የሶሪያ ጥያቄና የጀርመን መልስ | ዓለም | DW | 09.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሶሪያ ጥያቄና የጀርመን መልስ

የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አልአሳድ ጀርመን የሶሪያውን ቀውስ እንድትሸመግል እንደሚፈልጉ አስታወቁ። ፕሬዝዳንቱ ለአንድ የጀርመን መጽሔት እንዳሉት የጀርመን ልዑካን ሶሪያ መጥተው የሃገሪቱን አጠቃላይ ይዞታ እንዲመለከቱና በተጨባጩ ሁኔታ ላይ ከደማስቆ መንግሥት ጋር እንዲወያዩ ጠይቀዋል። ይሁንና የጀርመን መንግስት የአሳድን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

ተንታኞችም የበርሊን ውሳኔ ትክክለኛ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ሶሪያ በዓለም ዓቀፍ የኬሚካል ጦር መሣሪያ ጠበብት ቁጥጥር እየተደረገባት፣ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎቿን ክምችት መውደም በጀመረበት በአሁኑ ወቅት የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ጀርመን በሶሪያው ቀውስ ዲፕሎማሲያዊ ሚና እንድትጫወት መጠየቃቸው ብዙዎችን አስገርሟል። አሳድ DER SPIEGEL ለተባለው የጀርመን መጽሔት በሰጡት ረዘም ያለ ቃለ ምልልስ ለሶሪያው ብጥብጥ አንዳችም ሃላፊነት ከመውሰድ ተቆጥበዋል። ከዚያ ይልቅ ጀርመን የሶሪያውን ውዝግብ ሸምጋይ እንድትሆን እንደሚፈልጉ መልዕክት አስተላልፈዋል። «እርግጥ ነው የጀርመን ልዑካን ሶሪያ መጥተው ትክክለኛውን ሁኔታ አይተው እንዲወያዩ እፈልጋለሁ ሲሉ አሳድ ለመጽሔቱ አስታውቀዋል። ሶሪያን መጎብኘት ማለት መንግሥትን መደገፍ ማለት አይደለም ያሉት አሳድ ሶሪያ መጥቶ መነጋገር መወያየትና ማሳመን እንደሚቻልም ተናግረዋል። ሆኖም ሶሪያን ማግለል አለብን ብላችሁ ካሰባችሁ እናንተም ራሳችሁ ታገላላችሁ ብለዋል አሳድ። ይህን የአሳድ ግብዣ ግን ጀርመን ሙሉ በሙሉ አልተቀበለችም።

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ለሶሪያ ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶሪያ ልዩ ልዑክ ላክዳር ብራሂሚ መኖራቸውንና ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመሻት የጀመሩትን ሽምግልና ጀርመን ሙሉ በሙሉ እንደምትደግፍ አስታውቀዋል። ቬስተርቬለ ከዋና ከተማይቱ ደማስቆ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ በነሐሴ የተፈፀመውን የመርዛማ ጋዝ ጥቃት አሳድ መካዳቸውንም ተችተዋል፤ ማስተባበልና መወዛገብ ለሶሪያ ሰላማዊ መፍትሄ ፍለጋ አይበጅም ሲሉ። በኮሎኝ ዩኒቨርስቲ የዓለም ዓቀፍ ፖለቲካና የውጭ ፖለቲካ መምህር ቶማስ የገርም የመንግሥትን ውሳኔ ደግፈዋል። ጀርመን ልሸምግል ብትል እንኳን እንደማይሆን ነው ያስረዱት።«በተለይ ዩናይትድ ስቴትስና ሩስያ በሶሪያ ግጭት ተቃራኒ አቋም ነው ያላቸው። የጀርመን መንግሥት ዩናይትድ ስቴትስና ሩስያን ልሸምግል ቢል ከፖለቲካዊ እብሪት ነው የሚቆጠረው።»እንደ ዬገር የሸምጋይነት ሚና በራሱ ለጀርመን አጋሮች አደገኛ ምልክት ነው። ጀርመን ራሷን ከዓለም እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን ፖለቲካዊ ውዝግብ የመፍታት ችሎታ እንዳላት አድርጋ የምትወስድም ይመስልባታልም ብለዋል ዬገር። እናም ይላሉ ዬገር ጀርመን ብቻ ሳትሆን የአውሮፓ ሃገራት በሙሉ ከዚህ መቆጠብ ይኖርባቸዋል።«የአውሮፓ መንግሥታት ለሶሪያው ቀውስ መፍትሄ ፍለጋውም ሆነ ለመፍትሄው የሚበጅ አስተዋጥኦ ማደረጉ ከአቅም በላይ ሆኖባቸዋል። ውዝግቡ በውጭ አመራር ፖለቲካቸው ሊያስወግዱት የሚችሉት ጉዳይ አይደለም።»

ጀርመን ከሶሪያ በኩል የቀረበላትን የሽምግልና ጥያቄ አለመቀበሏ ትክክለኛ እርምጃ በመሆኑ የሚስማሙት በጀርመን ዓለም ዓቀፍና የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም የመካከለኛ ምሥራቅ ጉዳዮች ተንታኝ ጊዶ ሽታይንበርግ ደግሞ ሁኔታውን ጀርመን በአውሮፓ ካላት ተፅዕኖና በሶሪያ ላይ ከወሰደችው አቋምም ጋራ ያያይዙታል።«ጀርመን በሶሪያ ጉዳይ በአውሮፓ ደረጃ ያን ያህል ተፅዕኖ ማድረግ አትችልም። ይህ የሚሆነው ግን በጀርመን አቋም ምክንያት አይደለም። አዎ ጀርመን ፖለቲካዊ መፍትሄ ይፈለግ በሚለው አቋሟ እንደፀናች ነው። ወታደራዊ እርምጃን መፍትሄ አይሆንም በሚለው መሠረታዊ አቋም፣ አትቀበለውም። የጀርመናውያን አቋም ችግሩ ሁኔታው ቢለዋወጥም ምንም ዓይነት አካሄድ ቢኖረው የጀርመን አቋም የፀና መሆኑ ነው።»በተንታኝ ዬገር እምነት ጀርመን ሰብዓዊ እርዳታ በመስጠት መፅናትዋ ትክክል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ጀርመን ስለሶሪያ የሚካሄደው ውይይት ወደ መፍትሄው እንዲያመራ በማድረግም ልታግዝ ትችላለች።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic