የሶማሊያ ቀዉስና የሰላም ጉባኤ | ኢትዮጵያ | DW | 27.01.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የሶማሊያ ቀዉስና የሰላም ጉባኤ

የጅቡቲን ድርድር ያልተቀበለዉ-ወይም ገና ከጅምሩ በድርድሩ እንዲካፈል ያልተጋበዘዉ፥ አክራሪዉ ግን ጠንካራ ወታደራዊ ሐይሉ-አል-ሽባብ ባይደዋ ላይ አገኘሁት ያለዉ ድል-የጅቡቲዉ-ዉሳኔ የገጠመዉን አድናቆት-ትችት ገና ከጅምሩ በጅምር አቁሞታል

default

የሶማሊያ ድፈጣ ተዋጊዎች

የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ከተወሰኑት ተቃዋሚዎቹ ጋር ጅቡቲ ዉስጥ ሲደራደር፥የአል-ሸባብ ደፈጣ ተዋጊ ሐይላት ባይዶዋን መቆጣጠሩ ተዘግቧል።አል-ሸባብ የኢትዮጵያ ጦር የለቀቃቸዉን አካባቢዎች ተራ በተራ መቆጣጠሩ፥ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት የሽግግር መንግሥቱን ሕልዉና ላደጋ የሚያጋልጥ፥ የጅቡቲዉን ድርድርም ከንቱ የሚያስቀር ነዉ።የግጭቶችን ምክንያትና የሚወገዱበትን መንገድ የሚያጠናዉ የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የሶማሊያ ጉዳይ ተመራማሪ ረሺድ አብዲ እንደሚሉት ደግሞ የአሸባብ ድል ከተረጋገጠ የሽግግር መንግሥቱን ፍፃሜ ጠቋሚ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ረሺድ አብዲን አነጋግሯቸዉል።

ከባይደዋ ነቅለዉ ጅቡቲ የከተሙት የሶማሊያ የሽግግር ምክር ቤት አባላት «ለዘብተኛ» የሚባሉ ተቃዋሚዎቻቸዉንና የሲቢል ማሕበረሰብ ተወካዮችን ከምክር ቤታቸዉ ለማስገባት ወስነዋል።እንደራሴዎቹ እስካሁን 275 የነበረዉን የምክር ቤት መቀመጫቸዉን በእጥፍ ለመጨመር መወሰናቸዉ-ተቃዋሚዉን ለመቀበል እንደ ጥሩ መሠረት፥እንደ ድርድሩ በጎ ዉጤት መደነቁ አልቀረም።

የዚያኑ ያክል ገና በሁለት እግሩ የቆመ መንግሥት ለሌላት ሶማሊያ አምስት መቶ የምክር ቤት መቀመጫዎች ያሰፈለገበት ምክንያት፥ ምክር ቤቱን የሚሞሉት ሰዎች የሚወክሉት ወገን ማንነት ግራማጋባት፥ ማስወቀሱ አልቀረም።

የጅቡቲን ድርድር ያልተቀበለዉ-ወይም ገና ከጅምሩ በድርድሩ እንዲካፈል ያልተጋበዘዉ፥ አክራሪዉ ግን ጠንካራ ወታደራዊ ሐይሉ-አል-ሽባብ ባይደዋ ላይ አገኘሁት ያለዉ ድል-የጅቡቲዉ-ዉሳኔ የገጠመዉን አድናቆት-ትችት ገና ከጅምሩ በጅምር አቁሞታል።በኢንርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የሶማሊያ ጉዳይ ተመራማሪ ረሺድ አብዲ እንደሚሉት አል-ሸባብ ባይደዋን በርግጥ ተቆጣጥሮ ከሆነ የሽግግር መንግሥቱ አበቃለት።
ድምፅ

«ባይደዋ (ከደፈጣ ተዋጊዎቹ እጅ) ወድቃለች የሚለዉ ዘገባ እዉነትነት ከተረጋገጠ፥ የሽግግር መንግሥቱ ሶማሊያን መቆጣጠሩ ሙሉ በሙሉ እንዳበቃለት የሚያሳይ ታላቅ ምልክት ይመስለኛል።ሥለዚሕ በዉጤቱም የሽግግር መንግሥቱ የስደስት መንግሥት መሆኑን ጠቋሚ ነዉ።»
አል-ሸባብ ባይደዋን መቆጣጠሩን የከተማዋ ነዋሪዎች መስክረዋል።የሽግግር መንግሥቱ ግን እስከ ዛሬ ማምሻ ድረስ ሽንፈቱን አላመነም።ጅቡቲ የተያዘዉም ጉባኤ እንደቀጠለ ነዉ።መቀመጫ የሌለዉ ምክር ቤት፥ መሠረት ያጣዉ መንግሥት ድርድር ዉሳኔ የሚፈይደዉ ነገር መኖሩ አጠራጣሪ ነዉ።እንደገና ረሺድ አብዲ።
ድምፅ
«የሽግግር መንግሥቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ሽንፈት ቢገጥመዉም የጅቡቲዉ ጉባኤተኞች ድርድራቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።በተጨባጭ ያለዉ ሁኔታ ግን የጅቡቲዉን አጠቃላይ ሁኔታ አመልካች ነዉ።ተጨባጩን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ፖለቲካዊ ሒደት ከሌለሕ የሶማሊያን ግጭት ወይም ቀዉስ የሚያስወግድ መፍትሔ ልታገኝ አትችልም።»

የኢትዮጵያ ጦር የለቀቀዉን ሥልታዊ ስፍራ የተቆጣጠረዉ አልሽባብ ሰላም ለማዉረድ በሚደረገዉ ጥረት አይካፈልም።የማይከፍልበት ምክንያት ብዙ ነዉ።ዋናዉ ግን ቡድኑ አሸባሪ-መባሉ ነዉ።አብዲ ረሺድ በሶማሊያ እዉነተኛ ሠላም ለማስፈን ከተፈለገ አል-ሸባብ በሰላም ሒደቱ ሊጋበዝ ይገባል ባይ ናቸዉ።
ድምፅ
«የሶማሊያን ቀዉስ ለማስወገድ በሚደረገዉ ጥረት-የመጨረሻ መጨረሻ አል-ሸባብ መካፈል እንደማይቀር አልጠራጠርም።»

የኢትዮጵያ ጦር የዛሬ ሁለት አመት ሶማሊያ ሲገባ አሸባሪ-አክራሪ የተባሉ ሐይላት ለመደምሰስ፥ የሽግግር መንግሥቱን ለማጠናከር እንደነበር ከብዙ ጊዜ በላይ ተነግሯል።አሁን አብዛኛዉን ሶማሊያ የሚቆጣጠረዉ አል-ሽባብ ነዉ።ይሕ ለኢትዮጵያ ከድል ይቆጠር ይሆን።በጭራሽ-ይላሉ አብዲ ረሽድ።
ድምፅ

«ኢትዮጵያ በሶማሊያ የነበራት ሥልታዊ አላማ አልተሳካላትም።ይሕ እዉነት ነዉ።ከአላማዎቹ አንዱ የሶማሊያን የሽግግር መንግሥት አስተዳደር ማጠናከር ነበር።ሌላዉ በሐገሪቱ ሰላምና ሥርዓት ማስፈን ነበር።ይሕ አልተሳካም።»
ይሁንና ይቀጥላሉ ረሺድ።
ድምፅ
«ኢትዮጵያ የሽሪዓ ፍርድ ቤቶች ሕብረትን እንደ ሥልታዊ አደጋ አይታዉ ከነበረ ይሕንን ሐይል ከሥልጣን ማስወገዱ ተሳክቶላታል።እና ይሕ ለኢትዮጵያ እንደ ሥልታዊ ድል ሊቆጠር ይችላል።የዚሕ ዉጤት ግን ከ2006 ወዲሕ በታየዉ ሁኔታ መንምኗል።

ከአዉሮጳዉያኑ ሁለት ሺሕ ወዲሕ አስራ-ስድስት ሺሕ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።ብዙ ሺዎች ቆስለዋል።በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተሰደዋል።ወይም ተፈናቅለዋል።አል-ሸባብን የመሰሉ አክራሪ ሐይላት ተጠናክረዋል።-ሶማሊያ።

Negash Mohammed

Quellen: DW, Crisis Group,dpa, Afp,Reuters


ተዛማጅ ዘገባዎች