የሶሪያ ጦርነትና የሐያላኑ ዉዝግብ | ዓለም | DW | 26.09.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሶሪያ ጦርነትና የሐያላኑ ዉዝግብ

ከሶቬት ሕብረት መፈረካከስ በኋላ ወደ ወዳጅነት ተቀይሮ የነበረዉ የረጅም ጊዜ ጠባቸዉ በዩክሬን ፖለቲካዊ ቀዉስ ሰበብ ዳግም በተጋጋመበት ወቅት መሆኑ ነዉ።በዩክሬን ሰበብ   በማዕቀብ እየተቀጣጡ፤ በጦር ሐይል እየተዛዛቱ ሶሪያ ዉስጥ መሸጉ የሚባሉ አሸባሪዎችን በጋራ እንዉጋ የሚለዉን የሞስኮዎች ጥያቄ መቀበል ለዋሽግተኖች ፖለቲካዊ ኪሳራ  ነዉ። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:00

የሶሪያ ጦርነት

የሞስኮ፤ ዋሽግተን እና  ብራስልስ ሐያላን ለየታማኞቻቸዉ ከጦር መሳሪያ እስከ ሥልጠና፤ ከገንዘብ እስከ ወታደራዊ አማካሪ፤ ከመረጃ (ሥለላ) እስከ ፖለቲካዊ ድጋፍ  ይሰጣሉ። በየዲፕሎማሲዉ መድረክ የየታማኞቻቸዉን ጥሩነት እያደነቁ፤ የየታማኞቻቸዉን ጠላቶች አረመኔያዊነት እያወገዙ ይወዛገባሉ።የሶሪያ ሕዝብ ግን ያልቃል።ስደስተኛ ዓመቱ።ዛሬም ኒዮርክ ብራስልስ፤ ዤኒቭ ፤ላይ ከቃላት ዉዝግብ፤ አሌፖ ወይም ሐላብ ላይ ከእልቂት ፍጅት፤ረሐብ  ስደት እንግልት ሌላ፤ ሌላ ነገር አይሰማም።
                          
መስከረም 30 2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የሩሲያ ጦር ሶሪያ ዉስጥ የሸመቁ አሸባሪዎች የሚላቸዉን  ሐይላት በጦር ጄት መደብደብ ሲጀምር የሞስኮ ዓላማ ድብቅ አልነበረም።ማብቂያ ባጣዉ  ጦርነት ዋሽንግተን የምትመራቸዉ የምዕራባዉያንና የዓረብ መንግሥታት የሚረዷቸዉ አማፂያን አሸንፈዉ ብቻቸዉን ደማስቆን መቆጣጠር የለባቸዉም የሚል ግልፅ ዓላማ።
የሩሲያ ባለሥልጣናት ጦራቸዉ በቀጥታ ሶሪያን እንዲደበድብ ከማዘዛቸዉ ቀደም ብለዉ ግን የአዉሮፕላን ድብደባዉን ከዩናይትድ ስቴትስና ከተከታዮችዋ ጋር ለማቀናጀት ጠይቀዉ ነበር።ቢሆንላቸዉ ሶሪያን አይደለም ድፍን ዓለምን ብቻቸዉን መቆጣጠር የሚሽት አሜሪካና ተባባሪዎችዋ

የሩሲያዎችን ጥያቄ  አልተቀበሉትም።

የአሜሪካኖች ምክንያት እንደ ሩሲያ አላማ ሁሉ ስዉር አልነበረም።የፖለቲካ ተንታኞች ደጋግመዉ እንዳሉት ምክንያቱ እሁለት የሚጠቃለል ግን ብዙ ነዉ።የመጀመሪያዉ ሐያላኑ በሶሪያዉ ጦርነት በጦር ኃይል ጣልቃ የገቡት ከሶቬት ሕብረት መፈረካከስ በኋላ ወደ ወዳጅነት ተቀይሮ የነበረዉ የረጅም ጊዜ ጠባቸዉ በዩክሬን ፖለቲካዊ ቀዉስ ሰበብ ዳግም በተጋጋመበት ወቅት መሆኑ ነዉ።በዩክሬን ሰበብ   በማዕቀብ እየተቀጣጡ፤ በጦር ሐይል እየተዛዛቱ ሶሪያ ዉስጥ መሸጉ የሚባሉ አሸባሪዎችን በጋራ እንዉጋ የሚለዉን የሞስኮዎች ጥያቄ መቀበል ለዋሽግተኖች ፖለቲካዊ ኪሳራ  ነዉ። 

ሁለተኛዉ ምክንያት በአማፂያኑ ጥቃት ጥርስ-ጥፍሩ ረግፎ ዘመነ-ሥልጣኑ ከመጀጨረሻዉ መጀመሪያ ላይ የደረሰዉን የበሽር አል-አሰድን መንግሥት ከምትረዳዉ ሩሲያ ጋር መተባበር በተዘዋዋሪም ቢሆን የአሰድን ሥርዓት ከመደገፍ የሚቆጠር መሆኑ ነዉ።
የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ፤አምና ይኸኔ፤ ሩሲያ ገሚስ አካሉ በድን የሆነዉን የአሰድን መንግሥት መደገፍዋ የሚያመጣዉ ለዉጥ የለም እያሉም ነበርም።ሐያላኑ በይፋ እንደሚሉት አላማቸዉ አሸባሪን ለማጥፋት ከሆነ የማይተባበሩት ምክንት በርግጥ ባልነበረ።መተባበሩ ቀርቶ ላለመግባባት መስማማት አቅቷቸዉ ዉዝግባቸዉ መካከሩ ነዉ አሳዛኙ። ድብደባዉም። ቀጠለ። እልቂቱም።
                      
«ሐዘንተኛ ነኝ። ሌሎቹ ልጆች ሁለት እግር አላቸዉ፤ እኔ ግን አንድ ብቻ ነዉ ያለኝ።»ትላለች ናግማን።ዘጠኝ ዓመቷ ነዉ።የአሌፖ ስደተኛ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ መጋቢት 2011 በተጀመረዉ ጦርነት ከ250 ሺሕ በላይ ሰላማዊ ሰዉ አልቋል።4,9 ሚሊዮን ተሰዷል።ከ6,5 ሚሊዮን የሚበልጥ ተፈናቅሏል።ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ ደግሞ እንደ ናግማን አካላቸዉ ጎድሏል።የወደፊት ዕድል፤ ተስፋ፤ምኞታቸዉ ተቀጭቷል።
                                   
«መማር እፈልግ ነበር።እናቴ

ትምሕርት ቤት አስገብታኝ ነበር።ግን እኔ አንድ እግር ብቻ ስላለኝ ሌሎቹ ልጆች ያበሽቁኝ ጀመር።በዚሕም ምክንያት ትምሕርቱን ተዉኩት።ከዚያ ወደዚሕ መጣን ወደ ጋዚያንቴፕ (ቱርክ) እዚሕ ደግሞ ትምሕርት ቤት አልተከፈተም።»
ሐያላኑ ሲወዛገቡ፤ ሐያላኑ የሚያስታጥቋቸዉ የሶሪያ ፖለቲከኞች ሲጫረሱ ክፉ ደጉን የማያዉቁት ሕፃናት፤ አቅመቢስ አረጋዉያን እና ሴቶች ያለጥፋታቸዉ ያልቃሉ።
የሩሲያ ጦር የአሸባሪ ይዞታ የሚላቸዉን አካባቢዎች መደብደብ ከጀመረ ወዲሕ ክፉኛ ከጠፉት ከተሞች አንዷ የሶሪያዋ ትልቅ ከተማ አሌፖ ናት።ፕሬዝደት በሽር አልአሰድ ግን በሰላማዊ ዜጎቻቸዉ ላይ ከሚደርሰዉ እልቂት፤የአካል ጉዳትና ስደት፤ ይልቅ ለዘመነ-ሥልጣናቸዉ መራዘም የሩሲያ ጦር ያደረገላቸዉን ድጋፍ ማወደሱን ነዉ የመረጡት።
አሰድ አምና ሕዳር ማብቂያ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የሩሲያ ጦር ሶሪያ ዉስጥ የሸመቁ አሸባሪዎችን በማዳከሙ ረገድ በሁለት ወራት ዉስጥ ያስመዘገበዉ ዉጤት፤ ዩናይትድ ስቴትስ እና ተከታዮችዋ በአንድ ዓመት ዉስጥ ካስገኙት ዉጤት ብዙ የበለጠ ነዉ ነበር ያሉት።
የአሰድ መግለጫ ከተሰማ በኋላ የተጋለጠ አንድ ሚስጥር ግን አሰድም፤ የተቀረዉ ፖለቲከኛም ሥለ ምሥራቅ-ምዕራቦች ጠብ ልዩነት የሚናገር-የሚሰማዉን ከልቡ ከመቀበሉ በፊት ማሰብ፤ ማሰላሰል እንዳለበት አስጠንቃቂ ብጤ ነዉ።
ዩናይትድ ስቴትስ ድብደባዉን ለማቀናጀት ከሩሲያ የቀረበላትን  ጥያቄ ዉድቅ  ባደረገች በወሩ  ከሩሲያ ጋር በድብደባዉ የሚካፈሉት የሩሲያና የአሜሪካ መራሹ ጦር  ሶሪያ ዉስጥ እንዳይጋጩ የሚጠቅም  የመግግባቢያ ስምምነት ተፈራረመች።ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ ግን ከሚስጥሩ መጋለጥ ይልቅ የበሽር አል-አሰድን መግለጫ ወይም ሩሲያ  ባጭር ጊዜ የተሻለ ዉጤት የማምጣትዋን ሐቅ ለማጣጣሉ ቅድሚያ የሰጡ መስለዉ ነበር።

ኦባማ የአሰድ መግለጫ በተሰማ በሁለተኛዉ ቀን «ሩሲያ የምትመራዉ የሁለት ሐገራት ሕብረት ነዉ» አሉ ።«የራስዋ የሩሲያ እና የኢራን ሕብረት።» የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት።
ዩናይትድ ስቴትስ ከምትመራቸዉ አስራ-ሰባት መንግሥታት፤ እና ዘጠኝ አማፂ ቡድናት ጋር ሲነፃፀር ሩሲያ የምትመራቸዉ መንግሥታት ወይም ቡድናት በርግጥ ኢምንት ናቸዉ።ሰወስት መንግሥታት ምናልባት አራት አማፂ ቡድናት።
ይሁንና የሕዝብ እልቂት ፍጅት፤ ስደትን፤ የሐብት ንብረት ዉድመትን ለማባባስ የቁጥር እና የሐብት ብዛት ብዙም ትርጉም እንደሌለዉ ባለፈዉ አንድ ዓመት ሶሪያ ዉስጥ የታየዉ ግልፅ ምስክር ነዉ።ሩሲያ ጣልቃ ከመግባትዋ በፊት የአልአሰድ መንግሥት ካልተወገደ መፍትሔ የለም ሲሉ የነበሩት የዩናይትድ ስቴትስ እና የተባባሪዎችዋ መንግሥታት ባለስልጣናት ለሶሪያዉ ጦርነት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲፈለግ መጎትጎት መጀመራቸዉ የእኒያ ኢምንት ሐይላትን ተፅዕኖ አመልካች ነዉ።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተደረጉ ድርድሮች እና የተኩስ አቁም ስምምነቶች እስካሁን ያመጡት ተጨባጭ ዉጤት የለም።የመጨረሻዉ የተኩስ አቁም ስምምነት ካበቃ በኋላ አዲስ የተኩስ አቁም ዉል

ለማድረግ የሶሪያ ወዳጆች የሚባሉት መንግሥታት ባለፈዉ ሳምንት ኒዮርክ ዉስጥ ያደረጉት ድርድርም ያለዉጤት ነዉ ያበቃዉ።
በሶሪያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ስታፋን ደ ሚስቱራ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት ሐያላኑ መንግሥታት የየሚደግፏቸዉ ወገኞች ዉጊያዉን እንዲያቆሙ ካላደረጉ የተረፈዉ አማራጭ የእስካሁኑ ነዉ።ጦርነት።
                        
ተፋላሚ ሐይላት የደ ሚስቱራ ማስጠንቀቂያ እስከሚሰማ አልጠበቁም።በተለይ አሌፖ ላይ የቀጠሉት ጦርነት ካለፈዉ አርብ ወዲሕ ብቻ በትንሽ ግምት ከመቶ የሚበልጡ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል።በብዙ ሺሕ የሚቀጠሩ ምግብ፤ ዉሐና መድሐኒት አጥተዋል።ካለፈዉ አርብ ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ እንዳዲስ የቀጠለዉ ዉጊያ በዴ ሚስትሯ አገላፅ የሶሪያዉ ጦርነት ከተጀመረ ጀምሮ ከነበሩት ከፍተኛ ዉጊያዎች አንዱ ነዉ።
                  
«ያለፈዉ ሳምንት (ዉጊያ) ስደስተኛ ዓመቱን ሊደፍን ጥቂት በቀረዉ አጥፊ ጦርነት ከተደረጉ አስከፊ ዉጊያዎች አንዱ ነዉ።»የሶሪያ ወዳጆች የተባለዉ ስብብሰብ ተኩስ አቁሙ የሚራዘምበትን መንገድ ለመፈለግ ያደረገዉ ሙከራ ከከሸፈ በኋላ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ምክር ቤት ትናንት ሥለ ጦርነቱ ለመነጋገር ተሰብስቦ ነበር።ይሁንና የጦርነቱ ዘዋሪዎች የዩናይትድ ስቴትስና የሩሲያ ዲፕሎማቶች ከስብሰባዉ አዳራሽ የገቡት ከነልዩነታቸዉ በመሆኑ ስብሰባዉ እሰጥ አገባዉን ከማናር ባለፍ የተከረዉ የለም።
                    
«ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት አድን ርዳታ እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ ሩሲያና አሰድ የሰብአዊ ርዳታ የጫኑ ቅፍለቶችን፤ ሆስፒታሎችንና ርዳታ የሚያቀብሉ ወገኖችን በቦምብ ይደበድባሉ።ሩሲያ ዛሬ ይሕ ጥቃት አሸባሪነትን ለመዋጋት ያለመ ነዉ ብላ መከራከሯ የማይቀር ነዉ።በዚሕ ጥቃት የተገደሉት ሰዎች አሸባሪዎች ወይም ተባባሪዎቻቸዉ ናቸዉ ትልም ይሆናል።ይሕ እንቆቅልሽ ነዉ።»

የዩናይትድ ስቴትሷ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር።የሩሲያዉ አምባሳደር ቪታሊ ቹርኪን አሜሪካዊቷ አቻቸዉ የጠበቁትን አላሉም።አሰጥ አገባዉ ለመናሩ ግን መልዕክታቸዉ ምስክር ነዉ።ጦርነቱን ማስቆም የሩሲያ ብቻ ሐላፊነት አይደለም።
                               
«ይሕን ጦርነት ማስቆም የሩሲያ ጉዳይ ብቻ አይደለም።ለኛ በጣም አስፈላጊዉ ነገር አሜሪካ ከምትመራዉ ሕብረት ጋር ተባብረዉ የሚሰሩ ሰዎች  አል ኑስራ ከተሰኘዉ አሸባሪ ቡድን መነጠላቸዉ ነዉ። ከነዚሕኞቹ ወገኖች ይልቅ ከለዘብተኛ ተቃዋሚዎች ጋር ተባብረን መስራት እንፈልጋለን።»
የሐያላኑ መንግሥታት ባለሥልጣናት

ከቦምብ፤ መድፍ፤ ታንኩ ጮኸት በብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኙ ዉብ አዳራሽ- ሕንፃዎች ተቀምጠዉ ሲነታረኩ በየሥፍራዉ በላኩት፤ በሸጡ፤ ባስታጠቁት ጦር መሳሪያ ሺዎች ይረግፋሉ።ሚሊዮኖች ይቆስላሉ።ብዙ ሚሊዮኖች ይሰደዳሉ።ዛሬ የጎላዉ ሶሪያ ነዉ።
ከኢራቅ እስከ ደቡብ ሱዳን፤ ከሊቢያ እስከ አፍቃኒስታን፤ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እስከ የመን፤ ከምሥራቅ ዩክሬን እስከ አፍቃኒስታን የሆነና የሚሆነዉ ከሶሪያዉ የተለየ አይደለም።የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ባለፈዉ አርብ እንዳሉት ሐያላን መንግሥታት ግጭቶችን በዲሎማሲ ለመፍታት ካልፈቀዱ ዓለም እስካሁን ካየችዉ የከፋ ደም መፋሰስ ማየቷ አይቀርም። 
                                  
«ምርጫም አለን።የዲፕሎማሲያዊ ሐይልን ገቢር ማድረግ አለያም እጃችንን አጣጥፈን በመቀመጥ በሥፍራዉ የተቀጣጠሉ በርካታ ግጭቶች (ሲፋፋሙ) ማየት።ሶሪያ፤ ሊቢያ፤የመን፤ምሥራቃዊ ዩክሬን።ተስፋ ቆርጠን፤ እነዚሕ ግጭቶች እንዲባባሱ እንተዋቸዉ? ወይስ ሐላፊነታችንን ለመወጣት የሚገጥመንን ፈተና ተቋቁመን መፍትሔ ለማግኘት እንጣር? ምርጫዉ የኛ ነዉ።»

ምርጫዉ የሐያላኑ ነዉ።ከሁለት አንዱን መምረጥ-አለመምረጣቸዉን በግልፅ አለማሳወቃቸዉ እንጂ ክፋቱ።


ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ

                         
 

Audios and videos on the topic