የስፖርት ዜናዎች | ስፖርት | DW | 04.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የስፖርት ዜናዎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከአንጎላ አቻው ጋር ትናንት ሉዋንዳ ውስጥ ተጋጥሞ 1 ለባዶ ተሸንፏል። ማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ለዓለም የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ሚያሚ ውስጥ ለዋንጫ ይገናኛሉ። በሜዳ ቴኒስ ጥቁር አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስን በድል ጎዳና የሚያቆማት አልተገኘም። ጀርመናዊቷ ተፎካካሪዋን ከኋላ ተነስታ ድል ነስታለች።

ለዓለም የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ሁለቱ የእንግሊዝ ኃያላን የእግር ኳስ ቡድኖች፤ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ሚያሚ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሠዓታት በኋላ ይገናኛሉ። አሸናፊው 1 ሚሊዮን ዶላር ጭኖ ወደ እንግሊዝ ይገሰግሳል። የማንቸስተሮች ጉዞ ግን በጭንቅ የተሞላ ነው። አሠልጣኙ ከቡድኑ የሚያሰናብቷቸውን ተጨዋቾች ይፋ ለማድረግ ጥቂት ቀናት ብቻ ይቀራሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ የፖርቹጋሉ ተወላጅ ማሪያኖ ባሬቶ የኢትዮጵያን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ይዘው ወደ ሉዋንዳ በማቅናት ትናንት በአንጎላ ቡድን 1 ለባዶ ተሸንፈዋል። ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከትናንት በስትያ የመልስ ጨዋታውን አከናውኗል። ሴሬና ዊሊያምስ ዳግም ብቃቷን አስመስክራለች።

የማንቸስተር ዩናይትድ ቡድን ከወራት በፊት

የማንቸስተር ዩናይትድ ቡድን ከወራት በፊት

ማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ዛሬ ማምሻውን ሚያሚ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለዓለም የአሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ ፍልሚያ ይገናኛሉ። የማንቸስተር ዩናይትድን ቡድን ማሰልጠን ከጀመሩ ገና አንድ ወር ላልሞላቸው ሆላንዳዊው አሠልጣኝ ሉዊስ ቫን ጋል በፕሬሚየር ሊጉ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ ሰባተኛ ሆኖ የጨረሰው ቡድናቸው የዛሬውን ጨዋታ ቢያሸንፍ ድንቅ አጀማመር ይሆንላቸዋል። ፕሬሚየር ሊጉን በሁለተኛነት ያጠናቀቁት ሊቨርፑሎች ግን እንዲህ በዋዛ እጅ የሚሰጡ አይመስሉም።

የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋቾች ኦልድትራፎርድ ውስጥ የመቆየት ዕድላቸውን ከአሜሪካ ጉዞ መልስ በእዚህ ሣምንት ውስጥ እንደሚያውቁ ተገለጧል። የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሉዊስ ቫን ጋል በቡድኑ ውስጥ ወደፊት ማን እንደሚቆይ እና እንደሚሰናበት በጥቂት ቀናት ውስጥ ይፋ ያደርጋሉ ተብሏል። 25 አባላትን ያቀፈው የማንቸስተር ዩናይትድ ቡድን ለዓለም አቀፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ሚያሚ ከተማ ውስጥ ከሊቨርፑል ጋር ለፍፃሜ ገጥሞ ነገ ማለዳ ላይ ወደ እንግሊዝ ይመለሳል።

ሉዊስ ቫንጋል ከ5 ዓመታት በፊት የባየር ሙንሽን አሠልጣኝ የነበሩ ጊዜ የተነሱት

ሉዊስ ቫንጋል ከ5 ዓመታት በፊት የባየር ሙንሽን አሠልጣኝ የነበሩ ጊዜ የተነሱት

በማንቸስተር ዩናይትድ ውስጥ ወደፊት ብዙም ተስፋ የላቸውም ከተባሉ ተጨዋቾች መካከል፤ ዣቪየር ሔርናንዴዝ፣ ሺንጂ ካጋዋ ዊልፍሬድ ዛሃ፣ ማሮኔ ፌላኒ እና አንደርሰን ይገኙበታል። ሆላንዳዊው አሠልጣኝ «ከግጥሚያው በኋላ ውሳኔዬን አሳውቃለሁ። ሁሉም ተጨዋቾች የመጫወት ዕድል እንዲያገኙ አድርጌያለሁ። ስለእዚህ አሁን ከበፊቱ በበለጠ ብዙ ነገር አውቄያለሁ» ሲሉ ተደምጠዋል። ከሠዓታት በኋላ በሚጀምረው የማንቸስተር ዩናይትድ እና የሊቨርፑል የፍፃሜ ጨዋታ አሸናፊው ቡድን በሽልማት 1 ሚሊዮን ዶላር ተሸክሞ ወደ እንግሊዝ ያቀናል።

የዘንድሮው የተጨዋቾች ዝውውር ሊያበቃ ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ነው የቀረው። በቀሩት ጥቂት ቀናት የአውሮጳ ታላላቅ ቡድኖች ተጨዋቾችን በፍጥነት ወደ እየቡድናቸው ለማስመጣት እየተጣደፉ ነው። የጁቬንቱሱ 23 ቁጥር ለባሽ፣ አማካዩ አርቱሮ ቪዳል ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሊመጣ ይችል ይሆናል ተባለ። ባላቶሊ ወደ ሊቨርፑል ሊዛወር ነው መባሉ ስህተት መሆኑን ሊቨርፑሎች አስታውቀዋል። እነዚህን እና ሌሎች የደረሱንን የዝውውር ዜናዎችን ወደ በኋላ ላይ እናሰማችኋለን። አሁን በቅድሚያ የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ውጤቶችን እንቃኝ።

የጋና ቡድን ደጋፊዎች

የጋና ቡድን ደጋፊዎች

በቀድሞው የጋና ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በሮሜዎ ፊሌሞን ከሚሰለጥነው የአንጎላ ቡድን ጋር ትናንት መዲና ሉዋንዳ ላይ ለወዳጅነት ተገናኝቶ 1 ለዜሮ ተሸንፏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሞሮኮ ላይ በሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ለመሳተፍ የሚገጥማቸው አጠቃላይ ቡድኖች ታውቀዋል።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ምድብ ሁለት ጠንካራ እንደሆነ ተጠቅሷል። በምድብ ሁለት ኢትዮጵያ፤ ማሊ፣ አልጄሪያ እና ማላዊን ትፋለማለች። የአልጄሪያ ቡድን ዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የቻለ ብርቱ ቡድን ነው። ማሊ በርካታ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ያሉት ሲሆን፤ ቡድኑ በአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር በርካታ ልምድ አካብቷል። ዝቅተኛ ግምት የተሰጠው የማላዊ ቡድን ሲሆን፤ ቡድኑ እስካሁን ባደረጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች፤ ከሦስት ሣምንት በፊት ከሞዛምቢክ ጋር ተጋጥሞ አንድ እኩል አቻ ወጥቷል። በታንዛኒያ 1 ለባዶ ተሸንፏል። ከሁለት ሣምንት በፊት ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ደግሞ ከኡጋንዳ ጋር ዜሮ ለዜሮ ተለያይቷል።

ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች በሆኑ ታዳጊዎች መካከል በሚደረገው የእግር ኳስ ግጥሚያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ፉክክር የማለፍ ተስፋው በጋቦኑ አቻው መክኗል። ብሔራዊ ቡድኑ የጋቦን ተፎካካሪውን በመልስ ጨዋታ ከትናንት በስትያ ገጥሞ ሦስት ለባዶ በሆነ ሰፊ ልዩነት ተሸንፏል። ሁለቱ ቡድኖች የዛሬ 15 ቀን አዲስ አበባ ስታዲየም ተገናኝተው ያለምንም ግብ መለያየታቸው ይታወሳል። እጎአ በ2015 ኒጀር ውስጥ በሚካሄደው ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ግጥሚያ ለመሳተፍ 24 የተለያዩ አፍሪቃዊ ሃገራት ፉክክር በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የእግር ኳስ ተጨዋቾች ዝውውር ዜና

ጣሊያናዊው ማሪዮ ባሎቴሊ

ጣሊያናዊው ማሪዮ ባሎቴሊ

የኤስ ሚላን አጥቂ ማሪዮ ባሎቴሊ ወደ ሊቨርፑል ሊመጣ ነው የተባለው ውሸት መሆኑን የሊቨርፑል አሠልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ አስታወቁ። «ግልፅ ላደርግላችሁ የምፈልገው ነገር አለ» አሉ አሠልጣኙ ስለ ባላቶሊ ወደ ሊቨርፑል ሊመጣ ነው መባሉን ሲያስተባብሉ። «ማሪዮ ባሎቴሊ በቀጣዮቹ የበጋ ወራት ወደ ሊቨርፑል አይመጣም። በባለፈው የመጨረሻ ጋዜጣዊ መግለጫዬ ወቅት ስለ ማሪዮ ባሎቴሊ ተጠይቄ ልጁ ድንቅ ብቃት እንዳለው ተናግሬ ነበር። በሚቀጥለው ቀን ተጨዋቹን ልናስፈርመው እንደሆነ የሚገልፅ ጽሑፍ ወጣ ።» ሲሉ የተፈጠረውን ብዥታ ለማጥራት ሞክረዋል።

ሊቨርፑል ወሳኝ አጥቂው ሉዊስ ሱዋሬዝን ባለፈው ወር ወደ ስፔኑ የድንቆች ስብስብ ባርሴሎና ከላከ ወዲህ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ሪኪ ላምበርትን ከሳውዝ ሐምፕተን ቡድን ማስመጣት ችሏል። የቤልጂየሙ አጥቂ ታዳጊው ጂቮክ ኦሪጂን ከሊሌ ቡድን አስመጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ ወዲያውኑ ነበር ተጫዋቹ ወደ ፈረንሳዩ ቡድን በውሰት የተመለሰው።

ኮሪየር ዴሎ ስፖርት የተሰኘው የጣሊያን ጋዜጣ ዛሬ ባወጣው ዕትሙ እንዳስነበበው የጁቬንቱሱ አማካይ፣ ቺሊያዊው አርቱር ቪዳል ለገበያ አልቀረበም፤ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድም አይመጣም ብሏል። ሆኖም አርቱር ጁቬንቱስን ተሰናብቶ ለመሄድ ልቡ እንደቆመ የቱሪን ነዋሪዎች ተገንዝበዋል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ ውስጥ የሚከፈለው ደመወዝ በርካታ ተጨዋቾችን የሚያባብል ነው ሲልም ጋዜጣው አክሎ አስነብቧል።

የጀርመኑ ሽኮርዳን ሙስጣፊ በዓለም ዋንጫ

የጀርመኑ ሽኮርዳን ሙስጣፊ በዓለም ዋንጫ

የቀድሞው የኤቨርተን ተከላካይ ሽኮርዳን ሙስጣፊ የስፔኑ ቫለንሺያ ቡድን ዓይን ውስጥ ገብቷል። ቫለንሺያ በተጨማሪ ሮድሪጎ ሞሬኖ እና አንድሬ ጎሜዝን ከቤኔፊካ በማስመጣት የተከላካይ ክፍሉን ማጠናከር ይፈልጋል። ከምንም በላይ ግን ኤቨርተኖች የዓለም ዋንጫ ባለድሉ የጀርመን ቡድን ተከላካይ ሽኮርዳን ሙስጣፊን ለማስመጣት ቆርጦ እንደተነሳ ተገልጿል። ሽኮርዳን ሙስጣፊ ለዓለም ዋንጫ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ሊካተት የቻለው የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ኮከብ ማርኮ ሮይስ በጉዳት ከጀርመን ቡድን ለመውጣት በተገደደበት ወቅት ነበር።

ቶትንሀሞች የማቴዎ ሙሳቺዮ ወደ ቡድኑ መምጣት የማያጠራጥር መሆኑ ከተነገረ በኋላ ዮነስ ካቡልን ለመሸጥ ከጣሊያኑ ላትሲዮ ቡድን ጋር እየተደራደሩ መሆናቸውን London Evening standard የተሰኘው ዕለታዊ አስነብቧል።

የአውስትራሊያው ተከላካይ ጃሰን ዳቪድሰን የዌስት ብሮሚች ዝውውሩን ከፍፃሜ ለማድረስ ዛሬ ወደ እንግሊዝ መግባቱን Express & star አስነብቧል።

ቡጢ

በመለስተኛ ከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ሩስያዊው ሠርጂዮ ኮቫሌቭ በዳኛ ውሳኔ ብሌክ ካርፔሎን በሁለተኛው ዙር በማሸነፍ ቀበቶውን ከመነጠቅ አስጠብቋል። ዳኛው ጣልቃ ገብተው ጨዋታውን ከማቋረጣቸው በፊት ሩስያዊው ብሌክን ሁለት ጌዜያት ለመዘረር ችሎ ነበር።

የሜዳ ቴኒስ

ሴሬና ዊሊያምስ

ሴሬና ዊሊያምስ

በሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ለዓመታት ኃያል መሆኗን ያስመሰከረችው ጥቁር አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ ዘንድሮም አልበገርም ብላለች። ሴሬና ስታንፎርድ ካሊፎርኒያ ውስጥ በተካሄደው Bank of the west WTA በተሰኘው የሜዳ ቴኒስ ፉክክር ጀርመናዊቷ አንጄሊኬ ኬርበርን ከኋላ ተነስታ አሸንፋታለች። አንጄሊኬ ጨዋታው እንደተጀመረ 5 ለ1 በሆነ ሰፊ ነጥብ እየመራች ነበር ሆኖም ሴሬና ከኋላ ተነስታ 7 ለ6 እና 6 ለ3 በሆነ የነጥብ ልዩነት ለማሸነፍ ችላለች። ውድድሩን በማሸነፏ የ 710,000 ዶላር ተሸላሚ ትሆናለች። ሴሬና ይኽን መሰሉን ውድድር በ2012 እና 2011 ማሸነፏ ይታወቃል። የ6,5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት የሚያሰጠውን የBNP Parabis WTA ውድድርም እጎአ በ2013፣ በ2012 እና 2009 ማሸነፏ የሚታወቅ ነው።

የአርሰናሉ አሠልጣኝ አርሰን ቬንገር የመድፈኞቹ አጥቂ ኦሊቨር ጊሮድ በፍጥነት ወደ ብቃቱ እንደሚመለስ ያላቸውን ተስፋ ገለጡ። ኦሊቨር ለዓለም ዋንጫ ግጥሚያ ከፈረንሣይ ቡድን ጋር ከተጓዘ በኋላ ወደ አርሰናል የተመለሰው ዘግይቶ ነው። ትናንት አርሰናሎች በሞናኮ 1 ለባዶ ሲሸነፉ ኦሊቨር ብቃቱና የሰውነት አቋሙ ደካማ እንደነበር ተጠቅሷል። ይኽ ውጤት አርሰናል ለኮሚኒቲ ሺልድ ዋንጫ ማንቸስተር ሲቲን ሊገጥም ስድስት ቀናት እየቀሩት የተገኘ መሆኑ መድፈኞቹን እጅግ አሳስቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic