የሶሪያ ጊዜያዊ ሁኔታ፣ | ዓለም | DW | 28.07.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሶሪያ ጊዜያዊ ሁኔታ፣

ሶሪያ ውስጥ በመንግሥት ወታደሮችና በአማጽያን መካከል፣ በተለይ ፤ ከደማስቆ ቀጥላ በስፋት 2ኛ በሆነችው ሰሜናዊ የወደብ ከተማ አሌፖ፣ ውጊያው ተፋፍሞ እንደቀጠለ ሲሆን፤ ዛሬ ጧት 4 ሰዎች መገደላቸውን የሶሪያ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት

ገልጿል። የበሺር ኧል አሰድ መንግሥት፣ ወጊያውን፤ በታንክና መድፍ ብቻ ሳይሆን   በሄሊኮፕተር ጭምር ነው በማካሄድ ላይ የሚገኘው።

በቡድን ተሰባስበው ወሰን በማቋረጥ ዮርዳኖስ ለመግባት በሞከሩ ሲብሎች ላይ ተኩስ የከፈቱ የሶሪያ ወታደሮች ፣ አንድ የ 3 ዓመት ልጅ መግደላቸውንም፣ የዮርዳኖስ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።   

ከሀገሪቱ የፓርላማ አባላት መካከል፣ ከአሌፖ ተወክለው  የነበሩት፣ ኢካላስ ባዳዊ  የተባሉት ፤ በተቃውሞ ከብልለው ቱርክ በመግባት የመጀመሪያው የህዝብ እንደራሴ መሆናቸው  ተነግሯል። 

 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን፣ በሶሪያ ፣ ሰዎች ፤ ነጋ -ጠባ  የሚጨፈጨፉበት ድርጊት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቆም ዘንድ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትናንት መማጸናቸው የሚታወስ ነው።  አያይዘውም ፣  የሰብአዊ መብት ጥሰትን  መግታት ፤ የዓለም መንግሥታት ኀላፊነት  መሆኑን ነው  የጠቀሱት። በውጊያው፣  የብዙ ሲቭሎች ህይወት ሊጠፋ ይችላል የሚለው ሥጋት ፣ ዩናይትድ እስቴትስን ማሳሰቡን ፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ቪክቶሪያ ኑላንድ   አስታውቀዋል።

«ያሳሰብን ይህ ነው። በአሌፖ የህዝብ ጭፍጨፋ መታየቱ አይቀር ይሆናል። ይህን ለማድረግም ነው የሚመስለው ፈላጭ ቆራጩ የሶሪያ መንግሥት በዝግጅት ላይ የሚገኘው።»

ባለፉት ጥቂት ቀናትና  ሳምንታት፤ የአሰድ መንግሥት ፣ የፍጻሜውን ምዕራፍ አሐዱ ብሎ መጀመሩ ነው ተብሎ በፖለቲካ መሪዎች አንደበት የተነገረበት ሁኔታ ነበረ። አንዱም ባለፈው ሰኞ ተመሳሳይ ቃል የሰነዘሩት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቨለ ናቸው። እውን የበሺር ኧል አሰድ አገዛዝ የሚያከትምበት ጊዜ እጅግ ተቃርቧል!?

ቬስተርቨለ ፣ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

«ፍጻሜው ስለመቃረቡ ፣ እንዲህ ነው ብሎ በይፋ ለመናገር  ጊዜው ገና ነው። ይሁን እንጂ እየተናደ የሚሄድበት ሁኔታ ስለመጀመሩ መግለፅ ይቻላል።  ከጊዜ ወደ ጊዜ፤ ከሠራዊቱ  በከፊል፣  ከተለያዩ ክፍለ-ጦሮችም ከአሰድ አገዛዝ የሚሰናበቱትን  እያየን ነው። በሌላ በኩል፤ የምንሰማው ዜና፤ የአሰድ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ፣ በአየርና  በምድር ከባድ መሣሪያዎችን በመጠቀም፤ ተቃዋሚዎቹን ለማጥቃት በመዘጋጀት ላይ መሆኑ በጣም የሚያሳስብ ነው። ስለሆነም ቻይናና ሩሲያ፣ አሳድን የሚደግፈውን እጃቸውን ሰብሰብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ። በኒው ዮርክ፤ የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት፤ በአንድ ቋንቋ መናገሪያውና በኅብረት መላ መፈለጊያው ጊዜም አሁን ሊሆን ይገባል።»

የጋራ ቋንቋ ሲባል ምን ማለት ነው? ኀያላን መንግሥታት ፤ የዐረብ መንግሥታት ማኅበርም ቢሆን ፤ ጉዳዩን ከብሔራዊና አካባቢያዊ ጥቅም አኳያ እንጂ፤  ከዚያ በተለየ መልኩ የሚያየው አይመስልም። የአውሮፓው ኅብረት፤ በሶሪያ ላይ ማዕቀብን የሚያጠብቅ እርምጃ ፣  17 ጊዜ ወስዷል። ግን የተከረው ጉዳይ የለም። የማዕቀብ እርምጃ ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በጋራ የፖለቲካ አቋም  ይወስዳል መባሉ፤ እነዚህ ሁሉ፣  ቃላት በእርግጥ ፣ ከእንግዲህ ዋጋ አላቸው?፤ መፍትኄ ያስገኛሉ ተብሎ ታምኖበት ነው?!

«ይህ አባባል ልክ ነው ፣ ይገባኛል።  በኒው ዮርክ ፣ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት፣ ቻይናና ሩሲያ፣  ድምጽን በድምፅ የመሻር መብታቸው መግታታቸው፣ጥሩ የሚባል ተግባር  አይደለም። ይህ እንዲያውም የሚያስነቅፍ ሥራ በመሆኑም  በአንዳንድ ስብስባዎች ፣ በይፋ ያወገዝንበት ሁኔታም አለ። ወሳኙ ግን ፣ ለሶሪያ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መጻዔ - ዕድል፤ የፖለቲካ መፍትኄ ይገኝ ዘንድ ጥረት ማድረጉ ነው። ስለዚህም፤ በአንድ በኩል በኒው ዮርክ የፖለቲካ ውሳኔው ጉዳይ አለ። በተጨማሪም የዐረብ መንግሥታት ማኅበር ፤ በተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባዔ የሚያደርገውን እንቅሥቃሤ እንደግፋለን። ከዚህ ጋር ተያይዞም፣ ሰብአዊ እርዳታ እናቀርባለን። »

የአሳደን አገዛዝ ለመጣል፤ መላ በምምታት ላይ መሆናቸው የሚነገርላቸው፣  አሁን  ቱርክ ውስጥ በአንድ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙት ፤  የቀድሞው  የሶሪያ ከፍተኛ የጦር መኮንን፤  ብርጋዲዮር ጀኔራል  ፋየዝ አምር ፣ የለየለትን አውዳሚ አገር አቀፍ የአርስ በርስ ውጊያ ለመግታት ፤ ሁሉንም ያቀፈ ፤ ገዥውን ከፍል ጭምር ያካተተ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ይመሠረት ዘንድ ጥሪ አስተላልፈዋል። በደቡባዊው ቱርክ፤ አፓያዲን በተባለው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ፤ ከሚገኙት ሶሪያውያን ስደተኞች መካከል 27 ቱ የአሰድን መንግሥት ጦር ኃይል የከዱ ጀኔራሎች ናቸው።

ጀኔራል ፋየዝ አምር፤ በሶሪያ ነጻ ጦር ሠራዊትም ሆነ በተቀውሞው ም/ቤት በሶሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት መካከል የሚፈለገው አንድነት አይንጸባረቅም በማለት ተችተዋል። ብሔራዊው ም/ቤት እንደ ብርጋዲየር ጀኔራል አምር አስተሳሰብ፤ ደርዘን የሚሆኑትን  በተለያዩ ቦታዎች የሚታጋሉትን  ተፋላሚ ቡድኖች ፤  በአንድ አመራር ሥር እንዲዋጉ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 28.07.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15fgK
 • ቀን 28.07.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15fgK