1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ምርጫ ፤የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 6 2014

ከአንድ ዓመት በላይ ሲጠበቅ የነበረው የሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ነገ ይካሄዳል።በነገው ምርጫ አሸንፎ ስልጣን የሚይዘው ፕሬዝዳንት የሰርጎ ገቦች ጥቃትና ረሀብ ያስከትላል ተብሎ የሚያሰጋውን ድርቅ ጨምሮ በርካታ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል። በበርካታ የአፍሪቃ ሀገራት በድህነትና በኮሮና ሰበብ ህጻናት በግዳጅ ለጉልበት ስራ መዳረጋቸው ከቀድሞው ብሷል።

https://p.dw.com/p/4BHiU
Somalia Präsident Farmajo Premierminister Roble
ምስል Abdirahman Yusuf/AFP/Getty Images

የሶማሊያ ምርጫ ፣የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ በአፍሪቃ


የሶማሊያ የሕግ መምሪያና የሕግ መወሰኛ ምክርቤቶች ከ15 ወራት በላይ የዘገየውን የሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ነገ ያካሂዳሉ። ጎሳን መሰረት ባደረገው በዚህ ለስድስተኛ ጊዜ በሚካሄድ  ቀጥተኛ ባልሆነ  ምርጫ 39 እጩዎች ይወዳደራሉ። በተለምዶ ፎርማጆ የሚባሉትን ስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ፣ የቀድሞዎቹን ፕሬዝዳንቶች ሸሪፍ ሼክ አህመድ እና ሀሰን ሼክ ሞሐመድን እንዲሁም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሰን አሊ ኬህሬን ከእጩ ተወዳዳሪዎቹ መካከል ናቸው። የራስ ገዝዋ የፑንትላንድ ፕሬዝዳንት ሰዒድ አብዱላሂ ዳኒና የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋውዛ ዩሱፍ አደንም ለፕሬዝዳንትነት ይወዳደራሉ። ፋውዛ ዩሱፍ አደን ብቸኛዋ ሴት ፕሬዝዳንታዊ እጩ ናቸው። ፋውዛ ሶማሊያን ለመምራት ትክክለኛዋ ፕሬዝዳንት እኔ ነኝ ይላሉ። ብመረጥ ሃላፊነቴን በአግባቡ እወጣለሁ ብለዋል። 
« ሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ፍትህ ለሁሉም፣የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች ያስፈልጓታል። ትክክለኛዎቹ ሰዎች ሴቶችም ወንዶችም በትክክለኛው ቦታ መቀመጣቸው መረጋገጥ አለበት።እኔ ብመረጥ የኔ መንግሥት፣ በህገ መንግሥቱ መሰረት ሃላፊነቱን ይወጣል። ሁሉን አሳታፊና የሰብዓዊ መብቶችንም የሚያከብር ይሆናል። »
ሁሉም እጩዎች የሶማሊያን የተከማቹ ችግሮች ለመፍታትና በአሸባብ ጥቃት፣በዋጋ ግሽበትና በድርቅ ለሚሰቃዩ ዜጎች እፎይታ ለማምጣት ቃል ገብተዋል። ፎርማጆ ከዓመት በፊት በአዋጅ ስልጣናቸውን ለማራዘም ያደረጉት ሙከራ በተቀናቃኝ አንጃዎች መካከል ግጭት በማስነሳት በመቅዲሾ የጎዳና ላይ ውጊያን ቀስቅሶ ነበር። በኋላም ፎርማጆ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሮብሌ በተቀናቃኝ ወገኖች መካከል መግባባት እንዲፈጥሩ ቢሰየሙዋቸውም በተዛባ አካሄድና በፖለቲካ ጣልቃ ገብነትና  ሂደቱ አዝጋሚ ሆኖ ቆይቷል። በፎርማጆና በሮብሌ መካከል የተፈጠረው ጠብ ችግሩን በማባባስ የምርጫው ሂደት እንዲዘገይ ምክንያት ሆኗል። ሆኖም ከአንድ ዓመት በላይ የተገፋው የሶማሊያ ምርጫ ነገ ቢካሄድም ለሀገሪቱ መጠነ ሰፊ ችግሮች መፍትሄ ማምጣቱን የሚጠራጠሩ ያመዝናሉ። ከመካከላቸው በሶማሊያ የጎሳ ፖለቲካ ደስተኛ ያልሆኑት የፖለቲካ አራማጅ አያንሌ አብዲራሂማንአንዱ ናቸው ። 
« ቀጥተኛ ያልሆነው ምርጫ የእስከዛሬውን የሶማሊያ የፖለቲካ ምስቅልቅ የሚቀይር አይሆንም። ምክንያቱም 329 የምክር ቤት አባላት ብቻ ናቸው የሀገሪቱን ተራ ህዝብ እጣ ፈንታ የሚወስኑት። ሆኖም ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ሀገሪቱን ወደፊት የሚያራምድና ህዝቡም የወደፊት መሪዎቹን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወይም በአንድ ሰው፣ አንድ ድምጽ አማካይነት እንዲመርጥ ያደርጋል ብለን እጠብቃለን።
በሶማሊያ ምርጫ እያንዳንዱ ህዝብ ድምጽን በቀጥታ አይሰጥም።275 ቱ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላትና 54ቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በአጠቃላይ 329 የምክር ቤት አባላት ናቸው በሚስጥር ድምጽ መስጫ የሶማሊያን ፕሬዝዳንት የሚመርጡት። ሶማሊያ ከጎርጎሮሳዊው 1991 ዓም አንስቶ ጠንካራ መንግሥት የላትም። አሸባብ የተባለው ቡድን በምዕራባውያን የሚደገፈውን የሶማሊያ መንግሥት ለመጣል ውጊያ ያካሂዳል።መቅዲሾን ጨምሮ በሌሎች የሶማሊያ ከተሞችም ተከታታይ ጥቃቶችን ይጥላል። ከቅርብ ጊዜዎቹ ጥቃቶች መካከል ባለፈው ሳምንት 10 የብሩንዲ ሰላም አስከባሪዎች የተገደሉበት በአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪዎች ጦር ሰፈር ላይ የደረሰው ጥቃት አንዱ ነው።የአሸባብ ኃይሎች ከቅርብ ወራት ወዲህ ይዞታቸውን አስፍተዋል።በአሁኑ የሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማንም ያሸንፍ ማንም የሚጋፈጠው አጣዳፊ ጉዳይ አሳሳቢው የሀገሪቱ ጸጥታ ነው።ውስን በሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ሽምያ በተጠመዱ የክልል መንግስታት የተፈጠረውን ውጥረት ማርገብም ሌላው ከተመራጩ ፕሬዝዳንት የሚጠበቅ ተግባር ነው ።

Somalia Abstimmung Gesetzesentwurf zur Verlängerung der Amtszeit von Präsident Mohamed Abdullahi Mohamed
ምስል Feisal Omar/REUTERS

የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ በአፍሪቃ

TABLEAU | Internationaler Tag gegen Kinderarbeit 2021 | Äthiopien
ምስል Michael Runkel/ImageBroker/picture alliance

የካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ መንገዶች በታዳጊ ወጣት የጎዳና ነጋዴዎች ተጨናንቀዋል። እድሜያቸው ከሰባት እስከ 14 ዓመት የሚሆኑት እነዚሁ ታዳጊ ወጣቶች እስከ ውድቅት ድረስ ከትላልቅ አደባባዮች አይጠፉም። ትምህርት ቤት ተዘግቶላቸዋል። ይሁንና እረፍት የላቸውም።
 «በአዲሱ የትምህርት ዘመን ለትምህርት የሚያስፈልጉኝ መጻህፍት እንዲገዙልኝ ወላጆቼን ለማገዝ ውኃ እሸጣለሁ።» 
የስምንት ዓመቱ ኬቪን ነው ይህን የሚለው።የአስር ዓመቷ ሊያም ለትምህርቷ የሚያስፈልጋትን ገንዘብ ለማግኘት ኦቾሎኒ ትሸጣለች። እነዚህና ሌሎች ወጣቶቹ የሚገፉት ይህን መሰል ሕይወት የትምህርት ቤት ዳይሬክተር የሆኑትን ሻንታል ዛንጋን ያሳስባቸዋል።
 «ህጻናት በጎዳና ንግድ መሰማራታቸውን እቃወማለሁ። ህጻናት ጥበቃ የማግኘት መብት አላቸው። ሆኖም እኛ ወደ ጎዳና ከለቀቅናቸው ማን ሊጠብቃቸው ነው?» 
በዓለማችን የህጻናት ሰራተኞች ቁጥር 160 ሚሊዮን ይገመታል።ከነዚህም አብዛኛዎቹ አፍሪቃ ውስጥ ነው የሚገኙት። ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት በምህጻሩ «አይ ኤል ኦ» እንደሚለው ከሰሀራ በረሀ በስተደቡብ በሚገኙ ሀገራት ከ72 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተዋል።ይህም ማለት ከአምስት ልጆች አንዱ የችግሩ ሰለባ ነው። በተለይ በኮሮና ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ህጻናት ለጉልበት ብዝበዛ መዳረጋቸው አልቀርም።የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ እንደሚለው የህጻናትን የጉልበት ብዝበዛ ለማስቆም ከ20 ዓመት በፊት የተጀመረው ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ ተገቷል። ድርጅቱ እንደሚለው የህዝብ ቁጥር  መጨመር ፣በተለያየ ጊዜ የሚከሰቱ ቀውሶች፣ የከፋ ድህነት፣በቂ የማኅበራዊ ጥበቃ እርምጃዎች ባለመወሰዳቸው ባለፉት አራት ዓመታት ተጨማሪ 17 ሚሊዮን ህጻናት ከሰሀራ በስተደቡብ ባሉ ሀገራት በስራ እንዲሰማሩ አድርጓል።
ህጻናቱ የጎዳና ነጋዴዎች ለፀሐይና ቁር እንዲሁም  ለትራፊክ አደጋ የተጋለጡ ናቸው።በየቀኑ ወሲባዊ ጥቃት ሊደርስባቸውም ይችላል።የ12 ዓመቷ ጁልየተ ሌማና በያዉንዴ ጎዳናዎች ስለሚደርሱ አደጋዎች በቅጡ ታውቃለች፤በእናትዋ ትዕዛዝ ጎዳና ላይ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ትሸጣለች። አንዳንዴ ገበያ ውስጥ አለያም በመንገድ ላይ ባለመኪናዎች ነው በቀጥታ የምትሸጠው። እርስዋ እንደምትለው በቅርቡ አንዲት ጓደኛዋ ሞተር ቢስኪሌት በላይዋ ላይ ሄዶባታል። ይህን መሰሉ አደጋ ብቻ አይደለም የሚያሳስባት ፤አምሽተው መስራታቸውም ጭምር እንጂ። አንዳንዴ ቤት የምንሄደው በውድቅት ለሊት ስለሆነ፣አቅጣጫው ሊጠፋን ይችላል ትላለች። ካሜሩናዊቷ የመብት ተከራካሪ ፓውሊን ቢዮንግ እንደሚሉት ከሆነ፣በካሜሩን ህጻናትን ማሰራት በሕግ የተከለከለ ነው። 
«ካሜሩን ለህጻናት ጥበቃ ማድረግን የተመለከቱ በርካታ ሕጎችን አጽድቃለች። እነዚህ ሕጎች ሊከበሩ ይገባል።ሆኖም እንዳለመታደል ሆኖ በከተማችን ከእለት ወደ እለት የህጻናት ጉልበት በወላጆቻቸው ይበዘበዛል። ይህ የተለመደ አይደለም።»
ሲሉ የሴቶችና ህጻናት ትምሕርት ሊግ ሃላፊም የሆኑት  ቢዩንግ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
ህጻናት በለጋ እድሜያቸው እንዲሰሩ ከሚያስገድዷቸው ምክንያቶች ዋነኛው ድህነት ነው።በታንዛንያና በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ህጻናት ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ህልውና ሲሉ በማዕድን ማውጫ ስፍራዎች ይሰራሉ።በደቡብ ሱዳን ደግሞ በወታደርነት እየተሰለፉ ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ።በግብርናም ይሰማራሉ።  የሚያገኙት ገንዘብ ግን አነስተኛ ነው።በአይቮሪ ኮስት ካካዋ በሚመረትባቸው ስፍራዎች  በህጻናት ላይ ተመሳሳይ  በደል ይደርሳል። ሆኖም በዚያ የሚገኘው በዱቄት ወተት ምርት የሚታወቀው ኔስሌ የተባለው ኩባንያ ስሙን ለማደስ ምርቱ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ለህጻናቶች ትምሕርት ቤት ይገነባል፤ለሴቶች ደግሞ የመሰረተ ትምሕርት ዘመቻ ያካሂዳል።ይሁንና የኔስሌ የፕሮግራም ሃላፊ ቱሴንት ሉክ ንጉዌሳን ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ህጻናት አሁንም በአንዳንድ የካካዋ እርሻዎች ውስጥ ይሰራሉ።
በናይጀሪያም የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ከባድ ችግር ነው። አይ ኤል ኦ እንደሚለው ከአፍሪቃ ግዙፍ ኤኮኖሚ በምታንቀሳቅሰው በናይጀሪያ ፣ በዓለም አቀፍ ሕግጋት ተቀባይነት ባይኖረውም፣ እድሜያቸው ከአምስት እስከ 11 ዓመት ከሚሆኑ የናይጀሪያ ህጻናት 43 በመቶው በተለያዩ ስራዎች ላይ ይገኛሉ። ሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ ውስጥ በምትገኘው ማይዱጉሪ የሚኖር አንድ ወጣት አባቱ ስፌት እንዲማር እንዳመጡት ይናገራል።አንዳንድ ጊዜ የሚያገኘው ገንዘብ ከግማኅ ዩሮ ያነሰ ነው። 15 ልጆች ያሏቸው አባቱ ልጆቻቸው ቤተሰቡን የሚደጉም ገንዘብ እንዲያመጡ ጎዳና ወጥተው እንዲነግዱ ያደርጋሉ።ህጻናቱም ለቤተሰብ ሲሉ ብዙ መስዋዕትነት ይከፍላሉ። የመማርና የተሻለ ሕይወት የመምራት እድላቸውም ይጨናገፋል።  
በተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች ፣ 193ቱ የተመድ አባል ሀገራት አስገድዶ ማሰራትን፣ዘመናዊ ባርነትን በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ከቦታ ወደ ቦታ ማሻገርን ህጻናትን ለውትድርና መመልመልን ጨምሮ ልዩ ልዩ  የህጻናት ጉልበት ብዝበዛዎችን እስከ ዛሬ ሦስት ዓመት ድረስ ለማስቆም ቃል ገብተዋል።ይሁንና ችግሩ እልባት የማግኘቱ ተስፋ እስከዚህም ነው።የማይዱግሪዋ የመብት ተሟጋች ሉሲ ዩዋና ለዚህ መፍትሄ የሚሉት ቅጣት ነው  ። 
«እንደ ወላጅ ለልጆቻችን ያለንን ማቅረብ እንጂ እነርሱ ለኛ ሊያቀርቡ አይገባም። መንግስት የሆነ ፖሊሲ ሊኖረው ይገባል።  በቤት ሰራተኝነት ፣በልመና የተሰማሩ ልጆችን መንግስት መያዝ አለበት።ህጻናት  ልጆቻቸውን በቤት ሠራተኝነት የሚያስቀጥሩ  ወላጆች ሊታሰሩ ይገባል።ይህን የሚያደርጉ ወላጆች ፍርድ ቤት መቅረብ አለባቸው፤ወይም ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል።»

TABLEAU | Internationaler Tag gegen Kinderarbeit 2021 | Südsudan, Nyamlel
ምስል Stefanie Glinski/AFP/Getty Images
TABLEAU | Internationaler Tag gegen Kinderarbeit 2021 | Malawi, Lilongwe
ምስል Amos Gumulira/AFP/Getty Images

ማርቲና ሳቮሮቭስኪ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ