የሶማሊያ ጥገኝነት ጠያቂዎችና በሲዊድን | የሶማልያ ውዝግብ | DW | 18.12.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የሶማልያ ውዝግብ

የሶማሊያ ጥገኝነት ጠያቂዎችና በሲዊድን

የተቃጠለ ቤት፤ የወደመ ንብረት፣ ጥሎ በዉጊያ መሐል ሾልኮ ከሐገሩ ወይም ከከተማዉ የወጣ ሰዉ፤ ብዙ ኪሎ ሜትር በእግር፣ በባሕር አቋርጦ ሕይወቱን ያተረፈ ሰዉ መረጃዉን ከየት ያገኘዋል ነዉ

የመቅዲሾ አዉራ መንገድ

የመቅዲሾ አዉራ መንገድ

የሲዊድን መንግሥት ከሶማሊያ ርዕሠ-ከተማ መቅዲሾ ሸሽተዉ ሲዊድን ለገቡ የሶማሊያ ዜጎች ፈጣን የጥገኝነት መብት እንደማይሰጥ አስታወቀ።የሲዊድን የስደተኞች ጉዳይ ቦርድ እንደሚለዉ በሐገሪቱ ሕግ መሠረት የመቅዲሾዉ ግጭት የነፍጥ ዉጊያ አይደለም።በዚሕም መሰረት ከሶማሊያዋ ርዕሠ-ከተማ ሽሽተዉ ሲዊድን የገቡ የከተማይቱ ነዋሪዎች ጥገኝነት የማግኘት መብት የላቸዉም።ነጋሽ መሐመድ የቦርዱን ቃል አቀባይ ዮሐን ሮዉን በስልክ አነጋግሮ የሚከተለዉን ዘገባ አጠናቅሯል።

ቃል-አቀባይ ሮዉ እንደሚሉት ነገሩ የብያኔ ጥምዝምዝ፤ የቃላት ሥንጠቃ፣ አለያም የአይ-አዎ ግጭት ይመስላል።ሰዉ ሳይሞት፤ ሳይቆስል ጀምበር የማይጠልቅ፣ የማይወጣባት መቅዶሾ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የሲዊድን ሹማምንት ማወቃቸዉን ቃል አቀባዩ አልሸሸጉም።


«ሁኔታዉ በጣም አስቸጋሪ ነዉ።የመቅዲሾ ሁኔታ መጥፎ ሥለመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ሌሎች ሁኔታዉን የሚከታተሉ አለም አቀፍ ታዛቢዎች ከሚሉት ጋር እንስማማለን።ይሁንና እኛ ቦርዳችን የሚሠራዉ የሲዊድን ፓርላማ ባፀደቀዉ የሲዉድን ሕግ መሠረት ነዉ።»

የሲዊድን ቦርድ ከሲዊድን ሕግ ዉጪ ሊሰራ በርግጥ አይችልም።ሕጉ በተለይ ሥለ ጥገኝነት ጠያቂዎች አለም አቀፍ ዉሎችንና ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑን አያጠያይቅም።ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማስተናገድ፣ ወይም ድሆችን በያሉበት በመርዳት ከብዙዎቹ የበለፀጉ ሐገራት የተሻለ ጥሩ ስም ያላት ሰሜን አዉሮጳዊቷ ሐገር ጦርነት ከሚካሔድበት አካባቢ ለሚሰደዱ ችግረኞች ያለ ብዙ ዉጣ ዉረድ ከለላላ የሚያሰጥ ሕግም አላት።ሕጉ ለግጭት የሚሰጠዉ ብያኔ ግን ግራ አጋቢ ነዉ።ሮዉ


«የሐገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያወጣዉ ሕግ በሚያዘዉ መሠረት፣ ባንድ አካባቢ የሚደረግ ግጭት የነፍጥ ዉጊያ መሆኑን ለማረጋገጥ የተወሰኑ መመዘኛዎች መሟላት አለባቸዉ።ከነዚሕ መመዘኛዎች አንዱ ከመንግሥት ወይም ከመንግሥት ተባባሪዎች ጋር የሚዋጋዉ ሐይል የተወሰኑ አካባቢዎችን ለተወሰነ ጊዜ መቆጣጠር አለበት።በሞቃዲሾ ሁኔታ ግን እዚያ ያሉት ሐይላት (ደፈጣ ተዋጊዎቹ) የሚቆጣጠሩት ሥፍራ የለም።»

ዛሬ ቀትር ላይ ብቻ፣ ሰሜን መቅዲሾ ብቻ በተደረገ ግጭት ስድስት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። በሲዊድን መፅሐፈ-ሕግ መሥረት ግን መቅዲሾ ዉስጥ የነፈጥ ግጭት የለም።ግጭት ከሌለ ደግሞ የመቅድሾዉ ነዋሪ እድል፣ ገንዘብ፤ ደጋፊ ዘመድ ኖሮት ሲዊድን ቢገባ ግጭት ከሚካሔድበት አካባባቢ እንደተሰደደ ሰዉ ጥገኝነት ማግኘት አይችልም።አይባረርምም።ይሕ ነዉ ተቃርኖዉ።ጥገኝነት ሊያገኝም ይችላል።ይሕ ነዉ-ግራዉ ግን እንዴት።ግጭቱ ወይም የፀጥታዉ መታወክ ጥገኝነት ጠያቂዉን በግሉ ለመጉዳቱ ወይም ይጎዳል ብሎ ለማስጋቱ አመልካቹ መረጃ ካቀረበ።-ይላሉ ቃል አቀባይ ሮዉ.-

«ጥገኝነት የሚጠይቁት እያንዳዳቸዉ አመልካቾች የፀጥታዉ መታወክ በግል ያደረሰባቸዉ ወይም ያደርስባቸዋል ተብሎ የሚገመተዉ አደጋ ሥለመኖሩ መረጃዎቻቸዉን እያቀረቡ ጥገኝነቱ ይፈቀድላቸዉ ይሆናል።»

የተቃጠለ ቤት፤ የወደመ ንብረት፣ ጥሎ በዉጊያ መሐል ሾልኮ ከሐገሩ ወይም ከከተማዉ የወጣ ሰዉ፤ ብዙ ኪሎ ሜትር በእግር፣ በባሕር አቋርጦ ሕይወቱን ያተረፈ ሰዉ መረጃዉን ከየት ያገኘዋል ነዉ ጥያቄዉ።ባገባደድነዉ የአዉሮጳዉያን ሁለት ሺሕ ሰባት ሰወስት ሺሕ የሶማሊያ ዜጎች ስዊድን ገብተዉ ጥገኝነት ጠይቀዋል።እስካሁን የተፈቀዳላቸዉ ቃል አቀባዩ እንዳሉት አንድ ሺሕ ሰወት መቶ ቢሆኑ ነዉ።