የሶማልያ ወታደሮች ሥልጠና በጀርመን ጦር | አፍሪቃ | DW | 17.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሶማልያ ወታደሮች ሥልጠና በጀርመን ጦር

ከአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት የተውጣጡ የጦር መኮንኖች ባለፉት ሦስት ዓመታት ለ3,600 የሶማልያ ፀጥታ ኃይላት ሥልጠና ሰጥተዋል። ውዝግብ ባዳቀቃት ሶማልያ ውስጥ ሁኔታዎች አስተማማኝ ስላልነበሩ ሥልጠናው የተካሄደው በአንድ የዩጋንዳ ማዕከል ውስጥ ነበር።

የሶማልያ መንግሥት በመዲናይቱ ሞቃዲሾ ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ የመረጋጋት ሁኔታ መስፈኑን በማስታወቅ ሥልጠናው በመዲናይቱ እንዲካሄድ ጠይቋል። በዚህም መሠረት አውሮጳውያኑ የጦር መኮንኖች፣ ከጀርመናውያኑ በስተቀር ወደዚያ ለመሄድ ተዘጋጅተዋል። ጀርመናውያኑ አሠልጣኞች ወደ ሶማልያ ይሄዱ ዘንድ የፌዴራዊው ምክር ቤት አዲስ ውሳኔ ያስፈልጋል።

በደቡብ ምዕራብ ዩጋንዳ በሚገኘው የቢሀንጋ ማዕከል ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁት ሶማልያውያን ወታደሮች እና አሠልጣኞቻቸው በዩጋንዳ የጦር ሙዚቃ ቡድን ታጅበው የመጨረሻውን ሠልፋ ሲያካሂዱ ነበር የተሰማው። በዚሁ የመጨረሻ ሥነ ሥርዓት ለመገኘትም የአውሮጳ ኅብረት ጀነራል ከብራስልስ፣ የሶማልያ ጦር ምክትል ኃላፊ ደግሞ ከሞቃዲሾ ለዚሁ አጋጣሚ ወደ ቢሀንጋ ሄደዋል። ሶማልያውያኑ በዩጋንዳ የሦስት ዓመት ሥልጠና እንዳጠናቀቁ ጀርመናዊው የቡድኑ ዋና አዛዥ ቶማስ ሽፑርሴም አስረድተዋል።

«መሠረቱን በመጣላችን መርሀግብሩ በእርግጥም የተሳካ ነበር ለማለት ይቻላል። ለሥልጠና ወደ ማዕከሉ የመጡት ሶማልያውያን ልክ በፊልም ወይም በዜና እንደሚታየው የጦር መሣሪያ ይዘው እንዳሻቸው በዙርያቸው ይተኩሱ የነበሩ ተዋጊዎች ናቸው። አሁን ግን ባንድነት መሥራት የምንችልበትን መዋቅር ዘርግተናል። ይህ እንግዲህ ወደፊት በሶማልያ ለሚቀጥለው የሀገሪቱ ፀጥታ ኃይላት ሥልጠና መሠረት በመሆን ያገለግላል።»

3,600 ሶማሊያውያን በቢሀንጋ ዩጋንዳ ሥልጠና አግኝተዋል። በመጀመሪያ መሠረታዊ የሚባለውን ሥልጠና ካገኙ በኋላ ለምሳሌ የራድዮ ግንኙነት፣ የዜና አቀራረብ፣ በምሕንድስናው ዘርፍ እና የጦር ፖሊስ ስለሚፈፅማቸው ተግባራት እና በሲቭሉ ሕዝብ አኳያ መከተል ስላለባቸው አቀራረብ ልዩ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። የ22 ዓመቱ ሶማልያዊው ልየተናንት አህመድ ኑር ሥልጠናው ጠቃሚ እንደነበር አስረድቶዋል።

«በፈቃደኝነት ነበር እአአ በ 2010 ዓም የጦር ኃይሉን የተቀላቀልኩት። ፍላጎቴ ጠላትን መዋጋት እና ሀገሬን መከላከል ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩጋንዳ የመጣሁት በ2012 ዓም ሲሆን፣ በዚህ ያገኘሁት ሥልጠና ሀቀኛ ወታደር እንድሆን ረድቶኛል። ይህንን ዋና አዛዤ ወደ ሀገሬ ከተመለስኩ በኋላ ተመልክቶታል። ዘንድሮም ለቀጣይ ሥልጠና ወደ ዩጋንዳ ልኮኛል። አሁን በሶማልያ የአንድ ጦር ቡድን መሪ እሆናለሁ። ጠላታችን አሸባብ አሁንም ትልቅ ፈተና እንደደቀነ ይገኛል። ይሁንና፣ ጦራችን እየጠነከረ እና በሚገባ እየሠለጠነ በመጣ ቁጥር፣ ጠላት ደግሞ እየተዳከመ መሄዱ አይቀርም።»

በሶማልያ የተሠማሩት የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ጓድ ወታደሮች አሸባብን ከመዲናይቱ ሞቃዲሾ በማስወጣታቸው በመዲናይቱ መረጋጋት ይታያል።

በዚህም የተነሳ የሶማልያ መንግሥት የአውሮጳ ኅብረት ሥልጠናውን ወደ ሞቃዲሾ እንዲያዛውር ጠይቋል። አውሮጳውያኑ አሠልጣኞች በመጨረሻ ደረጃ በሚገኘው የሥልጠና ሂደት ላይ ከፊታችን ጥር ወር ወዲህ በዚያ ሶማልያውያኑን አሠልጣኞች በማማከር ተግባር ይረዳሉ። ሶማልያውያኑን የማሠልጠኑ ተግባር ከቢሀንጋ ወደ ሞቃዲሾ በሚዛወርበት ጊዜ ከጀርመናውያኑ በስተቀር ኢጣልያውያኑ፣ ስጳኛውያኑ፣ ፈረንሳውያኑ እና አየርላንዳውያኑ ወደዚያው ይሄዳሉ። ጀርመናውያኑ ግን የሀገራቸው ፌዴራዊ ምክር ቤት ለዚህ የሚያስፈልገውን ውሳኔ እስኪያሳልፍ ድረስ ወደ ሀገራቸው መመለስ ግድ ነው የሚሆንባቸው። ምክር ቤቱ ጀርመናውያኑን የጦር አሠልጣኞች ወደ ሶማልያ ስለመላክ አለመላኩ ጉዳይ ውሳኔ ማሳለፍ ያልቻለው ባለፈው መስከረም መጨረሻ ከተካሄደው ምክር ቤታዊው ምርጫ በኋላ በሀገሪቱ እስከትናንት ድረስ አዲሱ ጥምር መንግሥት ባለመመሥረቱ ምክንያት ነበር።

ዚሞነ ሽሊንድቫይን/አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic