የሶሪያ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መክሸፍ | ዓለም | DW | 06.08.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሶሪያ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መክሸፍ

ሰውዬው ለሶስት ወራት ከደማስቆስ ኒውዮርክ፤ ከሶሪያ አሜሪካ እግራቸው እስኪቀጥን ተመላልሰዋል። አሳድን በተማፀኑበት ልክ ተቃዋሚዎችን ወደ ሠላሙ መንገድ እንዲመጡ ለምነዋል። እንደጅረት የሚንዠቀዠቀውን የሶሪያውያን ደም ባስቸኳይ እንዲያስቆሙ ሩስያን፣ ቻይናን እና አሜሪካኖችንም ሳይታክቱ ወትውተዋል።

የአሜሪካኖቹም፣ የቻይኖቹም፣ የሩስያውያኖቹም ፍላጎት ግን ለየቅል ሆነና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መተባበር የተሳነው ሲመስል፤ አደራዳሪው ኮፊ አናን ድንገት በቃኝ አሉ። ጤናይስጥልኝ አድማጮች! «ዲፕሎማሲያዊ ውድቀት በሶሪያ» የዛሬው ማኅደረዜና  ማጠንጠኛችን ነው፤ አብራችሁን ቆዩ!

ሙዚቃ፥

የሆሊውዱ የፊልም ተዋናይ ቶም ክሩዝ በአንድ ወቅት በሚገባ አድርጎ ተውኖበታል፤  «mission imposible»፤ «የማይቻለው ተልዕኮ» የተሰኘው ፊልም። ለዓለማችን ታዋቂው አንጋፋ ዲፕሎማትም የሶሪያ የሽምግልና ተልዕኮ ብዙዎች አስቀድመው ይገልፁት እንደነበረው ከፊልሙ ርዕስ ጋ ሳይመሳሰልባቸው አልቀረም። ተልዕኮው በእርግጥም ለቀድሞው የተ.መ.ድ. ዋና ፀሀፊ ኮፊ አናን የማይቻል ሆኖ ተጠናቋል።

ድንገት በቃኝ ያሉት አደራዳሪው ኮፊ አናን

ድንገት በቃኝ ያሉት አደራዳሪው ኮፊ አናን

«ይህን አንዳንዶች የማይቻለው ተልዕኮ ሲሉ የጠሩትን ተግባር ሶርያውያንን ለመርዳት፤ ለደም አፋሳሹ ግጭትም ሠላማዊ መፍትሄ ለመሻት ተቀብየው ነበር።»

አናን ሐሙስ (ሐምሌ 26 ቀን 2004 ዓም) ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሶሪያ የሽምግልና ተልዕኮዋቸው ሲበዛ መታከታቸውን ሳይሸሽጉ ነበር የገለፁት። እናም ከእንግዲህ የሶሪያ ግጭት አደራዳሪነቴ መንገዱ እዚህ ላይ ያበቃል ሲሉም ከፍፃሜ ያልደረሰ ተልዕኮዋቸውን ለድምዳሜው እንዳበቁት  ለዓለም አርድተዋል። ኮፊ አናን በተሰጣቸው  የሠላም ልዑክነት ላለመቀጠል ለመወሰናቸዉ ያቀረቡት ምክንያት የሚከተለዉን ነዉ፤

«ከልብ የታሰበበት፤ ዓላማያለዉ እና የተባበረ የአካባቢዉን ኃይሎች ጨምሮዓ ለምዓቀፍጫና፤ ለእኔም ሆነ ለማንም በመጀመሪያ ደረጃ የ ሶርያን መንግስት እንዲሁም ተቃዋሚዎችን የፖለቲካ ሂደት እንዲጀመር አስፈላጊ ርምጃዎችን እንዲወስዱ ለማድረግ አዳጋች ነዉ። እኛም ሆንን የሶርያ ሕዝብ አንዳች ርምጃ  ሲወሰድ ለማየት ስንጠብቅ፤በ ፀጥታዉ ምክርቤት ዉስጥ አንዱ በሌላዉ ላይ ጣቱን መጠቆምና መወቃቀስ ጀመረ።»

የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጉባዔ በበኩሉ የጸጥታ ም/ቤቱን ተገቢውን ርምጃ በመውሰድ የሶሪያን ውዝግብ ለማስቆም ባለመቻሉ በሚል በሰፊ ድምጽ ኮንኖታል። 193 መንግሥታትን ያቀፈው ጠቅላይ ጉባዔ 17 ወራት በዘለቀው የሶሪያ ውዝግብ መባባስ ያደረበትን ስጋትም ገልጿል። ጠቅላይ ጉባዔው የጸጥታው ም/ቤት የሶሪያ ባልሥልጣናት ውሣኔዎቹን እንዲከተሉ ለመገፋፋት ሊስማማ ባለመቻሉም ነቀፌታ ሰንዝሯል።  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ባን ኪ ሙን የሶሪያ ቀውስን ተከትሎ ድርጅታቸው ከባድ ፈተና ላይ መውደቁን አሳውቀዋል።

አናን ከሶሪያው ፕሬዚዳንት ጋ ሲወያዩ

አናን ከሶሪያው ፕሬዚዳንት ጋ ሲወያዩ

«በሶሪያ ያለው ግጭት ይህ ድርጅት የቆመለት እያንዳንዱ ነገር የሚፈተንበት ነው። እናም የዛሬው የተ.መ.ድ. ያን ፈተና እንዲወድቅ አልሻም።»

በእርግጥም እንደ ባን ገለፃ የመንግስታቱ ድርጅት አጣብቂኝ ውስጥ ሳይገባ አልቀረም። ድምፅን በድምፅ የመሻር  ቬቶ መብታቸውን በመጠቀም የፀጥታውን ምክር ቤት ውሳኔ ሲያግዱ የቆዩት ሩስያ እና ቻይና አሁንም የፀጥታው ምክር ቤት በሶሪያ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ሳይቀበሉት ቀርተዋል። እንዲያም ሆኖ በተ.መ.ድ. የሩስያ አምባሳደር ቪታሊ ቹርኪን አናንየሶሪያየሽምግልና ተልዕኮዋቸውን ባቆሙበት ውሳኔማዘናቸዉንሳይጠቅሱ አላለፉም።  በብዙዎች ነገሩ የአዞ እንባ አይነት ተደርጎ ነው የተወሰደው።የሩስያው አምባሳደር ቪታሊ ቹርኪን፥

«ዉሳኔያቸዉን እንረዳለን፤ ሆኖም ይህን በመምረጣቸዉ እናዝናለን። የኮፊ አናንን ጥረት በጥንካሬ ስንደግፍ ነ በር። ለመሰናበት አንድ ወር ይቀራቸዋል፤ ይህ ወር በ ጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ደም መፋሰስን አስቁሞ ሶሪያን ወደ ፖ ለቲካዉ ሂደት ለማምጣት ዉጤታማ በሆነ መልኩ ይጠቅማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ዋና ፀሐፊዉ የሶሪያን ቀዉስ ለመግታት ኮፊ አናንን የሚተካ ለመሰየም በሚያደርጉት ጥረት ተበራትቻለሁ።»

የሶሪያ ግጭት ተባብሶ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ቱርክ፣ ሳኡዲ አረቢያ እና ቃታርን ከጎኗ ያሰለፈችው አሜሪካ የሶሪያ አማፂያንን እንደምትደግፍ ይነገራል። ልዕለ ሃያሊቱ ሀገር አማፂያኑን መሳሪያ በማቀበል ለመርዳት ባትፈቅድም እስካሁን 25 ሚሊዮን ዶላር ግን አበርክታላቸዋለች። ከዚያም ባሻገር የሲአይ ኤ የደህንነት ሰዎች አማፂያኑን ለመርዳት ወደ አካባቢው መላካቸው ተዘግቧል። የሲአይኤ ባልደረቦች ለሶሪያ አማፂያን መሳሪያ እንደሚያቀብሉ የሚነገርላቸውን ሳዑዲ አረቢያ እና ቃታርን ቱርክ ውስጥ ሆነው እንደሚያማክሩም መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። የአካባቢው ሁኔታ ስጋት እንዲገባት ያደረጋት ቱርክን እነዚሁ የሲአይ ኤ ወኪሎች ለማረጋጋት እየሞከሩ እንደሆነም የቀድሞው የሲ አይ ኤ ወኪል የነበሩት ቦብ ቤር ጠቅሰዋል።

አናን ከፑቲን ጋ ሲወያዩ

አናን ከፑቲን ጋ ሲወያዩ

«እንደማስበው በአካባቢው ያሉ ሀገራትን በተለይ ስጋት የገባት ቱርክን ለመርዳት የኦባማ አስተዳደር አካል የሆነው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ጭምር ነው።»

በሶሪያ የፀጥታ ሁኔታ ስጋት እንደገባት ትገልፅ የነበረችው ቱርክ በግዛቷ ከሚገኘው የኩርድ አማፂ ቡድን ጋር ጦር መማዘዝ ጀምራለች። የኩርድ የሠራተኛ ፓርቲ፤ በእንግሊዘኛ ምህፃሩ PKK ቱርክ  ላይ ጥቃት መሰንዘሩን የቱርክ መንግስት ትናንት ይፋ አድርጓል። ይህን አማፂ ቡድን የምትደግፈው እና የምታስታጥቀው ሶሪያ ናት ስትል ቱርክ ኮንናለች። የዓለማችንን ልዕለ ሃያላን እንደ አዙሪት ጎትቶ ያመጣው የሶሪያ ግጭት አሁን የጎረቤት ሀገራትን ማመስ ይዟል።  ሰበቡ ደግሞ የፀጥታው ምክር ቤት አንድ ሆኖ ሶሪያን በተመለከተ ፈጣን ውሳኔ ባለማሳለፉ እንደሆነ እየተነገረ ነው። እናም ምክር ቤቱ በሶሪያ ጉዳይ አንድ መሆን አቅቶት ፈተና ላይ በወደቀበት በዚህ ወቅት ኮፊ አናን የተማረሩበት መጠቋቆም እና መወቃቀስ የቀጠለ ይመስላል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሂላሪ ክሊንተን በግድምድሞሽም ቢሆን ለሶሪያው ግጭት ተጠያቂ ያሏቸውን ሐገራት በይፋ ጠቅሰዋል።

«የአሳድ መንግስት ደም አፍሳሽ ጥቃቱን በቀጠለበት ወቅት ከኢራን፣ ሩስያ እና ቻይና ብቻ ድጋፍ አግንቷል።»

አናን ከኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጋ ሲወያዩ

አናን ከኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጋ ሲወያዩ

ሩስያ፣ ቻይና እና ኢራን በበኩላቸው እንደ አሜሪካዋ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጣታቸውን በሌላው ላይ መቀሰራቸው አልቀረም። ኢራን በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ በኩል ለሶሪያው የሠላም ጥረት መክሸፍ ዩናይትድ ስቴትስን ተጠያቂ አድርጋለች። የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ አክበር ሳሌህ «ምዕራባውያን እና አንዳንድ የአካባቢው ሀገራት የአናን ጥረት ስኬታማ እንዳይሆን ደንቃራ ሆነዋል» ሲሉ ተችተዋል። ሳሌህ ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል አፍቃሬ አሜሪካን የአረብ ሀገራትን እንዲሁም ቱርክን ከጎናቸው አሰልፈው የሶሪያ አማፂያንን ይደግፋሉ ነበር ያሉት። ሚንስትሩ አፍቃሬ አሜሪካን የአረብ ሐገራት ሲሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሶሪያ አማፂያንን እንደሚደግፉ የሚነገርላቸውን ቱርክ፣ ቃታር እና ሳዑዲ አረቢያ ወርፈዋል። ኢራን የሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ መንግስትን በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብት እና በሠብአዊ ርዳታ የምትደግፍ ዋነኛ ሀገር እንደሆነች ይነገራል።

አናን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጋ

አናን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጋ

ሙዚቃ፥

የሶሪያ ግጭት ቀጥሎ ባለበት አማጺያን ሳኢዳ ዛይናብ የተሰኘውን የሺአቶች መቅደስ ሲጎበኙ የነበሩ 48 ኢራናውያንን ማገታቸውን አሳውቀዋል። ታጋቾቹ የኢራን የአብዮታዊ ዘብ አባል መሆናቸውን እና የሶሪያን መንግስት ሊረዱ መምጣታቸውን አማፂያኑ የታጋቾቹን መታወቂያ በማሳየት ገልፀዋል።  በሌላ አንፃር የኮፊ አናን ባለ 6 ነጥብ የሠላም ዕቅድ ከከሸፈ በኋላ በሶሪያ ያለው ግጭት እየተካረረ ሄዶ አሌፖ በተሰኘችው የሶሪያ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ከዚህ ቀደሙ የከፋ ከባድ ውጊያ ሊካሄድ እንደሆነ እየተነገረ ነው።  እስካሁን በአሌፖው ውጊያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል። 17 ወራት በዘለቀው የሶሪያ ግጭት ደግሞ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሶሪያ መንግስት ተቃዋሚዎች እና የመብት ተሟጋቾች  ገልፀዋል።  ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶሪያ ጠቅላይ ሚንስትር ሪያድ ሂጃብ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከሁለት ሚንስትሮች እና ሶስት የጦር ሀይል ባለስልጣኖች ጋር በአንድነት ከድተው ዛሬ ዮርዳኖስ መግባታቸውን የዮርዳኖስ መንግስት ገልጿል። እናስ ይህ የዲፕሎማሲው ውድቀት አንዱ ምልከታ ወይንስ የአሳድ መንግስት ፍፃሜ መዳረሻ? ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።

ሙዚቃ፥

«ዲፕሎማሲያዊ ውድቀት በሶሪያ» በሚል ርዕስ የሶሪያ ወቅታዊ ሁኔታን አካተን ያቀረብንላችሁ የማኅደረ ዜና ጥንቅር በዚህ ይጠናቀቃል። ለዝግጅቱ ማንተጋፍቶት ስለሺ ነኝ፤ ጤናይስጥልኝ!

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic