሐ፥ ካይሮና ቤይሩት የከተሙት የአማፂ ሐይላት መሪዎች ከሰወስት ሳምንት በፊት የገቡትን የድርድር ቃል ባለፈዉ ቅዳሜ ሻሩት።


የሶሪያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርና የተቃዋሚዉ የብሔራዊ ምክር ቤት መሪ ሞስኮ ዉስጥ ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ነበራቸዉ።«የሶሪያ ወዳጆች» የሚባለዉ ሥብስብ ባለሥልጣናት በመጪዉ ሳምንት ሮም ዉስጥ ይሰበሰባሉ ተብሎ ይጠበቃል።ብሔራዊዉ ምክር ቤት ባለፈዉ ቅዳሜ ባወጣዉ መግለጫዉ ግን «ሩሲያ ደማስቆን ሥለምታስታጥቅ» ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ያለዉ ስብስብ ደግሞ «በሶሪያ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመዉን በደል በዝምታ ሥላለፈ» ይላል፥ ምክር ቤቱ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ አይካፈልም።

አንድ ታዛቢ እንዳሉት የምክር ቤቱ ዉሳኔ፥ የራሱን መሪ ቃል ከማጠፍ ሌላ ማንንም አልጎዳ። በርግጥም የሶሪያ ሕዝብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ሰየመ፥ ታዛቢ ጦር አዘመተ፥ ተቃዋሚ ሐይላት ወይም ገዢዎቹ ድርድር-አሉ ጦርነት፥ ከጦርነት ጥፋት፥ ከሞት ሥደት አልዳነም።ሁለተኛ ዓመቱን አገባደደ።ይቀጥላልም ይሆናል።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ዛሬ ይብቃን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ


Audios and videos on the topic