የሶማሊያ ቀዉስና ኢትዮጵያ | አፍሪቃ | DW | 22.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሶማሊያ ቀዉስና ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ  ለቆ መውጣት በሶማሊያ የመረጋጋት ተስፋ ላይ ጫና ያሳድራል እየተባለ ነው። የኢትዮጵያ ጦር ከለቀቃቸው ከተሞች መካከል የተወሰኑት በአል-ሸባብ እጅ ወድቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ጦሩን ከሶማሊያ ለመውጣቱ ከሚሰነዘሩት ምክንያቶች መካከል የምዕራባውያኑን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ማርገብ አንዱ ሳይሆን አይቀርም እየተባለ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:58
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:58 ደቂቃ

የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ መውጣት አሉታዊ ተፅዕኖ

ሶማሊያ የዘመተው የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ጦር በጁባ ሸለቆ በአል-ሸባብ መዳፍ ሥር የሚገኙትን የባኮል እና ሒራን አካባቢዎች ለማስለቀቅ ተጨማሪ 4,000 ወታደሮች እንደሚያስፈልጉት ገልጧል።  ከኢትዮጵያ፤ ኬንያ፤ ጅቡቲ፤ ዩጋንዳ እና ብሩንዲ የተውጣጡ 21,129 ወታደሮች ያሉት አኅጉራዊው ሰላም አስከባሪ ኃይል ግን የተሰጠውን ተልዕኮ መወጣት ተስኖታል እየተባለ ይተቻል። የአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ (AMISOM) ቃል-አቀባይ ኮሎኔል ጆሴፍ ኪበት አል-ሸባብን ድል ለመንሳት በአጠቃላይ 49,000 ወታደሮች እንደሚያስፈልጉ ዘ ኢስት አፍሪቃን ለተሰኘው የኬንያ ጋዜጣ በዚህ ወር መጀመሪያ ተናግረዋል። ቃል-አቀባዩ የኢትዮጵያ ወታደሮች የለቀቋቸውን ስድስት የሶማሊያ ከተሞች የአል-ሸባብ ታጣቂዎች ቢቆጣጠሯቸውም ለጊዜው በተልዕኮው ላይ ተፅዕኖ አላሳደረም ብለዋል።

የአፍሪቃ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ሶማሊያ ከዘመተ ዘጠኝ አመታት በላይ ቢቆጠሩም የታቀደለትን ዓላማ ማሳካት ተስኖታል የሚል ወቀሳ ይቀርብበታል። የጸጥታ ተንታኞች በሰላም አስከባሪ ወታደሮች ዘንድ መሰላቸት ከመፈጠሩም ባሻገር እርስ በርስ ያለው የዕዝ ሰንሰለት ልል ነው ሲሉ ይተቻሉ። የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ቻላቸው ታደሰ ከአኅጉራዊው ሰላም አስከባሪ ኃይል ውጪ በሶማሊያ ዘምቶ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ጥሎ መውጣት በተልዕኮው ላይ ጫና እንደሚያሳድር ይናገራሉ። በተናጠል ወደ ሶማሊያ የዘመቱት የኢትዮጵያ ወታደሮች «ቀድሞ ቦታዎችን በማፅዳት አዳዲስ ነፃ ቦታዎችን በመፍጠር ለአሚሶም ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጥር የኖረ ነው። የዚህ ጦር መውጣት አሚሶምን ከፍተኛ ሥጋት ላይ ይጥለዋል።»  ይላሉ አቶ ቻላቸው

ሞኮሪ፤ኤል-አሊ፤ በለደዌይን እና የአልጋን ከተሞች የኢትዮጵያ ወታደሮች ከለቀቋቸው መካከል ይገኙበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሊያ ምርጫ ዋዜማ ወታደሮቹን ለምን ማስወጣት እንደፈለገ በግልፅ ያለው ነገር የለም። ገንዘብ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ለኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ገፊ ምክንያቶች ሳይሆኑ አይቀሩም የሚሉ መላ ምቶች ግን እዚህም እዚያም ተደምጠዋል። አቶ ቻላቸው ታደሰ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ያስወጣችው በአገር ውስጥ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ስለገጠማት ነው የሚለው ክርክር ውሐ አይቋጥርም የሚል እምነት አላቸው። በአቶ ቻላቸው ትንታኔ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮቹን ከሶማሊያ በማስወጣት ከምዕራባውያኑ የደረሰበትን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማርገብ ተጠቅሞበታል። ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ እና በተቃውሞ አያያዙ ግፊት እያሳደሩበት ነው የሚሉት አቶ ቻላቸው ግፊቱን «መንግሥት ስላልወደደው ከሶማሊያ ጦሩን በማስወጣት ከሶማሊያ ጦሩን በማስወጣት» ለማለዘብ ሞክሯል የሚል እምነት አላቸው።

«ምዕራባውያን አማራጭ እንደሌላቸው ኢህአዴግ ጠንቅቆ ያውቃል።» የሚሉት አቶ ቻላቸው የቀጣናው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ እድል መፍጠሩን ገልጠዋል። ደቡብ ሱዳን ተጨማሪ 4,000 ወታደሮች የምትፈልግ ሲሆን ኬንያ ጦር የማዋጣት ፍላጎት የላትም። ከደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ወግና የምትዋጋው ዩጋንዳ ጦር ልታዋጣ አትችልም። ይህ ኢትዮጵ በደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ እንድትፈለግ ቀዳዳ መፍጠሩን አቶ ቻላቸው ይናገራሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት «ሶማሊያ ላይ ያለውን የጸጥታ ትብብር እንደመሳሪያ እየተጠቀመበት ነው የሚለው ግምት የበለጠ ያመዝናል።» ሲሉም ያክላሉ።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሶማሊያን ለማረጋጋት እና በሁለት እግሯ ለማቆም አሁንም ጥረት እያደረኩ ነው ቢልም የውጊያ ሥልቱን ወደ ደፈጣ የቀየረው አል-ሸባብ እና በራስ ገዟ የፑንትላንድ ግዛት የቃንዳላ ከተማን የተቆጣጠረው እና ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ የሚጠራው ታጣቂ አሁንም ስጋት ናቸው። የፑንትላንድ ወታደሮች ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር ባሻሺን ከተባለች ከተማ ተዋግተው ሰባት ገደልን ማለታቸው አይዘነጋም። አቶ ቻላቸው አል-ሸባብ ተጠናክሮ ወደ ሞቅዲሹ ከገሰገሰ የኢትዮጵያ ጦር ተመልሶ ወደ ሶማሊያ መግባቱ አይቀርም ሲሉ ይናገራሉ።

አሚሶም ወደ ሶማሊያ ከዘመተበት የጎርጎሮሳዊው 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ከአውሮጳ ኅብረት ብቻ ወደ 1.25 ቢሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ አግኝቷል። ለአስር አመታት ያክል የበርካቶች ደም እና ከፍተኛ ወጪ የፈሰሰበት ተልዕኮ ግን እንደ ታቀደለት ሶማሊያን ለማረጋጋቱ በእርግጠኝነት የሚናገር አልተገኘም። በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. ሶማሊያን ለቆ ለመውጣት ያቀደው አሚሶም በፈረንጆቹ አዲስ አመት በአል-ሸባብ ላይ አዲስ ዘመቻ ሊጀምር ውጥን ይዟል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic