የሶማሊያ ዉጊያ፤ ኢትዮጵያና ወታደሮቿ | የሶማልያ ውዝግብ | DW | 02.04.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የሶማልያ ውዝግብ

የሶማሊያ ዉጊያ፤ ኢትዮጵያና ወታደሮቿ

የምስራቅ አፍሪቃዊቷ አገር የሶማሊያ ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየተባባሰ መሄድ ከጀመረ 5ኛ ቀኑን ይዟል።

የጋየዉ የኢትዮጵያ መኪና በሶማሊያ

የጋየዉ የኢትዮጵያ መኪና በሶማሊያ

በእርግጥ ዛሬ በከባድ መሳሪያዎች ተኩስ ስትናወጥ በከረመችዉ የመቃዲሾ ከተማ ዛሬ ሁኔታዎች ጋብ ማለታቸዉ ተነግሯል። ዛሬ ጠዋት በመዲናይቱ ከተሰማዉ ከባድ ፍንዳታና የመሳሪያ ተኩስ ባሻገር መቃዲሾ አንፃራዊ እርጭታ ተስተዉሎባታል። ካለፈዉ ሐሙስ ማለዳ ጀምሮ ከተማዋን ሲያናዉጥ አራት ቀናት የሰነበተዉ በሽግግር መንግስቱና በደጋፊዉ የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮችና በሸማቂዎቹ አማፅያን መካከል የተካሄደዉ ዉጉያ ያደረሰዉ ጉዳት ጠንከር ያለ እንደነበርም ተጠቅሷል። ኗሪዎቹ እንደሚሉት በመንግስት ወገን ወታደሮች ዉጊያዉ ከተከፈተ ጀምሮ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በመቶዎች ይቆጠራል። አንድ ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጎሳ ሚሊሺያ ለሮይተርስ ዘጋቢ እንደነገሩት ካለፈዉ ሐሙስ ወዲህ ትናንት ሌሊት ነዉ እንቅልፍ የተኙት። ይህችን ፋታም በርካቶች በየስፍራዉ የተዉትን ንብረት መሰብሰቢያ ወጣ ብሎም በጎዳና ለመተያየት ነዉ የተጠቀሙባት እንደ ሚሊሺያዉ ገለፃ። ከተማዋን በስፋት የተቆጣጠሯት የሃዉያ ጎሳ መሪዎች እንደሚሉት ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በእኛ በኩል ዉጉያ አቁመናል፤ እነሱም ከትናንት ማታ ጀምረዉ ይህን አክብረዋል ሲሉም አንዱ የዚሁ ጎሳ መሪ ለዘጋቢዎች ተናግረዋል።

እንዲህ እየበረደ የሚግለዉ የሶማሊያ የፈረሰ የፀጥታ ሁኔታ ምን መፍትሄ ተበጅቶለት እንደሆን ባይታወቅም የሽግግር መንግስቱ የፊታችን ሚያዝያ ስምንት ቀን ብሄራዊ የሰላም ጉባኤ የማካሄድ ዕቅድ እንዳለዉ ይታወቃል። እዚህ ጀርመን ላይብዚሽ ከተማ የሚገኘዉ የማክስ ፕላክ ተቋም የሶማሊያ ጎሳዎች ተንታኝ ዩታ ባኮኒ ሁሉንም ጎሳዎች በአግባቡ ለማካተት ግዜ ያስፈልጋል። ባፋጣኝ ይካሄድ ቢባል ዉጤቱ አይታየኝም ባይ ናቸዉ፣

«በሶማሊያ ሰላምና የሰላም ቀንን ለማምጣት ብዙ ጊዜ ይፈጃል። ምክንያቱም በርካታ ጎሳዎች ናቸዉ ያሉት። ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ሁሉንም ጎሳዎች ያካተተ የሰላም ጉባኤ ለማካሄድ ከተፈለገ እንዲህ በአጭር ጊዜ የሚቻል አይመስለኝም። ሌላዉ ቀርቶ ከሰሜን ሶማሊያ ወደደቡብ ለመምጣት ቀላል አይደለም። የረባ መሰረታዊ ልማት የለም። በየቦታዉ ደግሞ ወታደሮች ፍተሻ ያካሂዳሉ። ይህን ይህን ስናስብ ሁኔታዉ ዘበት ነዉ።»
እንደዉም ይላሉ ተንታኟ ፕሬዝደንት አብዱላሂ ዩሱፍ የሰላም ጉባኤዉን እንዲገፉበት በገንዘብም ሆነ በአስፈላጊዉ ድጋፍ ከጎን መቆምና ግፊት ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን የእሳቸዉ መንግስት ወይም ራሳቸዉ ዩሱፍ ሌሎች ጎሳዎች በስፋት መካከተት አለባቸዉ የሚል አቋም ቢይዝ ህልዉናዉ አስተማማኝ የመሆኑ ነገር ጥያቄ ላይ ይወድቃል።
እንደባኮኒ ገለፃ ከሆነ የሽግግር መንግስቱ ከዚህ በፊት ሲመሰረትም የተፈፀመ ግድፈት አለ። ከሁለት ዓመታት ተከታታይ ንግግርና ጥረት በኋላ ናይሮቢ ላይ የተመሰረተዉ የአሁኑ የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ወደአገሩ ሲመለስ ለሁለት ተከፍሎ ነበር። ያኔ ግን ይላሉ ተንታኟ ከመለያየት ይልቅ አንድነት እንዲፈጥሩ እንደማድረግ ዓለም ዓቀፉ ወገን ተገንጥሎ ለቀረዉ ቡድን እዉቅናና ድጋፉን ሰጠ። ያም ያስከተለዉ ዉጤት አሁን እየታየ ባለበት በዚህ ችግር ወቅትም ሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲኖራት የራሳቸዉን ወታደሮች ቁጥር ማብዛትና ማሰልጠን ብቻ ሳይሆን ለሰላም ጉባኤዉ ጊዜ ያስፈልጋል፣

«አስተማማኝ መሰረት ለመጣል ተጨማሪ ሰራዊት ማሰልጠን ያስፈልጋል። የሽግግር መንግስቱ ከኬንያ ወደአገር ቤት የገባዉ በ2005ዓ.ም ነዉ አገር ዉስጥ የከተመዉ ደግሞ ባለፈዉ ዓመት ነዉ። ወዲያዉ ግን በመካከሉ መከፋፈል ተፈጥሯል። ይሄ ክፍፍል ደግሞ የታሰበዉ እንዳይደረግ እንቅፋት ፈጥሯል። ያኔ ነበር ሰራዊት ከማቋቋማችሁ በፊት መከፋፈላችሁን ማስወገድ አለባችሁ ተብሎ ግፊት መደረግ የነበረበት። በተቃራኒዉ የሽግግር መንግስቱ ሲደገፍ ነዉ የነበረዉ ያ ትክክል አልነበረም።»

በሌላ ወገን ሲታይ ሽብርተኛ የሚባሉት እስላማዊ ሚሊሺያዎቹ ከደቡብ ሶማሊያ ቁልፍ ቁልፍ ስፍራዎች በኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች የጦር ኃይል እርዳታ ሲበታተኑ መቃዲሾ አሁን ትረጋጋለች ተብሎ ነበር። እዉነታዉ ግን ዛሬ የሚታየዉን ቀጣይ ዉጊያ፤ የበርካቶችን ህይወት ማጥፋትና ብዙዎችን ከመኖሪያ ቀያቸዉ ማፈናቀሉን ቀጥሏል። ዉጊያዉ በመቃዲሾ እንዳዲስ ያለፈዉ ሐሙስ ሲያገረሽ ኢትዮጵያ ሶማሊያ ምድር ከሚገኘዉ ሁለት ሶስተኛዉን ወታደራዊ ኃይሏን ማስወጣቷን አስታወቀች። ዛሬ ደግሞ የዜና አዉታሮች በይፋ እንደሚሉት ተጨማሪ ጦር ወደስፍራዉ ዳግም ልካለች። ዩታ ባኮኒ ድርጊቱ ችግሩን ከማባባስ በቀር መፍትሄ አይሆንም ነዉ ያሉት፤

«ሶማሌዎች በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ይበልጥ መነሳሳታቸዉ የማይቀር ነዉ። እዚህ ላይ ተጨማሪ ጦር መላኩ ሰላም ለማምጣትና አገሪቱን ለማረጋጋት ሳይሆን በኢትዮጵያና በሶማሊያ ህዝቦችመካከል ጠላትነትን ለመትከል ነዉ ማለት እችላለሁ። በሌላ በኩል ይኼ የሽግግር መንግስት ህጋዊነቱ ያን ያህል ሰምሮ የማይታየዉ በራሱ ሳይሆን በኢትዮጵያ ተደግፎ የመጣና ከመቃዲሾ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶቶች ህብረትን ያባረረ በመሆኑ ነዉ።»