የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 21.11.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ያለፈው ሣምንት ለመጪው 2012 ዓ.ም. የአውሮፓ የእግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ማጣሪያው ዙር የተጠናቀቀበት፤ በርካታ የወዳጅነትና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎችም የተካሄዱበት ነበር። የአውሮፓ ቀደምቱ ሊጋዎች ውድድርም በአስደናቂ ሁኔታ ቀጥሏል።

default

የጀርመን ብሄራዊ ቡድን

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ሢቲይ በዚህ ሣምንትም የአምሥት ነጥብ አመራሩን ጠብቆ መቀጠሉ ሰምሮለታል። ቡድኑ ባለፈው ቅዳሜ በሜዳው ባደረገው ግጥሚያ እስከዚያው አንዴም ሽንፈት ሳይደርስበት የቆየውን ኒውካስል ዩናይትድን 3-1 ሲረታ በጠቅላላው 34 ነጥቦች አሉት። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ማንቼስተር ዩናይትድም ስዋንሢ ሢቲይን 1-0 በመርታት በሁለተኝነቱ ቀጥሏል። ማንቼስተር ዩናይትድ አንዳች ጎል ሳይቆጠርበት ሲያሸንፍ የሰንበቱ በተከታታይ አምሥተኛ ግጥሚያው መሆኑ ነው።

ኒውካስል ዩናይትድ በማንቼስተር ሢቲይ ቢሸነፍም በሶሥተኝነቱ ሲቀጥል አራተኛው ቼልሢይ ከፍ ለማለት ያጋጠመውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ቼልሢይ ትናንት በሊቨርፑል 2-1 ሲረታ ይሄውም በሜዳው በተከታታይ ሁለቴ መሽነፉ ነው። ቶተንሃም ሆትስፐር፣ ሊቨርፑልና አርሰናል እንደ ቼልሢይ ሁሉ እኩል 22 ነጥብ ኖሯቸው ይከተላሉ። ቶተንሃም ሆትስፐር እንዲያውም በዛሬው ምሽት ቀሪ ግጥሚያው ኤስተን ቪላን ካሽነፈ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ሊቃረብም ይችላል።

የጀርመን ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር በታላቅ ጉጉት ሲጠበቁ የሰነበቱት ጠንካራና ማራኪ ግጥሚያዎች የተካሄዱት ያልተጠበቀ ሃዘንና ድንጋጤ ጋርዷቸው ነበር። ለዚህም ምክንያት የሆነው የኮሎኝንና የማይንስን ግጥሚያ እንዲመራ የተመደበው ዳኛ ባዳክ ራፋቲ በዕለቱ ደም ስሩን በመቁረጥ ራሱን ለመግደል መሞከሩ ነበር። ይሄው ግጥሚያ አስደንጋጩ ዜና እንደተሰማ ከዕለቱ ፕሮግራም እንዲሰረዝ ሲደረግ የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሺን ፕሬዚደንት ቴዎ ስቫንሢገር የ 41 ዓመቱ ጎልማሣ መዳን በተቀዳሚ ዋናው ነገር እንደሆነ ነበር በአዘኔታ የገለጹት።

“በመጀመሪያ ባዳክ ራፋቲ ጤንነቱን እንዲያገኝ ተሥፋ ማድረግ አለብን። ከሁሉም በላይ ዋናው ነገር ይሄው ነው። የጤንነቱ ሁኔታ መረጋጋቱና መልሶ ጤና መሆኑ! እርግጥ ለዚህ ዕርምጃ ያበቃውን ምክንያትም ማወቅ ይኖርብናል። ሰው መቼም ከችግሩ መውጫ ካላጣ በስተቀር ራሱን እስከመግደል ድረስ አይሄድም። እናም ሊረዳ ይችል ዘንድ ይሄው ግልጽ ሊሆን ይገባል”

ባዳክ ራፋቲ በእግር ኳሱ የስፖርት መድረክ ግፊቱን መቋቋም አቅቶት ራሱን ለመግደል ይሞክር ወይም ሌላ ምክንያት ይኑረው ገና በውል አልተረጋገጠም። ቢሆንም ድርጊቱ በዚህ በጀርመን ከጥቂት ዓመታት በፊት የአንዴው የብሄራዊ ቡድን በረኛ ሮበርት ኤንከ ሕይወቱን በራሱ ያሳለፈበት ሁኔታ እንደገና በብዙዎች እንዲታወስ ነበር ያደረገው። ለማንኛውም ይህን ለጊዜው በዚሁ ተወት እናድርገውና በስፖርቱ ረገድ የሰንበቱ የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች በተለይም ሊጋውን ከአንድ እስከ አራት በመከታተል ይመሩ በነበሩት መካከል የተካሄዱት ጨዋታዎች እጅግ ግሩምና አስደናቂም ነበሩ።
በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋና በጀርመን ቡንደስሊጋ ውስጥ ፍጹም ልዕልና ሲታይበት የቆየው ባየርን ሙንሺን ካለፈው ወቅት ሻምፒዮን ከዶርትሙንድ ጋር በገዛ ሜዳው ባደረገው ግጥሚያ ምናልባትም ያልጠበቀው መሪር ሽንፈት ደርሶበታል። ዶርትሙንግ በወጣት ብሄራዊ ተጫዋቹ በማሪዮ ገትሰ አማካይነት ብቸኛዋን የድል ጎል ሲያስቆጥር የባየርን ተከላካዮች አልፎ አልፎ ያረጁ መስለው ነው የታዩት። የባቫሪያው ክለብ ተጫዋቾች ውጤቱን ለመቀየር ብዙ የማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም ጎል ማስገባቱ ጨርሶ አልሆናቸውም። ታዲያ የዶርትሙንድ ድል በብዙዎች ዘንድ በአድናቆት ቢታይም የመሃል ሜዳ ተጫዋቹ ኬቪን ግሮስክሮይስ በበኩሉ ስኬቱ ጨርሶ ያልተጠበቀ እንዳልነበር ነው የገለጸው።

“ለምን አስደናቂ ይሆናል! በዛሬው ጨዋታም ለተጋጣሚያችን ብዙ የጎል ዕድል አልሰጠንም። ሁላችንም ኳሷን በጥሩ ሁኔታ በመቆጣጠር ነው የተጫወትነው። እናም ትግል በተመላው ጨዋታ ባየርንን በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ ለማሽነፍ በቅተናል። ከዚህ የበለጠ የሚያስደስት ነገር ያለ አይመስለኝም”

ሌላው በመንሸንግላድባህና በብሬመን መካከል የተካሄደው የሰንበቱ ዓቢይ ግጥሚያም ለአስተናጋጁ ክለብ የፌስታ ነበር የሆነው። ግላድባህ ብሬመንን 5-0 በመቅጣት ከሶሥተኛው ቦታ ሲፈነቅል በግሩም አጨዋወቱ ተመልካቹን ሲበዛ ነበር ያስፈነደቀው። በተለይ ደግሞ ከአምሥት ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው የብሄራዊው ቡድን ወጣት ተጫዋች ማርኮ ሮይስ ድንቁ መንኮራኩር ነበር።

“የጨዋታውን ውጤት ለብቻዬ ወስኛለሁ ብዬ አላስብም። የመላው ቡድን ውጤት ነው። ዛሬ እንደገና ጥሩ ጨዋታ ነበር ያሳየነው። ለተጋጣሚያችን የጎል ዕድል አልሰጠነውም። ከ 13 ጨዋታዎች በኋላ በሊጋው አመራር ላይ ካሉት ክለቦች አንዱ መሆናችን እርግጥ በጣም ነው የሚያስደስተኝ። ሆኖም ግን ወደፊትም ለእያንዳንዷ ነጥብ መታገል እንደሚኖርብን አምናለሁ”

የብሬመን ቡድን በአንጻሩ ካለፉት ጥቂት ሣምንታት የስኬት ጉዞ በኋላ መለማመጃ መስሎ ነበር የታየው። ቡድኑ በዚሁ ከባድ ሽንፈቱ ወደ አምሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል ከሊጋው አመራር ጋር ንኪኪውን ጨርሶ እንዳያጣ መጠንቀቅ ይኖርበታል።

በስፓኝ ላ-ሊጋ ሬያል ማድሪድ ቫሌንሢያን 3-2 በማሸነፍ አመራሩን ወደ 31 ነጥቦች ከፍ ሲያደርግ ባርሤሎናም በበኩሉ ግጥሚያ ሣራጎሣን 4-0 በመርታት ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ በሁለተኝነት መከተሉን ቀጥሏል። የሰንበቱ ተሸናፊዎች ቫሌንሢያና ሌቫንቴ ደግሞ በአንዲት ነጥብ ልዩነት በመከታተል ሶሥተኛና አራተኛ ናቸው። በኢጣሊያ ሤሪያ-አ እስካሁን አንዴም ያልተሽነፈው ጁቬንቱስ ፓሌርሞን 3-0 ሲረታ ሌላው ቀደምት ክለብ ላሢዮ ደግሞ ከናፖሊ ባዶ-ለባዶ ተለያይቷል።
ሁለቱም ቡድኖች በእኩል 22 ነጥቦች በአመራሩ ሲቀጥሉ ሶሥተኛው ከፊዮሬንቲና 0-0 የተለያየው ኤ.ሢ.ሚላን ነው። ኡዲኔዘ በፓርማ 2-0 በመሸነፉ በተመሳሳይ ነጥብ ቢሆንም በአራተኝነት መወሰኑ ግድ ሆኖበታል። ቀደምቱ ጁቬንቱስና ላሢዮ በፊታችን ሰንበት እርስበርስ የሚገናኙ ሲሆን ጨዋታው በተመልካቾች ዘንድ በታላቅ ጉጉት ይጠበቃል። በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ፓሪስ ሣንት-ዠርማንና ሞንትፔሊዬር በእኩል ሰላሣ ነጥቦች ቀደምቱ ሲሆኑ በኔዘርላንድ አልክማር አይንድሆፈንን በሶሥት ነጥቦች ልዩነት አስከትሎ ይመራል።

ማጣሪያና የወዳጅነት ግጥሚያዎች

ያለፈው ሣምንት ማክሰኞ በርካታ የወዳጅነትና የተለያዩ ማጣሪያ ግጥሚያዎችም የተካሄዱበት ነበር። በዚህ በአውሮፓ ከተካሄዱት ግጥሚያዎች መካከል ለምሳሌ እንግሊዝ በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲዮም የዓለምና የአውሮፓ ሻምፒዮን የሆነችው ስፓኝን 1-0 ብታሸንፍም ሰፊውን ትኩረት የሳበው በልምድ ብርቱ ፉክክር የሚታይበት የጀርመንና የኔዘርላንድ ግጥሚያ ነበር። በእርግጥም ጀርመን ድንቅ ጨዋታ በማሳየት ኔዘርላንድን 3-0 ስታሸንፍ ልዕልናዋ በመጪው የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ጠንካራዋ ልትሆን እንደምትችል ያመለከተ ነው። የኔዘርላንድ ፕሬስ ሳይቀር የጀርመንን ቡድን እንደ ግሩም ኦርኬስትራ ሲያወድስ በአንጻሩም የራሱን ተጫዋቾች የሰከሩ ጥሩምባ ነፊዎች ብሏቸዋል።

እንግሊዝ ከስፓኝ ሌላ ስዊድንንም 1-0 በመርታት የተሳካ ሙከራ ስታደርግ በነገራችን ላይ ይሄው ድል ከ 43 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነበር። ስፓኝ በአንጻሩ ከዌምሌይ ሽንፈቷ በኋላ ከኮስታ ሪካ ጋር 2-2 ስትለያይ የማዕከላዊ አሜሪካ ተጋጣሚዋን ሳትንቅ እንዳልቀረች ነው የሚታመነው። ከብዙ በጥቂቱ በሌሎች የወዳጅነት ግጥሚያዎች ኡሩጉዋይ ኢጣሊያን በሜዳዋ 1-0 ስታሸንፍ ሩሜኒያ ግሪክን 3-2 ረትታለች። ፈረንሣይና ቤልጂግ ደግሞ ባዶ-ለባዶ ተለያይተዋል። ከዚሁ ሌላ ፖርቱጋል፣ አየርላንድ፣ ቼክ ሬፑብሊክና ክሮኤሺያ ደግሞ ለኤውሮ-2012 ፍጻሜ ውድድር ለማለፍ በቅተዋል።

BdT Berlin Marathon

አትሌቲክስ

ሃይሌ ገ/ሥላሴ ትናንት በኔዘርላንድ-ኒምቬገን በተካሄደ የ 15 ኪሎሜትር ሩጫ ውድድር በማሸነፍ የመሻሻል አዝማሚያ ቢያሳይም ርቀቱን ከ 42 ደቂቃዎች በታች በሆነ ጊዜ ለማቋረጥ የነበረው ውጥን ሳይሰምርለት ቀርቷል። ሃይሌ ሩጫውን በ 42 ደቂቃ ከ 42 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም ለለንደኑ ኦሎምፒክ ለማለፍ በፊታችን ጥርና የካቲት ዱባይ ወይም ቶኪዮ ላይ በሚካሄዱት የማራቶን ሩጫዎች የመጨረሻ ዕድል ይኖረዋል። ሃይሌ ገ/ሥላሴ ባለፈው መስከረም የበርሊን ማራቶን በትንፋሽ ችግር ሩጫውን አቋርጦ ሲወጣ እስከዚያው ይዞት የቆየው የዓለም ክብረ-ወሰንም በኬንያዊው በፓትሪክ ማካዉ መሰበሩ የሚታወስ ነው።

በትናንትናው ዕለት ዮኮሃማ ላይ በተካሄደ የሴቶች ማራቶን ሩጫ ጃፓናዊቱ ርዮኮ ኪዛኪ የአገሯን ልጅ ዮሺሚ ኦዛኪን በሁለተኝነት አስከትላ ስታሸንፍ የብሪታኒያ ተወዳዳሪ ማራ ያማኢቹ ሶሥተኛ ሆናለች። ከኢትዮጵያ ሮቤ ጉታ ደግሞ ስድሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽማለች። በሌላ የአትሌቲክስ ዜና የጃማይካው የቀድሞ የዓለም ሻምፒዮን ስቲቭ መሊንግስ የተከለከለ የአካል ማዳበሪያ መድሃኒት በመውሰድ በአገሩ የጸረ-ዶፒንግ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ጥፋተኛ መሆኑ ሲረጋገጥ በዛሬው ዕለት እገዳ እንደሚጣልበት እየተጠበቀ ነው። መሊንግስ በ 2009 የበርሊን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአራት ጊዜ አንድ መቶ ሜትር የዱላ ቅብብል ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያ ተሽላሚ መሆኑ ይታወሣል።

Flash-Galerie Rafael Nadal Wimbledon 2011

ራፋኤል ናዳል

ቴኒስ

በለንደን የዓለም የቴኒስ ፍጻሜ ውድድር ራፋኤል ናዳልና ሮጀር ፌደረር ትናንት የመጀመሪያውን መሰናክል በስኬት ለማለፍ ችለዋል። ናዳል በምድብ-ሁለት መክፈቻ ግጥሚያ አሜሪካዊውን ማርዲይ ፊሽን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 ሲያሸንፍ ፌደረርም የፈረንሣይ ተጋጣሚውን ጆ-ዊልፍሪድ-ትሶንጋን በተመሳሳይ ውጤት ረትቷል። በምድብ-አንድ ውስጥ የሚወዳደሩት ኖቫክ ጆኮቪች፣ ኤንዲይ መሪይ፣ ፌሬርና ቤርዲች ናቸው። በነገራችን ላይ ዛሬ የወጣ አዲስ የዓለም የማዕረግ ተዋረድ ዝርዝር የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪችና የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ በየጾታቸው አመራራቸውን ይዘው መቀጠላቸውን አመልክቷል።

በእግር ኳስ ለማጠቃለል በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ 16 ቡድኖች ወደሚቀሩበት ጥሎ ማለፍ ዙር ለመሻገር ወሣኝ የሆኑ ጨዋታዎች የሚገኙባቸው የምድብ ግጥሚያዎች በዚህ ሣምንት ይካሄዳሉ። ከነዚሁ ዓበይት የሆኑትን ለመጥቀስ በነገው ምሽት ከሚካሄዱት መካከል ናፖሊ ከማንቼስተር ሢቲይ፤ ማንቼስተር ዩናይትድ ከቤንፊካ ሊዝበን፤ ሬያል ማድሪድ ከዲናሞ ዛግሬብና ኦላምፒክ ሊዮን ከአያክስ አምስተርዳም ይገኙበታል። በማግሥቱ ረቡዕ ደግሞ ኤ.ሢ.ሚላን ከሻምፒዮኑ ከባርሤሎና፣ ባየር ሌቨርኩዘን ከቼልሢይ፣ ኦላምፒክ ማርሤይ ከኦሎምፒያኮስ ፒሬውስና አርሰናል ከዶርትሙንድ ዋነኞቹ ናቸው።

መሥፍን መኮንን


አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic