የሶማሊያ ፕሬዝደንት አላሚ | አፍሪቃ | DW | 04.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሶማሊያ ፕሬዝደንት አላሚ

ሶማሊያ ዉስጥ ትወለድ እንጂ በስደት አድጋ ተምራ ነዉ የራሷን ቤተሰብ ያፈራችዉ። አሁን የአራት ልጆች እናት የሆኑት ፋዱሞ ዳይብ በቅርቡ የሶማሊያ የመጀመሪያዋ የሴት ፕሬዝደንት የመሆን ህልም ሰንቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:07
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:07 ደቂቃ

ሶማሊያ

ምንም እንኳን እስከ 14 ዓመቷ ድረስ ማንበብ እና መጻፍን የመማር ዕድል ባታገኝም ዉላ አድራ ባደረገችዉ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም ጀምሮ በሄልሲንኪ ዩኒቨርሲቲ በሴቶች የመንግሥት አስተዳደር ተሳትፎ እና ከግጭት ማግስት ኅብረተሰብን የማንቃት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪያቸዉን የያዙት ዳይብ የሶማሊያን የፀጥታ ችግር እለዉጣለሁ ባይ ናቸዉ።።

በጎርጎሪዮሳዊዉ 1989ዓ,ም ሶማሊያ ዉስጥ በተባባሰዉ የእርስ በርስ ግጭት ጦርነት ከወላጆቻቸዉ ጋር ታስረዉ ከሀገር ተሰደዱ። የከባድ መኪና ሾፌር ከሆኑ አባት እና ከአርብቶ አደር እናቷ ጋር ኬንያ ዉስጥ የቆዩባቸዉን ጊዜያት ወደኋላ ያስታዉሱታል። የስደት ህይወት ኬንያ ዉስጥ ሳይደላቸዉ የፊንላንድ መንግሥት ጥገኝነት ሰጥቷቸዉ ወደሄልሲንኪ ተጓዙ። በትንሿ የፋዱሞ ዳይብ አዕምሮ ዉስጥ ግን በኬንያም ሆነ ፊንላንድ ማኅበረሰብ ያለመፈለግ ምሬት ተቀርፆ አድጓል። ቀደም ሲል በነርስነት ፊንላንድ ዉስጥ ሲያገለግሉ የቆዩት ዳይብ፤ በተመድ በመቀጠር ወደፑንትላንድ ተጉዛ በሴቶች እና እናቶች የጤና ዘርፍም ሠርተዋል።

Anschlag Mogadishu Somalien

የፍንዳታ ጥቃት በሶማሊያ

ሴራሊዮን እና ፊጂም በሙያቸዉ አገልግለዋል። በሌሎች ሃገራት ያስተዋሉት ሰላም እና ፀጥታ በትዉልድ ሀገራቸዉም ቢሆን የሚመኙት ፋዱሞ ዳይብ የሀገራቸዉ ፕሬዝደንት በመሆን ከሶማሊያ የመንግሥት ኃይል እና ከ22 ሺህ የአፍሪቃ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ጋር የሚፋለመዉን የፅንፈኛ ታጣቂ ቡድን አሸባብን ጥቃት ለማክተም አስበዋል። ለዚህ ያነሳሳቸዉን ሲገልፁ፤

«ለፕሬዝድንነት ለመወዳደር ያነሳሳኝ ሶማሊያ ዉስጥ ቀጣይ የደም መፋሰስን የማስቆም የሞራል እና የሲቪል ግዴታ አለብን ብዬ ስለማምን ነዉ። ከዳር ሆነን ከ25 ዓመታት በላይ ተመልክተነዋል። እናም ወደፊት መጥተን ይህን ኃላፊነት መዉሰዳችን ወሳኝ ነዉ። የበፊቱ አስተዳደርም ሆነ የአሁኑ አላሳኩልንም። ስለዚህ ጉዳዮችን በራሳችን እጅ ማስገባት ይኖርብናል።»

ዳይብ በምርጫዉ ለመፎካከር መዘጋጀታቸዉን በመጪዉ ሐምሌ ወር ለሶማሊያ ምክር ቤት ማቅረብ እና ማረጋገጫ ማግኘት ይኖርባቸዋል። በዚያም ላይ ወደ20ሺህ ዶላር ገደማ ማስያዣ ማስገባትም ይጠበቅባቸዋል። በሶማሊያ ማኅበረሰብ ይህ አልተለመደምና ምን ያህል ድጋፍ አገኛለሁ ብለዉ ያስቡ እንደሆነ ከዶቼ ቬለ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ ዳይብ እንዲህ ይላሉ።

«ይህ ዓለም አቀፍ ክስተት ነዉ። ሂራሪ ክሊንተንን አሜሪካን ዉስጥ ተመልከት። ሶማሊያዊ አይደሉም ነገር ግን ተመሳሳይ ሁኔታ ነዉ የገጠማቸዉ።ስለዚህ እኔም የሚያጋጥመኝ ሌሎች ሴቶችም ያጋጠማቸዉን ነዉ። ከዚህ ባሻገር ለአዲሱ ትዉልድ የግለሰቡ ማንነት ሳይሆን የሚያሳስበዉ ወደጠረጴዛዉ ላይ የሚያመጣዉ ምንድነዉ የሚለዉ ነዉ። በዚያም ላይ ከፆታቸዉ ይልቅ ችሎታና እና የአስተዳደር ብቃታቸዉን ነዉ የሚመለከተዉ።»

ፋዱሞ ዳይብ ይህን ይበሉ እንጂ ከወዲሁ ተከታታይ የግድያ ዛቻዎች ደርሰዋቸዋል። ግን ደግሞ አስፈራጊዎቻቸዉ ራሳቸዉ ፈርተዋል ነዉ የሚሉት።

Harvard University Fadumo Dayib

የሶማሊያ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዝደንት ለመሆን ያለሙት ዳይብ

«ይህ በጣም ግራ አጋቢ ነገር ነዉ። በዚያም ላይ እንዲህ ያለ ማስፈራሪ ለሚደርሳቸዉም ሆነ እኔን እንገልሻለን ብለዉ ለሚያስፈራሩኝ ሰዎች ትክክለኛዉን ነገር መሥራት እንዳለብኝም የሚያሳስብ ነዉ። እነዚህ ሰዎች በጣም ስጋት ገብቷቸዋል ማለት ነዉ፤ እኔን በማስፈራራትም ወደሀገሪቱ ላመጣ ያሰብኩት ነገር አስፈላጊ መሆኑን እያመኑም ነዉ። በእኔ ዉስጥ የአስተዳደር ችሎታ ተመልክተዋል፤ ራዕይ ያለዉ መሪ፤ ህዝቡን አገልጋይ መሪ አይተዋል ማለት ነዉ። እንዲህ ያለ ነገር ስላለመዱ አስፈራርቷቸዋል። ምክንያቱም እኔ ኃላፊነቱን ከያዝኩ ህልዊናቸዉ ስጋት ላይ እንደሚወድቅ ያዉቃሉ ማለት ነዉ።»

ስጋት ማስፈራራቱ ታልፎ ፋየዱሞ ዳይብ የሶማሊያ ፕሬዝደንት የመሆን ህልም እዉን ቢሆን ሁለት አስርት ዓመታትን የተሻገረዉን የሀገሪቱን ያልተረጋጋ የፀጥታ ይዞታ ለመለወጥ በሶማሊያ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል ያሉት የአራት ነጥብ አምስት የተሰኘ የስልጣን ክፍፍል አሠራር እንደሚለዉጡ አመልክተዋል።

«ይህ አሠራር ነዉ ሶማሊያ ዉስጥ አለመረጋጋትን የፈጠረዉ። ይህ ነዉ ሶማሊያ ዉስጥ በሺዎች ለሚቆጠሩት ሞት ምክንያት የሆነዉ። ይህ አሠራር ነዉ በሀገሪቱ ሽብር እንዲቀጥል ያደረገዉ። ስለዚህ እንዲህ ያለዉ አሰራር እንዲቀጥል ህጋዊ አላደርገዉም። ቀጣዩ ምርጫ የራሳቸዉን ጥቅም ብቻ የሚያስቡ ጥላቻን የተሞሉ የጎሳ መሪዎች የሚመረጡበት ከሆነ በጣም የተበላሸ ስርዓት ነዉ የሚሆነዉ። በዚህ በአራት ነጥብ አምስት አካሄድ የሚመረጥ ማንኛዉም ፕሬዝደንት ከፍተኛ ብቃት የሌለዉ እና ሙሰኛ ሰዉ ነዉ የሚሆነዉ። ያንንም እናዉቃለን።»

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic