የሶማሊያ እስላማዊ አንጃዎች ዉጊያ | ኢትዮጵያ | DW | 01.10.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የሶማሊያ እስላማዊ አንጃዎች ዉጊያ

የጠላትሕ-ጠላት ወዳጅሕ ነዉ አይነት-መርሕ አንድ-አስመሰላቸዉ እንጂ በርግጥ አንድ አልነበሩም።አሁን ደግሞ ወትሮም የተጠጋጋነዉ ትብብር-ባይፈረካከስ ተሰነጠቀ

default

የሶማሊያን የሽግግር መንግሥት በሐይል ለማስወገድ ግንባር ፈጥረዉ ይዋጉ የነበሩት የአል-ሸባብና የሒዝቢ ኢስላም አንጃዎች ደቡባዊ ሶማሊያ ዉስጥ የገጠሙት ዉጊያ ዛሬ እስከማርፈጃዉ እንደቀጠለ ነዉ።ሁለቱ ሐይላት ዉጊያ የገጠሙት የደቡባዊ ሶማሊያ የወደብ ከተማ ኪስማዩን በተለይም ወደቡን ለማስተዳደር በፈጠሩት ጠብ ነዉ።በዉጊያዉ በትንሹ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸዉ ተዘግቧል።በርካታ የኪስማዩ ነዋሪዎች ከተማይቱን ጥለዉ እየሸሹ ነዉ።የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የአፍሪቃ ቀንድ የፕሮጄክት ሐላፊ ኢ.ጄይ. ሆሕንዶርም እንደሚሉት የሁለቱ እስላማዊ አንጃዎች ዉጊያ ለሶማሊያ በጎም መጥፎም ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ሆሕንዶርምን በስልክ አነጋግሯቸዋል።

የጠላትሕ-ጠላት ወዳጅሕ ነዉ አይነት-መርሕ አንድ-አስመሰላቸዉ እንጂ በርግጥ አንድ አልነበሩም።አሁን ደግሞ ወትሮም የተጠጋጋነዉ ትብብር-ባይፈረካከስ ተሰነጠቀ።ምክንያቱ ብዙ ዉስብስም አይነት ነዉ።በግልፅ የሚታወቀዉ ግን-የግጭቶችን ምክንያትና መፍትሔን የሚያጠናዉ ተቋም-የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የምሥራቅ አፍሪቃ የፕሮጄክት ሐላፊ ኢ ጄይ ሆሕዶርም እንደሚሉት- እብለት እና ጥቅም ነዉ።

«ምክንያቱ እኛ እስከሚገባን ድረስ ሁለቱ ቡድናት ኪስማዩን በተቆጣጠሩበት ጊዜ ከተማይቱን በተለይ ደግሞ ወደቡን በፈረቃ ለማስተዳደር ነበር-የተስማሙት።አሁን እንደሚገመተዉ ሒዝቢ ኢስላም ሥልጣን እንዲይዝ አሸባብ አልፈቀደም።ይሕ ወደ ቅራኔ፥ አሁን ደግሞ ወደ ግጭት እንዲያመሩ ምክንያት ሆኗል።ምናልባት ወደፊትም ወደ ከፋ ዉጊያ ይቀየርም ይሆናል።»

ኪስማዩን ከትናንት ማምሻ ጀምሮ የሚያተረማምሰዉን ዉጊያ ባንድ በኩል ባሸናፊነት ለመወጣት በሌላ በኩል ደግሞ ተኩስ ለማስቆም የሁለቱ አንጃ መሪዎች ዛሬን ሲባትሉ ነዉ-የዋሉት።ደም መፋሰሱን እንዲቆም፥ ወይም የሁለቱን አንጆች አንድነት የሚሹ ወገኖችም ሊያደራድሩ እየጣሩ ነዉ።የድርድሩ አማራጭ ቢሳካ እንኳን ዳር የሁለቱን ሐይላት አንድነት ከሚያፀና ዉል መደረሱ አጠራጣሪ ነዉ።

«ዉጊያዉ በርግጥ ትብብሩ በጣም ለንቋሳ እንደሆነ አመልካች ነዉ።እኛ አሁን ባለን መረጃ መሠረት ከተኩስ አቁም ሥምምነት እና ከአዲስ መግባባት ላይ የሚያደርስ ድርድር ለማድረግ እየተሞከረ ነዉ።ይሁንና በአል-ሸባብና በሒዝቢ ኢስላም መካካል ቆየት ያለ ሽኩቻም እንዳለ እናዉቃለን።በአሸባብ በራሱ ዉስጥም አለመግባባት አለ።ይሕ ልዩነት አሸባብ የተለያዩ ሐይላትን የሚያስተባብር ድርጅት እንዳልሆነ አመልካች ነዉ።የተወሰኑ የአሸባብ ሐይላት ሌሎቹ የሚያደርጉትን ሌሎቹ አይፈልጉት ይሆናል።»

የሽግግር መንግሥቱ ፕሬዝዳት ሽኽ ሸሪፍ ሸኽ አሕመድ ሥልጣን ሲይዙ-ጠላት ካደረጓቸዉ ከድሮ ጓዶቻቸዉ ጋር በቀጥታም በተዘዋዋሪም መነጋገር-መደራደራቸዉ አልቀረም።ሸሪፍ በድርድር ንግግሩ ሒደት «አይንሕን ላፈር» የሚሏቸዉን እየራቁ፥ በመጠኑም ቢሆን ከሚግቧቧቸዉ ጋር-እየተቀራቡ በተለይ ሼኽ ዳሒር አዌስ ላይ አይናቸዉ ካረፈ ከረምረም ብለዋል።አዌስም አልጠሉትም።

መቀራረቡ ወደ መጠጋጋት ካደገ ወዲሕ አዌስ የሚመሩት ሒዝቢል ኢስላምን ከአል-ቃኢዳ ጋር ያብራል በሚባለዉ በአል-ሸባብ ላይ ለማሳማፅ ፕሬዝዳት ሸሪፍ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ማቀነባበራቸዉ አልቀረም።ይሕ ያሁኑ ግጭት አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል።ሆነም-አልሆነ ግን ለሽግግር መንግሥቱ ሆሕንዶርም እንደሚሉት በርግጥ ብስራት ነዉ።

«ይሕ ለሽግግር መንግሥቱ መልካም አጋጣሚ መሆኑ ግልፅ ነዉ።ምክንያቱም ጠላቶቹ በእርስ በርስ ዉጊያ እየተዳከሙለት ነዉ።የሽግግር መንግሥቱ ሥልጣን ለማጋራት ከሁለቱም ማለት ከሒዝቢ ኢስላምና ከአሸባብ በተለይም ለዘብተኛ ከሚባሉት የአሸባብ ሐይላት ጋር እየተነጋገረ ነበር።አሁን የተከሰተዉ ሁኔታ የሽግግር መንግሥቱ ባለሥልጣናት የሚሽቱን ለማድረግ፥-ማለት ከሁለቱም ሐይላት የተወሰኑትን ለመነጠል ይረዳቸዋል።»

የዚያኑ ያክል መርዶም ሊሆን ይችላል።-በሁሰወስት ምክንያት።ሰላማዊ ሰዉ-ይሞታል።-አንድ። ሰብአዊ እርዳታ ይታወካል-።የመንግሥት ሸማቂዎች ድርድርም ይወሳሰባል። የሁለቱ አንጃዎች ግጭት በኪስማዩ ካልተገደበ ደግሞ-ሽኽ ሸሪፍ መቅዲሾ ሆነዉ-ፖለቲካዊ ዉጤቱን ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ ድቀቱንም እኩል ማስላት ግዳ ቸዉ ነዉ-የሚሆን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ