የስፖርት ጥንቅር | ስፖርት | DW | 05.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የስፖርት ጥንቅር

ጀርመናዊው የአርሰናል አማካይ ተጨዋች ሉቃስ ፖዶልስኪ ወደ ጣሊያኑ ኢንተር ሚላን በዝውውር በማቅናት ልምምድ ማድረጉ ታውቋል። ኢትዮጵያዊቷ ማሬ ዲባባ በሣምንቱ ማሳረጊያ ቻይና ውስጥ የማራቶን ድል ተቀዳጅታለች። በበረዶ መንሸራተት የከፍታ ዝላይ ጀርመን ከ12 ዓመታት በኋላ አሸናፊ ለመሆን ችላለች።

እሁድ ታኅሣሥ 26 ቀን 2007 ዓም በተከናወኑ የእንግሊዝ FA Cup ጨዋታዎች ዋነኞቹ ቡድኖች አሸናፊ ሆነው ወደ አራተኛ ዙር ለማለፍ ችለዋል። ማንቸስተር ሲቲ ሼፊልድ ዌንስዴይን 2 ለ1 አሸንፏል። አርሰናል ሁል ሲቲን 2 ለዜሮ ረትቷል። ማንቸስተር ዩናይትድ በ65 ደረጃዎች ዝቅ ብሎ ከስሩ የሚገኘው የዎቪል ታውንን 2 ለባዶ ሸኝቷል። የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣንኝ ሉዊስ ቫን ጋል በገና ሰሞን ያገኘናቸው ድሎች አስደሳች ናቸው ብለዋል። ቸልሲ ዋትፎርድን 3 ለምንም አሰናብቷል። እንዲያም ሆኖ አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ የዳኛ በደል ደርሶብናል ብለው ማማረራቸው አልቀረም። ወዲያው ግን ይቅርታ ጠይቀዋል።

ጆሴ ሞሪንሆ

ጆሴ ሞሪንሆ

ጨዋታውን የመሩት የመኻከል ዳኛ ኬቪን ፍሬይንድ የሎይች ሬሚ የኳስ አያያዝን አይቼ ነው ፍፁም ቅጣት ምት ያልሰጠኹት ብለዋል። በእርግጥም ጥፋት በተሰራ በጥቂት ሠከንዶች ውስጥ ሎይች ኳሷን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። «በቴሌቪዥን ቀደም ብዬ ስለሰጠኹት ትችት ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ» አሉ የቸልሲው አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ። ቀጠሉ፥ « ዳኛው ያከናወኑት ድንቅ ዳኝነት ነው። ፍፁም ቅጣት ምት እንደሚያሰጥ አይተዋል፤ መስጠትም ይችሉ ነበር። ሆኖም ኳሷ ሎይች ሬሚ እግር ላይ መሆኗን ሲመለከቱ ጥቂት ደቂቃዎችን ጠበቁ። ኳሷን መቆጣጠር ባይችል ወይንም ግብ ባይቆጠር ፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጡ እንደነበር ነግረውኛል። ቅሬታዬን አቅርቤያለሁ ግን ዳኛው ጥሩ ነው የሠሩት» ብለዋል። ጆዜ ሞሪንሆ ከዚህ ቀደምም ከተለያየ አቅጣጫ ቡድኔ ላይ የተቀነባበረ ዘመቻ ተከፍቶብኛል ብለው ቅሬታ ማሰማታቸው ይታወሳል።

የእንግሊዝ FA Cup ጨዋታ ዛሬም ይቀጥላል። ቶትንሐም ከበርንሌይ ጋር ይጋጠማል። ሊቨርፑል እና ዌምብልደንም ወደ አራተኛ ዙር ለመግባት ይፋለማሉ። ሊቨርፑል በFA Cup ጨዋታ ታሪክ አራተኛ ዙር ላይ ሳይደርስ አንድም ጊዜ ተሸንፎ አያውቅም። 12 ጨዋታዎችን አከናውኖ 10ን አሸንፏል። ለ2 ጊዜ አቻ ወጥቷል። ዌምብልደን ግን ማሸነፍ የቻለው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው።

ሪቻርድ ፍራይታግ በበረዶ ዝላይ

ሪቻርድ ፍራይታግ በበረዶ ዝላይ

አትሌቲክስ

ቻይና ሺያመን ውስጥ በተከናወነው የማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን ድል ቀንቷቸዋል። በሴቶች ፉክክር ማሬ ዲባባ ውድድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 2 ሠዓት፣ ከ19 ደቂቃ፣ ከ52 ሠከንድ ነበር። ማሬ ባለፈው ዓመት ያስመዘገበችውን የዓለም ክብርወሰን በ1 ደቂቃ ከ40 ሠከንድ ማሻሻል መቻሏም ተዘግቧል። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት መሠረት ለገሰ ኹለተኛ ስትወጣ፣ ኬንያዊቷ ሚሪያም ዋንጋሪ ተከትላት ሦስተኛ ሆናለች።

በወንዶች የማራቶን ሩጫ ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያውያን ኹለተኛ እና ሦስተኛ ለመውጣት ችለዋል። የውድድሩ አሸናፊ ኬኒያዊው ሞሰስ ሞሶፕ ነው። ሞሰስ ውድድሩ ሊጠናቀቅ 5 ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩት አንስቶ በፍጥነት በማፈትለክ ነበር አንደኛ የወጣው። ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት 2 ሠዓት፣ ከ6 ደቂቃ፣ ከ19 ሠከንድ መሆኑም ተዘግቧል። ሞሰስ የራሱን ክብር ወሰን በ1 ደቂቃ ከ13 ሠከንድ ማሻሻል ችሏል። ጥላሁን ረጋሣ በ2 ሠዓት፣ ከ6 ደቂቃ፣ ከ54 ሠከንድ ኹለተኛ ወጥቷል። አብርኃ ምላው ከጥላሁን በ1 ደቂቃ ከ15 ሠከንድ ዘግይቶ ሦስተኛ ወጥቷል።

ቻይና ቲያናማን አደባባይ

ቻይና ቲያናማን አደባባይ

በበረዶ መንሸራተት ከፍታ ዝላይ ውድድር የጀርመን ቡድን ከ12 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያ ድል ማስመዝገብ ችሏል። የ23 ዓመቱ ወጣት ስፖርተኛ ሪቻርድ ፍራይታግ ነበር ትናንት ኢንስብሩክ ውስጥ በተኪያሄደው ውድድር ጀርመንን ለዚህ ድል ያበቃው። ሪቻርድ እግሮቹ ላይ ባሰራቸው መንሸራተቻ ዘንጎች የበረዶ ግግሩ ላይ ቁልቅል በፍጥነት ተንሸራቶ አየር ላይ 133,5 ሜትር ርቀት በመክነፍ ነው ለድል የበቃው። የትናንትና ድሉ በዓለም አቀፍ መድረክ አምስተኛ ሆኖ የተመዘገበለት ጀርመናዊው ሪቻርድ ፍራይታግ ደስታውን እንዲህ ነበር የገለጠው።

«እጅግ በጣም ደስ የሚል ነው። ትናንት ልምምድ ሳደርግም በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። እዚህ የሰዉ ድጋፍ ወደር የለውም። ድንቅ ነው።»

በዚህ ውድድር ኦስትሪያዊው ሽቴፋን ክራፍት ኹለተኛ ለመውጣት ችሏል። ጃፓናዊው ኖሪያኪ ካሳዪ እና የስዊዘርላንዱ ሲሞን አማን በበኩላቸው የሦስተኛ ደረጃን በጣምራ ተካፍለዋል።

አዳዲስ የዝውውርና አጫጭር ዜናዎችን እናሰማለን

ሉቃስ ፖዶሊስኪ

ሉቃስ ፖዶሊስኪ

ጀርመናዊው ሉቃስ ፖዶሊስኪ ከ13 ጊዜ የእንግሊዝ ባለድሉ አርሰናል ወደ 18 ጊዜ የጣሊያን ሴሪኣ ዋንጫ ባለቤቱ ኢንተር ሚላን በዝውውር ያቀናው በሳምንቱ ማሳረጊያ ላይ ነበር። ሉቃስ ፖዶልስኪ ወደ ኢንተር ሚላን ገና ከመምጣቱ ከአዲስ ጓደኞቹ ጋር በፍጥነት ልምምድ ማድረጉም ታውቋል። ከዚያ ቀደም ብሎ የማይቀረው የሕክምና ምርመራ በተሳካ ኹናቴ መጠናቀቁ ተዘግቧል። የሉቃስ ፖዶልስኪ አማካሪ ናሲም ቶይሪ ዛሬ ለአንድ የስፖርት ዜና አውታር « የቀሩት አንድ ኹለት ሠነዶች ብቻ ናቸው። ከዚያ ውጪ ሁሉም ነገር ተጠናቋል» ሲሉ ተናግረዋል። ሌሎች መረጃዎች እንደሚጠቅሱት ከሆነ ደግሞ የኢንተር ሚላኑ አሠልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ ቡድናቸው ነገ ከጁቬንቱስ ጋር ለሚያደርገው ፍልሚያ «ዝውውሩ ሙሉ ለሙሉ ከተጠናቀቀ» ሉቃስ ፖዶልስኪን እንደሚያካትቱ ይፋ አድርገዋል።

በነገራችን ላይ ከሉቃስ ፖዶልስኪ በተጨማሪ ከዓመታት በፊት ለኢንተር ሚላን በመጫወት ድል ያስመዘገቡ ሦስት ጀርመናውያን የኳስ ዝነኞችም ይታወሳሉ። ጀርመናውያኑ ሎታር ማቲያስ፣ አንድሬ ብሬሔሚ እና አሁን የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ የሆነው የርገን ክሊንስማን። ሦስቱም የዛሬ 24 ዓመት የኢንተር ሚላን መለያን ለብሰው በመጫወት የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ UEFA ዋንጫን ለማሸነፍ የቻሉ ናቸው።

የሴኔጋል የእግር ኳስ ቡድን

የሴኔጋል የእግር ኳስ ቡድን

ያኔ በወቅቱ ሉቃስ ፖዶልስኪ ጨዋታውን በአንዳች መንገድ ተከታትሎ ሊሆን ይችል ይሆናል። ማስታወሱን ግን እንጃ። የዛሬ 24 ዓመት ግድም ሉቃስ ፖዶልስኪ የ5 ዓመት ህፃን ሳለ Jugened 07 Bergheim ለሚባል የሕፃናት ቡድን ግን ተሰልፎ ነበር። የሉቃስ ፖዶልስኪ አባት ቫልደማር ፖዶልስኪ የእግር ኳስ፣ እናቱ ክሪስቲና ፖዶልስኪ ደግሞ የእጅ ኳስ ተጨዋቾች እንደነበሩ ይታወሳል።

የሴኔጋል ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በቅርቡ ለሚጀመረው የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎች ጉዳት የደረሰበት የሳውዝ ሐምፕተኑ አማካይን ለማሰለፍ ጥሪ ማድረጉን አስታወቀ። የሳውዝ ሐምፕተን ቡድን በበኩሉ ሣዲዮ ማኔ በደረሰበት ጉዳት የተነሳ ለበርካታ ሣምንታት ከውድድር ውጪ እንደሚሆን ማስታወቁ ይታወቃል። የሴኔጋል ቡድን ግን ተጨዋቹ የደረሰበት የጡንቻ መሸማቀቅ በመሆኑ ከ23ቱ የቡድኑ ተጨዋቾች መኻከል ተመርጧል ብሏል። ከሣዲዮ በተጨማሪ ቡድኑ የዌስትሐም ዩናይትዱ አጥቂ ዲያፍራ ሳካሆንም ማካተቱን ይፋ አድርጓል። ዲያፍራም እንደ ሣዲዮ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ጉዳት እንደደረሰበት ተነግሯል። የሴኔጋል ቡድን ከኹለት ሣምንት በኋላ ማንጎሞ ውስጥ ከጋና ጋር ይገጥማል። በምድቡ አልጀሪያ እና ደቡብ አፍሪቃም እንደሚገኙ ይታወቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic