የስፖርት ጥንቅር-ጥቅምት 22፤ 2008 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 02.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ጥንቅር-ጥቅምት 22፤ 2008 ዓ.ም.

ኬንያውያን በነገሱበት የኒውዮርክ አመታዊ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያኑ አሰለፈች መርጊያ እና ትዕግስት ቱፋ በእንስቶቹ ጎራ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል። በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ በሳምንቱ መጨረሻ በቼልሲው ጆሴ ሞሪንሆ ላይ ድል ተቀዳጅተዋል። ቤከን ባወር ሌላ ቅሌት አለባቸው እየተባለ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:06
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:06 ደቂቃ

የስፖርት ጥንቅር-ጥቅምት 22፤ 2008 ዓ.ም.

ትናንት በተካሄደው የኒውዮርክ ማራቶን ኢትዮጵያውያን እንስቶች ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ጨርሰዋል። ኬኒያዊቷ ሜሪ ኪታኒ ባሸነፈችበት የ42 ኪ.ሜ. የሩጫ ውድድር አሰለፈች መርጊያ በ2:25:32 ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ትዕግስት ቱፋ ደግሞ በ2:25:50 ሶስተኛ ደረጃን አግኝታለች። በዚሁ በኒው ዮርክ አመታዊ የማራቶን ውድድር ኬንያውያን ወንዶች ነግሰውበት ታይቷል። በውድድሩ ስታንሌ ቢወት በ2:10:34 በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ ሌላው የአገሩ ልጅ ጌዎፌሪ ካምዎረር ከ14 ሰከንዶች በኋላ ተከትሎታል። ኢትዮጵያውያኑ ሌሊሳ ደሲሳ ሶስተኛ የማነ ጸጋዬ ደግሞ አምስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።

ሳምንታዊ የአውሮጳ የሊግ ውድድሮች

በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱ የአውሮጳ የሊግ ውድድሮች በቀዳሚነት ሽንፈትና ወቀሳ የበዛባቸው ፖርቹጋላዊው የቼልሲ አሰልጣኝ በቀዳሚነት ይገኛሉ። ሰውየው እሰጥ አገባ ይወዳሉ። አሰልጣኞች ይተቻሉ።ዳኞችን ይሸረድዳሉ። ለተጫዋቾቻቸው ሐኪምም አልተመለሱም። ዘንድሮ ግን ሁሉም ነገር በሳቸው ላይ የበረታ ይመስላል።

በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቅዳሜ ለት የለንደኑ ቼልሲ በሜዳው ሊቨርፑልን ሲገጥም ሞሪንሆ ካደረጓቸው 10 ጨዋታዎች በአምስቱ ተሸንፈው ሁለቱን በአቻ አጠናቀው በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ እየተንደፋደፉ ቢሆንም ብዙዎች ተስፋ ነበራቸው። የቀድሞው ቦሩሺያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ለእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እንግዳ ናቸው። የመጀመሪያ ጨዋታቸውም የተጠናቀቀው በአቻ ነበር። በእለተ ቅዳሜው የስታምፎርድ ብሪጅ ጨዋታ በአራተኛው ደቂቃ ራሚሬዝ ባስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ መሪነቱን የጨበጡት ቼልሲዎች ምን አልባት ከተከታታይ ሽንፈታቸው ሊያገግሙ ነው ተብሎ ቢጠበቅም አልተሳካም። ብራዚላዊው ፊሊፕ ኮንቲኒሆ በ47ኛና 74ኛ ደቂቃ እንዲሁም ከተቀያሪ ወንበር የተነሳው ክርቲያን ቤንቴኬ በ83ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ለጆሴ ሞሪንሆ የሳምንቱን መጨረሻ የጭንቅ አድርገውታል። መያዣ መጨበጫው የጠፋቸው ፖርቹጋላዊም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አምስት ጊዜ «የምለው የለኝም።» ሲሉ ተደምጠዋል። ተጨዋቾቻቸውም ወቅታዊው ሁኔታ ለጆሴ ሞሪንሆ ጥሩ አለመሆኑን አልሸሸጉም።

የስፖርት ተንታኞች በበኩላቸው ቼልሲ ያለፈው አመት አሸናፊነቱን መድገም ቀርቶ ከአንድ እስከ አራተኛ ባለው ደረጃ ማጠናቀቅ እንደማይሆንለት ሲከራከሩ ተደምጧል። ጆሴ ሞሪንሆ ከቼልሲ የሚባረሩበትን ጊዜና ሁኔታ እያጣቀሱ የጻፉም አልታጡም።

እንግዳው የርገን ክሎፕ በአንጻሩ የሊቨርፑል ደጋፊዎች የሚጠብቁባቸውን ለማሳካት የነደፉት እቅድ አዋጪ ይመስላል። በእንግድነት በተገኙበት ስታንፎርድ ብሪጅ ቀድሞ ጎል ቢቆጠርባቸውም በአጭር ቅብብልና የተቀናጀ የቡድን ስራ ማሸነፋቸውን ተናግረዋል።

በሌሎች የሳምንቱ ጨዋታዎች በደረጃ ሰንጠረዡ አናት የተቀመጠው ማንችስተር ሲቲ ኖርዊች ሲቲን 2 ለ 1 አሸንፏል። ኒኮላስ ኦታሜንዲ በጨዋታ የአይቮሪኮስቱ ኮከብ ያያ ቱሬ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠሯቸው ጎሎች ሲቲን ለአሸናፊነት አብቅተውታል። የማንችስተር ሲቲው ጎል ጠባቂ ጆ ሃርት የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ካሜሮን ጄሮሜ ያስቆጠራት ጎል ለኖርዊች ሲቲ ማስተዛዘኛ ሆና ተመዝግባለች።

አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር በአርሰናል የስራ ዘመናቸው 2,000ኛ ጎላቸውን ተመልክተዋል። የጎሉ ባለቤት ደግሞ በውድድሩ መጀመሪያ ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርበት የነበረው የክለቡ አጥቂ ኦሊቨር ጅሩ ነበር። ተከላካዩ ሎረን ኮሸንሊ ሁለተኛውን የ23 አመቱ አጥቂ ጆኤል ካምቤል ደግሞ ሶስተኛውን ጎል አስቆጥረው በዌልስ የስዋንሲን ተስፋ አጨልመዋል። በጨዋታው ጀርመናዊው ሜሱት ኦዚል ድንቅ ሆኖ አምሽቷል። በውጤቱ ደስተኛ ነኝ ያሉት አርሰን ቬንገር ግን ከባየርን ሙኒክ ጋር የሚያደርጉት የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ያሳሰባቸው ይመስላል። ከምድባቸው በሁለት ጨዋታ ተሸንፈው አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ቬንገር በሙሉ ጨዋታው ሲከላከሉ ማምሸት እንደማይሆንላቸው ተናግረዋል። «ከጨዋታው ነጥብ ይዤ መውጣት እችላለሁ።» ያሉት ፈረንሳዊው የአርሰናል አሰልጣኝ በባየር ሙኒክ የማጥቃት ብቃት በእለተ ረቡዕ በሚደረገው ጨዋታ ለ90 ደቂቃ ሲከላከሉ ማምሸት አስቸጋሪ መሆኑን አልሸሸጉም።

ቅዳሜ ዕለት ክሪስታል ፓላስን የገጠመው ማንችስተር ዩናይትድ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። በሁሉም ውድድሮች ሶስተኛ አቻውን ያስመዘገበው የልዊስ ቫንጋል ማንችስተር ዩናይትድ በጨዋታው በተቀናቃኙ ብልጫ ተወስዶበታል። ተጨዋቾቻቸው ጨዋታውን መቆጣጠር እንደተሳናቸው የተናገሩት አሰልጣኙ ልዊስ ቫንጋልም ቢሆኑ ክሪስታል ፓላስ የተሻለ ቡድን እንደነበር ተናግረዋል። ነገ በቻምፒየንስ ሊግ የሩሲያውን ሲኤስኬ ሞስኮ የሚገጥመው ቡድናቸው የገጠመው የግብ ድርቅ እንዳሳሰባቸው አልሸሸጉም።

በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ማንችስተር ሲቲ እና አርሰናል በተመሳሳይ 25 ነጥቦች በሰንጠረዡ አናት ጉብ ብለዋል። በግብ ልዩነት ሲቲ ቀዳሚነቱን ይዟል። እስካሁን በአንድ ጨዋታ ብቻ የተሸነፈው ሌስተር ሲቲ ሶስተኛ ማንችስተር ዩናይትድ አራተኛ፤ ዌስት ሐም ዩናይትድ አምስተኛ ላይ ናቸው። ቼልሲና ጆሴ ሞሪንሆ ከመሪዎቹ በአስራ አራት ነጥብ ርቀው ስድስት የጎል እዳ ታቅፈው 15ኛ ደረጃን ይዘዋል።

በስፔን ላሊጋ ላስ ፓልማስን የገጠመው የዋና ከተማዋ ሪያል ማድሪድ 3 ለ 1 አሸንፏል። በጨዋታው ኢስኮ፤ክርቲያኖ ሮናልዶና ጄሴ ኳስን ከመረብ ማገናኘት ችለዋል። ሄርናን ለላስ ፓልማስ የማስተዛዘኛ ግብ አስቆጥሯል። ሎስ ብላንኮስ በቻምፒዮንስ ሊግ ከፈረንሳዩ ሀብታም ክለብ ፓሪስ ሴይንት ዠርሜን ይጫወታሉ።

ሊዮኔል ሜሲን በጉዳት ያጣው ባርሴሎና በኔይማርና ልዊስ ሱዓሬዝ ጎሎች ጌታፌን ሁለት ለምንም አሸንፏል። በጨዋታው ያልተጠበቀው የመሀል ሜዳ ተጫዋች ሰርጊ ሮቤርቶ ኮከብ ሆኖ አምሽቷል። ሁለቱንም የባርሴሎና ጎሎች አመቻችቶ ያቀበለው የ23 አመቱ ሮቤርቶ ከቀድሞው የሪያል ማድሪድ አማካኝ ተጫዋጭ ዚነዲን ዚዳን ጋር ያነጻጸሩትም አልጠፉም።

ላሊጋውን 10 ተጫውቶ ሰባቱን በአሸናፊነት የተወጣው ሪያል ማድሪድ በ24 ነጥቦች በቀዳሚነት ይመራል። ባርሴሎና በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሴልታ ቪጎ፤አትሌቲኮ ማድሪድና ቪያሪያል ከሶስት እስከ አምስት ያለውን ደረጃ በቅደም ተከተል ይዘዋል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ የዚህ አመት መርኃ-ግብር ሁሉንም ጨዋታዎች በአሸናፊነት የተወጣው ባየር ሙኒክ ወደ ፍራንክ ፈርት አቅንቶ አቻ ተለያይቷል። በኮሜርስባንክ አሬና ኢንትራክት ፍራንክፈርትን የገጠመው ባየር ሙኒክ በሙሉ ጨዋታው የበላይ ሆኖ መቆየት ቢችልም የፈጠራቸው የግብ እድሎች ግን ውስን ነበሩ። በአስር ጨዋታዎች 13 ጎሎች ያስቆጠረው ሮበርት ሎዋንዶውስኪም ይሁን የቡድን ባልደረቦቹ በፍራንክፈርት ጎል ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ቬርደር ብሬመን በቬሰርስታድዮን ቦሩሺያ ዶርትሙንድን አስተናግዶ 3ለ1 ተሸንፏል። ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው የቦሩሺያ ዶርትሙንዱ ማርኮ ሬውስ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ታይቷል። ሽቱትጋርት ዳርምሽታትን ሁለት ለምንም አሸንፏል። ቮልፍስበርግ ባየር ሊቨርኩሰንን 2ለ1 ሲያሸንፍ ሻልከ ከኢንጎልሽታት አቻ ተለያይቷል። ቡንደስሊጋውን ባየር ሙኒክ በ31 ነጥቦችና 29 ንጹህ የጎል ክፍያ በአንደኝነት ተቆጣጥሮታል። ቦሩሺያ ዶርትሙንድ በ26 ነጥብ ሁለተኛ ቮልፍስበርግ በ21 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በጣልያን ሴሪ አ ፊዮሬንቲና ትናንት ባለ ድል ሆኗል። ፍሮሲኖኔን በሜዳው ያስተናገደው ፊዮሬንቲና በጎል ተንበሽብሾ 4ለ1 አሸንፏል። በሳምንቱ ትልቅ ጨዋታ ኢንተር ሚላን እና ሮማ ተገናኝተው ኢንተር 1ለምንም አሸንፏል። ቺሊያዊው ጋሪ ሞዴል በሮማ መረብ ላይ ያሳረፋት አስደናቂ ኳስ የሮቤርቶ ማንሲኒውን ኢንተር ሚላን በሜዳው ድል አጎናጽፋለች። ጄኖዋ ከናፖሊ ያደረጉት ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቋል። ኤሲ ሚላን ላዚዮን 3ለ1 ሲያሸንፍ ጁቬንቱስ በቶሪኖ ላይ የ2ለ1 ድል ተቀዳጅቷል። በሴሪ አ የደረጃ ሰንጠረዥ ፊዮሬንቲናና ኢንተር ሚላን በእኩል 24 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። ሮማ በ23 ነጥቦች ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ናፖሊ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

አዲስ ቅሌት -ፍራንዝ ቤንከን ባወር

በጀርመንና ባየርሙኒክ የእግር ኳስ ታሪክ ዝና ያተረፈው ፍራንዝ ቤንከን ባወር ለማልታ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ250,000ዶላር ጉቦ አከፋፈል ሂደትን በማመቻቸት አዲስ ወቀሳ ቀርቦበታል። ቤከን ባወር ጀርመን እንደ ጎርጎሮሳዊው በ2006 ላዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ውድድር የማልታ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን የድጋፍ ድምጽ ለማግኘት ከባየር ሙኒክ እግር ኳስ ክለብ ጋርም የወዳጅነት ጨዋታ በማመቻቸቱ ሂደት ውስጥም እጁ አለበት ተብሏል። የእንግሊዙ ሜይል ጋዜጣ ይፋ ያደረገው ጽሁፍ ቤከን ባወር የዓለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ የስራ አስፈጻሚ አባላትን ድምጽ ለማግኘት ህገ-ወጥ ሂደት ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል። ጋዜጣው በጎርጎሮሳዊው ሰኔ 2000 ዓ.ም. የማልታ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ከባየር ሙኒክ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያደርግና የአገሪቱ እግርኳስ ፌዴሬሽንም 250,000 ዶላር ክፍያ እንዲፈጸምለት የተደረሰ ስምምነት አግኝቻለሁ ብሏል። ጋዜጣው ይፋ ያደረገውና በቀድሞው የማልታ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ሚስፉድ ከወቅቱ የባየር ሙኒክ ፕሬዝዳንትና የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ የበላይ ፍራንዝ ቤከን ባወር ጋር የተፈራረሙት ስምምነት በሚስጥር ሊያዝ የታቀደ ነበር። ቤከን ባወር ከዚህ ቀደም የጀርመኑ ዴር ሽፒግል የተሰኘ ጋዜጣ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነትን ለማግኘት ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ሆኗል። እጁም አለበት ሲል መወንጀሉ አይዘነጋም። ቤከንባወር ውንጀላውን መሰረተ ቢስ ሲል ያጣጥል እንጂ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ የስነ-ምግባር ኮሜቴ ምርመራ ላይ ይገኛል። ጀርመን የ2006ቱን የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት የተቀዳጀችው በእንግሊዝ ላይ የበላይነት አግኝታ ነበር።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic