የሶማሊያ የእርቀ-ሠላም ጉባኤና ተቃዋሚዎቹ | የሶማልያ ውዝግብ | DW | 13.07.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የሶማልያ ውዝግብ

የሶማሊያ የእርቀ-ሠላም ጉባኤና ተቃዋሚዎቹ

«የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያ የሰፈረዉ አለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደዉ መሠረት አይደለም።ታሕሳስ ሁለት ሺሕ ስድስት የፀጥታዉ ምክር ቤት ያሳለፈዉ ዉሳኔ ነበር።ዉሳኔዉ ከኢጋድ አባል ሐገራት የተዉጣጣ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት እንዲሠፍር የሚጠይቅ ነበር።

መቅዲሾ ዛሬም ታሰጋለች

መቅዲሾ ዛሬም ታሰጋለች

በመጪዉ እሁድ ሊደረግ የታቀደዉ የሶማሊያ የእርቀ ሠላም ጉባኤ ከጎሳ ጉባኤ ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረዉ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ተቃዋሚዎች አስታወቁ።አስመራ የሚገኙት ተቃዋሚ ሐይላት እንደሚሉት ጉባኤዉ የሶማሊያን ችግር ለመፍታት የሚጠቅመዉ የለም።በዚሕ ምክንያት በጉባኤዉ ላይ አይገኙም።ከተቃዋሚዎቹ መካካል የቀድሞዉን የሶማሊያ አምባሳደርና የምክር ቤት አባል የሱፍ ሐሰን ኢብራሒምን የአስመራዉ ወኪላችን ጎይቶም ቢሆን አነጋግሯቸዋል።ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

በቅርቡ የሶማሊያ ፖለቲካ ተፅዕኖ ማሳረፍ ይችላሉ ከሚባሉት ፖለቲከኞች የሽግግር መንግሥቱ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት ሑሴን ፋራሕ አይዲድ፣ የሽግግር ምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ሐሰን ሼሕ አደን፤ የቀድሞዉ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ሕብረት መሪ ሼሕ ሸሪፍ ሼሕ አሕመድና ሌሎች በጉባኤዉ እንደማይካፈሉ ካንዴ በላይ አስታዉቀዋል።

ከነዚሑ ሰዎች ጋር አስመራ የሚገኙት የቀድሞዉ የምክር ቤት አባል እና አምባሳደር የሱፍ ሐሰን ኢብራሒም ትናንት ደገሙት።

«በጭራሽ አይሳተፉም።እነዚሕ የጠቀስካቸዉ ግለሰቦች እና ሌሎችም በርካቶች በጉባኤዉ ላይ አይሳተፉም።»
ምክንያት፣-የሱፍ ሐሰን ኢብራሒም ቀላል ይሉታል።

«ይሕ ጉባኤ የሶማሊያ ጉዳይ የሚመለከታቸዉ ወገኖችን በሙሉ ይሁንታ ያገኘ አይደለም።ሥለዚሕ ጉባኤዉ የጎሳ ጉባኤ እንዲሆን ታቅዶ መቅዲሾ በሚገኘዉ መንግሥት የተጠራ ነዉ።የዛሬዉ የሶማሊያ ግጭት ደግሞ የጎሳ ጉዳይ አይደለም።የፖለቲካ ጉዳዮች እንጂ።ሥለዚሕ ከመቅዲሾ ዉጪ የሚገኙ የመንግሥትም ሆነ የምክር ቤት አባላት በዚሕ ጉባኤ ላይ አይሳተፉም።»

በሶማሊያ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የሚበጀዉ የሱፍ ሐሰን ኢብራሒም እንደሚያምኑት ሁሉም ወገኖች የሚሳተፉበት፤ ከገለልተኛ ሐገር የሚካሔድ፣ በመጨረሻ ዉጤቱም ሁሉን አቀፍ መንግሥት የሚያዋቅር ጉባኤ ቢደረግ ነበር።

«የመቅዲሾ መንግሥትና ከመቅዲሾ ዉጪ የሚገኙት ተቃዋሚዎች እየተጣሉ ነዉ።ሥለዚሕ ይሕንን ጠብ ወይም ዉዝግብ ለመፍታት ጉባኤዉ ሁሉም ወገኖች የሚሳተፉበት መሆን አለበት።መንግሥትና ተቃዋሚዎቹ በሰላማዊ መንፈስ፤ በገለልተኛ ሥፍራ፣ የሶማሊያን ተጨባጭ ችግሮች አንስተዉ የሚነጋገሩበት ጉባኤ መሆን አለበት።»


በየሱፍ ሐሰን አገላለፅ የመቅዲሾን መንግሥት የሚቃወሙት ሐይላት የሽግግር መንግሥቱን የምትረዳዉን ኢትዮጵያንም አጥብቀዉ ይቃወማሉ።ኤርትራ የመኖር፣ አስመራ ዉስጥ ሌላ ጉባኤ የመጥራታቸዉም ምክንያት፣ «የጠላትሕ ጠላት---» ተብሎ በሚጠራዉ ነባር ብሒል የሚገለፀዉ አይነት ነባር የፖለቲካ ፈሊጥ መሆኑ አላነጋገረም።

የኢትዮጵያ ጦር ሰማሊያ መሥፈሩ ኢትዮጵያን የመቃወማቸዉ ዋናዉ ምክንያት ነዉ።የቀድሞዉ ዲፕሎማት እንደሚሉት ተቃዉሟቸዉ የአለም አቀፍ ሕግ ድጋፍም አለዉ።

«የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያ የሰፈረዉ አለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደዉ መሠረት አይደለም።ታሕሳስ ሁለት ሺሕ ስድስት የፀጥታዉ ምክር ቤት ያሳለፈዉ ዉሳኔ ነበር።ዉሳኔዉ ከኢጋድ አባል ሐገራት የተዉጣጣ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት እንዲሠፍር የሚጠይቅ ነበር።ይሑንና ዉሳኔዉ ባካባቢዉ ያለዉን ሁኔታ በማገናዘብ ከኢጋድ አባል ሐገራት መካካል ከሶማሊያ ጋር የሚዋሰኑት ሐገራት ወታደር እንዳያዘምቱ ይከለክላል።ኢትዮጵያ ደግሞ የሶማሊያ ድንበርተኛ በመሆንዋ ወታደሮችዋን ወደ ሶማሊያ ማዝመት አልነበረባትም።

ዩሱፍ ሀሰን ኢብራሂም ሌላም ምክንያት አክለዉ የኢትጵያ ጦር ሶማሊያ የሠፈረዉ በሽግግር መንግሥቱ ፕሬዝዳትና ጠቅላይ ሚንስትር ፍቃድ ብቻ በመሆኑ ባስቸኳይ መዉጣት አለበት ይላሉ።