የስፖርት ጥንቅር | ስፖርት | DW | 02.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ጥንቅር

በዛሬው የስፖርት ጥንቅር በዋናነት እግር ኳስን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ክንውኖችን እንቃኛለን። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፣ የጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ፣ የስፔን ላሊጋ እና የጣሊያኑ ሴሪኣ ቅኝት ተደርጎባቸዋል። የእስያ ቱጃሮች፣ የሩስያ ከበርቴዎችና የአሜሪካን ባለፀጎች ከምንግዜውም በላይ የአውሮጳ ክለቦች ላይ አይናቸውን ጥለዋል። ዳሰሳ ይኖረናል።

ቸልሲ፥ ተፎካካሪዎቹ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ነጥብ ጥለው ሲንሸራተቱለት አርሰናልን መጣሁብህ እያለው ነው። ዝርዝሩን እንመለስበታልን። ከሁሉም ቀዳሚው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበር የሴካፋ ውድድር ነው። ኢትዮጵያ ዛንዚባርን 3 ለ1 ረትታለች፣ ኤርትራውያን ተጫዋቾች ኬንያ ውስጥ መጥፋታቸው ታውቋል።

ኬንያ ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበር የዋንጫ ውድድር ሁለት ኤርትራውያን ተጨዋቾች መጥፋታቸው ተዘገበ። ተጨዋቾቹ በምስራቅ አፍሪቃዊቷ ኬንያ ጥገኝነት ሳይጠይቁ አልቀረም ተብሏል። የኤርትራ ተጨዋቾች ከሀገር ውጪ በሚደረጉ ውድድሮች ወቅት ከቡድናቸው እየተነጠሉ ሲጠፉ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ባለፈው ዓመትም እንዲሁ 17 የኤርትራ እግር ኳስ ቡድን አባላት የቡድኑ ሐኪምን ጨምሮ ኡጋንዳ ውስጥ ጥገኝነት መጠየቃቸው ይታወሳል።

ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ አስቀድሞ ደግሞ 13 የኤርትራ ተጨዋቾች ታንዛኒያ ለውድድር በሄዱበት ሳይመለሱ የውሃ ሽታ መሆናቸው በወቅቱ ተዘግቧል። እጎአ በ2009 በደርዘን የሚቆጠሩ የኤርትራ እግር ኳስ ቡድን አባላት ኬንያ ውስጥ ድምፅ አጥፍተው መሰወራቸው ይታወቃል።

በእዚሁ የሴካፋ ውድድር ኢትዮጵያ ከትናንት በስትያ ሁለተኛ ጨዋታዋን ከዛንዚባር ጋር አከናውና 3 ለ1 አሸንፋለች። ለኢትዮጵያ በአምስተኛው፣ 37ኛው እና 86ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ያስቆጠሩት፤ ፋሲካ አስፋው፣ ሳላህዲን ባርጊቾ እና ዮናታን ከበደ ናቸው።

ከምድቡ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በ4 ነጥብና እኩል የግብ ክፍያ እኩል ደረጃ ላይ ሲገኙ ዛንዚባር በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዛንዚባር ቀደም ሲል 2 ለ1 የተሸነፈችው ደቡብ ሱዳን በባዶ ነጥብ እና 5 የግብ እዳ ከምድቡ በመጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ኤርትራ ከሚገኙበት ምድብ ሱዳን ኡጋንዳን በእኩል 3 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ቀድማ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ሩዋንዳ እና ኤርትራ በባዶ ነጥብ ተከታትለው ሩዋንዳ በአንድ የግብ ክፍያ ሶስት የግብ ክፍያ ዕዳ ያለባትን ኤርትራን ቀድማ ትገኛለች። ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ፣ ብሩንዲ እና ሶማሊያ ከሚገኙበት ምድብ ታንዛኒያ እና ዛምቢያ በእኩል 4 ነጥብ እና የግብ ክፍያ እኩል ደረጃ ላይ ሲገኙ፤ 0 ነጥብ እና 3 የግብ ክፍያ ያለባትን ሶማሊያ ብሩንዲ በ3 ነጥብና በ1 የግብ ዕዳ አስከትላ 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በቀጥታ ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ነው የምናመራው። ሊቨርፑል በሁል ሲቲ በአስደንጋጭ ሁኔታ 3 ለ 1 ተሸንፎ ነጥብ መጣሉ ማንቸስተር ሲቲ እና ቸልሲ የትናንቱን ምሽት በታላቅ ፈንጠዝያ ለማሳለፍ አስችሏቸዋል። ትናንት የደረጃ ሰንጠረዡን በሁለተኛነት ተቆናጦ ወደ ሜዳ የገባው ሊቨርፑል ለመጀመሪያ ጊዜ በሁል ሲቲ 3 ለ 1 ሲረታ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ተንሸራቶ ነበር። አፍታም አልቆየ ቸልሲ ሳውዝ ሐምተንን በተመሳሳይ 3 ለ1 ሲያሰናብት ሊቨርፑል ከደረጃ ሰንጠረዡ አሁንም ዝቅ ብሎ አራተኛ ለመሆን ተገዷል።

የደረጃ ሰንጠረዡን አርሰናል በ31 ነጥቦች ሲመራ ቸልሲ በ27 ነጥብ ይከተላል። ማንቸስተር ሲቲ ሊቨርፑልን በአንድ ነጥብ ቀድሞ በ25 ነጥብ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የማንቸስተር ሲቲው ሰርጂዮ አጉዌሮ በ10 ከመረብ ያረፉ ግቦች ቀንደኛ የፕሬሚየር ሊግ ግብ አዳኝነቱን አስመስክሯል። የሊቨርፑሎቹ ዳንኤል ስቱሪጅ እና ሉዊስ ሱዋሬዝም እያንዳንዳቸው በ9 ግቦች ዋዛ አለመሆናቸውን አሳይተዋል። የአርሰናሉ አሮን ራምሴይ፣ የማንቸስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ እና የኤቨርተኑ ሮሜሉ ሉካኩም ብዙም አልራቅንም ሲሉ ስምንት ስምንት ግቦችን አስመዝግበዋል።

ትናንት ማንቸስተር ሲቲ ስዋንሲን 3 ለ ባዶ ረትቷል። ማንቸስተር ዩናይትድ ከቶትንሐም ጋር ሁለት እኩል በመሆን ነጥብ ተጋርቷል። ቸልሲ የትናንቱን ጨዋታ በአስደንጋጭ ሁናቴ ነበር የጀመረው። ልክ ጨዋታው በተጀመረ 13ኛው ሰከንድ ላይ የሳውዝ ሐምተኑ ሮድሪጌዝ የመጀመሪያዋን ግብ ከመረብ በማሳረፍ ቸልሲዎችን ምትሃት የወረደባቸው ያህል አስደንግጧቸው ነበር። በእርግጥ ለቸልሲ ለ400ኛ ጊዜ የተሰለፈው ጆን ቴሪ እና ጋሪ ካሂል ተቀይሮ ከገባው ዴምባባ በፊት የማረጋጊያዋን ግብ በማስቆጠር ቡድናቸውን ከድንጋጤ ለመታደግ ችለዋል።

የቸልሲው አሰልጣን ጆዜ ሞሪንሆ «13ኛ ሰከንድ ላይ ግብ ሲያስቆጥሩብህ ምን ታደርጋለህ?» ሲሉ በወቅቱ መደንገጣቸውን ለጋዜጠኞች ገልፀዋል። አያይዘውም «ተረጋጋን ከእዚያም በሁለተኛው አጋማሽ እንቅስቃሴያችን በእውነቱ በጣም ጥሩ ነበር። በመጠኑ ምርጥ የሆነ ጨዋታ እና ወኔያችንን አሳይተናል።» ሲሉ በውጤቱ መኩራታቸውን ገልፀዋል።

ሊቨርፑልን 3 ለ 1, ጉድ ያደረገው ሁል ሲቲ የእግር ኳስ ቡድን ባለቤት ግብፃዊው ባለሀብት አሰም አላም ቡድኑን ከ«ሁል ሲቲ» ነት ወደ «ሁል ታይገርስ» እቀይራለው ብለው መነሳታቸው የቡድኑ ደጋፊዎችን አስቆጥቷል። ደጋፊዎች በትናንቱ ግጥሚያ የስም ለውጡን በመቃወም «እስከዕለተ ሞታችን ድረስ ምንጊዜም ሲቲ» ሲሉ በስታዲየሙ ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል። የሁል ሲቲ ባለቤት ግብፃዊው ባለፀጋ በበኩላቸው «ጥሩ ኳስ ማየት ለሚሹት ብዙኃኑ ደጋፊዎች ቡድኑን ትተው እስከሄዱ ድረስ በፈለጉበት ቅፅበት ሊሞቱ ይችላሉ።» ሲሉ ለስም ለውጡ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳውቀዋል።

እንደ ግብፃዊው ቱጃር ሁሉ በርካታ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች በአውሮጳ የእግር ኳስ ቡድኖች ላይ አይኖቻቸውን መጣል ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ሩስያዊው ከበርቴ ሮማን አብራሞቪች ኃያሉን ቸልሲ በባለቤትነት ሲያስተዳድሩ 10 ዓመታትን አስቆጥረዋል። የእስያ ቱጃሮች፣ የሩሲያ ከበርቴዎች፣ የአረብ ሼኪዎች እና የአሜሪካን ባለፀጎች ከምን ግዜውም በላይ የአውሮጳ ክለቦችን በቋመጡ አይኖቻቸው መማተራቸውን ቀጥለዋል።

ከቸልሲ አንስቶ በቅርቡ በኢንዶኔዢያው የመገናኛ ብዙኃን ባለፀጋ ኤሪክ ቶይር የተገዛው የጣሊያኑ ግዙፍ የእግር ኳስ ቡድን ኢንተር ሚላንን ጨምሮ የአውሮጳ ቡድኖች የውጭ ሀገር ከበርቴዎች የአይን ማረፊያ ከሆኑ ሰነባብተዋል። በእንግሊዝ ብቻ እጅግ በናጠጡ ከበርቴዎች ከሚተዳደሩ 20 የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል 11ዱ በውጭ ሀገር ቱጃሮች ቁጥጥር ስር የሚገኙ ናቸው። ባለሀብቱ ከእንግሊዝ ቡድኖችም ባሻገር ቅኝታቸውን ወደ አውሮጳ የእግር ኳስ ቡድኖች እያደረጉ ነው። ያም በመሆኑ የፈረንሳዩ ፓሪስ ሳንጀርሜይን ቡድን በቃታር የስፖርት መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ቁጥጥር ስር ከዋለ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሮዋል። የሩሲያው ቢሊየነር ዲሚትሪ ሪቦሎቬቭ ሞናኮን በተመሳሳይ ዓመት ነበር የገዙት።

ሁናቴው ወደ ጀርመን ሲጠጋ ግን ለየት ያለ ቅርፅ ይይዛል። አንድ የውጭ ባለሀብት ጀርመን ውስጥ የሚገኙ የእግር ኳስ ቡድኖች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ቢፈልግ ከቡድኖቹ 49 ከመቶ የላቀ ድርሻ እንዳይኖረው የሚስገድድ ሕግ በመኖሩ ብዙም መጓዝ አይችልም። በእዚህም አለ በእዚያ የውጭ ሀገር ባለፀጎች የአውሮጳ የእግር ኳስ ቡድኖች ላይ ገንዘባቸውን በማፍሰስ ትርፍ ማጋበሳቸውን ተያይዘውታል።

በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ባየር ሙንሽን አሁም ኃያልነቱን በማስመስከር ላይ ይገኛል። የደረጃ ሰንጠረዡን በ38 ነጥቦች የሚመራው ሙንሽን ከትናንት በስትያ አይንትራህት ብራውንሽቫይግን 2 ለምንም በሆነ ውጤት አሸንፏል። በ4 ነጥብ ዝቅ ብሎ የሚከተለው ባየር ሌቨርኩሰን በበኩሉ ኤፍ ሲ ኑረንበርግን 3 ለባዶ አሰናብቷል። ሌላኛው የቡንደስ ሊጋ ዋነኛ ተፎካካሪ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከትናንት በስተያ ኤፍ ኤስ ቫው ማይንትስን 3 ለ 1 ቢረታም 31 ነጥብ ይዞ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት ሀኖቨር 96 አይንትራህት ፍራንክፉርትን 2 ለዜሮ አሸንፏል። ቦሩስያ ሞንሽንግላድባህ በበኩሉ ኤስ ሲ ፍራይቡርግን 1 ለዜሮ በማሸነፍ ነጥብ ለመያዝ ችሏል።

በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ የቦሩሲያ ዶርትሙንዱ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ 11 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ኮከብ ግብ አግቢነቱን አስመስክሯል። የባየር ሌቨርኩሰኑ ሽቴፋን ኪስሊንግ 9 ግቦችን፣ እንዲሁም የባየር ሙንሽኑ ማሪዮ ማንቹኪክ 8 ግቦችን በማስቆጠር በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የቦሩሲያ ዶርትሙንዱ ፒየር ኤመሪክ አውባሜያንግ እና የሽቱትጋርቱ ቬዳድ ኢቢሴቪችም እንዲሁ በ8 ግቦች ከማንቹኪክ እኩል ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና የመጀመሪያውን ሽንፈት ቀምሷል። ትናንት በአትሌቲክ ነበር 1 ለባዶ የተረታው። አትሌቲክ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ በደረጃ ሰንጠረዡ ባርሴሎና ከአትሌቲኮ ማድሪድ እኩል 40 ነጥብ በመያዝ እኩል ደረጃ ላይ ይገኛል። ሪያል ማድሪድ በ3 ነጥብ ዝቅ ብሎ የግብ ዕዳዎችን ተሸክሟል።

በትናንቱ ግጥሚያ ሴቪላ ግራንዳን 2 ለ1፣ ቫሌንሺያ ኦሳሱናን 3 ለምንም አሸንፈዋል። ሪያል ቤቲስ እና ራዮ ቫሌካኖ 2 እኩል ወጥተዋል። ከትናንት በስተያ ሪያል ማድሪድ ሪኢል ቫላዶይድን 4 ለባዶ የረታበት ግጥሚያ በላሊጋው ኃያል ሆኖ ተመዝግቧል።

በላሊጋው የሪያል ማድሪዱ ጎል አዳኝ ክርስቲያኖ ሮናልዶ 17 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ቀዳሚ ስፍራ ይዟል። የአሌቲኮ ማድሪዱ ዲዬጎ ኮስታ በ15 ግቦች እንዲሁም የሪያል ሶሴዳዱ አንቶኒዮ ግሪስማን በ9 ግቦች ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ግብ አዳኝነታቸውን አስመስክረዋል።

በጣሊያን ሴሪኣ ጁቬንቱስ በ37 ነጥብ መሪነቱን እንደያዘ ሲሆን፤ ሮማ በ34 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ ይከተለዋል። ኢንተር ሚላን በ27 ነጥቦች ሶስተኛ፣ ፍሎረንቲና በ24 ነጥቦች አራተኛ ደረጃን ይዘው በመፎካከር ላይ ናቸው።ከእግር ኳስ ሳምንታዊ ግጥሚያዎች ስንወጣ በቴኒሱ ዓለም በልዩ ሁናቴ የምትታየው የሽቴፌ ግራፍ አባት በ75 ዓመታቸው ማረፋቸው ተዘግቧል። በነቀርሳ በሽታ ትናንት ያረፉት የሽቴፊ ግራፍ አባት ፔተር ግራፍ እጎአ ከ1987 እስከ 1991 ድረስ የሽቴፊ አሰልጣኝ የነበሩ ሲሆን፤ በጀርመን የቴኒስ ጨዋታ መምህርነት ታላቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ባለሙያ ናቸው።

ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ ከታች ያለውን የድምፅ ማጫወቻ ይጫኑ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic