የሶሪያ ሕዝባዊ አመፅ መነሻና መለያዉ | ዓለም | DW | 28.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሶሪያ ሕዝባዊ አመፅ መነሻና መለያዉ

ፕዝዳት በሽር አል-አሰድ በዉጪዉ ግፊትም ሆነ በራሳቸዉ ስሕተት ወደራሳቸዉ መምጣቱ የማይቀረዉን ተቃዉሞ ፈጥነዉ ካለበረዱት ደማስቆ ቱኒስ፥ ካይሮ ወይም ሠነዓ መሆንዋ አይቀርም።

default

ደማስቆ

28 03 11


የቤን ዓሊን ሥርዓት ከቱኒዝ፥ የሙባረክን ከካይሮ አብያተ-መንግሥታት የመነገለዉ፥የሳሌሕን ያፍረከረከዉ ሕዝባዊ አመፅ ሊቢያ ላይ አጓጉል ባርቆ ሰሜን አፍሪቃዊቱን ሐብታም ሐገር በቦምብ-ሚሳዬል እያንቀረቀባት ነዉ።ከሊቢያ ጎረቤት አልጄሪያ መዳፈኑ፣ ባሕሬን ላይ መደፍለቁ ተነግሮ ሳያበቃ ሶሪያን እጨጓጎፋትነዉ።የሶሪያዉ ሕዝባዊ አመፅ ሰበብ፥ምክንያት ጅምሩም የሌሎቹን ቢመስልም የደማስቆ ገዢዎችን እንደ ቱኒዝ፥ ካይሮ፥ሰነዓ ብጤዎቻቸዉ አልጨከነባቸዉም።የጥንታዊቱ አረባዊት ሐገር ሕዝባዊ አመፅ መነሻችን፥ ከሌሎቹ መለየቱ ማጣቃሻ፥ የመለየቱ ምክንያት መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

በሳምንቱ ማብቂያ ከደማስቆ ሠላሳ ኪሎ ሜትር ግድም ወደ ምትርቀዉ ከተማ ያቀኑት ከቤተሰብ፥ ዘመድ ጓደኞቻቸዉ ጋር አረፍ፥ዘና ለማለት ነዉ።ግን ያዉ የሐገር መሪ ናቸዉና አንጋች የቅርብ ረዳቶቻቸዉ አልተለዩአቸዉም።ትላልቅ አጃቢ ረዳቶቻቸዉን ካረፉበት ትልቅ ግፅር ግቢ ትተዉ ሁለት ነጭ ለባሽ አጃቢዎቻቸዉን ብቻ አስከትለዉ ወደ ከተማይቱ መሐል በእግራቸዉ ያዘግሙ ያዙ።

የዕረፍት ቀን በመሆኑ የወትሮዉ ግርግር እና ትርምስ የለም።አየሩ ግን ይወብቃል።ደክሟቸዉ፥ ዉሐ ጠምቷቸዉ፥ ወበቁን ሸሽተዉ ይሁን ወይም ሌላ ምክንያት ኖራቸዉ ይሁን ያኔም፥ አሁንም ከሳቸዉ ሌላ የሚያዉቅ አልነበረም።ብቻ በጉዞዉ መሐል ከትንሿ ከተማ መሐል ካለችዉ ካንዲት አነስተኛ ሻይ ቤት ገቡና ሚሪንዳ አዘዙ።ከእስሳቸዉ ፈንጠር ብለዉ የተቀመጡት አጃቢዎቻቸዉም የሚሹትን አዘዉ አይናቸዉን ከሰዉዬዉ ላይ እንደተከሉ ነዉ።

ከባንኮኒዉ ጀርባ የቆሙት የትንሿ ሻይ ቤት ባለቤት እድሜ የተጫጫናቸዉ አይኖችም ከባንኮኒዉ ፊት ለፊት በቆመዉ አዲስ ደንበኛቸዉ ላይ እንደተሰካ ነዉ።«ይሕን ልጅ የት ነዉ የማዉቀዉ እያልኩ ሳስብ ነበር አሉ ኋላ «የለበሰዉ ጂስ፥ ቲሸርት፥ ያጠለቀዉ ጥቁር መነፅርም ያዉ ተራ ነዉ። ቁመቱ ግን----» እያሉ ሽማግሌዉ ሲያሰላስሉ «ሂሳብ ስንት ነዉ» አናጠባቸዉ ተስተናጋጁ።

Syrien Protest Demonstration Daraa NO FLASH

ዴራዓ

«ተከፍሏል----እኔ እኔነኝ የምከፍለዉ---» አሉ ሽማግሌዉ «ለምን?» ጠየቀ ተስተናጋጁ «እ----አዲሱ ፕሬዝዳንታችንን ሥለምትመስል አላስከፍልሕም» መለሱ እየተፍለቀለቁ አለ በዚያ ሰሞን የታተመዉ የእንግሊዝኛ መፅሔት።2001 ነበር (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።)

በርግጥም ያ አንገተ ረጅም ወጣት አዲሱ ፕሬዝዳንት ነበሩ።በሽር ዓል አሰድ።ካንገትም ሆነ ካንጀት ያኔ የነበረዉ አይነት ዉዴታ አክብሮት ዛሬ ብዙ የለም።ከደቡባዊቷ ዴራዓ ከተማ አደባባይ የሚሰማዉ ደግሞ የአል-አሰድ ሥርዓትን የሚቃወም ሠልፍ፥ የአሰድ ባለሥልጣናትን የሚያወግዝ መፈክር-ነዉ። ዴራዓ የተጀመረዉ የተቃዉሞዉ ሠልፍ ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት ለመቀየር ሳምንትም አልፈጀበት።

የተባበሩት መንግሥታት የሥደተኞች መርጃ UNHCR ቃል አቀባይ ሩፐር ኮልቪለ እንዳስታወቁት ፀጥታ አስከባሪዎች እስካለፈዉ ቅዳሜ ድረስ ብቻ በወሰዱት የሐይል እርምጃ በትንሹ ሰላሳ-ሰባት ሰዉ ተገድሏል። «ሶሪያ ዉስጥ ያለዉ ሁኔታ ካለፈዉ ሳምንት ወዲሕ በጣም እየከፋ ነዉ።ሁለችንም እንዳየነዉ የሐገሪቱ ፀጥታ አስከባሪዎች በተቃዋሚ ሠልፈኞች ላይ በከፈቱት ተኩስና አስለቃሽ ጢስ ዴራዓ ዉስጥ ብቻ ሁለት ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ ሰላሳ ሰባት ሰዉ ገድለዋል።»

ፀጥታ አስከባሪዎች ዴራዓን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በሰወሰዱት እርምጃ እስካሁን ድረስ 61 ሰዎች ተገድለዋል።በ1970 ደም ባልፈሰሰበት መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት ጄኔራል ሐፊዝ አል-አሰድ «የማስተካከያ አብዮት» ያሉት መርሐቸዉ በያኔዉ የሐገራቸዉ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት አትርፎላቸዉ ነበር።አል-አሰድ ከፈረንሳይ ቅኝ አጋዛዝ ነፃ ከወጣችበት ከ1946 ጀምሮ በመፈንቅለ መንግሥት፥ በነገዶች ልዩነት፥ ከእስራኤል ጋር በተደረገዉ ተደጋጋሚ ጦርነት ግራ ቀኝ ሥትላጋ የነበረችዉን ጥንታዊት ሐገር አሻሽለዉ አረጋግተዋትም ነበር።

አል-አሰድ በግራ ዘመሙ የባዕዝ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም መሠረት የእምነትና የጎሳ፥ እኩልነትን በመፈቀዳቸዉ፥ ትምሕርት በማስፋፋታቸዉ፥ የምጣኔ ሐብቱን መስክ ለቀቅ በማድረጋቸዉ ጥንታዊዉን የኤብላ፥ የሱመር፥ የአካዳ፥ የአሞሪያስ ሥልጣኔን የምታስተናግደዉን ሐገር የዕድገት ጎዳና አፋጥነዉት ነበር።የሊባኖሱ ጦርነት፥ ማብቂያ ያጣዉ የአረብ-እስራኤሎች ግጭትና ፍጥጫ የሚቦረቡረዉ ምጣኔ ሐብት የዓለም ሶሻሊስታዊ ጎራ መዳከም ከጀመረበት ጀምሮ ግን ባለበት ይረግጥ ያዘ።

ከ1990 ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ ቁል ቁል የሚንደረደረዉን ምጣኔ ሐብት አል-አሰድ በሽማግሌ ጉልበት ብልሐታቸዉ የሚያቆሙት አልነበረም።እድሜም፥ ጤናም አዳክመዋቸዉ በሁለት ሺሕ ሲሞቱ መንበራቸዉን የወረሱት በሽር አል-አሳድ ሐገሪቱን ከገባችበት ማጥ ለማዉጣት በአዲስ ጉልበት አዲስ ብልሐት ይቀይሳሉ ነበር የሐገሬዉ ተስፋ።

በሙስና በላሻቀዉ፥ ባረጀዉ፥ የሐፊዝ አል-አሳድ ሥርዓት ቅር የተሰኘዉ አብዛኛዉ የሶሪያ ሕዝብ እምነት ብሪታንያ የተማሩት የዓይን ሐኪም ከወጣትነታቸዉ ጋር የምዕራቡን ዓለም አስተሳሰብ በማወቃቸዉ ሐገራቸዉን ከዘመኑ ብቸኛ ሐያላን ጋር የገጠመችዉን አተካራ ማስወገዱ አይገዳቸዉም ነበር።አስራ-አንድ አመት።ለብዙዉ ሶሪያዊ ብዙ የተለጠ ነገር የለም።ጀርመናዊዉ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጉዳይ አዋቂ ኡዶ ሽታይንባሕ እንደሚሉት ደግሞ የምጣኔ ሐብቱ ድቀትና ሙስና በተለይ በሐገሪቱ በስተደቡብ እንደባሰ ነዉ።

«የምጣኔ ሐብቱ ዉድቀት፥ የሙስናዉ ስፋት የፈጠረዉ ሥጋት አለ።መገለልና ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዉዉ ተሳትፎ አለመኖር በተለይ ከደማስቆ በጣም በራቀዉና የምጣኔ ሐብቱ ችግር ከሌሎቹ አካባቢዎች ሁሉ እጅግ ባየለበት በሐገሪቱ ደቡባዊ ግዛት በሰፊዉ ይታያል።በዚሕም ምክንያት ከደማስቆ ወይም ከአሌፖ ግዛት የከፋ ቅሬታ አለ።»

ቅሬታዉ በለሌሎቹ የአረብ ሐገራት ከተያዘዉ ሕዝባዊ አመፅ ጋር ተዳምሮ ከሁለት ሳምንት በፊት ዴራዓ ላይ ፈንድቷል።በማከታተል የሌሎች ከተሞች ሕዝብም አደባባይ መዉጣቱ አልቀረም።የፀጥታ አስከባሪዎች መስጊድ ድረስ ገብተዉ በተቃዋሚ ሠልፈኞች ወይም አደራጆች ላይ የወሰዱት ጠንካራ እርምጃ ሕዝቡን በጣሙን ወጣቱን እያሸማቀቀ ነዉ።

ሕዝቡን ለተቃዉሞ የሚያደራጀዉ ሐይልም ደካማ ነዉ።ከዚሑ ጋር በሽር አል-አሰድ እንደ ሙባረክ ከመሳሰሉት የቀድሞ አቻዎቻቸዉ ጋር ሲወዳደር የሚወገዙ፥ የሚወቀሱበት የአገዛዝ ጭካኔ ወይም የአመራር ድክመት ብዙ የጎላ አይደለም።በዚሕም ምክንያት ሕዝባዊዉ አመፅ እስካሁን ድረስ በአልበሽር ላይ በቀጥታ አላነጣጠረም።የደማስቆ ገዢዎችን መንበረ-ሥልጣን የሚገዘግዝ አይነትም አልነበረም።ሐዳት የተሰኘዉ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ፊራስ አል ካሰስ ግን ባለፈዉ ሮብ ምኑን አይታችሁ አይነት ይላሉ።

«በመሠረቱ የተቃዉሞ ሠልፉ ዴራዓ ከተማ ብቻ የታጠረ አይደለም።ካሚሲሊ ዉጥም የተቃዉሞ ሠልፍ ነበር።በአሌፖ ከተማም የተቃዉሞ ሥልፍና ግጭትም ነበር።እኔ እምነት የተቃዉሞ ሠልፉ ወደ ሁሉም አካባቢዎች እየተስፋፋና ከጊዜ ወደ ጊዜም እየተጠናከረ የሚሔድ ነዉ።ከዉስጥ ካሉ ምንጮች ባለኝ መረጃ መሠረት በቅርቡ ትልቅ የተቃዉሞ ሠልፍ የሚደረግበት እንቅስቃሴ እንዳለ መናገር እችላለሁ።ሁሉንም የሐገራችንን የሶሪያን ክፍል የሚያዳርስ ሰልፍ ለመጥራት ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነዉ።»

Syrien Daraa Proteste Demonstration

ባለፈዉ አርብ ከጁማዓ ሶላት በሕዋላ ደማስቆ ዉስጥ በተጠራዉ የተቃዋሞ ሠልፍ ግን የታሰበዉን ያሕል ሕዝብ አልተካፈለም።ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት ደማስቆ አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ ቁጥር ከሁለት መቶ ብዙም የሚበልጥ አልነበረም።ያም ሆኖ የተቃዉሞ ሠልፉ አደራጆች ተስፋ አልቆረጡም።እንደ ደማስቆና አሌፖ በመሳሰሉት ትላልቅ ከተሞች የሚኖረዉ ሕዝብ አደባባይ እንዲወጣ በተለያየ መንገድ መቀስቀሳቸዉን ቀጥለዋል።

ፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ ዎል ስትሪት ጆርናል ለተሰኘዉ ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ሐገራቸዉ የቱኒዚያ እና የግብፅ አይነት ሕዝባዊ አመፅ አያሰጋትም።በአሰድ እምነት ሶሪያ የተረጋጋች ነች።የምጣኔ ሐብት አዋቂዉ ሰሚር ሳይፋን ግን ተቃራኒዉን ነዉ-የሚሉት።

«ከሕዝባችን ሠላሳ ከመቶዉ የሚኖረዉ በቀን ከሁለት ዶላር ባነሰ ገቢ ነዉ።ይሕ የሐገሪቱን መረጋጋት ለአደጋ ያጋልጠዋል።ሶሪያ ልትጠነቀቅ ይገባል።የሕዝቡ ኑሮ እንዲሻሻል፥ የምጣኔ ሐብታችንን መርሕ ክፍት ማድረግ አለብን።ብዙ ማምረት፥ ወደ ዉጪ ብዙ በላክ፥ ትሩ ክፍያ ያለዉ ሥራ ለሕዝባችን ማዳረስ አለብን።»

እስካሁን የነበረዉ ተቃዉሞ በፕሬዝዳት አሳድ ላይ በቀጥታ ከማነጣጠር ይልቅ በአሳድ ከአባታቸዉ በወረሷቸዉ ባለሥልታናት ላይ ያተኮረ ነዉ።ብዙዎቹ በሙስና የተዘፈቁ፥ የአዲሱ ትዉልድን ፍላጎትና ጥያቄ ለመቀበል የማይፈልጉ ናቸዉ።በዚሕም ምክንያት እስካሁን አሰድ እንደ የቱኒዚያ፥ እንደ ግብፅ፥ እንደ የመን መሪዎች ቀጥታ ዉግዘትና ተቃዉሞ አልገጠማቸዉም።

ከእስራኤል-እስከ ኢራቅ፥ ከሊባኖስ እስከ ቴሕራን ባለዉ ፖለቲካዊ ምሥቅልቅል እጃቸዉ አለበት እየተባሉ በምዕራባዉያን የሚወገዙት፥ ማዕቀብ የተጣለባቸዉም በሽር አል-አሰድ ሕዝባቸዉ ትንሽ ካንገራገረባቸዉ ከምዕራቡ የሚጠብቃቸዉን ግን አይዘነጉትም።እንደ ቃዛፊ ሊያጣፋቸዉ ባይጣደፍ እንኳን እንደ ቤን-ዓሊ፥ እንደ ሙባረክ ወይም እንደ ሳሌሕ እንደማይታገሳቸዉ ያዉቁታል።

ጊጋ በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የጀርመን የፖለቲካ ጥናንት ተቋም ባልደረባ አንድሬ ባንክ እንደሚሉት ደግሞ ፕዝዳት በሽር አል-አሰድ በዉጪዉ ግፊትም ሆነ በራሳቸዉ ስሕተት ወደራሳቸዉ መምጣቱ የማይቀረዉን ተቃዉሞ ፈጥነዉ ካለበረዱት ደማስቆ ቱኒስ፥ ካይሮ ወይም ሠነዓ መሆንዋ አይቀርም።

«(ሶሪያ ከሌሎቹ) የምትለይባቸዉ እዉነታዎች ከተጨፈለቁ እና ተቃዉሞዉ እንደ ቤን ዓሊ ፥እንደ ሙባረክ ወይም እንደ ሳሌሕ በቀጥታ በወጣቱ በሽር አል-አሰድ ላይ ማነጣጠር ከጀመረ የቅርብ ዘመኗ ሶሪያ የማታዉቀዉ ታሪክ ታያለች።»

አሰድ ዉሉ አድሮ ከሳቸዉ የሚደርሰዉን አደጋ ለማስቀረት የሕዝቡን ምጣኔ ሐብታዊ ጥያቄ ፈጥነዉ መመለስ በርግጥ አይችሉም።የፖለቲካ እና የሰብአዊ መብት ይዞታን እንደሚያሻሽሉ ግን አስታዉቀዋል።ከ1962 ጀምሮ የፀናዉን ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማንሳት ቃል ገብተዋል።የመገናኛ ዘዴዎችን ሕግ ለማሻሻል እና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለመፍቀድም ማቀዳቸዉን አስታዉቀዋል።
ባለፈዉ ቅዳሜ ከሁለት መቶ በላይ የፖለቲካ እስረኞችን ለቀዋል።

አሰድ እስካሁን ቃል የገቡትን የማሻሻያ ለዉጥ ነገ በይፋ ያስታዉቃሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነዉ። ተቃዋሚዎች ግን መንግሥት ቃል የሚገባዉ ጊዜ ለመግዣ ነዉ በማለት የለዉጡን ተስፋ አጣጥለዉታል።የቱርኩ ጠቅላይ ሚንስትር ሬሴብ ተይብ ኤርዶኻን ዛሬ እንዳስታወቁት ግን አሰድ ቃል የገቡትን ለዉጥ ገቢር እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዉላቸዋል።አባታቸዉ ከአርባ ሁለት አመት በፊት «የማስተካከያ አብዮት» ባሉት እርምጃ የባዕዝን የእስኪያ ዘመን መርሕ ለዉጠዉታል።በሽርስ? ይደግሙት ይሆን? ወይስ በሕዝባቸዉ አብዮት አድዮስ?።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ