የሶማልያ ጊዜያዊ ሁኔታና ስደተኛው መንግሥት፧ | የጋዜጦች አምድ | DW | 23.02.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የሶማልያ ጊዜያዊ ሁኔታና ስደተኛው መንግሥት፧

በአሁኑ ጊዜ፧ በዓለም ውስጥ፧ ማዕከላዊ መንግሥት የሌላትና ሥርዓት አልበኛነት ፲፬ ዓመታት ያህል እንደነገሠባት የምትገኝ ብቸኛ ሀገር፧ ሶማልያ መሆኗ እሙን ነው። የዓለም ኅብረተሰብም እስከቅርብ ጊዜ ደንታ ሳይሰጠው ቆይቶ፧ አንዲት የ ቢ ቢ ሲ ጋዜጠኛ ሞቃዲሾ ውስጥ ከተገደለችና፧ በአፍሪቃ ኅብረት የልዑካን ቡድን በተቃጣ ጥቃትም ፪ ሰዎች ከተገደሉ ወዲህ ነው፧ እንደገና የሶማልያን ጉዳይ አሳሳቢ አድርጎ መመልከት የጀመረው። ባለፈው ጥቅምት፧ ናይሮቢ፧ ኬንያ

ውስጥ የተመሠረተው የሽግግር መንግሥት፧ ወደ ሞቃዲሹ ለመዛወር ካቀደ ወራትም ሆኑ ሳምንታት አልፈዋል። የወዲያኛው ሰሞን የጥቃት ዓላማ፧ በስደት የተመሠረተው መንግሥት አገር እንዳይገባና ህግና ሥርዓት እንዳያስከብር፧ ሰላምም እንዳያሠፍን፧ ለመግታት ያቀዱ ወገኖች ደባ ይሆን? የዶቸ ቨለ ራዲዮ ባልደረባ፧ ማያ ድራየር፧ የሶማልያን ይዞታ እንዲህ ዳሳለች።

የሶማልያ የስደት መንግሥት፧ ፀጥታው አስተማማኝ ስላልሆነለት፧ ወደ መዲናይቱ ሞቃዲሹ የሚያመራበትን ጉዞ ማሸጋሸግ ግድ ሆኖበታል። የሶማልያ መዲና በዓለም ውስጥ፧ እጅግ አደገኛ ከሚሰኙት መዲናዎች መካከል አንዷ ናት። የተለያዩ የጦር አበጋዞች ሚሊሺያ ጦረኞች፧ ከተማይቱን ተከፋፍለው በቁጥጥራቸው ሥር ማቆየታቸው የታወቀ ነው። በተሽከርካሪዎች ላይ ከባድ መትረየስ ጠምዶ መዘዋወር፧ ለጦር አበጋዞች የክብር ምልክት ሆኖ ነው የሚታያቸው። ጠቅላይ ሚንስትር አሊ መሐመድ ገዲ፧ የትውልድ ቦታቸውን ሞቃዲሹን ለጊዜው በመተው፧ የሚንስትሮች ምክር ቤት
አባላት ከሚገኙበት አንድ የልዑካን ቡድን ጋር፧ ጊዜያዊ የመንግሥት መቀመጫ ፍለጋ ተሠማርተዋል። የመንግሥት ቃል አቀባይ ዩሱፍ ባሪባሪ እንደሚሉት፧ አሊ መሐመድ ገዲ፧ የአቋም ገለልተኛነትን ጠብቆ ለመገኘት ሰፊ ጥረት ነው የሚያደረጉት።
O-ton(Eng.)
«ይህ በፖለቲካ መለኪያ ሳቢያ የደረሱበት ውሳኔ አይደለም። መንስዔው፧ የጸጥታ ይዞታ፧ እንዲሁም የስንቅና ትጥቅ ጉዳይ ነው« ብለዋል።
ዩሱፍ ባሪባሪ፧ ካለው ስሜታዊ ፖለቲካ ነክ ሁኔታ በመነሣት፧ በትንቃቄ መናገርን ነው የሚመርጡት። በሶማልያ በፖለቲካ፧ ከ ፪፻ በላይ የጎሣ ክፍልፋይ ቡድኖች ናቸው፧ በትጋት የሚሳተፉት። ከ ፲፬ ዓመት ገደማ በፊት፧ ኅብረት በመፍጠር አምባገነኑን ሲያድ ባሬን፧ ከሥልጣን ለማስወገድ ተባብረው ቢዋጉም፧ የመጀመሪያው ግባቸው ከመታ በኋላ እርስ በርስ ሲጋጩ መቆየታቸው የሚታበል አይደለም። ግጭቱ ተስፋፍቶ ወደየእርስ በርስ ጦርነት በተሸጋገረበት ወቅት፧ የተባበሩት መንግሥታት ጦር ኃይልና የዩ ኤስ አሜሪካ ኃይልም ቢሆን፧ ለማስቆም ሳይችል መቅረቱ አይዘነጋም። የአሁኑ አዲስ የሽግግር መንግሥት፧ ሰላም ለመመሥረት፧ ጥረት የተደረገበት፧ ፲፬ኛው የጦር አበጋዞች ሙከራ ውጤት ነው። የሶማልያ ጎሣዎችና የሃይማኖት ተጠሪዎች፧ ተስማምተው የስደት መንግሥት ኬንያ ውስጥ እስኪያቋቁሙ ድረስ፧ ፪ ዓመት ወስዷል። እያንዳንዱ የጎሣ የጦር አበጋዝ የሚንስቴር ሥልጣን የሚያገኝ ሲሆን፧ ጠቅላይ ሚንስትር ገዲ፧ ፺ ያህል ሚንስትሮችና ምክትል ሚንስትሮች እንዳሏችው ታውቋል። እጅግ ብዙ ባለሥልጣናት ናቸው። ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ዩሱፍ፧ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲላክላችው የጠየቁትም እንዚህን ሁሉ ባለሥልጣናት ጭምር መጠበቅ ይቻል ዘንድ ነው። የተጠየቀው ከአፍሪቃ ኅብረትና ከአረብ መንግሥታት ማኅበር የተውጣጣ ኃይል እንዲሠማራ ነው።
አንድ ሚንስትር፧ ሰላም አስከባሪ ኃይል በፍጹም ሊሠማራ አይገባም ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል። ሞቃዲሹ ውስጥ ብርቱ ኃይል ባላቸው የጎሣ ጦር አበጋዝ፧ ሼክ ሐሰን፧ የሚመሩ እስላማውያን፧ የውጭ ኃይል እንዳይገባ! ብለዋል። እነዚህ ወገኖች ጥቂቶች ናችው ቢባልም በሰላሙ ሂደት ፍጹም ባለመሳተፋቸው፧ እጅግ አደገኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው የሚገመተው። ዋና ጽህፈት ቤቱ በብራሰልስ፧ ቤልጅግ የሚገኘው ዓለም አቀፍ፧ የውዝግቦች አጥኚ ቡድን የሶማልያ ጉዳይ ተከታታይ ማት ብራይደን እንዲህ ይላሉ።
O-ton(
«አስፈሪው አደጋ፧ ከ አዋሳኝ አገሮች መካከል፧ ኢትዮጵያ፧ ሰላም አስከባሪ ጦር ኃይል፧ ወደ ሶማልያ ከላከች ነው። እስላማውያኑ ድጋፍ በማሰባሰብና ከሌሎች ቡድኖች ጋር በመተባበር፧ የእርስ-በርሱ ጦርነት፧ ከዚህ ቀደም ባልታየ አሸባሪነት፧ ክፉኛ ሊያገረሽ ይችላል« ባይ ናችው።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት፧ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ሶማልያ ውስጥ እንዳይገባ በማለት አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች እንደነበሩ በጊዜው ተዘግቧል። እነዚህ ወገኖች፧ የወሰን ውዝግብን፧ እንዲሁም ኢትዮጵያ፧ አንዳንድ የሶማልያን የጎሣ ጦር አበጋዞች ትደግፋለች በማለት አመኔታ እንዳልጣሉባት ነው የሚነገረው። አዲሱ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ዩሱፍ ራሳቸው፧ በኢትዮጵያ ድጋፍ ተጠናክረው በመውጣት፧ ከዚህ ደረጃ በመድረሳቸውም፧ የተለያዩ አንጃዎችን ሁሉ በተሳካ ሁኔታ ማስተባበር የመቻላቸው ሁኔታ ያጠራጥራል ነው የሚባለው።
ሶማልያ፧ ተረጋግታ መንግሥታዊ ተግባራትን ማከናወን እስኪቻል ድረስ ገና ጊዜ ያስፈልጋል።