የሶማሊያ ምግብ እጥረት መባባስ | አፍሪቃ | DW | 05.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሶማሊያ ምግብ እጥረት መባባስ

ሶማሊያ ዳግም ለአዲስ የምግብ እጥረት ችግር መጋለጧን ሕፃናት አንድ የተሰኘዉ ግብረ ሰናይ ድርጅት አመለከተ። ድርጅቱ ዛሬ ይፋ እንዳደረገዉ ሶማሊያ ዉስጥ ከመኖሪያ ቀያቸዉ የተፈናቀሉ ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁ ወገኖች ግጭት፤ የዝናብ እጥረትና

 በዘገየዉ የአዝመራ ወቅት ለምክንያት ለረሃብ ተጋልጠዋል። በሶማሊያ ካደረጉት የመስክ ጉብኝት መመለሳቸዉን የገፁት ኬንያ የሚገኘዉ የድርጅቱ የሶማሊያ መርሃግብር የፕረስ ጉዳይ ኃላፊ ማሪየን ሜከን የሚታየዉ የከፋ ሁኔታ አሳሳቢ ነዉ ይላሉ።

«ሶማሊያ ዉስጥ የሚታየዉ የከፋዉ ሁኔታ በጣም አሳስቦናል። ለዚህ መከሰት የተለያዩ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፤ በርካታ ቡድኖች የሚሳተፉበት የማያባራዉ ግጭት በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ከመኖሪያ ቀየዉ እንዲፈናቀል ምክንያት ሆኗል። በአንድ ወገን ከግጭቱ የሸሹ እርሻቸዉን ተረጋግተዉ ማረስ ያልቻሉ የተፈናቀሉ ገበሬዎችና ከብቶቻቸዉ አሉ፤ በዚያ ላይ የተዳከመ የአዝመራ ሁኔታ ነዉ ያለዉ፤ ምክንያቱም ብቸኛዉ የሶማሊያ የዝናብ ወቅት የነበረዉ ዝናብ እጅግ አነስተኛ ከመሆኑ በላይ ዘግይቶና በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ነዉ የነበረዉ።»

የህፃናት አድን ድርጅት የሶማሊያ መርሃግብር የፕረስ ጉዳይ ኃላፊ ማሪየን ሜከን እንደሚሉት የተዳከመዉና ዘግይቶ ሶማሊያ ዉስጥ የዘነበዉ ዝናብ ከወትሮዉ ያነሰ አዝመራ ብቻ ነዉ ያስገኘዉ። ኅብረተሰቡም ለዓመታት ከዘለቀዉ ግጭት እና ጦርነት ጋ ተዳምሮ ባለፈዉ ዓመት ሀገሪቱ ያጋጠማት የረሃብ አደጋ ካስከተለበት ድንጋጤ ባለመላቀቁ ተዳክሟል። በሶማሊያ ካካሄዱት የመስክ ሥራ መመለሳቸዉን የገለፁት ሜከን በስፍራዉ ተገኝተዉ በአይናቸዉ ለማየት የቻሉትን እንዲህ ይገልፁታል፤

«በርካታ ሴቶችና ህፃናትን ካገኘሁበት ከመቃዲሾ ገና መመለሴ ነዉ፤ ላለፉት ሳምንታት ምግብና ዉሃ ያላገኘት፤ ለሰባት ቀናት የተጓዘች አንዲት እናት አግኝቻለሁ። ሶስቱ ትንንሽ ልጆቿ ወደመቃዲሾ ስትጓዝ መንገድ ላይ ሞተዉባታል። እናም ስትመለከችዉ ሰዎች በከፋ ሁኔታ ላይ ነዉ የሚገኙት። ልጆች አሁንም ሶማሊያ ዉስጥ በየቀኑ በረሃብ እና ከርሃብ ጋ በተገናኙ በሽታዎች ምክንያት ይሞታሉ። እናም እንደገለፅኩት ሁኔታዉ እየከፋ ነዉ።»

የሶማሊያን ወቅታዊ የረሃብ ችግር በቅርብ የተመለከቱት ማሪየን ሜከን በድርጅታቸዉ ስም፤ ግለሰቦችም ሆኑ ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ እነዚህን ወገኖች እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል። ሶማሊያ ዉስጥ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎች በግጭትና ረሃብ ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸዉን መፈናቀላቸዉን የተመድ ያመለክታል። እነዚህ ወገኖች የሚገኙበትን ሁኔታ አሳሳቢነት ያመለከቱት የረድኤት ሠራተኛ በአሁኑ ሰዓት ያስፈልጋል ስላሉት ርዳታም ገልፀዋል፤

«በአሁኑ ወቅት የተመጣጠነ ይዞታ ያላቸዉ ምግቦች ያስፈልጉናል። በተመጣጠነ የምግብ እጥረት የተጎዱ ህፃናት አሉ፤ ሶማሊያ ዉስጥ ሶስት መቶ ሺህ ህፃናት የተመጣጠነ በቂ ምግብ አያገኙም። ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎች በመቃዲሾ አካባቢ ይገኛሉ፤ ከነልጆቻቸዉ ንፅህና ከሌለዉ ዉሃ በቀር የላቸዉም። ምግብ እና መጠለያ የላቸዉም፤ መጠለያ፤ የተመጣጠነ ምግብ፤ ዉሃና የንፅህና መጠበቂያ ልንሰጣቸዉ ይገባል።»

የረድኤት ሠራተኛዋ እንዳመለከቱት የህፃናት አድን ድርጅት እዚያዉ ሶማሊያ ዉስጥ ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት መርሃግብር ዘርግቷል። በዚህ አማካኝነትም መሠረታዊ የሆኑትን መጠለያ፤ የተመጣጠነ ምግብ፤ ንፁህ ዉሃና የንፅህና መጠበቂያዎችን ለተፈናቃዮቹ ያቀርባል። እንዲያም ሆኖ የፀጥታ ሁኔታዉ ለረድኤት አገልግሎቱ እንቅስቃሴ አመቺነት እንደሌለዉ ነዉ ማኪን ያመለከቱት፤

«የፀጥታዉ ሁኔታ AMISOM እና የሽግግሩ መንግስት ኃይሎች በቅርቡ ከወሰዱት ርምጃ ባሻገር ሶማሊያ ዉስጥ በጣም አደገኛ ነዉ። ባለፉት ዓመታትም ምንም አልተሻሻለም። ወደታሰበበት ለመድረስ አሁን በጣም አዳጋችና በጣም አደገኛ ነዉ። ባልደረቦቻችን ሶማሊያ ዉስጥ በየቀኑ ህይወታቸዉ ለአደጋ የተጋለጠ ነዉ።»

በተደጋጋሚ የረሃብ አደጋና ግጭት የተጨነቁት ወገኖች ወደጎረቤት ሀገሮች ድንበር አልፈዉ እንደሚሻገሩና ወደኢትዮጵያም ሆነ ኬንያ እንደሚገቡ ሲገለፅ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ግን ይህ እንደሌለ ነዉ ማኪን ያመለከቱት፤

«በአሁኑ ጊዜ ምናልባት እንደሚታወቀዉ ድንበር ለመሻገር ሁኔታዉ በጣም አስቸጋሪ ነዉ። ኬንያ የሚገኘዉ ዳዳብ የስደተኛ መጠለያ አዲስ ስደተኞችን መመዝገብ አቁሟል። በዚያ ላይ ሀገራቸዉን ጥለዉ ወደጎረቤት ሀገር መሻገር ለእነዚህ ሰዎች እጅግ አደገኛ በመሆኑ ከመኖሪያ ቀያቸዉ እዚያዉ አገር ዉስጥ የሚፈላቀሉበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ። የተመድ ሶማሊያ ዉስጥ ወደአንድ ነጥብ አራት ይገምታል የስደተኞችን ቁጥር።»

እሳቸዉ እንደሚሉት ከተፈናቃዮቹ ገሚሱ በጎዳና ዳር እራሳቸዉ ከጨፈቃና መሰል ቁሳቁሶች በሠሯቸዉ መጠለያዎች ሲቀመጡ በመቃዲሾ አካባቢ ብቻ ምግብና ዉሃ ለሌላቸዉ ተፈናቃዮች የሚሆኑ ወደ500 መጠለያዎችም ይገኛሉ። 

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic