የሶሪያ ጦረንትና የሸምጋዩ ስንብት | ዓለም | DW | 19.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሶሪያ ጦረንትና የሸምጋዩ ስንብት

የሶሪያ ሕዝብ ጉልበት፤ሐብቱ ሞልቶ የተረፋቸዉ የሚችሉትን እስኪያደርጉ መጠበቅ አልቻለም።ያልቃል።ከመቶ ሐምሳ ሺሕ እስከ ሁለት መቶ ሺሕ የሚደርስ ህዝብ ተገድሏል።ሌላዉ ይሰደድ-ይፈናቀላል።ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተሰዷል ወይም ተፈናቅሏል።ቀሪዉ ይሸማቀቃል።

የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን የካቲት 2012(ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያን አቆጣጠር ነዉ)የሶሪያ ተፋላሚዎችን እንዲያደራድሩ ሲሾሙ ዓመት የደፈነዉ ጦርነት በሰላም የሚቆምበት ጭላንጭል የፈንጥቀ መስሎ ነበር ።ግን ሥድስት ወር አልፈጀም።በነበርመቅረቱተረጋገጠ።አናን ቢሔዱ ላኻዳር ብራሒሚ ተተኩ።ሃያ ወር።ብራሒሚም ሔዱ።ሶሪያ የተረፋት ጦርነት፤ እልቂት፤ ዉድመት ሥደት ነዉ።ላፍታ እንዴት ለምን እንበል አብራችሁኝ ቆዩ።

የደማስቆ ገዢዎች በጥይት፤ ቦምብ አረር፦ እልቂት ትርምሱ መሐል ምርጫ ይላሉ።ዋሽግተኞች ዘንድሮም እንዳምና ሐቻምናዉ የደማስቆ ገዢዎችን ያወግዛሉ።«አሰድ ያዘጋጁት ምርጫ፤ ለሶሪያ ሕዝብ፤ለዴሞክራሲ ለዓለምም ቧልት ሥድብና ማወናበጃ መሆንን በአንድነት አዉግዘናል።»

የዩናኅትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ባለፈዉ ሳምት።የለንደኖች ጠንከር ከረር ያለ ነዉ።ይዝታሉ፤ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊሊያም ሔግ መንግሥታቸዉና አጋሮቹ ባለፉት ሰወስት ዓመታት እንዳደረጉት ሁሉ የፕሬዝዳንት በሽር አል-አሰድን መንግሥት ለማስወገድ አበከረዉ እንደሚጥሩ እስታዉቀዋል።

«ለለዘብተኛ ተቃዋሚዎች፤ለብሔራዊ ሕብረት፤ ለወታደራዊዉ ላዕላይ ምክር ቤትና ለተባባሪዎቹ ታጣቂ ቡድናት የምንሰጠዉን ድጋፍ እናጠናክራለን።የአሰድን ሥርዓት ለሚያደርሰዉ ሽብር ተጠያቂ ለማድረግ አቅማችን የፈቀደዉን ሁሉ እናደርጋለን።»

የሶሪያ ሕዝብ ጉልበት፤ሐብቱ ሞልቶ የተረፋቸዉ የሚችሉትን እስኪያደርጉ መጠበቅ አልቻለም።ያልቃል።ከመቶ ሐምሳ ሺሕ እስከ ሁለት መቶ ሺሕ የሚደርስ ህዝብ ተገድሏል።ሌላዉ ይሰደድ-ይፈናቀላል።ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተሰዷል ወይም ተፈናቅሏል።ቀሪዉ ይሸማቀቃል።

ሞስኮዎች ከዚሕ ቀደም እንዳደረጉት ሁሉ የደማስቆ ገዢዎችን በሐይል ለማስወገድ ምዕራባዉን መንግሥታትና የመካከለኛዉ ምሥራቅ ተከታዮቻቸዉ የሚያደርጉትን ጥረት ተቃዉመዉታል።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩሲያዉ አምባሳደር ቪታሊ ቹርኪን ባለፈዉ ማክሰኞ ለፀጥታዉ ምክር ቤት ስብሰባ እንደነገሩት የአሰድን መንግሥት ለመወንጀል የሚደረገዉን ጥረት ሩሲያ ትቃወማለች።

ከደማስቆ- ሪያድ-ዶሐ፤ ከአንካራ-ዋሽግተን-ለንደን-ሞስኮ እንደተሰማዉ ጦርነቱ በርግጥ ይቀጥላል።በዚሕ መሐል ማነዉ ሰላማዊ መፍትሔ የሚፈልገዉ።«ማንም አይችልም» ይላሉ-አንቶኒ ኮርድስማን።መንበሩን ዋሽግተን ያደረገዉ ጥናት ተቋም የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ ጉዳይ አጥኚ።

«አሁን ባለበት ሁኔታ ሠላማዊ መፍትሔ ለማምጣትም ሆነ፤ ሠብዓዊ ድቀቱን ለማስቆም የሚችል ማንም የለም።ጥፋቱን እያየን ነዉ።ጦርነቱ እየከፋ ነዉ።ይሕንን ማንም ሊያስቆም አይችልም።»

አልጄሪያዊዉ ዲፕሎማት ላኽዳር ብራሒሚም ዓመት-ከመንፈቅ ሞከሩ። አልቻሉም።ባለመቻላቸዉ አዘኑ፤ ልክ እንደ ድሮ አለቃቸዉ እንደ ኮፊ አናን በቃኝ አሉ-በቀደም።«ሶሪያን በዚሕ መጥፎ ሁኔታ ትቼ ይሕን ሐላፊነቴን በመልቀቄ በጣም አዝናለሁ።»

መጋቢት 2011 የሶሪያ ሕዝብ አመፅ-ከቱኒዚያ ግብፆ ብጤዉ ይልቅ እንደ ሊቢያ ባፍታ ወደነፍጥ ዉጊያ ሲለወጥ በዓለም ሁሉንም ማድረግ የሚችሉት-ሠላማዊ መፍትሔን እንዲቻል አላደረጉትም ነበር።የዓለም አድራጊ ፈጣሪዎች ባለመፈለጋቸዉ የማይቻለዉ እንዲሕ ቀጠለ።

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ፤ እግረኛ ጦር ሳያዘምት ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ገድሎ፤ የአርባ ዘመን አገዛዛቸዉን ማጥፋቱ የዓለም ምርጥ ጦር ድፍን አስር-ዓመት አፍቃኒስታን ዉስጥ ለገጠመዉን ኪሳራ ማካካሻ፤ ለሞራሉ ማነቃቂያከሁሉም በላይ ኒኮላይ ሳርኮዚን በመሳሰሉ አዛዦቹ ላይየሚሰነዘረዉን ትችት ወቀሳ ያስወገደ ነበር።

የዋሽንግተን፤ለንደን፤ ፓሪስ ፖለቲከኞች ሊቢያየጣሉትን ግዳይ እና ያገኙትንድል በደማስቆ ገዢዎች ላይ በሚያንቆረቁሩት ዛቻ ማጀባቸዉ፤ምርጥ ጦራቸዉ በሽር አል አሰድን ዳግማዊ ቃዛፊ ወይም ሳልሳዊ ሳዳም፤ ሶሪያን ዳግማዊት ሊቢያ ወይም ኢራቅ ሳያደርግ ከሚሽጉ አይገባም አሰኝቶ ነበር።

ይሁንና ኔቶ ሕዳር 2011 ባወጣዉ መግለጫ ከፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ካልተጠየቀ በተስቀር ሶሪያን የመደብደብ ዕቅድ እንደሌለዉ በማስታወቁ ጦሩ ሶሪያን ይመታል አይመታም የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞችን መላምት፤የመገናኛ ዘዴዎችን ዘገባ፤የደማስቆና የደጋፊዎቻቸዉን ሥጋትም መረገዉ።

አሜሪካ መራሹ የምዕራባዉያን የጦር ድርጅት የምዕራባዉያኑን ጠላት ለማጥፋት ሶሪያንእንደማይ ደበድብ ከብራስልስ ባስታወቀበት ሳምንት ግን አሜሪካ መራሹ ጦር ሳዳም ሁሴንን አስወግዶ የባግዳድን ቤተ-መንግሥት ያሰረከባቸዉና አሜሪካ መራሹ ኔቶ ቃዛፊን ገድሎ ትሪፖሊ ቤተ-መንግሥት የዶላቸዉ የምዕራቦቹ ታዛዦች ግራ አጋቢ፤አስቂኝ፤ አሳዛኝ እርምጃ ተሰማ።

ነገሩ እንዲሕ ነዉ። አዲሶቹ የትሪፖሊ ገዢዎች በጦርነት የወደመች፤በየጦር አበጋዞች ወይም በጎሳ መሪዎች በየአዉራጃዉ የተከፋፈለች ሐገራቸዉን ከመጠገን፤ይልቅ ቃዛፊ ያጠራቀሙትን ዶላርና ጠመንጃ እየቀረቀቡ ለሶሪያ አማፂያን ያስታቅፉ ገቡ።በመቶ ሚሊዮን ከሚገመተዉ ገንዘብና ግምቱ ካልታወቀዉ የጦር መሳሪያ በተጨማሪ ሕዳር 2011 ብቻ ከስድት መቶ የሚበልጡ ሊቢያዉያን ታጣቂዎች የደማሶቆ መንግሥትን ለመዉጋባት ሶሪያ ዘምተዋል።

ከትሪፖሊዎች ቀድመዉ የባግዳድን ቤተ-መንግሥትን ከአሜሪካኖች የተረከቡት የኢራቅ ገዢዎች ባንፃሩ የሿሚ፤ሸላሚዎቻቸዉ ዋና ጠላት ኢራንለፕሬዝዳት በሽር አል አሰድ መንግሥት የምትልከዉ ጦር መሳሪያ በኢራቅ በኩል እንዲጓዝ ፈቀዱ።ለአሰድ መንግሥት የናፍጣ እርዳታም ይሰጡ ገቡ።

ምዕራባዉያን ትሪፖሊና ባግዳድ ላይ በተመሳሳይ መንግድ ለገዢነት ያበቋቸዉ ሐይላት ተቃራኒ አቋም የመያዛቸዉ ሕቅ ግራ የማጋባት፤ የማሳደመም ማስፈገጉን ያክል የሶሪያዉ ጦርነት ከፖለቲካ አልፎ ዘርን፤ ከጥቅም ርቆ፤ ስልታዊነትን፤ ከሃያላኑ ተሻግሮ ብዙዎችን እንዲነካካ የመደረጉ እዉነት ገና በተጀመረበት ዓመት መፍጠጡ በርግጥ አሳዛኝ ነበር።ነዉም።

ዩናይትድ ስቴትስ የባግዳድን ቤተ-መንግሥት ያስረከበቻቸዉ የኢራቅ የሺዓ ገዢዎች ከዩናትድ ስቴትስ ጠላት ከሺአዋ ኢራን ጋር አብረዉ የአላዊቶቹን የደማስቆ ገዢዎችን ሲረዱ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅ ዉስጥ አሸባሪ በማለት ስትወጋቸዉ የነበሩት የሱኒ ሸማቂዎች ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ከሚረዱቸዉ የሶሪያ አማፂያን ጋር ሆነዉ የደማስቆ ገዢዎችን ይወጋሉ።

ዩናይትድ ስቴትስ የምተመራቸዉ መንግሥታት የአሰድን መንግሥት ለሚወጉ አማፂያን ድጋፍ ርዳታቸዉን ለማቀናጀት «የሶሪያ ወዳጆች»ያሉትን ማሕበር ሲመሰርቱ፤የሶሪያን መንግሥት የምትደግፈዉ ሩሲያ ለአሰድ መንግሥት የምሰጠዉንጦር መሳሪያ አጠናከረች።በዚሕ መሐል ነዉ የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ጦርነቱ በድርድር የሚፈታበትንብልሐት እንዲፈልጉ የተሾሙት።የካቲት 2012።

የሶሪያን ጦርነት ግራ-ቀኝ ቆመዉ የሚጋግሙት የዓለም ሐያልን-የአረብ-ፋርስ ቱጃሮችን የቃል-ድርጊት ፤ የጥቅም-ሠብአዊነት ተቃሮኖን፤ የዓለምን ግዙፍ ማሕበር ለስምት ዓመታት ከመሩት ኮፊ አናን ይበልጥ የሚያዉቅ ዲፕሎማት ማግኘት ሲበዛ ከባድ ነዉ።ይሁንና ጋናዊዉ የዓለም ምርጥ ዲፕሎማት አንድም አስከፊዉን እልቂት ለስቆም ልሞክር ከሚል ቅንነት፤ ሁለትም የሐያላኑን ግፊት በመፍራት፤ ሰወስትም እንደ አብዛኛዉ ተራ ሰዉ ከሐያላኑ ድርጊት ይልቅ-በቃል ብሂላቸዉ ተታለዉ ሐላፊነቱን ተቀበሉት።የሠላም ዕቅድ ነደፉ።የፀጥታዉ ጠበቃ ምክር ቤትም ዕቅዳቸዉን አፀደቀዉ

«ፖለቲካዊ ዉይይት እንዲደረግ፤ሕዝብ ከሚኖርባቸዉ ማዕከላት ከባድ የጦር መሳሪዎችና ወታደሮች እንዲነሱ፤ሠብአዊ ርዳታ እንዲቀርብ፤እስረኞች እንዲለቀቁ፤ የመንቀሳቀስ ነፃነት እንዲከበር እና ጋዜጠኞች ተዘዋዉረዉ እንዲዘግቡ የሚጠይቀዉን ዕቅድ (የፀጥታዉ) ምክር ቤት አፅድቆታል።»

የአናን የሠላም ዕቅድ መጽደቁ ከኒዮርክ ሲዘገብ-በምክር ቤቱ ዉስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ካላቸዉ የሰወስቱ፤የዩናትድ ስቴትስ፤የብሪታንያና የፈረንሳይ ሹማምንት ፓሪስ ላይ ተሰብስበዉ ለሶሪያ አማፂያን የሚሰጡትን «ገዳይ ያልሆነ» ያሉትን የትጥቅና ስንቅ ድጋፍ ለማጠናከር ወስነዉ ነበር።ሐምሌ 2012።

ከፓሪሱ ዉሳኔ፤ ጥቂት ሳምታት ቀድሞ ብሎ የዩናይትድ ስቴትሱ የስለላ ድርጅት CIA ባለሙያዎች የሶሪያ አማፂዎችን ዮርዳኖስና ቱርክ ዉስጥ ማደራጀት ፀረ-ታንክን ጨምሮ የተለያዩ ጦር መሳሪዎችን ማስታጠቃቸዉ ተዘገበ።የአራተኛዋ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላት ሩሲያ ባንፃሩ እስር መለስተኛ የጦር መርከቦቹዋን ወደ ሜድትራንያን ባሕር አዘመተች።ከዚያ በፊት በርካታ የሩሲያ የጦር አማካሪዎች ደማስቆ መግባታቸዉ በሰፊዉ ሲነገር ነበር።

ቀጠርና ሳዑዲ አረቢያ የሶሪያ አማፂያንን ቱርክ ዉስጥ ለማሰልጠንና ለማስታጠቅ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በይፋ መርጨት የጀመሩትም አናን ባለሥድስት ነጥብ ያሉትን የሰላም ዕቅድ ተፋላሚ ሐይላትና አፋላሚ መንግሥታት ከልባቸዉ እንዲቀበሉት ሽቅብ ቁል ቁል በሚሉበት ወራት ነበር።

የሶሪያን አማፂያን ለማስታጠቅ፤ለማሠልጠንና የደማስቆ መንግሥት ወታደሮችን ለማስኮብለል አንዲት ሳዑዲ አረቢያ ብቻ አራት ቢሊዮን ዶላር ከስክሳለች።ቀጠር ሰወስት ቢሊዮን።ኩዌት፤ ባሕሬን፤ሊቢያ ቱርክ፤ዮርዳኖስም በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አዉጥተዋል።

UN-Informationsgipfel, Weltinformationsgipfel in Tunis, Kofi Annan

ኢራን በተቃራኒዉ ለደማስቆ መንግሥት ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ሰጥታለች።የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቡላሕ ተዋጊዎቹን አዝምቷል።እስራኤል በተቃራኒዉ የሶሪያን ወታደራዊ ይዞታዎች ካንዴም ሁለቴ በጦር አዉሮፕላን ደብድባለች።

በዚሕም ብሎ በዚያ የፕሬዝዳንት በሽር አል-አሰድን መንግሥት ለማስወገድ ዩናትድ ስቴትስ የምትመራና የምታስተባብራቸዉ ሰባ ሐገራት «የሶሪያ ወዳጆች» በሚል ማሕበር ባንድ አድመዋል።በነዚሕ መንግሥታት የሚደገፉት ከሱኒ ደፈጣ ተዋጊዎች እስከ አልቃዳ አሸባሪዎች፤ ከከዱ የጦር አባላት እስከ ኩርድ አማፂዎች የደማስቆ መንግሥትን ይወጋሉ።ከሞስኮ እስከ ቤጂንግ፤ ከቴሕራን እስከ ባግዳድ፤ከአልጀርስ እስከ ፒዮንግዮንግ የሚገኙ መንግሥታት፤ ሒዝቡላሕን የመሳሰሉ በደፈጣ ዉጊያ የተካኑ ሸማቂዎች አንድም የአሰድን መንግሥት ይደግፋሉ አለያም የአሰድ መንግሥት ጠላቶችን ይጠላሉ።

ግማሽ ዓለምን ያዉም የምድራችን አድራጊ ፈጣሪዎችን ግራ-ቀኝ ያሠለፈዉ ጦርነት በጋመበት መሐል አናን ባለ-ሥድስት ነጥብ የሠላም ዕቅድ ነድፈዉ ከዋሽግተን፤ ሞስኮ፤ከቤጂንግ፦ ለንደን፤ ከፓሪስ፤ በርሊን፤ ከኒዉ ዮርክ-ካይሮ ከተሕራን ሪያድ፤ ከዶሐ አንካራ፤ ከአማን ደማስቆ ባተሉ።በስድስተኛ ወራቸዉ እጅ ሰጡ።

«እኛም የሶሪያ ሕዝብም ተጨባጭ እርምጃ ባስቸኳይ በምንፈልግበት ባሁኑ ወቅት፤ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት፤ አንዱ በሌላዉ ላይ ጣቱን መቀሰሩ እና መዘላለፉ ቀጥሏል።ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፤የአካባቢዉ ኋላትን ጨምሮ ከልብ የመነጨ ግፊት ካላደረጉ በስተቀር የሶሪያ መንግሥትና ተቃዋሚዎቹ ለፖለቲካዊ መፍትሔ የሚያስፈልገዉን እርምጃ እንዲወስዱ ማሳመን እኔም ሆንኩ ሌላ ማንም ሰዉ አይችልም።ሥለዚሕ (የመጀመሪያዉ) ዘመነ-ሥልጣኔ ነሐሴ ማብቂ ሲያበቃ ተልዕኮዬን እንደማልቀጥል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ለአረብ ሊግ ዋና ፀሐፍት አሳዉቄያለሁ።»

ኮፊ አናን እኔም ሆንኩ ሌላ ማንም አይችልም ያሉትን ሐላፊነት የሰማንያ አመቱ አልጄሪያዉ ዲፕሎማት ላኽዳር ብራሒሚ እችለዋለሁ አሉ።ወይም ይችሉታል ተባሉ።ወይም አናን እንደ አስፈላጊ ያሉት ዓለም አቀፍ ግፊት ይደረጋል ተባሉ።ብቻ ባናዱ ወይም በሁሉም ምክንያት አናን ቢሄዱ ብራሒሚ ተተኩ።

አሮጌዉን ጦርነት ባዲስ ሥልት ለማስቆም፤ አሮጌዉ ዲፕሎማት አዲስ አቅድ ነድፈዉ እንደቀዳሚያቸዉ ከርዕሠ-ከተማ ርዕሠ-ከማ ይባትሉ ገቡ።ጦርነት ሽብሩ ግን ባሰ እንጂ አልቀነሰም።የሶሪያ ሕዝብም ከሞት፤ ስደት፤ ከረሐብ እንግልት ሌላ የተረፈዉ የለም።ጥንታዊቱን፤ ታሪካዊቱን ሐገር ለመቆጣጠር የሚራኮቱት የዓለም ሐያል-ሐብታም መንግሥታት አቋምም አልተለወጠም።ወራት መጥተዉ ሔዱ።ሃያ።ብራሂሚም እንደ አናን በቃኝ አሉ።

«ቀዉሱ እንደሚቆም እርግጠኛ ነኝ።ጥያቄዉ ግን፤ እና ደግሞ በጉዳዩ ሐላፊነት ያለባቸዉና ተፅዕኖ ማደረግ የሚችሉ ሁሉ ማወቅ ያለባቸዉ ጥያቄ ሶሪያ የምናዉቃት ሶሪያ ዳግም እስክትሆን ድረስ ስንት ተጨማሪ አስከሬን መቆጠር፤ ምን ያሕልስ ተጨማሪ ጥፋት መድረስ አለበት የሚለዉ።»

በርግጥም የሐያል ቱጃሮቹ የጥቅም ጥማት ምን ያሕል ደም፤ ያረካዉ ይሆን።ምን ያሕል ጥፋስ ይበቃዉ ይሆን-እና እስከመቼ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ።ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic