የሶማሊያ የውጭ ምንዛሬ ቀውስ | አፍሪቃ | DW | 21.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሶማሊያ የውጭ ምንዛሬ ቀውስ

ከ 20 ዓመታት በላይ በሶማሊያ የተረጋጋ መንግሥት አይስተዋልም። ስለሆነም በሀገሪቱ ይፋና መደበኛ የሆነ የባንክ አሰራር ስርዓት የለም። ለአመታት በዘለቀው የርስ በዕርስ ጦርነት ምክንያት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ከሀገራቸው ተሰደዋል።

በውጭው ሀገር ራሳቸውን የቻሉ ሶማሊያውያንም ሰላም ባልሰፈነባት ሀገር ለሚኖሩ ዘመድ አዝማዳቸው የውጭ ምንዛሬ በየጊዜው ይልካሉ፤ ይህም ሁሌ በይፋ በሚታወቅ መንገድ አልነበረም። በዚህ ከውጭ በሚላክ ምንዛሬ 40 ከመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ እንደሚተዳደር ይታመናል። አብዛኛው ገንዘብ የሚላከው ከዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ ሲሆን አሁን ግን በሁለቱም ሀገራት የሚገኙ ባንኮች ምንም አይነት የገንዘብ ዝውውር እንዳይፈፅሙ ታግደዋል። የእገዳው ምክንያት እንደ አሸባብ ያሉ የአሸባሪ ቡድናት ከውጭ በቀላሉ ገንዘብ እንዳያገኙ ፤ ለማደናቀፍ ነው። የዶይቸ ቬለዋ ቤቲና ሩህል በስፍራው ሆና እንደታዘበችው ከሆነ ከውጭ ገንዘብ እየተላከላቸው ይተዳደሩ የነበሩ ቤተሰቦች አሁን ከፍተኛ ቀውስ ላይ ወድቀዋል።

አሻ ጌሌ ፋራህ ሞቃዲሾ ውስጥ ግድግዳው በፈራረሰ እና በአንድ ባረጀ ቤት ውስጥ ይኖራሉ። ፋራህ በሁለት ክፍል ቤት ውስጥ 10 የቤተሰብ አባላት አላቸው። ሌሎቹን ክፍሎች ሌላ ቤተሰብ ተከራይቶ ይኖራል። ምንም እንኳን ብዙ ቁጥር ያለው ቤተሰብ በሁለት ክፍል ቤት ቢኖርም፣ ከሌሎች ሞቃድሾ ከሚኖሩ ሶማሊያውያን ጋር ሲነፃጸር አሻ ፋራህ የተሻለ ኑሮ ይኖራሉ።

Geldbeutel mit Geldscheinen

በውጭው ዓለም የሚገኙ ሶማሊያውያን በየጊዜው የውጭ ምንዛሪ ለቤተሰቦቻቸው ወደ ሶማሊያ ይልካሉ

« ወንድሜ አሜሪካ ነው የሚኖረው። በየወሩ 300 ዶላር ይልክልን ነበር። ገንዘቡ ለትምህርት ቤት ክፍያ፤ ለቤት ኪራይ ፣ ለመድሀኒት እና ለምግብ ፤ ብቻ ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ ለመግዛት ይበቃል። ነገር ግን ካለፉት 2 ወራት አንስቶ ወንድሜ ገንዘብ ልኮልን አያውቅም፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ የቤት ኪራያችንን መክፈል አልቻልንም። ልጆቹም ትምህርት ቤት መሄድ አቁመዋል። የትምህርት ቤቱ ዳሬክተር፤ ያለ ክፍያ ትምህርት የለም ብሎን ልጆቹ ከዚያን ጊዜ አንስቶ እቤት ተቀምጠዋል።»

የአሻ ፋራህ ወንድም ገንዘብ የማይልከው ፤ ማንኛውም ባንክ ገንዘቡን ለመላክ ፍቃደኛ ባለመሆኑ ነው። ምክንያቱ ትንሽ ውስብስብ እና ከዩናይትድ ስቴትስ ጥብቅ መመሪያ ጋር የተያያዘ ነው። ህጉ ከዩናይትድ ስቴትስ በግል ወደ ሶማሊያ የሚዘዋወሩ ገንዘቦችን በመከልከል በሶማሊያ የሚገኙ አማፂያን ገንዘብ እንዳያገኙ ለማገድ የታለመ ነው። በዚህ እገዳ ከአልቃይዳ ቡድን ጋር ጥምረት ያለው የአሸባብ ቡድን የገንዘብ ችግር ቢገጥመው ለዩናይትድ ስቴትስ ትልቅ ስኬት ነው። ምንም እንኳን በሶማሊያ ይፋና መደበኛ የሆነ የባንክ አሰራር ስርዓት ባይኖርም፤ በአንዳንድ የገንዘብ መላኪያ ተቋማት የሚላኩ የውጭ ምንዛሬዎች ያለምንም ችግር ይደርሳሉ። በነዚህ ይፋ ባልሆኑ ተቋማት የሚላኩ ምንዛሬዎችን መጠን ለመቆጣጠር ግን ቀላል አይደለም። በዚህም የተነሳ ሁሉም በዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ የሚገኙ ባንኮን ወደ ሶማሊያ የገንዘብ ዝውውር አቁመዋል።

« ከወንድሜ ጋር በስልክ ስናወራ እና በየዕለቱ ስለሚገጥመን ችግር ስነግረው ፤ ስልክ ላይ ያለቅሳል። ምንም ላደርግ አልቻልሁም ይለኛል። ስራ እንዳለው እና ለኛም የሚሆን በቂ ገንዘብ እንዳለው አውቃለሁ። ምን ያደርጋል ዶላሩን ሊልክልን አልቻለም። ተስፋ የምናደርገው የአሜሪካ ባንኮች ወደ ሶማሊያ ገንዘብ የሚላክበትን መንገድ መልሰው እንዲፈቅዱ እና ፤ ልጆቻችንን መልሰን ትምህርት ቤት እንድንልክ ነው።

Somalia Sicherheitskräfte in Mogadischu

ሰላም አስከባሪዎች ፤ በሞቃድሾ

የፋራህ ወንድም ሁለት ልጆቹን እህቱ ጋር ትቶ ነው በአሜሪካ የሚኖረው። ኑሮው ከአሜሪካ ጋር ሲነፃፀር ልጅ ማሳደጉ በሞቃድሾ ይረክሳል። ከአሜሪካ ለሁለቱ ልጆች በሚልከው ገንዘብ ሞቃድሾ ውስጥ መላው ቤተሰቡን ያስተዳድራል። ነገር ግን ይህ አህጉር የተሻገረ የስራ ክፍፍል ከአሁን በኋላ አይሰራም።

የባንክ ተወካይ የሆኑት አዴን ሀሳን በሁኔታው አዝነዋል። ሀሳን « ካህ ኤክስፕረስ » በተባለ የገንዘብ ተቋም ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ ያገለግላሉ። እጅግ ጥብቅ የሆነው የአለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር በጣም ውስብስብ ስለሆነ ተቋማቸው ጭራሽ ወንጀለኛ እንዳይባል ሰግተዋል። ማንኛውም ተቋም ጥፋተኛ መባልን አይፈልግም።

«ሰዎች ሲቸግራቸው ሌላ መላ መፈለጋቸው አይቀርም። ችግር ላይ ከሆኑ ደግሞ ህገ ወጥ የሆነ መንገድም ይጠቀሙ ይሆናል። ይህ ለሁለቱም ፦ ለባንኩም ይሆን ለተጠቃሚው መጥፎ ነው።»

እስካሁን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሶማላዊያን በየአመቱ አንድ ቢሊዮን የሚደርስ ዶላር ወደ ሀገራቸው እንደላኩ ይታመናል። ይህ ደግሞ ለልማት እና ለአደጋ ጊዜ ተብሎ ከሚቀርበው ርዳታ የበለጠ ነው። የውጭ ምንዛሬ ወደ ሶማሊያ እንዳይላክ ከተከለከለ ጊዜ አንስቶ ግን በርካታ ቤተሰቦች አስከፊ ችግር ውስጥ ይገኛሉ።

ቤቲና ሩህል

ልደት አበበ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic