የሶማልያ ወቅታዊ ሁኔታ | አፍሪቃ | DW | 01.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሶማልያ ወቅታዊ ሁኔታ

ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ እሁድ እስላማዊ ታጣቂዎች ሶማልያ መቃዲሾ በሚገኘዉ የሀገሪቱ ማዕከላዊ የደህንነት ቢሮ ላይ ጥቃት በመጣል በቅጥር ግቢው ዉስጥ ባለው ወህኒ ቤት እስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪ አሸባሪዎችን ለማስለቀቅ ሞክረዉ እንደነበር ታዉቋል።

በሌላ በኩል በዚሁ በሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ የአፍሪቃ ኅብረት ወታደሮች ከሶማልያ መንግሥት ጦር ጋር በመተባበር በጀመሩት «የህንድ ዉቅያኖስ ተልዕኮ» በሀገሪቱ የሚገኙ አሸባብ አክራሪ ኃይሎችን በማደን ላይ ይገኛሉ። የመቃድሾ የዛሬ ዉሎ ምን ይመስላል? በሶማልያ የማኅበረሰቡ ዕለታዊ ኑሮስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? አዜብ ታደሰ በሶማልያ መቃድሾ ነዋሪ የሆነዉን የዶይቼ ቬለ ወኪል መሀመድ ኦመር ሁሴይንን አነጋግራ ዘገባ አጠናቅራለች፤


የአፍሪቃ ኅብረት ወታደሮች እና የሶማልያ የመንግሥት ወታደሮች፤ በደቡባዊ ሶማልያ በአሸባብ አክራሪ ኃይላት ተይዛ የነበረችዋን የቡላማሬን ከተማ መልሰዉ መቆጣጠራቸዉና፤ የአሸባብ አማፅያን ጠንካራ ይዞታ ወደ ሆነዉ ባራዊ ከተማ መቃረባቸዉ ተመልክቶአል። አሸባብ በጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓ,ም የመቃዲሾ ከተማ ይዞታን ከተነጠቀ በኋላ፤ በሀገሪቱ የሚገኙ የአሸባብ ኃይሎችን ለማስወጣት የሚደረገዉ ጥረት የቀጠለ ሲሆን፤ በያዝነዉ ዓመት መጀመርያ ላይ ከተደረገዉ ትግል በኋላ፤ ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ባነቃቃው «የህንድ ዉቅያኖስ» በተሰኘው ተልዕኮ አሸባብን ለሁለተኛ ግዜ የማሳደድ ሂደት ጀምሮዋል። የአሸባብ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ከጎርጎረሳዊ 2006 ዓ,ም እስከ 2011 ዓ,ም አብዛኛዉን የሶማልያ ደቡባዊ ክፍል ተቆጣጥሮ እንደነበር ይታወሳል። ይሁንና፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ መዲናይቱ መቃድሾን ጨምሮ በርካታ ከተሞች በአፍሪቃ ኅብረት ጦርና በሶማልያ ወታደሮች እጅ ገብተዋል። እንድያም ሆኖ የተለያዩ የሶማልያ ገጠር እና ከተሞች አሁንም በአሸባብ አማፂ ቡድን እጅ ሥር ይገኛሉ። መቃዲሾ የሚገኘዉ የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ መሃመድ ኡመር ሁሴይን እንደሚለዉ፤ የአፍሪቃ ኅብረት ጦርና የሶማልያ ወታደሮች ባለፈው በቅዳሜ ባንድነት ባካሄዱት ዘመቻ ቡላመሪር የተሰኘችዉን ከተማ ከአሸባብ ማስለቀቅ ተሳክቶላቸዋል።

« የአፍሪቃ ኅብረት ወታደሮች እና የሃገሪቱ ወታደሮች በሶማልያ የሚገኙ የአሸባብ አክራሪ ኃይሎችን ለመታገል «የህንድ ዉቅያኖስ ተልዕኮ» በሚል ዘመቻ ጀምረዋል። ባለፈዉ ቅዳሜ ከመቃዲሾ በግምት 170 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉ ቡላመሪር ደቡባዊዋን ከተማንም ተቆጣጥረዉ በእጃቸዉ አስገብተዋል። ኃይሉ በቀጣይ ትግሉን ወደ ኪስማዮ እንደቀጠለም ነዉ የተነገረዉ።»
ህንድ ዉቅያኖስን በሚያዋስኑት የሶማልያ አካባቢዎች የተጀመረዉ «የህንድ ዉቅያኖስ ተልዕኮ» ድል መመዝገቡን የደቡብ ሶማልያ ግዛት ሃገረ-ገዥ አብዱል ቃድር ሞሃመድ ለብዙሃን መገኛዎች ገልፀዋል። እንደ ሶማልያ መንግሥት እምነት በዚህ ትግል፤ በሀገር ዉስጥ እና በዉጭ ሀገራት ጥቃት ለመጣል እቅድ ላይ የነበሩ የአሸባብ ደፈጣ ተዋጊዎች ተከማችተዉ ከሚገኙበት ቦታ እንዲለቁ ነዉ የተደረገዉ። በዚሁ ባሳለፍነዉ ሳምንት መጀመርያ ላይ የአፍሪቃ ኅብረት እና የሶማልያ መንግሥት ወታደሮች፤ በሰሜናዊ ምዕራብ ሶማልያ ኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ተዋግተዉ ባኮል አዉራጃ የምትገኘዉን ታይግሎ ከተማን ማስለቀቃቸዉ ይታወቃል።


በሌላ በኩል ትናንት ማለዳ አንድ ቦምብ የተጠመደበት ተሽከርካሪ መዲና በመቃዲሾ የብሔራዊውን ማዕከላዊ የደኅንነት ህንፃን ጥሶ በመግባት በህንፃው ምድር ቤት ዉስጥ በሚገኘው «ጎድካ ጃልዎ» በተባለዉ ወህኒ ቤት ውስጥ በእስር ላይ የነበሩ ተጠርጣሪ እስላማዊ አክራሪዎችን ነፃ ለማስለቀቅ ጥረት ማድረጉ ተመልክቶአል። የዶይቼ ቬለዉ ጋዜጠኛ መሃመድ ኡመር ሁሴይን ዛሬ ከመቃዲሾ እንደገለፀዉ፤ የሶማልያ ብሔራዊ የደህንነት መስሪያ ቤት ትናንት ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ቢያንስ አንድ ሲቪልና ሶስት የመንግሥት ወታደሮች ሞተዋል፤ በአሁኑ ሰዓት የከተማዋ የፀጥታ ሁኔታም ከፍተኛ ጥበቃ ሥር ነዉ፤
« አልሸባብ በህንፃዉ ላይ ጥቃት በጣለበት ጊዜ ቢያንስ ሰባት አጥቂዎች ነዉ የተገደሉት። በጥቃቱ አራት ወታደሮች እና አንድ ሲቪልም ቆስለዋል። ከጥቃቱ በኋላ የከተማዋ የፀጥታ ጥበቃ ጉዳይ ከምን ጊዜዉም በላይ ተጠናክሮዋል፤ እያንዳንዱ ጎዳና በቁጥጥር ዉስጥ ነዉ።»

እንድያም ሆኖ ይላል መሃመድ ኡመር ሁሴይን ፤ የከተማይቱ ሕዝብ ኑሮውን እንደተለመደው በመምራት ላይ ይገኛል።
« በከተማዉ ዉስጥ የሚታየዉ የሰዉ ቁጥር እጅግ ብዙ ሆንዋል። የመንግሥት የጦር ኃይል እና የአፍሪቃዉ ኅብረት ጦር አሸባብ ላይ ጥቃት ካደረሰበት ቦታዎች ላይ የነበሩ አብዛኛ ነዋሪዎች ወደ መቃዲሾ መምጣት ከመጀመራቸዉ በስተቀር፤ ከተማዋ ተረጋግታለች፣ ጥሩ እንቅስቃሴም ይታይባታል።»

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic