የሶሪያ ሕዝብ እልቂት | ዓለም | DW | 23.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሶሪያ ሕዝብ እልቂት

የሶሪያ መንግስት፤ አሸባሪ ይባሉ ለዘብተኛ ደፈጣ ተዋጊዎች በሕዝብ ላይ የሚያደርሱት ግፍ በደል የሚገታዉ ጦርነቱ ሲቆም መሆኑን የሚጠረጥር የለም።ጦርነቱን ለማቆም የሚረዳዉ ድርድር ግን በየጊዜዉ መጀመሩ ከመነገሩ መፍረሱ ነዉ የሚሰማዉ።ተፋላሚ ሐይላትን የሚሸመግሉት ስቴፋን ደ ሚስቱራ እንዳሉት አሁንም ስምምነት አይደለም የድርድሩ ተስፋ ራሱ ሩቅ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:46

የሶሪያ ሕዝብ እልቂት

አምስተኛ ዓመቱን የደፈነዉ የሶሪያ ጦርነት በሐገሪቱ ሕዝብ ላይ ያደረሰዉ ጥፋት እጅግ የከፋ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን አስታወቀ።ጦርነቱ በተለይ በሠላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሰዉን መከራ ያጠኑት ባለሙያዎች ለድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ እንደነገሩት የሠላማዊዉ ሰዉ እልቂት፤ ስደት፤ እና መከራ እስካሁን ከሚታሰበዉ የከፋ ነዉ።በሠላማዊ ሰዎች ላይ ለሚፈፀመዉ ግፍ ባለሙያዎቹ ባብዛኛዉ የሶሪያ መንግሥት ሐይላትን ተጠያቂ አድርገዋል።በድርጅቱ የሶሪያ አምባሳደር ግን ወቀሳዉን አልተቀበሉትም።

ከየስድስቱ የዓለም ስደተኛ አንዱ ሶሪያዊ ነዉ።የዓለም አቀፉ ድርጅት አጥኚዎች እንደሚሉት መሰደድ፤ መፈናቀል፤ መሸሽ ያልቻለዉ አንድም ይሰቃያል-አለያም ያልቃል።ሶሪያ፤ በባለሙያዎቹ መግለጫ «አንድ ትዉልድ አጥታለች።» ከአጥኚዎቹ አንዱ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠብአዊ መብት ጉዳይ ተወካይ ኢቫን ሲሞኖቪች ምሳሌ ይጠቅሳሉ።

«ገና አስራ-አምስተኛ ዓመቱን የደፈነ ወጣት ወደ ትምሕርት ቤት ይጓዝ ነበር።ዴር አልሱር ከሚገኘዉ የመንግስት ሐይላት ኬላ ሲደርስ ተያዘና ወታደራዊ ደሕንነቶች ወደ ደማስቆ ወሰዱት።ታሰረ።ተገረፈ።በዱላ ብዛት ሞተ።»

ሌላ ቀን፤ ሌላ ሥፍራ፤ ሌላ ግድያ።አጥኚዎቹ የመንግሥት እና የተባባሪዎቹ (ሩሲያን በስም ላለመጥራት ይመስላል) የጦር ጄቶች ኢዲሊብ በሚገኝ አንድ የአሳ መሸጫ መድብር ላይ በጣሉት ቦምብ ዘጠኝ ሰዉ ገደሉ።ሁለቱ የ15 እና የ16 ዓመት ወጣቶች ነበሩ።ሲሞኖቪች እንደሚሉት አሸባሪ ቡድናትም በራሳቸዉ መንገድ ይገላሉ።የ16 ዓመቱን ወጣት በድንጋይ ወግረዉ ገደሉት።የወጣቱ ወንጀል «ቡሽቲ» ነዉ-የሚል ጥርጣሬ ነዉ።አንዷን የዛይዲ ልጃገረድ ደግሞ አፈኗት።ደፈሯት።የዓለም አቀፉ ድርጅት የአስቸኳይ ርዳታ ተጠሪ ስቴፋን ኦ ብሬይን በበኩላቸዉ ሌላ አሳዛኝ ታሪክ ይተርካሉ።«ሶሪያ ዉስጥ 590 ሺሕ ሕዝብ ተከብቧል።አብዛኛዉ የተከበበዉ በሶሪያ መንግሥት ጦር ነዉ።»

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶሪያ አምባሳደር በሽር አል ጃአፈሪይ በመንግሥታቸዉ ላይ የሚሰነዘረዉን ወቀሳ አጣጥለዉ ነቅፈዉታል። አምባሳደሩ እንደሚሉት ዉንጀላዉ በሙሉ መንግሥታቸዉን ለማሳጣት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ ነዉ።

አምባሰደሩ ለስብሰባዉ ባደረጉት የአስራ-አምስት ደቂቃ ንግግር ሳዑዲ አረቢያን አሸባሪዎችን ታደራጃለች፤ ታስታጥቃለች፤ ከሶሪያ አልፋ የመንን ትደበድባለች በማለት በተደጋጋሚ ወቅሰዋታል።የሶሪያ መንግሥት እንደ ጦር ግንባሩ ሁሉ በዲፕሎማሲዉም ፍልሚያ የሩሲያ ድጋፍ አልተለየዉም።

ይሁንና የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ርዳታ ጉዳይ ሐላሪ ኦብሬይን የሶሪያ መንግስት ለዜጎቹ የተላከ የርዳታ እሕል ሳይቀር ይቀማል ባይ ናቸዉ።

«የሶሪያ ዜጋ አማካይ እድሜ በዚሕ አጭር ጊዜ በሐያ ዓመት ቀንሷል።ከሕዝብ የሚቀማዉ የርዳታ ቁሳቁስ ከሚታመነዉ በላይ ነዉ።የልጆች የዱቄት ወተት ሳይቀር ይቀማል።እንዲዉ በፈጣሪ ይሕ ምን ማለት ነዉ።»

የሶሪያ መንግስት፤ አሸባሪ ይባሉ ለዘብተኛ ደፈጣ ተዋጊዎች በሕዝብ ላይ የሚያደርሱት ግፍ በደል የሚገታዉ ጦርነቱ ሲቆም መሆኑን የሚጠረጥር የለም።ጦርነቱን ለማቆም የሚረዳዉ ድርድር ግን በየጊዜዉ መጀመሩ ከመነገሩ መፍረሱ ነዉ የሚሰማዉ።ተፋላሚ ሐይላትን የሚሸመግሉት ስቴፋን ደ ሚስቱራ ለተሰብሳቢዎች እንዳሉት አሁንም የሰላም ስምምነት አይደለም የድርድሩ ተስፋ ራሱ ሩቅ ነዉ። «ምናልባት በመጪዉ ሐምሌ ቀጠሮ እይዝ ይሆናል።አሁን አይደለም።»ለቀጠሮዉ እንኳ እርግጠኛ አይደሉም።

ካይ ክሌመንት/ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

 

Audios and videos on the topic