የሶማሊያ ምርጫ ዉጤትና እይታዉ | አፍሪቃ | DW | 09.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሶማሊያ ምርጫ ዉጤትና እይታዉ

ሶማሊያ አዲስ ፕሬዝደንቷን ትናንት መርጣለች። ሀገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቀደም ብለዉ ያገለገሉት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ በሁለተኛዉ ዙር ምርጫ በ184 ድምጽ በማግኘት የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ሆነዉ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። በመጀመሪያዉ ዙር ሲመሩ የነበሩት ስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዝደንት ሀሰን ሼኽ መሐመድም ሽንፈታቸዉን አምነዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:42

ሶማሊያ ፕሬዝደንቷን መረጠች

ፎርማጆ ይሏቸዋል በቅጽል ስም። በ50ዎቹ የዕድሜ አጋማሽ ላይ ናቸዉ መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ። በሶማሊያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር በጎርጎሪዮሳዊዉ 1985ዓ,ም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የተጓዙት ፎርማጆ ከኒዉዮርክ ቡፋሎ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸዉን ወስደዋል። የዛሬ 7 ዓመት ወደ  ሀገራቸዉ ተመልሰዉም ለስምንት ወራት በጠቅላይ ሚኒስርነት አገልግለዋል። ለምርጫ ቅስቀሳ ያቀረቡት ታሪካቸዉ እሳቸዉ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ታጣቂዉ ፅንፈኛ ቡድን አሸባብ ከመቃዲሾ መባረሩን ያመለክታል። ከብዙ ዉጣ ዉረድ በኋላ ባለፈዉ ነሐሴ ወር ሶማሊያ አዲስ ፕሬዝደንት ለመምረጥ መዘጋጀቷን ይፋ ስታደርግ የመላዉ ዓለም ዓይን አተኮረባት። በተለያዩ ምክንያቶች ሲገፋ ቆይቶም ትናንት መርጣ እፎይ አለች። ከስፍራዉ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ሶማሊያዉያን ትንፋሻቸዉን ዋጥ አድርገዉ በቴሌቪዥን መስኮቶች ላይ አተኩረዉ ነዉ ቀኑን ያሳለፉት። የመሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ማሸነፍ እንደተሰማ ከተማዋ በደስታ ተኩስ መድመቋም ተዘግቧል። በመጀመሪያዉ የምርጫ ዙር ሲመሩ የነበሩትና የኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ እንዳላቸዉ የሚነገረዉ የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ሀሰን ሼኽ መሐመድ ሽንፈታቸዉን አምነዋል። በምርጫዉ ዉስጥ ጎረቤቶቿን ጨምሮ የዉጭ ሃገራት እጅ እንደገባበት ሲናገሩ ከነበሩት  የሀገሪቱ ምሁራን መካከል አንዱ መሐመድ ሹሬን ከዚህኛዉ የምርጫ ዉጤት ጀርባስ ማን እንደሚጠረጠር ለቀረበላቸዉ ጥያቄ ይህን ይላሉ።

Somalia | Mohamed Abdullahi Farmajo

አዲሱ ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ


«ምላሻችንን የምንሰጠዉ በመሬት ላይ ያለዉን በመገምገም እና ከሰዎች የምንሰማዉን መሠረት በማድረግ ነዉ። ይህን ስናገር አራት ግንባር ቀደም ተፎካካሪዎች እንዳሉ ጠቁሜያለሁ። ትናንት ያየነዉ ግን እኔ ከሰጠሁት አስተያየት ሙሉ ለሙሉ አቅጣጫዉ መቀየሩን ነዉ። የማን ጣልቃ ገብነት አለ ብለሽ ነዉ የጠየቅሽኝ፤ ኢትዮጵያን፤ የአረብ ኤሜሬት እና ሌሎች የአረብ ሃገራት፤ እንዲሁም ኬንያ እጃቸዉ እንዳለ ተናግሬ ነበር። አሁን እዚህ መቃዲሹ ሁሉም የሚነግረኝ የተመረጡት ፕሬዝደንት ፎርማጆ በጣም ጠንካራ ብሔርተኛ  እንደሆኑ እና የኢትዮጵያዉ ሰዉ መሸነፋቸዉን ነዉ። ምክንያቱም በጊዜዉ ሁሉም ሰዉ የቀድሞዉ ፕሬዝደንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳላቸዉ ያምናል።»
ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ ጥንካሬ ለማረጋገጥ ሶማሊያ ምርጫ እንድታካሂድ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል። ዩናይትድ ስቴትስም በቅርብ ዓመታት ፖለቲካና ኤኮኖሚዉ እንዲያንሰራራ በመቶ ሚሊየኖች የሚገመት ዶላር አፍስሳለች። አዲስ የተመረጡት ፕሬዝደንትም የሀገሪቱን ሰላም በማጠናከር በመላዉ ዓለም የተበተኑ ዜጎቿ ተመልሰዉ ሀገሪቱን ዳግም እንዲገነቡ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል። መቀመጫዉን አዲስ አበባ ያደረገዉ እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንዳለዉ የተገለጸዉ የምክር፣ የጥናት እና ትብብር ማዕከል በእንግሊዝኛ ምህጻሩ CDRC የሶማሊያ መረጋጋት እንዲፀና ፕሬዝደንቱ ከሃዉዬ ጎሳ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ከዳሩድ ቢሆን እንደሚበጅ የሶማሊያን ሁኔታ በተነተነበት ጽሑፍ በቅርቡ አሳስቧል። የምርጫዉን ዉጤትእና አስተያየቱን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ወደ ማዕከሉ ስልክ ብንደዉልም የሚመለከታቸዉን ለዛሬ ማግኘት አልቻልንም። መሐመድ ሽሬ ግን ይህ ዘመን ያለፈበት አስተሳሰብ ነዉ ባይ ናቸዉ።
«ያ ልክ እንዳልሆነ ታይቷል። እኔም ይህ ትንታኔ ጠንካራ እንዳልሆነ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ከሃዉያ ያልሆኑ መሪዎች በቀድሞዉ ፕሬዝደንት አብዱላሂ ዩሱፍ ጊዜም ነበሩን። አሁን የተመረጡት ፕሬዝደንት ፎርማጆም ሃዉያ አይደሉም። እንደሚመስለኝ ይህ ያረጀ አስተሳሰብ ነዉ። አክትሟል። ሶማሌዎች አሁን ሀገራቸዉን ለመገንባት እየጠበቁ ነዉ። የኢትዮጵያ ተንታኞች ይህን በትክክል አልተረዱም።»


ሶማሊያን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሲያተራምሳት የቆየዉ የጎሳና የጦር አበጋዞች የእርስ በርስ ግጭት እና ጦርነት እየሰከነ የሄደ ይመስላል። ሆኖም የአሜሪካም ጭምር ዜግነት ያላቸዉ አዲሱ ፕሬዝደንት ይከተላል ተብሎ የሚሰጋዉን የጎሳዎችን እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ አቻችለዉ ሀገሪቱን በአንድነት የማስተዳደሩ ኃላፊነት ከፊታቸዉ ተጋርጧል። መሐመድ ሽሬም ፕሬዝደንቱ ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠብቃቸዉ ያምናሉ። 
«የተመረጡት ፕሬዝደንት ትልቅ ሥራ ከፊታቸዉ ተደቅኗል። በዚህ ጉዳይ ላይ ስሜታዊ አልሆንም። ተግዳሮቱ ከፍተኛ ነዉ። በዚህ ጉዳይ ላይም በተቻለ ፍጥነት የምጽፈዉ ይኖረኛል። ፕሬዝደንቱ በርካታ ተግዳሮቶቹ ይጠብቋቸዋል። ህዝቡን ወደ አንድነት ማምጣት ይኖርባቸዋል። በሶማሊያ የፖለቲካ ግንባታ ዉስጥ ኃይሎችን አንድ ማድረግ አለባቸዉ፤ ከአሸባብ ስጋት ጋር በተገናኘም ከማንም በላይ በጸጥታ ጉዳይ ላይ መሥራት ይኖርባቸዋል። ሶማሊያ ላይ ፍላጎት ካላቸዉ የአካባቢዉ ሃገራት ጋርም መሥራት ይኖርባቸዋል።»
ከምንም በላይ ደግሞ የሀገሪቱን መንግሥት ራዕይ የሚያሳካ ብቃት ያለዉ ጠቅላይ ሚኒስትር መምረጥ እንደሚገባቸዉም ጠቅሰዋል። አዲሱ ፕሬዝደንት ለሁለተኛ ዲግሪያቸዉ መመረቂያ በፃፉት የጥናት ጽሑፍ ከሶማሊያ ችግር ዉስጥ ኢትዮጵያ ተለይታ እንደማታዉቅ «በሶማሊያ የኢትዮጵያ ሚና» በሚል ርዕስ ሰፊ ትንታኔና አቋማቸዉን አስፍረዋል።  

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ 

Audios and videos on the topic