የሶሪያ ግጭትና የዓለም አቋም | ዓለም | DW | 20.03.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሶሪያ ግጭትና የዓለም አቋም

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንና የአረብ ሊግን የወከሉት የአፍሪቃዊዉ ዲፕሎማት ጥረት ይቀጥላል።የሶሪያም እልቂት-እንዲሁ።አናን የሚደርሱበት ዉጤት-አይነት ግጭት ግድያዉ የሚቆምበት ጊዜ ግን ያዉ ለጊዜ ብይን የሚተዉ ነዉ።

In der Omajaden-Moschee In der Omajaden-Moschee, Damaskus Schlagworte: ARD-Auslandsreportagefonds, Damaskus, Syrien, Stefanie Markert Rechte: Stefanie Markert für DW Aufnahmedatum: Oktober Aufnahmeort: Syrien Eingestellt Oktober 2009

ደማስቆ-የጥንት ቅርሷ


ሰዉ ሰዉነቱ ከታወቀበት-የዘመን ሒደት የእዉቀት ምጥቀት ዛሬ እስከደረሰበት ጊዜ ድረስ ሰዉ ተለይቷት አያዉቅም።ዛሬ የመንግሥትና የተቃዋሚዎቹ ቦምብ-ጥይት ያነጥርባታል።የነዋሪዎችዋ ደም ከጥንታዊዉ እዉቅ ወንዟ ዉሐ ይቀየጥባታል።ደማስቆ።ዲማሽቅ፥ ወይም አ-ሻም።ሰዉ የባራዳን-ወንዝ ተከትሎ ከሰፈረባት ከዘጠኝ ሺሕ ዓመተ-ዓለም ጀምሮ የሰዉ ሁለት ባሕሪ፥ ደግነት-ክፋቱ፥ሁለት ምግባር ልማት-ጥፋቱ፥ ሁለት-ልዩነቶቹ-ሥልጣኔ-ሥይጣኔዉ ግራቀኝ-ቀኝ ንረት ተለይቷት አያዉቅም።ዛሬም።ደማስቆ።የዛሬ-እዉነቷ መነሻ፥ ያለፈ ታሪኳ ማጣቀሻ የዓለም አቋም መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
            
የቱኒዚያዊ ወጣት የመሐመድ ቡአዚዚ አስተምሕሮት ሰሜን ምሥራቅ ሶሪያዊቱ  ከተማ አል-ሐሳካሕ ሲደገም ከቡዓዚዝ ሞት በሕዋላ ቱኒዚያ የሆነዉ ሶሪያም ይደገማል ነበር የብዙዎች እምነት።ቡአዚዚ እራሱ ላይ የለኮሳዉ እሳት ለሁለት ሳምንት ያክል አሰቃይቶ በገደለዉ፥ በሁለተኛዉ ሳምንት-ጥር ሃያ ስድስት 2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ዓል-ሐሳካሕ አደባባባይ እራሱን ያጋየዉ ሐሰን ዓሊ አክሌሕ ከቡአዚዚ የተለየ ምኞት፥ አላማ፣ ፍላጎትም አልነበረዉም።

የወጣቱ ማንንነት፥ አለማ፥ ፍላጎቱም የቡአዚዚን ያክል እዉቅና፥ መስዋዕትነቱም ቱኒዚያና ግብፅ ላይ የታየዉን አይነት አጣዳፊ ሕዝባዊ ሰላማዊ ተቃዉሞ፥ ፈጣን የሥርዓት ለዉጥ በርግጥ አላስከተለም። የድፍን ሶሪያ ሕዝብን የእስካሁን ሕይወት-ባጠቃላይ የደማስቆ ነዋሪዎችን ኑሮ፥ ፖለቲካዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴን ለዉጦታል።
          
የፕሬዝዳንት በሽር አል-አሰድ መንግሥት ተቃዋሚዎች ያደራጁት ሠልፈኛ ።የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎችም ደማስቆን በአፀፋ የአደባባይ ሠልፍ ለማጥለቅለቅ አልሰነፉም።ደማስቆ በመንግሥት ደጋፊና ተቃዋሚዎች ሠልፍ ግራ-ቀኝ መርገጥ የጀመረችዉ ሐሰን ዓሊ አክሌሕ እራሱን ካጋየ ከወር በላይ ቆይቶ ነበር።

የአክሌሕ እራሱን ባጋየ በሁለተኛዉ ቀን-አር ረቃሕ ከተማ ዉስጥየኩርድ ዝርያ ያላቸዉ ሁለት ወታደሮች ተገደሉ።ግድያዉ አክሌሕ የተሰዋለት፥ ምናልባትም አብዛኛዉ የሶሪያ ሕዝብ የተመኘዉ  ሰላማዊ ትግል ዉል መሳቱ ጠቋሚ ነበር።በርግጥም አመፁ ከሰሜን ሶሪያ ቀስ በቀስ ወደ ደቡብ እየወረደ ከዚች ዉብ ጥንታዊት፥ታሪካዊት ከተማ ደማስቆ ሲደርስ ቱኒዚያና ግብፅ ላይ የታየዉን ሕዝባዊ ሠላማዊ ይዘቱን እያጣ እንደ ሊቢያዉ በነፍጥ-ዉጊያ ደም እያረጫ ነበር።

Hamidieh Markthalle in Damaskus in Syrien The Hamidieh market in Damascus pictured on Tuesday, 29 June 2004. The market, with its perforated metal roof, dates back to 1863 A.D. and extends from Bab al-Basr in the west to the Umayyad Mosque in the east. The market is famous for its garmet stalls and traditional industries.. Foto:Youssef Badawi epa dpa

ዘመናይ መልኳደማስቆ ላይ የታየዉ ሌላዉ ጋ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊዉ አመፅ፥ በማዕከላዊዉ መግሥት ጠንካራ እርምጃ፥ ተዳከምዉ ለረጅም አመታት አድፍጠዉ ለነበሩት ለኩርድ አማፂያን፥ለጎሳና ለሐይማኖት ሐራጥቃ አቀንቃኞች ጥሩ አጋጣሚነቱ አላጠራጠረም።አማፂያኑ ሕዝባዊዉን አመፅ ተላብሰዉ ከየተቀበሩበት ብቅ ማለታቸዉ ደግሞ ለፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ ተቃዋሚዎቻቸዉን ሰላማዊዉን ሕዝብ ጨምሮ ለመወንጀል ጥሩ ምክንያት ነዉ የሆነዉ።
                 
«ከአሽባሪዎች ጋር እርቅ ብሎ ነገር የለም።የትጥቅ አመፃቸዉን እያስፋፉ ነዉ፥ ከዉጪ ሐይላት ጋር ተመሳጥረዉ እኛ ለማጥፋት ከተነሱ ሐይላት ጋር እርቅ የለም።»

የዉጪ ሐይላት።ደማስቆ።የሐይክሶስ ሥርወ-መንግሥት ከነገሰባት-የአርማይኮች እስከ ሠፈሩባት፥ ሂትያዎች ከሰለጠኑባት፥ከ ኢዛሮን እስከ አመፀባት፥ አሲሪያዎች ከገዙበት-አሌክሳንደር ትልቁ እስከ ማረኳት ድረስ ከቁጪ ሐይላት ተፅዕኖ ርቃ አታዉቅም።ፋርሶች፥አዩቢዶች፥ አረቦች፥ ቱርኮች እየገቡ ሲወጡ፥ እየገነቡ ሲንዷት ዘመነ-ዘመናት ያስቆጠረችዉ ደማስቆ እንደ አብዛኛዉ የአካባቢዉ ሐገራት-ከተሞች ሁሉ የአሁን መልክና ባሕሪዋን የያዘችዉ የመጀመሪያዉ የዓለም በሚባለዉ ጦርነት ዋዜማ ነበር።

እርግጥ ነዉ፥ የኦስማን ቱርኮች እንደ ቅኝ ገዢ፥ ያን ሥልታዊ፥ ጥንታዊ፥ የሐይማኖት መፍለቂያ  ምድርን እንደያዙ ለመቀጠል፥ ጀርመኖች እንደ ቱርክ ተባባሪ፥ ብሪታንያና ፈረንሳይ ደግሞ ያን ምድር ከቱርኮች ለመቀማት እንደሚያሴር ሐይል፥ አንዳደቸዉ የሌላቸዉን እንቅስቃሴ እርምጃ ያዉቁታል።

የአስራ-ዘጠኝ አመቱ ፖላንዳዊ አይሁድ አላማ ፍላጎቱ ፥ ጉዞ-እርምጃዉ ጭምርም  ፖለቲካዊ መሆኑን የማወቅ-መገንዘቡን ያክል የእሱና የብጤዎቹ የቃል-ኪዳን ምድር የሚሸረብ የሚገመድባትን  ብዙ አያውቅም ነበር።በዚያ ለጋ እድሜዉ ወደዚያ ምድር የሔደዉ፥ ቴዎድሮ ሔርሴል ከ1895 ጀምሮ ለአይሁዳዉያን ነፃነት የሰበከ፥ የፃፈዉን አስተምሕሮት፥ የቀየሰ-የወጠነዉን እቅድ ገቢር ለማድረግ ነበር። ፅዮናዊነት።

ቅኝ ገዢዎች «የዓለም» እና የመጀመሪያ ያሉትን ጦርነት ለመጫር የገጠሙት ዛቻ-ፉከራ የዉጊያ ዝግጅት ጢስ አለም በሚያዉድበት በዚያ ወቅት ብሪታንያ ፈረንሳይ በፈራሚ-ዲፕሎማቶቻቸዉ ስም ሳይኬሰ-ፒኮት ብለዉ የሰየሙትን ስምምነት መፈራረማቸዉን ከአዉሮጳ ለተጓዙት ቀርቶ እዚያዉ ላሉት አይሁድ-አረቦችም ሚስጥር ነበር።

የሁለቱ ቅኝ ገዢዎች ዉል-እቅድ፥ ከአረቦች ጋር አብረዉ ቱርክን ወግተዉ ከዚያ ምድር ካስወጡ በሕዋላ አረቦችን አግልለዉ፥ አካባቢዉን ለሁለት ተቀራምተዉ መግዛት ነበር።የዉሉን ይዘት ቀርቶ-ዉል መፈረሙንም በቅጡ የማያወቀዉ ያ ወጣት እዚያ ምድር ሲደርስ አብዝቶ ያሰሰበዉ ነገደ-አይሁድ የሚግባባት አንድ ቋንቋ የሌለዉ መሁኑ ነበር።  


የያኔዉ ፖላንዳዊ ወጣት የወገኖቹን የቋንቋ ልዩነት እንዳስተዋለ በፅዮናዉያኑ የሠራተኞች ማሕበር ጋዜጣ ሒብሩን የመማር አስፈላጊነትን ይፅፍ ገባ።የመጀመሪያ ፅሁፉን እንደጨረሰ ከግርጌዉ «ዴቪድ» ብሎ የመጀመሪያ ሥሙን ፃፈ፥ ሁለተኛዉንም «ግሪን» ብሎ እንዳከለበት ያስብ ገባ።ወዲያዉ «የለም-አልኩ» አሉ አንቱ ከተባሉ ከብዙ አመታት በሕዋላ፥ «ሒብሩ የሚያስተምረዉ አይሁድ ፀሐፊ ስም የአይሁድ መሆን አለበት።

እና ሁለተኛ ስሙን ሰርዞ፥ ባዲስ ቀየረዉ። ቤን ግሪዮን ብሎ (የአንበሳ ደቦል እንደማለት ነዉ-ፍቺዉ አሉ)። የአንበሳዉ ደቦል ፅሁፍ እየሩሳሌም ዉስጥ በተሰራጨ በወራት እድሜ፥ አንደ አይሁዶች ሁሉ የአረቦችን ነፃነት የሚመኙ ሰባት የአረብ ወጣቶች እዚያች ከተማ ተሰበሰቡ።ደማስቆ።ፋታት (ወጣትዋ ኮረዳ እንደማለት ነዉ ፍቺዉ) የመጀመሪያዉን ዘመናይ የአረብ የፖለቲካ ማሕበር በሕቡዕ መሠረቱ።

የብሪታንያና የፈረንሳይ የአረቦቹን ምድር ለሁለት ለመቀረማት በሚስጥር የተፈራረሙትን ዉል ለመጀመሪያ ጊዜ በ1917 ያጋለጡት በዚያ ሰሞን የሞስኮን ቤተ-መንግሥት የተቆጣጠሩት የሩሲያ ኮሚንስቶች ነበሩ።ዛሬ በአብዛኛዉ ዓለም እንደሚሆነዉ ሁሉ የዚያን አካባቢ ባጠቀላይ፥ የሶሪያን ሁለንተናዊ ሒደት በተለይ የምትበይን ወይም ለመበየን የምትሞክረዉ ከሁለተኛዉ ትልቅ ጦርነት በሕዋላ የለንደንና የፓሪስን የመሪነት ሥልጣን የተረከበችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።
             
«መልዕክታችን ቀላል ነዉ።የተሐድሶ ለዉጥ የሚጠይቀዉን አደጋ ለመጋፈጥ ዝግጁ ከሆኑ የዩናይትድ ስቴትስን ሁለንተናዊ ድጋፍ ታገኛላችሁ።ፕሬዝዳት አሳድ ምርጫ አላቸዉ።ይሕን ለዉጥ መምራት ይችላሉ።አለበለዚያ መንገድ መልቀቅ አለባቸዉ።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ።የለንደንና የፓሪሶች አቋም ከዋሽንግተኖች ይለያል ብሎ ማሰብ ጅልነት ነዉ።ፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ ግልፅ መልስ ነበራቸዉ «የኛ የተሀድሶ ለዉጥ ሁለት ገፅታ አለዉ። ፖለቲካዊ ነዉ እና አሸባሪነትም መዋጋት።   

epa03148392 A handout photograph released by the Syrian Arab news agency (SANA) shows Syrian security officers inspecting the site of a bombing in Damascus, Syria 17 March 2012. Reports state that a number of civilians and Syrian security men died in two explosions targeting two intelligence centers, one targeted a building of security, criminal in the customs area and second in the region and targeted Air Intelligence Center in Kassa'a area in Damascus Syria. EPA/SYRIAN NEWS AGENCY SANA / HANDOUT HANDOUT EDITORIAL USE ONLY/NO SALES +++(c) dpa - Bildfunk+++

ጥፋቷ

የሞስኮ ኮሚንስቶች የለንደን ፓሪሶችን ድብቅ ዉል ሲያጋልጡ መታለላቸዉ የገባቸዉ አረቦች አረጌዎቹን ቅኝ ገዢዎቻቸዉ በተባበረሩ ማግስት ለአዲሶቹ አዉሮጳዉያን ቅኝ ገዢዎቻቸዉ መስገድ-አለያም ለነፃነት ባዲስ መልክ መፋለም ግድ ነበረባቸዉ።

በዚሕም ሰበብ የፖላንዳዊ ወጣትና የብዙ ብጤዎቹ ትግል አይሁድን ወደ ታላቅ ነፃ-መንግሥትነት በሚያደርሰዉ ጉዞ አንድ ሁለት ሲል፥ ደማስቆ ላይ ለአረብ ነፃነት የሚታገል ማሕበር የመሠረቱት ወጣቶች ትግል ሌላ አቅጣጫ መከተል፥ ሌላ ዘመን መቁጠር ነበረበት።ጉዞዉ ወዴትም ሄደ-የትም ደረሰ ካዲሶቹ ቅኝ ገዢዎች ጋር የተፋለሙትም፥ ላዲሶቹ ቅኝ ገዢዎች የሰገዱትም አረቦች ዛሬ ካንድነት ይልቅ ብዙነታቸዉ እንደደመቀ ነዉ።በሶሪያ ጉዳይ ግን የዶሐ፥ የሪያድ፥ የአማን አምባገነን ነገስታትም፥በሕዝባዊ አመፅ ሥልጣን የያዙት የቱኒዝ፥ የካይሮ መሪዎችም፥ በምዕራባዉኑ ጦር ዘመቻ ለትሪፖሊ ቤተ-መንግሥት የበቁትም አንድ ናቸዉ።ፀረ-ደማቅቆ።

ቱርኮችም-የሶሪያ፥ የኢራቅ፥ ይሁን የኢራን ኩርዶች ጉዳይ፥ ጉዳያቸዉ በመሆኑ ብቻ የጥንት ጠላቶቻቸዉን አቋም ይጋራሉ።የቱርኩ ፕሬዝዳት አብዱላሕ ጉል።
               
«የአንድ ሐገር ችግር ድንበር የሚሻገር አይነት ከሆነ ችግሩ የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ፥ የመላዉ የሰዉ ልጅ ነዉ-የሚሆን።አሁን ሶሪያ ዉስጥ ያለዉ ሁኔታ ይሕ ነዉ።በየዕለቱ ሰዉ ይገደላል።በሶሪያ መንግሥት ላይ ያለዉ እምነት ተቦርቡሯል።»

አመት ባስቆጠረዉ ዉጊያ ግጭት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚገምተዉ ከዘጠኝ ሺሕ በላይ ሰዉ ተገድሏል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ተሰዷል።ደማስቆም ትሸበራለች።ጉል አለም አቀፍ ያሉት ችግር ሰበብ-መሠረት ምዕራቦችም፥ አረቦችም፥ ቱርኮችም፥ እንደሚያምኑት የፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ መንግሥት ነዉ።እንደገና ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ።
            
«የሶሪያ መንግሥት በተቃዉሞ ሠልፈኞች ላይ መተኮሱን ማቆምና ሰላማዊ ሠልፍን መፍቀድ አለበት።የፖለቲካ እስረኞችን መልቀቅና ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎች ማሰሩን ማቆም አለበት። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዳራንን ጨምሮ ግጭት የሚደረግባቸዉን አካባቢዎች እንዲጎበኙ መፍቀድ አለበት።ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን ለማፋጠን ከምር መደራደር አለበት።»

ሩሲያ ግን ግጭት ጦርነት ካለ-የሚጋጩ፥ የሚያዋጉት ሐይላት እኩል መጠየቅ፥ እኩል መከሰስ-መወንጀል አለባቸዉ ባይ ናት።ቻይናም ተመሳሳይ አቋም ነዉ ያላት።በዚሕም ምክንያት ሁለቱ ሐገራት የሶሪያ መንግሥት እንዲቀጣ አረቦችና ምዕራባዉን ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አቅርበዉት የነበረዉን ረቂቅ የዉሳኔ ሐሳብ ዉድቅ አርገዉታል።

በቅርቡ በፕሬዝዳንትነት የተመረጡት ጠቅላይ ሚንስትር ቭላድሚር ፑቲን እንዳሉት ደግሞ የአሰድ መንግሥት ጦር ግጭትና ዉጊያ ከሚደረግበት አካባቢ ይዉጣ ማለት ተቃዋሚዎች ሥልጣን ይያዙ ከማለት እኩል የሚቆጠር ነዉ።
                  
«(ምዕራባዉያኑ) አሳድ ወታደሮቻቸዉን እንዲያስወጡ የሚጠይቁት ተቃዋሚዎቻቸዉ በቀጥታ እንዲቆጣጠሩት ሥለሚፈልጉ ነዉ?ይሕ ሚዛናዊ ብይን ነዉ።ሶሪያ በርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ ናት።የእኛ አለማ ከተፋላሚ ወገኖች አንዱን ማለት ተቃዋሚዎችንም ሆነ መንግሥትን በወታደራዊ  ሐይል መደገፍ አይደለም።ይልቅእዬ የሶሪያዉን የርስ-በርስ ጦርነት ለማስቆም፥ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ነዉ።ሊቢያ ዉስጥ የተፈፀመዉ ሶሪያ እንዲደገም አንፈልግም።የምንፈልገዉ ተፋላሚ ወገኖችን እርስበርስ መገዳደላቸዉን እንዲያቆሙ ከድርድር ጠረጳዛ ላይ ማስቀመጥ ነዉ።»

ለዘመናት እንደለመደችዉ ላለፈዉ አንድ አመት-ከዉስጥ ሁለት ሐይላትን የምታዋጋ፥ የምታጋድለዋ፥ ከዉጪ  ብዙ ሐይላትን እሁለት ከፍላየምታወዛግበዋ ደማስቆ የዉጪዉን የዉስጡንም ባንድ ሰዉ ባንድ ያቆመች መስላለች።በኮፊ አናን።«ኮፊ አናን የሚሰጡትን አስተያየት እንዲያዳብሩ ጊዜ ሥፍራ ልንሰጣቸዉ እንደልጋለን።ለሳቸዉ ከፍተኛ አክብሮት አለን።ተቀናቃኝ ወገኞችን የማስታረቅ የተረጋገጠ ታሪክ አላቸዉ።»

የዩናይትድ ስቴትስዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን።ሩሲያዊ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭም ከአሜሪካዊቷ አቻቸዉ ብዙ አልተለዩም።«እንደሚመስለኝ መሰራት ሥላለበት ሥለያንዳዱ መርሐ-ግብር፥ ለመወሰን አሰተሳሰባችንን መሰብሰብ የኛ ፈንታ ነዉ።በኮፊ አናን ተልዕኮ ከፍተኛ እምነት ነዉ ያለን።»

የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሶሪያ ፕሬዝዳት ከበር ሽር አል-አሰድ ጋር ያደረጉት ሁለት ዙር ዉይይት ከሁነኛ ዉጤት አላደረሳቸዉም።ቢሆንም ተስፋ አልቆረጡም።ዲፕሎማት ተስፋ አይቆርጥም።ባለፈዉ አርብ በሰጡም መግለጫ እንዳሉት ደግሞ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት መቀራረብ  ለሥራቸዉ አበረታች ነዉ።

U.S. Secretary of State Hillary Rodham Clinton, right, listens as British Foreign Minister William Hague, left, addresses a Security Council meeting at United Nations headquarters, Monday, March 12, 2012. The bloody conflict in Syria is likely to dominate public and private talks Monday as key ministers meet at the United Nations on the Israeli-Palestinian conflict and challenges from the Arab Spring. (Foto:Richard Drew/AP/dapd)

ተመድ


               
«ዛሬ ከሰዓት በሕዋላ ከፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት (አባላት ጋር) ባደረጉት ዉይይት የተሰጠኝ ጠንካራ ድጋፍ አበረታች ነዉ።ምክር ቤቱ በጋራ ለመስራት ወስኗል።ይሕን ሥል አንዳዶቻቸሁ ፈገግ እንደምትሉ አዉቃለሁ።ልዩነት ነበር።ግን ያም ቢሆን የተለመደ ነዉ።በቅርቡ ከምክር ቤቱ አንድ የጋራ ድምፅ እንደምትሰሙ ተስፋ አደርጋለሁ።»

እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንና የአረብ ሊግን የወከሉት የአፍሪቃዊዉ ዲፕሎማት ጥረት ይቀጥላል።የሶሪያም እልቂት-እንዲሁ።አናን የሚደርሱበት ዉጤት-አይነት ግጭት ግድያዉ የሚቆምበት ጊዜ ግን ያዉ ለጊዜ ብይን የሚተዉ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ

 


 

 

 

Audios and videos on the topic