የሶሪያ ሕዝባዊ አመፅና የዉጪዉ ሐይል | ዓለም | DW | 21.11.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሶሪያ ሕዝባዊ አመፅና የዉጪዉ ሐይል

የዓረብ ሊግ መስራቺቱ፥ ጠንካራዊቱ ሐገር ሶሪያ ከአባልነት እንድታተገድ፥ የዉጪ ታዛቢ ጣልቃ እንድታስገባ ቀነ-ገደብ እንዲቆረጥባት ገፋፊዋ ደግሞ ዘጠኝ መቶ ሺሕ ሕዝብ ያላት ትንሽ ሐገር ናት።ቀጠር።

default

ተቃዉሞ ሠልፈኛዉ

21 11 11

የፕሬዝዳንት በሺር አል-አሰድ ሥርዓት በርግጥ ተናግቷል።ሥርዓቱን ካንገዳገደዉ ሕዝብ እኩል የዉጪ ሐይላት በሥርዓቱ ላይ ማደማቸዉ ግን ብዙ ያነጋግራል።ለቤን-ዓሊና ለሙባረክ እስከ ፍፃሜያቸዉ ድረስ ሙሉ ድጋፋቸዉን ሲሰጡ የነበሩት፣የባሕሬንን ሕዝባዊ አመፅ የደፈለቁት፣የየመንን ሕዝብ ጥያቄ ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉት ከሁሉም በላይ የየራሳቸዉን ሕዝብ ያፈኑት ሐይላት ከሊቢያ ሕዝብ በላይ ሊቢያዊ የመምሰላቸዉ-ተቃርኖ አነጋግሮ ሳበቃ፣ የሶሪያ ሕዝብ አፈቀላጤ የመሆናቸዉ ዚቅ በርግጥ ያጠያይቃል።የሶሪያ ሁነት፣ የአነጋጋሪ-አጠያያቂዉ ተቃርኖ እንዴትነት ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።

መሐመድ ቦዓዚዚ ለቱኒዚያዎች እንደነበረ ሁሉ ሐሰን ዓሊ አክሌሕ የሶሪያዎች ነዉ።ቡዓዚዚ ሰዉነቱ ላይ ያርከፈከፈዉ ቢንዚን-የለኮሰዉ እሳት የወጣት ሕይወቱን ቀጥፎ-የቱኒዚያን ሕዝባዊ አብዮት ባቀጣጠለ በወር-ከሳምንቱ ሶሪያዊዉ ወጣት ደገመዉ።ሐሰን ዓሊ አክሌሕ-የሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ ከተማ የአል-ሐሳካሕ ነዋሪ ነበር።

ሐሰን ጥር ሃያ-ስድስት ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ነዉ) እራሱ ላይ የረጨዉ ቤን-ዚን የለኮሰዉ እሳት በቱኒዚያ ፍጥነት የሶሪያን ሕዝብ ለአደባባይ አመፅ አላሳደሙ-እርግጥ ነዉ።በወራት እድሜ ግን አብዛኛዉን ሶሪያዊ አነቃነቀዉ።የደማስቆ መንግሥትን የሐይል አጸፋም እንዲሁ።የሶሪያ ሕዝብ መጀመሪያ-ሐገሪቱን ለረጅም ጊዜ የገዛዉን የባዓዝ ፓርቲን አገዛዝ፥ ኋላ ደግሞ የፕሬዝዳት በሽር-ዓል አሰድን አመራር በመቃወም በተከታታይ ያደረገዉን የአደባይ ሠልፍ ለማስቆም የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች በወሰዱት እርምጃ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።

Syrien Schüsse auf Regierungsgebäude Damaskus

በተቃዋሚ ታጣቂዎች የተመታ ሕንፃ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምት መሥረት የሶሪያ ሕዝብ 3 500ኛዉን ሟች ባለፈዉ ዓርብ ርዕሠ-ከተማ ደማስቆ አጠገብ ቀበረ።

ሰዉ ቀድሞ ከሰፈረ-ከሥለጠናባቸዉ አስራ-አምስት አካባቢዎች ከፊት ከሚሰለፉት ጥቂቶች አንዷ ናት።ግሪኮች፣ ሮሞች፣ ሞንጎሎች፣ አይሁዶች፣ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች፣ የመስቀል ጦረኞች ቱርኮች፣ ፈረንሳዮች በየዘመናቸዉ ገድለዉ-እየገዙ፣ተገድለዉ-እየተገዙ፣እየገነቡ-ሲፈርሷት፣እያለሙ ሲያደቋት-ሥልጥነዉ-ሲሰየጡንባት ዘመነ-ዘመናት አሳልፋለች።ሶሪያ።

በ1946 ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ሥትላቀቅ-የጥንት ሥልጣኔ ፣ሐብት ዉበትዋን ብታጣ ለወደፊቱ መደርጀት፣ የሕዝቧን ሠላም ነፃነት ማስከበሩ አይገዳትም ነበር-የዚያ ዘመን ትዉልዷ ተስፋ-እምነት። ሁለተኛ የነፃነት በዓሏን ሳታከብር ፍልስጤም ይባል የነበረዉ ግዛት-እሁለት ተገምሶ ባንደኛዉ ግማደ-ግዛት እስራኤል መመስረቷ፥ ለብልጣብጥ የጦር መኮንኖቿ ለሥልጣን መወጣጫ-ሰበብ፥ለፈላጭ ቆራጭ ሥርዓታቸዉ ቀጣይነት ምክንያት- ሆነ።የአዲሱ ዘመን-አዲስ ትዉልድ ተስፋ ምኞችም ያፍታ ቅጭት።

የሶሪያ የጦር ጄኔራሎች በአረብ-እስራኤሎች ጦርነት ሰበብ በነፃነት ማግሥት ተመስርቶ የነበረዉን ምክር ቤታዊ ሥርዓት አስወግደዉ የዚያችን ሐገር ሥልጣን ይፈራረቁበት ያዙ።በ1963 ቀዳሚዎቻቸዉን አስወግደዉ ሥልጣን የያዙት የባዓዝ ፓርቲ አባላት የጦር መኮንኖች ደግሞ ምናልባት ከቀዳሚያቸዉ ሁሉ የከፋዉን እስከ ዛሬ የዘለቀዉን የፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት መሠረቱ።

ሐሰን ዓሊ አክለሕ እራሱን በእሳት ባያያዘ በወሩ አብዛኛዉን ሶሪያ ያዳረሰዉ ሕዝባዊ ሰልፍ፥የባዓዝ የጦር መኮንኖች 1963 በደነገጉት የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን የሙስሊም ወድማቾች፥ የኮሚንስት ፖርቲ አባላትን፤ የኩርድ ፖለቲከኞችን እያሳደዱ የመረሸን፣ ማሳር፥ማጋዛቸዉ ግፍ፥ ከትሩን የመጣሱ፥ ተራዉን ሕዝብ ጠፍንገዉ ያሰሩበት ሰንሰለት የመዛጉ ግልፅ ምልክት ነዉ።

ፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ በቀደም እንዳሉት ግን መንግሥታቸዉ የአመፁን ምክንያት፥ ሕዝባዊነቱንም አይቀበለዉም።

«ታጣቂዎች አሁን የሚያደርጉትን ማስቆም አለብን።ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸዉን፥ በተለያዩ የሶሪያ ክፍሎች የሚፈፅሙትን ጭፍጨፋ መግታት አለብን።ከአጎራባች ሐገራት ድንበር በኩል ወደ በሶሪያ የሚገባዉን የጦር መሳሪያ፥ ለታጣቂዎቹ መርጃ አሁን በጎረቤት ሐገሮች ድንበር በኩል የሚገባዉን ገንዘብ ማስቆም አለብን።ይሕ ማድረግ ያለብን ነዉ።»

አሰድ-ሕዝባዊዉን አመፅ ለመደፍለቅ ጦራቸዉ የሚወስደዉን እርምጃ ትክክል ለማስመሰል ካሉት የተሻለ የሚሉት በርግጥ አልነበረም።የዚያኑ ያክል ያሉት ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነዉ-ማለት አይቻልም። ሕዝባዊዉ አመፅ-እንደ ቱኒዚያ፥ እንደ ግብፅ ብጤዎቹ የገዢዎቹን እርምጃ መቋቋም-አለመቋቋሙ በቅጡ ሳይታወቅ፥ አመፁን እንደ ሊቢያ ለየራስ ጥቅማቸዉ ለማዋል የሚሹ የዉስጥ ታጣቂዎች፥ ባንድ በኩል፥ ሥልታዊ ጥቅም፥ ቂም በቀል-ያሳደማቸዉ የአጎራባችና የሐያል መንግሥታት በሌላ በኩል አቃርጠዉ መያዛቸዉ ሐቅ ነዉ።

ሶሪያ በነገድ፣ አረቦችን ከኩርዶች፣ ከአሰሪያዎች፣ በሐይማኖት፣ ሱኒ ሙስሊሞችን፣ ከአላዊቶች፣ ከዱርዞች፣ ሙስሊሞችን ከክርስቲያኖች አሰባጥራ የያዘች ሐገር ናት።ካጠቃላዩ ሕዝቧ ሰባ አራት ከመቶዉ ሱኒ ሙስሊም ነዉ።ከ1963 ጀምሮ ሕዝቡን ረግጠዉ የሚገዙት ግን ከሐገሪቱ ሕዝብ አስራ-ሰወስት በመቶ የሚሆነዉ አላዊት የተሰኘዉ የሺዓ ሙስሊም ሐራጥቃ እምነት ተከታዮች ናቸዉ።

የአናሳዎች የበላይነት ብዙሐኑን ሱኒ ቅር ማሰኘቱ አልቀረም።የአረቦች አገዛዝ በተለይ ኩርዶችን ለጠመንጃ አመፅ መጋበዙ እዉነት።ሶሪያ በመልካዓ-ምድር አቀማመጧ የሱኒ፥ የዱርዝ፥ የሺዓ፥ ሙስሊሞችን ከተለያዩ የክርስቲያን ሐራጥቃ ተከታዮች ጋር አሰባጥራ የያዘችዉ ሊባኖስን፥ ኩርዶች ለነፃነት የሚፋለሙባትን ቱርክን፥የሺዓዎች የመንግሥትነት ሥልጣን የያዙባትን ኢራቅን፥ ሱኒዎች የሚበዙባትን ዮርዳኖስን እና አይሁዳዊቷን እስራኤልን ታዋስናለች።

በኩርዶች ሰበብ ከቱርኮች፥ በፖለቲካ ግድያ ሰበብ ከሊባኖስ፥ኢራንን በመወዳጀትዋ ምክንያት ከስዑዲ አረቢያ፥ ቀጠርንና ዮርዳኖስን ከመሳሰሉት አጎራባቾችዋ አንድም-ደም ተቃብታለች አለያም ተቀያይማለች።እነዚሕ ሐገራት እንደ ትሪፖሊ ሁሉ ደማስቆ ላይ የቋጠሩትን-ቂም ቁርሾ ለማወራረድ ሕዝባዊዉ አመፅ በፈጠረዉ አጋጣሚ በነፍጥ የሚዋጉ ሐይላትን ማስታጠቅ፥ በገንዘብ መርዳት፥ ማደራጃታቸዉ አያነጋግርም።

«እና እንደሚመስለኝ ለዉጊያ የቆረጡ፥ በቅጡ የታጠቁ፥ እና ምናልባትም በቂ የገንዘብ ድጋፍ ያላቸዉ ተቃዋሚዎች በመኖራቸዉ የርስ በርስ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል።»

የዩናይትድ ስቴትስዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን ባለፈዉ ቅዳሜ።

የዩናይትድ ስቴትስንና የወዳጆችዋን መንግሥታት ዲፕሎማሲያዊ ሚስጥር ያጋለጠዉ ዊኪሊክስ የተሰኘዉ አምደ መረብ ባለፈዉ ሰሞን እንደዘገበዉ ዩናይትድ ስቴትስ የሶሪያን መንግሥት ለሚቃወሙ ሐይላት ስድስት ሚሊዮን ዶላር ትረዳለች።ስዑዲ አረቢያና ቀጠርም በየፊናቸዉ የደማስቆ ተቃዋሚዎችን ይረዳሉ።ክሊንተን የጠቀሱት ጠመንጃና ገንዘብ በአብዛኛዉ ወደ ሶሪያ የሚገባዉ ደግሞ ብዙዎች እንዳሉት በሊባኖስ በኩል ነዉ።

የተለያዩ የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚዎች የሊቢያዉን መሰል ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት የመሠረቱት በቀድሞዋ የአረቦች ገዢ፥ የቱርኮችን መብት በማፈኗ በምትወቀሰዉ ቱርክ ዉስጥ ነዉ።ቱርክ ለተመሠረተዉ ምክር ቤት እዉቅና የሰጠችዉ ግን ቱርክ አይደልችም።ሊቢያ እንጂ።

ሶሪያ እንደ አብዛኛዉ አረብ የእስራኤል ጠላት፥የኢራን ልዩ ወዳጅ፥ በዉጤቱም የዩናይትድ ስቴትስ ጠላት፥ የዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ወዳጆች የሚባሉት የዮርዳኖስ፥የስዑዲ አረቢያ፥ የሊባኖስ እና የቀጠር ባላንጣ ናት።በሌላ በኩል የሶሪያ የቅርብ ጎረቤት ኢራቅ ሥልጣን ላይ ያለዉ መንግሥት በዩናይትድ ስቴትስ ጦር ወረራ፥ በዩናይትድ ስቴትስ ሁለንተናዊ ድጋፍ የተመሠረተ፥ የዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ወዳጅነቱ ሊያነጋግር አይገባም።

ሶሪያ ከዓረብ ሊግ አባልነት እንድትታገድ አባል መንግሥታት ድምፅ ሲሰጡ ድምፅዋን ያቀበችዉ ብችኛ አባል ሐገር-ግን ኢራቅ ናት።ምክንያት-ተንታኖች እንዳሉት ሺዓ በአላዊት አይጨክንም።የዓረብ ሊግ መስራቺቱ፥ ጠንካራዊቱ ሐገር ሶሪያ ከአባልነት እንድታተገድ፥ የዉጪ ታዛቢ ጣልቃ እንድታስገባ ቀነ-ገደብ እንዲቆረጥባት ገፋፊዋ ደግሞ ዘጠኝ መቶ ሺሕ ሕዝብ ያላት ትንሽ ሐገር ናት።ቀጠር።

የቀጠሩ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሐሚድ ቢን ጃሲም-አ ሳኒ፥ ባለፈዉ ሐሙስ ራባት-ሞሮኮ የተሰየመዉ የዓረብ ሊግ ለሶሪያ የሰጠዉን የሰወስት ቀነ-ገደብን ደማስቆዎች እንዲያከብሩ አስጠነቀቁ።

«አንድ የመጨረሻ እድል እንስጥ ሥለሚባል ነገር መነጋገር አንፈልግም።ምክንያቱም እርምጃዉ ማስጠንቀቂያ እንዲመስል እኔ ሥለማልፈልግ።መናገር የምችለዉ የአረብ ሊግ እስካሁን ያቀረበዉ ሐሳብ ከፍፃሜዉ መድረሱን ነዉ።የሶሪያ ወንዶሞቻችን ይሕን ጥፋት ለማስቆም የምናደርገዉን ጥረት ይረዱን ዘንድ ለፈጣሪ እንፀልያለን።ተስፋም እናደርጋለን።»

ትንሺቱ አረባዊት ሐገር ከ19ኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ከአ-ሳኒ ቤተ-ሰብ ፍፁም ዘዉዳዊ አገዛዝ በስተቀር ሌላ ሥርዓት አታዉቅም።ከዚሕ ቀደም ለሊቢያ፥ ዛሬ ደግሞ ለሶሪያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ጥያቄ ዋና ተሟጋችዋ ግን ዲሞክራሲ የማታዉቀዉ ቀጠር ናት። የየመን ሕዝብ ጥያቄ የሚደርስበት ግፍ በደልም ከሶሪያ ወይም ከሊቢያ ሕዝብ የተለየ አይደለም።

አብዛሐዉ የሶሪያ ሱኒ ሙስሊም ሕዝብ በአናሳዉ የአላዊት ሙስሊም ሐራጥቃ መገዛቱ ተገቢ ካልሆነ-የባሕሬን አብዛኛ የሺዓ ሙስሊም በአናሳዉ የሱኒ ነገሥታት መገዛቱ እንደ በጎ የሚታይበት ምክንያት አይኖርም።የባሕሬንን ሕዝባዊ አመፅ በታንክ ያስደፈለቁት፥ ለየመን ገዢዎች ሙሉ ድጋፍ የሚሰጡት የስዑዲ አረቢያ፥ የቀጠር፥ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፥ የኦማን፥ የኩዌትና የባሕሬን ገዢዎች የደማስቆን መንግሥት ለማስወገድ ዋና ተዋኞች ናቸዉ።


የቱኒዝያ ሕዝባዊ አመፅ እንደተቀጣጠለ አመፁ ቀደሞ ከተዛመተባቸዉ ሐገራት አንዷ ዮርዳኖስ ናስ።የዮርዳኖሱ ንጉስ አብደላሕ ዘዉዳዊ ሥርዓታቸዉን ከሕዝብ ቁጣ ያተረፉት ካለፈዉ ጥር-ወዲሕ ሰወስት ጠቅላይ ሚንስትሮችን በመቀያየር ነዉ።ንጉስ አብደላሕ በቀደም «በሸር አል-አሰድ ሥልጣን መልቀቅ አለባቸዉ-አሉ።ሶሪያን ከአባልነት-ያስወገደዉ፥ ለቅጣት የወሰነዉን የዓረብ ሊግ ጉባኤ ያስተናገዱት ደግሞ እንደ ዮርዳኖስ ብጤያቸዉ ሁሉ ሕዝባዊዉን አመፅ ጠጋግነዉ-ያዳፈኑት የሞሮኮ ንጉስ መሐመድ-ስድስተኛ ናቸዉ።አጃኢብ ይል ይሆን አረብ።

Syrien Präsident Bashar al-Assad

የአሰድ ደጋፊዎች

የቱኒዚያ ሕዝብ ትግል ጅምርም ቢሆን-የበጎ ጭላጭል ፈንጥቆበታል።የግብፅ ሕዝብ ግን ብቻዉን -የታገለለትን የመብት፥ እኩልነት፥ የፍትሕ-ፍሬ ለማየት ዛሬም ዳግም መሠለፍ፥ የቀሪ ወገኖችን ሕይወት መገበር ግድ ሆኖበታል።በዓለም ሐያላን ሚሳዬል-ቦምብ የተገኘዉ የሊቢያ ለዉጥ ለሐገሬዉ ሕዝብ የሚኖረዉ ፋይዳ አልታወቀም።ሶሪያ፥ቱኒዚያ፥ ግብፅ ወይም ሊቢያን-መሆን አለመሆኗ-ያዉ ጊዜ ነዉ በያኙ።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌAudios and videos on the topic