የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 05.12.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በእግር ኳሱ ዓለም ሰንበቱ ያለፈው ከባድ ሃዘን በጋረደው መንፈስ ነው። የአንዴው የ”ሤሌሣዎ” ድንቅ ተጫዋችና አምበል የሶክራቴስ በሞት መለየት ብራዚልን ጥልቅ ሃዘን ላይ ጥሏል።

default

ዶር/ሶክራቴስ

የብራዚሉ ድንቅ ተጫዋች የሶክራቴስ ሞት በብራዚል ብቻ ሣይወሰን በመላው ዓለም የሚገኙ የእግር ኳስ ስፖርት አፍቃሪዎችን ብርቱ ሃዘን ላይ ነው የጣለው። በሙሉ ስሙ ሶክራቴስ ብራዚሊየሮ ሣምፓዮ ዴ ሱዛ ቪየራ ዴ ኦሊቪየራ በሙያ መጠሪያው ዶር/ሶክራቴስ ባደረበት የአንጀት ሕመም በ 57 ዓመት ዕድሜው ከዚህች ዓለም የተለየው ባለፈው ቅዳሜ ነበር። ሶክራቴስ ዶክተርነቱ በሕጻናት ሃኪምነት ብቻ የተወሰነ አልነበረም። በአጨዋወቱ የኳሷም ሃኪም ነበር ቢባል ጨርሶ ማጋነን አይሆንም። በነገራችን ላይ ሶክራቴስ ተጫዋችነቱን ካበቃ በኋላ በሕጻናት ሃኪምነት ሙያው ሲያገለግል እርግጥ ዚኮን ከመሳሰሉት ከአንዴ የብሄራዊ ቡድን ባልደረቦቹ ጋር የብራዚል እግር ኳስ የቅርብ ታዛቢም ነበር።

ሶክራቴስ በብራዚል የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ፔሌን ቶስታኦንና ጀርዚኞን የመሳሰሉትን የኳስ ተዋንያን ካቀፈው በ 1970 ሜክሢኮ ላይ ለብራዚል ሶሥተኛዋን የዓለም ዋንጫ ካስገኘው ግሩም ቡድን እንኳ ጠንካራው እንደነበር ለሚነገርለት ብሄራዊ ቡድን በመሰለፍ እ.ጎ.አ. በ 1982 በስፓኝኛ ከዚያም በ 1986 በሜክሢኮ በተካሄዱት ሁለት የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድሮች ተሳትፏል። ያስገርማል የዋንጫ ባለቤት የመሆን ዕድል ግን አልገጠመውም። ይሁን እንጂ የብራዚል እግር ኳስ ታሪክ በተነሣ ቁጥር እንደ ፔሌ፣ እንደ ጋሪንቻ ወይም ቶስታኦ ምንጊዜም የሚታወስ ግሩም የኳስ ጠቢብ ነው። የዶር/ሶክራቴስ የቀብር ስነ ስርዓት ትናንት ከሣኦ ፓውሎ 300 ኪሎሜትር ወጣ ብላ በምትገኘው ኳስ መጫወት በጀመረባት መንደር በቢቤይራኦ ፕሬቶ ተከናውኗል።
የብራዚል እግር ኳስ ፌደሬሺንም ትናንት በአገሪቱ በተካሄዱት መላ ግጥሚያዎች ኮከቡ በደቂቃ ጸሎት እንዲታሰብ አድርጓ ነበር። ከሁሉም በላይ ትልቁ ክብር ግን 297 ጊዜ የተጫወተለት ክለብ ኮሪንቲያንስ ትናንት ለአምሥተኛ ጊዜ የብራዚል ሻምፒዮን መሆኑ ነው። ለክለቡ ስድሥት ዓመታት ሙሉ የተጫወተው ሶክራቴስ ራሱ በጊዜው 176 ጎሎችን ሲያስቆጥር ትናንት ሕያው ሆኖ ድሉን ቢያይ ምንኛ አስደሳች በሆነ ነበር። ከብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች መካከል ብዙዎቹ ሶክራቴስን በአርያነት በማወደስ ሃዘናቸውን ሲገልጹ ከመካከላቸው አንዱ ሮናልዶም በሃዘን መልዕክቱ ”ዶር/ሶክራቴስ፤ የሰላም ዕረፍት ይሁንልህ” ብሎታል። እኛም ምኞታችን ዕረፍቱን የሰላም እንዲያደርግለትና ዓለም እርሱን መሰል መታሰቢያዎቹን እንድታፈራ ነው።

የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር ዕጣ

በኡክራኒያና በፖላንድ የጋራ አስተናጋጅነት በመጪው የጎርጎሣውያኑ 2012 ዓ.ም. ለሚካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባለፈው አርብ ምሽት ኪየቭ ላይ የወጣው ዕጣ የክፍለ-ዓለሚቱ ውድድር የዓለም ዋንጫን ያህል ማራኪ ሊሆን እንደሚችል ያመለከተ ነበር። በምድብ-አንድ ፖላንድ፣ ሩሢያ፣ ግሪክና ቼክ ሬፑብሊክ በአንድ ሲደለደሉ በምድብ-ሁለት ውስጥ ጀርመን፣ ኔዘርላንድ፣ ፖርቱጋልና ዴንማርክ ከጅምሩ ከባድ ፈተና ተጥሎባቸዋል። ይሄው ምድብ ከሁሉም የጠነከረው ሲሆን እያንዳንዱ ግጥሚያ የፍጻሜን ያህል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የኔዘርላንዱ ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ በርት-ፋን-ማርቪይክ ዕጣው ከወጣ በኋላ በሰጠው መግለጫ ይህንኑ ነበር ያረጋገጠው።

“በምድባችን ውስጥ ሁሉንም አሠልጣኖች እንደታዘብኩት አንዱም ገጽታው ላይ ደስታ የሚታይበት አልነበረም። ትልቅ የእርስበርስ መከባበር ነው ያለው። ምድቡ ከተቀሩት ሁሉ ከባድ በመሆኑ ሁሉም ይስማማሉ”

በምድብ-ሶሥትም ሻምፒዮኗ ስፓኝ ከኢጣሊያ፣ ከክሮኤሺያና ከአየርላንድ ስትደለደል ይህም ቀላል የሚባል አይሆንም። በምድብ-አራትም እንዲሁ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ስዊድንና ኡክራኒያ ገና ከጅምሩ ብርቱ ትግል ነው የሚጠብቃቸው። እ.ጎ.አ. ሰኔ ስምንት ዋርሶው ላይ በፖላንድና በግሪክ ጨዋታ የሚከፈተው የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር ሐምሌ አንድ ቀን ኪየቭ ውስጥ በሚካሄድ ፍጻሜ ግጥሚያ ይጠቃለላል። ዕጣው ከወዲሁ ሲለይለት ከእንግዲህ የሚቀረው የዝግጅቱ መጠቃለል፤ ለምሳሌ በጀርመን ትብብር የሚሠራው የኪየቭ ስታዲዮምና ፖላንድ የምታንጸው አውራ ጎዳና ሥራ በጊዜው መጠናቀቅ ነው።

ታንዛኒያ ውስጥ የሚካሄደው የምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪቃ ዋንጫ ውድድር የምድብ ዙር ደግሞ ባለፈው ሰንበት ተጠናቆ ወደ ሩብ ፍጻሜው ዙር ተሸጋግሯል። ከአራቱ ምድቦች በአንደኝነትና በሁለተኝነት ስምንት ሃገራት ወደ ሩብ ፍጻሜው ሲያልፉ ዛሬና ነገ እርስበርስ ይጋጠማሉ። እነዚሁም ሱዳን ከኡጋንዳ፤ ሩዋንዳ ከዛንዚባር፤ ማላዊ ከታንዛኒያ፤ እንዲሁም ቡሩንዲ ከዚምባብዌ ናቸው። ባለፈው ዓመት እስከ ግማሽ ፍጻሜ ዘልቃ የነበረችው ኢትዮጵያ ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር ተወስና ቀርታለች። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ ጨዋታዎቹ ከሱዳንና ከማላዊ እኩል ለእኩል 1-1 ሲለያይ በኬንያ ደግሞ 2-0 ተረትቶ የምድቡ መጨረሻ ሆኗል።
በዚያው በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የሞሮኮው ክለብ ማግሬብ-ፌስ ደግሞ ትናንት የዘንድሮው የአፍሪቃ ኮንፌደሬሺን ዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቅቷል። ቡድኑ በመደበኛ ጊዜው የቱኒዚያ ተጋጣሚውን ክለብ-አፍሪኬንን 1-0 ሲረታና የመጀመሪያውን ዙር ግጥሚያ ውጤት ሲያስተካክል ለዋንጫ የበቃው በፍጹም ቅጣት ምት 6-5 በማሸነፍ ነው። የሞሮኮው ክለብ በረኛ አናስ ዝኒቲ ሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶችን በመያዝ የቡድኑ ድል ዋስትና ነበር። የቱኒዙ ክለብ አፍሪኬን በአንጻሩ የቻድ ተወላጅ ተጫዋቹ በ 60ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳ ሲወጣበት በዚሁ መጎዳቱ አልቀረም። በጥቅሉ ቱኒዚያ ካለፈው ወር የኤስፔራንስ የአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ ዋንጫ በኋላ ድሏን እጥፍ ለማድረግ የነበራት ዕድል ከንቱ ሲሆን በሌላ በኩል ለፌስ የትናንቱ የመጀመሪያው የክፍለ-ዓለም ውድድር ዋንጫ መሆኑ ነው።

Fußball Bundesliga FC Bayern München - Werder Bremen

ቡንደስሊጋ/የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ባየርን ሙንሺን ባለፈው ሣምንት ለዶርትሙንድ አስረክቦት የነበረውን አመራር መልሶ ሊጨብጥ ችሏል። ባየርን ለዚህ የበቃው ዶርትሙንድ ከግላድባህ ባደረገው ግጥሚያ በ 1-1 ውጤት በመወሰኑ ነው። ባየርን በፊናው በ 15ኛው የቡንደስሊጋ ግጥሚያ ብሬመንን 4-1 ሲያሸንፍ አሁን ዶርትሙንድንና ግላድባህን በአንዲት ነጥብ ልዩነት በማስከተል በ 31 ይመራል። በባየርን አንጻር ብሬመን በደካማ አጨዋወቱ አሠልጣኙን ቶማስ ሻፍን ጨምሮ ብዙዎች ደጋፊዎቹን ነው ያሳዘነው።

“በመከላከል ረገድ ጥቂትም ቢሆን የተሣካ የመቋቋም ጥረት አድርገናል። ግን ለኔ ወሣኙ ጥያቄ ኳስ መቆጣጠር በቻልንባቸው ጊዜያት ምን ያህል ተጠቅመንባቸዋል የሚል ነው። ባየርንን በሚገባ አልተፈታተንንም። አንዴም ፈተና ላይ አልጣልናቸውም። እናም በእንዲህ ዓይነቱ ጨዋታ ማሸነፍ የማይቻል ነገር ነው”

ለማንኛውም የብሬመን መሽነፍ ለሻልከ ባጣሙን በጅቶታል። ክለቡ አውግስቡርግን 3-1 በመርታት በ 28 ነጥቦች ወደ አራተኛው ቦታ ከፍ ሲል ብሬመን በማቆልቆል በ 26 አራተኛ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ሢቲይ ኖርቪች ሢቲይን 5-1 አሸንፎ በመሸኘት በአምሥት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ሲቀጥል ሁለተኛው ማንቼስተር ዩናይትድም ኤስተን ቪላን 1-0 ረትቷል። ቶተንሃም ሆትስፐር ሶሥተኛ፣ ቼልሢይ አራተኛ፣ አርሰናል አምሥተኛ! በስፓኝ ላ-ሊጋም ቀደምቱ ሬያል ማድሪድና ባርሤሎና በየፊናቸው በማሸነፋቸው በአመራሩ ላይ የተከሰተ ለውጥ የለም። ሬያል ማድሪድ ጊዮንን 3-0 ሲያሸንፍ ባርሤሎናም ሌቫንቴን 5-0 ሸኝቷል። ሬያል በሶሥት ነጥብ ብልጫ የሚመራ ሲሆን ባርሤሎና ሁለተኛ፤ እንዲሁም ቫሌንሢያ ሶሥተኛ ነው። ከዚሁ ሌላ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ፣ በፈረንሣይ ሞንትፔልየርና በኔዘርላንድ ደግሞ እክማር ቀደምቱ እንደሆኑ ነው።

በተረፈ በትናንትናው ዕለት ጃፓን-ፉኩኦካ ላይ በተካሄደ የማራቶን ሩጫ ኬንያውያን አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ለማሸነፍ በቅተዋል። ጆሴፋት እንዳምቢሪ ሙሉውን የማራቶን ርቀት ሲያቋርጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ያሽነፈው በሁለት ሰዓት ከሰባት ደቂቃ 36 ሤኮንድ ጊዜ ነው። ሁለተኛውም የኬንያው ተወላጅ ጀምስ ንዋንጊ ሲሆን ሁለቱም የሚኖሩትና የሚሰለጥኑት በዚያው በጃፓን ነው። ታዋቂው 64ኛ የፉኩኦካ ማራቶን እንዳምቢሪን ጨምሮ በአንዳንድ አትሌቶች ዘንድ በመጪው ዓመት የለንደን ኦሎምፒክ ለማሳተፍ የአቅም መፈተሻ ሆኖ መታየቱ አልቀረም። ይሁንና ኬንያ በርካታ ጠንካራ ሯጮች ስላሏት ፉክክሩ ቀላል እንደማይሆን ግልጽ ነው። ከብዙ በጥቂቱ ባለፈው መስከረም ወር ፓትሪክ ማካዉ በበርሊን ማራቶን የሃይሌ ገ/ሥላሴን የዓለም ክብረ-ወሰን ሲያሻሽል አቤል ኪሩዊም በዴጉ የዓለም ሻምፒዮን መሆኑ አይዘነጋም።
በዓለም የቴኒስ ዴቪስ-ካፕ ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ስፓኝ አርጄንቲናን በማሽነፍ ለአምሥተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ሆናለች። ራፋኤል ናዳልና ዴቪድ ፌሬር የስፓኝን ድል ሲያረጋግጡ በተለይም ለናዳል ስኬቱ በዚህ ለርሱ ብዙም መልካም ባልነበረው ዓመት መጨረሻ ጥሩ መጽናኛ ነው የሆነው። ናዳል ባለፈው አርብ ሁዋን ሞናኮን በፍጹም ልዕልና ከረታ በኋላ ትናንት የስፓኝን ድል ያረጋገጠው ዴል ፖትሮን በማሽነፍ ነበር።

በእግር ኳስ ለማጠቃለል ነገና ከነገ በስቲያ ረቡዕ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የምድብ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ከነዚሁ ዋና ዋናዎቹም ቼልሢይ ከቫሌንሢያ፤ ዶርትሙንድ ከኦላምፒክ ማርሤይ፤ ኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ ከአርሰናል፤ ማንቼስተር ሢቲይ ከባየርን፤ ቪላርሬያል ከናፖሊ፤ ኢንተር ሚላን ከሞስኮና አያክስ አምስተርዳም ከሬያል ማድሪድ ናቸው። እስካሁን አርሰናል፤ ሌቨርኩዝን፤ ባየርን ሙንሺን፣ ባርሤሎና፣ ሚላን ወዘተ ወደ ተከታዩ የጥሎ ማለፍ ዙር ሲያልፉ ቀሪዎቹም በዚህ ሣምንት ይታወቃሉ።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic