የስፖርት ጥንቅር፦ ጥር 4 ቀን፣ 2007 | ስፖርት | DW | 13.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የስፖርት ጥንቅር፦ ጥር 4 ቀን፣ 2007

አትሌቲክስን፣ እግር ኳስን እና የዝውውር ዜናዎችን የሚመለከቱ ዘገባዎች ቅኝት ተደርጎባቸዋል። የፊታችን ቅዳሜ ስለሚጀምረው የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎች እና ፕሬሚየር ሊግን ጨምሮ በአውሮጳ ስለተከናወኑ ግጥሚያዎች ዳሠሣ ይኖረናል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በሣውዝሐምፕተን 1 ለባዶ በመረታቱ በደረጃ ሠንጠረዡ አራተኛ ለመሆን ተገዷል። የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ሉዊስ ቫን ጋል ቡድናቸውን በፕሬሚየር ሊጉ በአስተማማኝ ሁናቴ ባለድል ለማድረግ ምናልባት ሦስት ዓመታት ያስፈልገኛል ብለው ነበር። አንዳንድ ተንታኞች የትናንትናውን ሽንፈት በማጣቀስ አሠልጣኝ ሉዊስ ቫን ጋል ቡድናቸውን አስተማማኝ ባለድል ለማድረግ ምናልባትም ረዥም ጊዜ ሳያስረልጋቸው አይቀርም ብለዋል።

ሉዊስ ቫን ጋል ማንቸስተር ዩናይትድን ለማሠልጠን ወደ እንግሊዝ ከመጡ ገና ግማሽ ዓመታቸው ነው። አሠልጣኙ ለቡድናቸው ጠንካራ ተጨዋቾችን ለማምጣት በሚል ከ226ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጋቸው ይታወቃል። ሆኖም በማንቸስተር ዩናይትድ ታሪክ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንት በሜዳቸው ኦልትራፎርድ እና ደጋፊያቸው ፊት ግብ ማግባት ተስኗቸው ውጤት ለመጣል ተገደዋል። ቡድናቸው ማንቸስተር ዩናይትድ በ37 ነጥብም ተወስኗል።

ሦስቱ የዓለም ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋቾች

ሦስቱ የዓለም ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋቾች

ትናንት በተከናወነ የፕሬሚየር ሊግ ሌላ ጨዋታ የማንቸስተር ዩናይትድ ተፎካካሪው አርሰናል ግን ቀንቶታል። ስቶክ ሲቲን ገጥሞ 3 ለ ምንም ሸኝቷል። አርሰናል በትናንቱ ድል ያገኘው 3 ነጥብ ተደምሮለት አምስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። አርሰናል በሰበሰበው 36 ነጥብ በአራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ የሚለየው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው። ሳውዝ ሐምተን 39 ነጥብ አለው፤ ደረጃው ሦስተኛ ነው። ማንቸስተር ሲቲ ከሳውዝ ሐምተን ፊት ኹለተኛ ሆኖ ይገኛል። 47 ነጥብ አለው። ቸልሲ 49 ነጥብ ይዞ ፕሪሚየር ሊጉን አሁንም በአንደኝነት እየመራ ይገኛል። ከትናንት በስትያ ሰንደርላንድን 1 ለዜሮ ማሸነፍ የቻለው ሊቨርፑል ከአርሰናል በሦስት ደረጃዎች ርቀት እና በ4 ነጥብ ልዩነት 32 ነጥብ ይዞ 8ኛ ደረጃ ላይ መሽጓል።

በስፔን ላሊጋ ዋነኞቹ ተፎካካሪ ቡድኖች ትናንት ባደረጉት ግጥሚያ ባርሴሎና መሪው ሪያል ማድሪድን 3 ለ1 በሆነ አስተማማኝ የግብ ልዩነት ለማሸነፍ ችሏል። ሪያል ሶሴዳድ ከግራናዳ ጋር አንድ እኩል ወጥቷል። ሴቪላ አልሜሪያን 2 ለምንም አሸንፏል። በደረጃ ሠንጠረዡ ሪያል ማድሪድ 42 ነጥብ ይዞ መሪነቱን ተቆናጧል። ኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባርሴሎና ከሪያል ማድሪድ በአንድ ነጥብ ነው ልዩነቱ። ሦስተኛ ደረጃ የያዘው አትሌቲኮ ማድሪድ 38 ነጥቦች አሉት።

ግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖየር

ግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖየር

የባርሴሎናው የኳስ ጥበበኛ ሊዮኔል ሜሲ ባርሴሎናን ትቶ ወደሌላ ቡድን ሊያቀና ነው የሚባለውን ጭምጭምታ ተጨዋቹ አስተባበለ። ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎናው አሠልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ጋር ባጋጠመው አለመግባባት የተነሳ ቡድኑን ትቶ ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ያቀናል ነበር የተባለው። ሆኖም አርጀንቲኒያዊው አጥቂ የተባለው ነገር ሁሉ ውሸት መሆኑን ከባርሴሎና ቴሌቪዥን ጋር ትናንት ባደረገው ቃለምልልስ አስታውቋል። ሊዮኔል ሜሲ እንዲህ ሲል ነበር ያስተባበለው።

«ቡድኑ ውስጥ ለመቆየት ይኼ ያስፈልገናል ያልኩት ተጨማሪ ነገር የለም፤ ምክንያቱም መሄድ አልፈልግም። »

ባርሴሎና ትናንት ሪያል ማድሪድን 3 ለ 1 ካሸነፈ በኋላ በተደረገለት ቃለመጠይቅ በዕለቱ ኮከብ የነበረው ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ የሚከተለውንም አክሎ ተናግሯል።

«አባቱ ከቸልሲ እና ማንቸስተር ሲቲ ጋር እየተነጋገረለት ነው የሚባል ነገርም ሰምቻለሁ። ግን ይኼ ውሸት ነው።»

የ27 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ የባርሴሎና አሠልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ በሚተገብሩት የአጨዋወት ስልት እና ስልጠና ደስተኛ አለመሆኑ እየተነገረ ነው።

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቡድኖች የሚሰለፉ አፍሪቃውያን ተጨዋቾች ለአፍሪቃ ዋንጫ ወደየሀገራቸው ማቅናታቸው ቡድኖቹ ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ተጠቅሷል። የጀርመን ቡንደስ ሊጋ 7 ዝነኛ ተጨዋቾች ሀገራቸውን ወክለው ወደ አፍሪቃ ማቅናታቸው ታውቋል። የተጨዋቾቹ ወደ እየ ሀገራቸው መሄድ በቡድኖቹ ላይ ችግር መፍጠሩም ተጠቅሷል። በምዕራብ አፍሪቃ የተዛመተው የኢቦላ ተሐዋሲ ዋነኛው የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።

የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሠልጣኝ ዬርገን ክሎፕን ኹለት ነገሮች ሳያሰጓቸው አልቀሩም። በኢኳቶሪያል ጊኒ የፊታችን ቅዳሜ ለሚጀመረው የአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎች ለመሰለፍ በማቅናቱ ወሳኝ አጥቂያቸውን አጥተዋል። የሚያሠለጥኑት ቡድናቸው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ወሳኝ የመልስ ጨዋታውን ያለ ጋቦኒያዊው ፒየር ኤመሪክ አውባሜያንግ ለማድረግ መገደዱ አይቀርም። በቡንደስ ሊጋው የሚዋዥቀው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከወራጅ ቃጣና ለመውጣት የሚያደርገው ቀጣይ ፍልሚያ ያለ ጋቦኑ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ የ25 ዓመቱ ፒየር ከባድ እንደሚሆንበት ተነግሯል።

ሊዮኔል ሜሲ ከፊት

ሊዮኔል ሜሲ ከፊት

ከጀርመን ቡንደስ ሊጋ ለአፍሪቃ ዋንጫ ሀገራቸውን ወክለው የሚሰለፉት ቀሪዎቹ ስድስት ተጨዋቾች የሚከተሉት ናቸው። የሔርታ ቤርሊኑ ሳሎሞን ካሉ የአይቮሪኮስት መለያን ለብሶ ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል። የቬርደር ብሬመኑ ቼድሪክ ማኪዳ የኮንጎ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ነው። ሀገሩ ኮንጎ የፊታችን እሁድ ዛምቢያን ትገጥማለች። የአውስቡርገሩ አብዱል ራህማን ባባ ለጋና ቡድን ተሰልፎ ብቃቱን ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል። ጋና በአፍሪቃ ዋንጫ የመጀመሪያ ግጥሚያዋን የምታከናውነው ከአልጄሪያ ጋር ሲሆን፤ ለዓርብ ሣምንት ሞንጎሞ ስታዲየም ውስጥ ቀጠሮ ተይዞላታል።የሐኖቨሩ ሣሊፍ ሳኔን ልክ የዛሬ ሣምንት ከሴኔጋሎች ጋር ሞንጎሞ ስታዲየም እንመለከተው ይሆናል። የሞይንሽን ግላድባሑ ኢብራሒም ትራኦሬ ሀገሩ ጊኒ የነገ ሳምንት ከአይቮሪኮስት ቡድን ጋር ለምታደርገው ጨዋታ ማላቦ ስታዲየም ውስጥ ይሰለፋል ተብሏል።የሻልካው ኤሪክ ማክሲም ቾፖ ሞቲንግ በተመሳሳይ ቀን በተመሳሳይ ሜዳ ግን ከሠዓታት በኋላ ቡድኑ ካሜሩን ከማሊ ጋር ለሚያደርገው ከባድ ፍልሚያ እንደሚሰለፍ ተገልጧል።

ከትናንት በስትያ እዚህ ጀርመን ሀገር በመኪና አደጋ ሕይወቱ ያለፈችው የዎልፍስቡርግ አማካይ ተጨዋች ጁኒየር ማላንዳ በወቅቱ የአደጋ መከላከያ የደኅንነት ቀበቶ አለማሰሩን ፖሊስ ይፋ አድርጓል። ጁኒየር ማላንዳ እጅግ በፍጥነት ከምትሽከረከረው መኪና ተስፈንጥሮ በመውጣት ነው ለሞት የተዳረገው። በአማካይ እና አጥቂ ቦታ የሚጫወተው የባየር ሙይንሽኑ ፍራንክ ሪቤሪ ሐዘኑን በዚህ መልኩ ገልጧል።

«እኔ ስለዛ ለመናገር ይከብደኛል። ሕይወት በቃ እንዲህ ናት። በቅፅበት ምን እንደሚከሰት ማወቅ አትችልም። ሁላችንም ልባችን ከእሱ እና ከቤተሰቡ ጋር ነው።»

የብሪስባኑ የሜዳ ቴኒስ ፍፃሜ ባለድል ሩስያዊቷ ማሪያ ሻራፖቫ የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሴሬና ዊሊያምስ ላይ በነጥብ እንደደረሰችባት ተገለጠ። የሴቶች ቴኒስ ማኅበር ዛሬ ይፋ ባደረገው ዘገባ መሠረት ማሪያ በሴሬና የምትበለጠው እጅግ በጠበበ የነጥብ ልዩነት ነው። በዩናይትድ ስቴትሱ ሆፕማን ዋንጫ ድል የራቃት ሴሬና ዊሊያምስ በሴቶች ቴኒስ ማኅበር ስሌት 8,016 ነጥቦችን ይዛለች። በኹለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ማሪያ ሻራፖቫ በበኩሏ 7,335 ነጥቦችን ሰብስባለች። ሩማኒያዊቷ ሲሞና ሐሌፕ በ6,571 ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic