የሶማሊያ የሠላም ዉልና ትርጓሜዉ | ኢትዮጵያ | DW | 17.03.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የሶማሊያ የሠላም ዉልና ትርጓሜዉ

አሕሉ ሱና ወል ጀመዓ ባጭር ጊዜ የተጠናቀረዉ፥ አል-ሸባብን የመሰለ ጠንካራ ተዋጊ ሐይልን መጋፈጥ፥ አንዳድ ሥፍራዎች ማሸነፍ የቻለዉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ዙሪያ መለስ ድጋፍ ስለሚያገኝ ነዉ ተብሎ ይወቀሳል

default

የሶማሊያ የሽግግር መንግሥትና አሕሉ ሱና ወል ጀማዓ የተሰኘዉ ለዘብተኛ እስላማዊ ቡድን ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ዉስጥ የተፈራረሙት የሰላም ዉል ለሐገሪቱ ሠላም የሚኖረዉ ፋይዳ እያጠያየቀ ነዉ።ሥምምነቱን አንዳድ ወገኖች ወደፊት ለሚደረጉ ሌሎች ድርድሮች በር ከፋች ሲሉት ሌሎች ደግሞ በቅርቡ የተጠናከረዉን አሕሉ ሱና ወል ጀመዓን ከማዳከም ባለፍ የሚጠቅመዉ የለም ይላሉ።በሶማሊያ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ወኪልና የዶቸ ቬለ ተባባሪ ዘጋቢ ሙስጠፋ ሐጂ አብዲኑር እንደሚለዉ ደግሞ አብዛኛዉ የሐገሪቱ ሕዝብ ሥምምነቱን በጥርጣሬ ነዉ የሚመለከተዉ።ነጋሽ መሐመድ ሙስጠፋ ሐጂን በስልክ አነጋግሮት ነበር።

«አሁን በጣም ተፅዕኖ ማድረግ የሚችል ቡድን ነዉ።በጦርነት ወይም ጠመንጃ ይዞ በመዋጋት አይታወቅም ነበር።አሁን ግን በጣም ተደማጭነት ያለዉ ቡድን ነዉ።የሽግግር መንግሥቱ በዚሕ ወቅት የዚሕ ቡድንን ድጋፍ ማግኘቱ በጣም ይጠቅመዋል።»

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሐይማኖታዊ ጉዳዮችን ሲያከናዉን እንጂ በሶማሊያ ፖለቲካ ጨርሶ አይታወቅም።በሐገሪቱ ከሚንቀሳቀሱት ሐይማኖታዊ ቡድኖች ሁሉ በጣም ለዘብተኛ የሚባልም ነዉ።የአለም አቀፉ አሸባሪ ድርጅት የአል-ቃኢዳ ተባባሪ የሚባለዉ አል-ሽባብ እየተጠናከረ፥ አብዛኛዉን የሶማሊያ ግዛት መቆጣጠር ሲጀምር ግን ያ-ለሐይማኖታዊ ተልዕኮ የተሰባሰበዉ ቡድን ተዋጊ ሐይል ሆነ።አሕሉ ሱና ወልጀመዓ።

አል ሸባብን በጠመንጃ ሐይል የተቋቋመ፥ በአንዳዳድ አካባቢ በተለይም በማዕከላዊ ሶማሊያ ግዛት የአልሸባብ ሐይላትን እየመታ የተለያዩ ከተሞችን መቆጣጠር የቻለ ብቻዉ ቡድንም ለመሆን በቃ።ከሽግግር መንግሥቱ ጋር ወትሮም ቢሆን ይተባበር ነበር።ከትናንት በስቲያ ደግሞ በይፋ የሰላም ዉል ተፈራረመ።
ዉሉን የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚንስትር ኡመር አብዲረሺድ ዓሊ ሸርማርኬ ለሰላም «ታላቅ ድል፥ ለሰላም አደፍራሾች ደግሞ ከፍተኛ ዉድቀት» ብለዉታል።እዉነት እንዲያ ይሆን? ጋዜጠኛ ሙስጠፋ አብዲኑር አይ-አዎ ነዉ መልሱ።

«በርግጥ እንደዚያ ማለት ትችላለሕ።በሌላ በኩል ግን ሥምምነቱ ባለፉት ሃያ አመታት በግጭት በምትተረማመሰዉ በዚች ሐገር ዘላቂ ሠላም የሚያስገኝ ነዉ ማለት አይችልም።ሥምምነቱ ለተጨማሪ ድርድርና ለሰላም ሥምምነት በጣም ጠቃሚ፥ አንድ እርምጃና ጥሩ ነዉ።»

አሕሉ ሱና ወል ጀመዓ ባጭር ጊዜ የተጠናቀረዉ፥ አል-ሸባብን የመሰለ ጠንካራ ተዋጊ ሐይልን መጋፈጥ፥ አንዳድ ሥፍራዎች ማሸነፍ የቻለዉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ዙሪያ መለስ ድጋፍ ስለሚያገኝ ነዉ ተብሎ ይወቀሳል።ወቀሳዉን ቡድኑም ኢትዮጵያም አይቀበሉትም።ሙስጣፋም ተጨባጭ መረጃ አለያሁም ይላል ግን ደግሞ ወቀሳዉ መሠረት የለዉም ማለትም አይቻልም።

«ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸዉ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ መረጃ ግን የለንም። በሌላ በኩል ግን እንዲሕ አይነት ግንኙነት የላቸዉም ማለትም አይቻልም።ምክንያቱም የሚዋጉት በጣም ጠንካራ ከሆነ ቡድን ጋር ነዉ።ከአል-ሸባብ።ሥለዚሕ ሥለዚሕ ወታደራዊዉን ድጋፍ ማግኘት ከሚችሉበት ቦታ ሁሉ ማግኘቱን አይጠሉትም።»

አዲስ አበባ ዉስጥ ከትናንት በስቲያ የተፈረመዉን የሠላም ዉል የአፍሪቃ ሕብረት፥ የአዉሮጳ ሕብረት ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶችና ሐገራት ደግፈዉታል።ከአሕሉ ሱና ወል ጀመዓ መሪዎች ቢያንስ ሁለቱ ግን ሥምምነቱን አልተቀበሉትም።አብዛኛዉ የሶማሊያ ሕዝብም የስምምነቱን ዉጤት በርጋታ ማየቱን የመረጠ ነዉ-የሚመስለዉ።

«ብዙዎቹ ይሕ ስምምነት የአሕሉ ሱና ወጀመዓ ቡድንን ያዳክመዋል ብለዉ ነዉ የሚያስቡት።አንዳዶች እንዲያዉም ቡድኑን ለማፈራረስ ያለመ ነዉ ይላሉ።ምክንያቱም ቡድኑ ባለፉት ጥቂት ወራት እየተጠናከረ፥ ማዕከላዊ ሶማሊያን እየተቆጣጠረ ነዉ።ሥለዚሕ መንግሥት ሥምምነቱን ያደረገዉ ቡድኑ አል-ሸባብን ከማዕከላዊ ሶማሊያ ሙሉ በሙሉ ካስወጣ በሕዋላ ይበልጥ ተጠናክሮ ለመንግሥት ሌላ ጠላት እንዳይሆንበት በማሰብ ነዉ የሚሉም አሉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic