የሶማሊያ ጦር ግሥጋሤና የአሸባብ እጣ | አፍሪቃ | DW | 08.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሶማሊያ ጦር ግሥጋሤና የአሸባብ እጣ

የሶማልያ ብሄራዊ ጦርና የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል ‘አሚሶም’ከአሸባብ አክራሪ ኃይል ጠንካራ ይዞታዎች መካከል አንዷ ነች የተባለችውን የባራዌ የወደብ ከተማ ከቀናት በፊት ነፃ አዉጥተዋል። ለበርካታ ዓመታት ከሶማልያ ማዕከላዊ መንግስት ቁጥጥር ውጪ ሆና የቆየችው የባራዌ ከተማ ለአሸባብ ዋንኛ የገቢ ምንጭም ነበረች።

የአሸባብ አክራሪ ኃይል ከባራዌ በፊት እ.ኤ.አ. በ2011 ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ፤ በ2012 ከኪስማዩና ባይዶዋ ለመልቀቅ መገደዱ አይዘነጋም።

ከ23 ዓመታት በኋላ በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ የምትገኘው የባራዌ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማልያ ብሄራዊ ጦር ቁጥጥር ሥር ገብታለች። ከሶማልያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በ200 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የምትገኘው ባራዌ እስከ ሰኞ ድረስ የአሸባብ ጠንካራ ይዞታና ዋንኛ የገቢ ምንጭ ሆና ቆይታለች። በአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ጦር አሚሶም ድጋፍ የሚደረግለት የሶማልያ ጦር ከተማዋን ሲቆጣጠር ከአሸባብ አክራሪ ታጣቂዎች ይህ ነው የሚባል መከላከል እንዳልገጠመው ተሰምቷል። ከአሸባብ ሽንፈትና ሽሽት በኋላ በባራዌ ከተማ መረረጋጋት መስፈኑን በሶማልያ የሚገኘው የዶይቼ ቬሌ ተባባሪ ዘጋቢ መሃመድ ኡመር ይናገራል።

«'የህንድ ውቅያኖስ ተልዕኮ ተብሎ በሚጠራው ዘመቻ አሸባብ በመንግስት ኃይሎችና የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ የባራዌ ከተማ ተረጋግታለች። የከተማዋ ነዋሪዎችም የመንግስትና የአፍሪካ ህብረትን ኃይሎች በመልካም ሁኔታ ተቀብለዋቸዋል። ምክንያቱም አሸባብ በነዋሪዎቹ ላይ ጥብቅ ሕጎችን ተግባራዊ አድርጎ ነበር። ሕግጋቱን የተላለፈ በአደባባይ በድንጋይ ተወግሮ ይገደላል። እናም ነዋሪዎቹ በዚህ መከራ ውስጥ በማለፋቸው የመንግስትና የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪዎችን መርጠዋል።»

የቡሩንዲና ዩጋንዳ ወታደሮችን ያቀፈው የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ እና የሶማልያ ብሄራዊ ጦር አሁን የባሬዌ ነዋሪዎችን ለማረጋጋት በጥረት ላይ ናቸው። አልሸባብ በከተማዋ የሚገኘውን ወደብ ወታደሮች፤ የጦር መሳሪያና ፈንጂዎች ለማስገባትና ለከሰል ንግድ ይጠቀምበት ነበር። እንደ መሃመድ ኡመር አባባል ከሆነ የባራዌ ሽንፈት ለአሸባብ የመጨረሻው መጀመሪያ ነው።

«ባራዌ የአሸባብ ብቸኛ ጠንካራ ይዞታ አልነበረችም። ቢሆንም ከከሰል ንግድና በአካባቢው ከሚካሄደው የንግድ እንቅስቃሴ ቀረጥ ከሌሎቹ ይዞታዎቹ የተሻለ ገቢ የሚያገኝበት ቦታ ነበር። አሁን ከባራዌ ሽንፈት በኋላ አሸባብ ምንም አይነት ገቢ የሚያገኝበት መንገድ አይኖርም። ተዋጊዎቹም ሸሽተዋል። የተወሰኑ ታጣቂዎች እጃቸውን ለመንግስት መስጠታቸውም እየተሰማ ነው። የመንግስት ወታደሮችና የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪዎች በመካከለኛው ጁባ ወደምትገኘው ጅሊብ እያመሩ ነው። ቀድሞ መካከለኛውና ደቡባዊ ሶማልያን ይቆጣጠር የነበረው አሸባብ ተዋጊዎች አሁን ከመሸሽ ወይም እጃቸውን ከመስጠት ውጪ ምርጫ የላቸውም።»

የሶማልያ ብሄራዊ ጦርና የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል በጋራ የሚያካሂዱት የህንድ ውቅያኖስ ተልዕኮ አሁንም ቀጥሏል። አሸባብን ከመውጋት ጎን ለጎን አለመተማመንና የጎሳ ፖለቲካ የተጫናትን ሶማልያ ማረጋጋት እና መንግስታዊ መዋቅሩን መዘርጋት የፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ መሃመድ መንግስት ቀጣይ የቤት ሥራ ነው። ለአሁን ግን የሶማልያ ጦርና የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ በጋራ አሸባብን ሙሉ በሙሉ እንደሚያሸንፉት እርግጠኛ ናቸው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic