የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 14.11.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በሚቀጥለው 2012 ዓ.ም. ኡክራኒያና ፖላንድ በጋራ በሚያስተናግዱት የአውሮፓ አግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን ለቀሩት አራት ቦታዎች ባለፈው ሣምንት የማጣሪያ-ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር።

default

የክሮኤሺያ ቡድን ፈንጠዝያ

በኤውሮው ማጣሪያ እንጀምርና ቼክ ሬፑብሊክ ፕራግ ላይ ሞንቴኔግሮን 2-0 ስትረታ አየርላንድ ታሊን ላይ የባልቲኳን ሬፑብሊክ ኤስቶኒያን 4-0 አሸንፋለች። ክሮኤሺያም እንዲሁ ቱርክን ኢስታምቡል ላይ ግልጽ በሆነ 3-0 ውጤት ስታሸንፍ ቦስናና ፖርቱጋል ደግሞ ባዶ-ለባዶ ተለያይተዋል። አየርላንድና ክሮኤሺያ አስተማማኝ በሆነ የውጭ ድላቸው ወደ ፍጻሜው ለመዝለቅ ብዙ የተቃረቡ ነው የሚመስለው። በመደበኛው ማጣሪያ ዙር በግሪክ ተሽንፎ በቀጥታ ለማለፍ ላልቻለው የክሮኤሺያ ብሄራዊ ቡድን ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠሩት ኢቪትሣ ኦሊች፣ ማሪዮ ማንጁኪችና ቬድራን ቾርሉካ ነበሩ። የክሮኤሺያ ተጫዋቾች ነገ ዛግሬብ ላይ በሚካሄደው የመልስ ጨዋታ ሜዳ የሚገቡት ከፍተኛ በራስ መተማመን በሰፈነበት ሁኔታ ነው።

አየርላንድ ደግሞ ከኤስቶኒያ ባደረገችው ግጥሚያ የአስተናጋጇ አገር ተከላካይ አንድሬይ ስቴፓኖቭ ቀይ ካርድ ተሰጥቶት ገና ከአረፍት በፊት ከሜዳ በመውጣቱ በከፍተኛ ውጤት ለማሸነፍ ዕድሉን በሚገባ ተጠቅማበታለች። በነገው ምሽት ዳብሊን ላይ በሚካሄደው የመልስ ግጥሚያ ኤስቶኒያ አራት ለዜሮውን ውጤት መለወጥ መቻሏ ሲበዛ የሚያጥራጥር ነው። በሌላ በኩል የተቀሩት ሁለት ማጣሪያ ግጥሚያዎች ገና ያልለየላቸው ናቸው። የሞንቴኔግሮ ቡድን ምንም እንኳ ፕራግ ላይ 2-0 ተሸንፎ ቢመለስም ውጤቱን ነገ በአገሩ ሊለውጠው ይችል ይሆናል። ቦስናን የምታስተናግደው ፖርቱጋል በአንጻሩ ከመጀመሪያው ዙር ባዶ-ለባዶ ውጤት በኋላ በጣሙን መጠንቀቅ ይኖርባታል። ምክንያቱም ከ 0-0 በላይ የሆነ እኩል ለአኩል ውጤት ለቦስና የሚበጅ በመሆኑ ነው።

ለማንኛውም የኤውሮ-ማጣሪያ ከነገዎቹ አራት የመልስ ግጥሚያዎች በኋላ የሚጠቃለል ሲሆን በአንጻሩ ከሶሥት ዓመታት በኋላ ብራዚል ውስጥ ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ደግሞ ማጣሪያው ቀጥሏል። አፍሪቃ ውስጥ ወደ ምድቡ ዙር ለማለፍ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄዱት የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ባዶ-ለባዶ ተለያይታለች። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አንድ ተጫዋቹ በ 60ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳ ወጥቶበት በጎዶሎ ቢጫወትም ሶማሊያ ዕድሉን ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ኢትዮጵያ በፊታችን ሰንበት አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደው ግጥሚያ አሸናፊ እንደምትሆን በሰፊው ቢገመትም ሶማሊያም ጎል ማስቆጠር ከቻለች ወደ ምድቡ ዙር ለመሻገር 1-1 ውጤት ይበቃታል። ግጥሚያው በሞቃዲሾ የጸጥታ ሁኔታ አስጊነት የተነሣ የተካሄድ ጂቡቲ ውስጥ ነው።

አንድ ቀን ቀደም ሲል ባለፈው አርብ ደግሞ ሤይሼልስ ከኬንያ 0-3፤ ጊኒ ቢሣው ከቶጎ 1-1፤ ጂቡቲ ከናሚቢያ 0-4፤ ኮሞሮዎች ከሞዛምቢክ 0-1፤ ኤኩዋቶሪያል ጊኒ ከማዳጋስካር 2-0፤ ሌሶቶ ከቡሩንዲ 1-0፤ ኤርትራ ከሩዋንዳ 1-1፤ ስዋዚላንድ ከዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ 1-3፤ እንዲሁም ሣኦ ቶሜ ፕሪንሢፔና ኮንጎ ብራዛቪል 0-5 ተለያይተዋል። ሰንበት ባለው በደቡብ አሜሪካው ማጣሪያ ምድብ ሶሥተኛ ግጥሚያ ባለፈው አርብ አርጄንቲና በገዛ ሜዳዋ ቦሊቪያን ማሸነፍ ተስኗት 1-1 በሆነ ውጤት ተወስናለች። አርጄንቲና ባለፈው ወር በቬኔዙዌላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሸነፍ አሁን ከሶሥት ግጥሚያዎች በኋላ በአራት ነጥቦች የምድቡ ሶሥተኛ ናት። ቡድኑ ነገ ለሚያካሂደው አራተኛ ግጥሚያ ትናንት ወደ ኮሉምቢያ ተጉዟል።
የሁለት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ኡሩጉዋይ በአንጻሩ ባለፈው ዓመት በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ወቅት ባሳየችው ጥንካሬዋ በመቀጠል ቺሌን ሞንትቴቪዴዎ ላይ 4-0 ስትሸኝ የደቡብ አሜሪካውን ምድብ በሰባት ነጥቦች ለብቻዋ ትመራለች። ለኡሩዎች አራቱንም ጎሎች’ ያስቆጠረው ድንቁ አጥቂ ሉዊስ ስዋሬስ ነበር። ኡሩጉዋይ በነገው ዕለት ደግሞ ሮማ ላይ ከኢጣሊያ የወዳጅነት ግጥሚያ ታካሂዳለች። በደቡብ አሜሪካው ምድብ ኮሉምቢያ፣ አርጄንቲና፣ ፓራጉዋይና ቬኔዙዌላ በእኩል አራት ነጥብ ኡሩጉዋይን የሚከተሉ ሲሆን ኮሉምቢያ ገና አንድ ጨዋታ ይጎላታል።
በነገራችን ላይ ብራዚል አስተናጋጅ አገር በመሆኗ በማጣሪያው አትሳተፍም። በቀጥታ ወደ ፍጻሜው ዙር አልፋለች። ዘጠኝ አገሮችን ካቀፈው የደቡብ አሜሪካ ማጣሪያ ምድብ የመጀመሪያዎቹ አራት ቡድኖች በቀጥታ ለፍጻሜ የሚያልፉ ሲሆን አምሥተኛው ደግሞ ለተሳትፎ ለመብቃት ከሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ ከኮንካካፍ ምድብ አራተኛ ጋር መጋጠም ይኖርበታል። የእሢያው ማጣሪያም ከነገው ግጥሚያዎች በኋላ ወደ አራተኛ ዙሩ ይሽጋገራል። ለዚሁ አሥሩ የመጨረሻ አገሮች ለሚዘልቁበት ዙር ለመድረስ ከወዲሁ እንደሚታየው አውስትራሊያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ኡዝቤኪስታንና ሳውዲት አረቢያ ጥሩ ዕድል አላቸው። የሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ ማጣሪያም ወደ ሁለተኛው ዙር ሲሻገር ከአካባቢው ሃያላን ከሜክሢኮና ከዩ.ኤስ.አሜሪካ ጋር በውድድሩ የሚቀጥሉት ኮስታሪካ፣ ኒካራጉዋ፣ ጃሜይካ፣ ኩባ፣ ኤል-ሣልቫዶር፣ ካናዳ ፓናማና ጉዋቴማላ ይሆናሉ።

Fußball Freundschaftsspiel Ukraine gegen Deutschland November 2011

ኡክራኒያ

የወዳጅነት ግጥሚያዎች

በተቀረ በዓለምአቀፍ ደረጃ በርከት ያሉ የእግር ኳስ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ሲካሄዱ እንግሊዝ የአውሮፓና የዓለም ሻምፒዮን የሆነችውን ስፓኝን በዌምብሌይ ስታዲዮም 1-0 ለማሸነፍ ችላለች። ፍራንክ ላምፓርድ ብችኛዋን ጎል ሲያስቆጥር ድሉ ምናልባት ከእንግሊዝ ቡድን ጥንካሬ ይልቅ የስፓኝ አጥቂዎች ዕድላቸውን አለመጠቀማቸው የወለደው ነው የሚመስለው። እንግሊዝ በነገው ምሽት በዚያው በዌምብሌይ ከስዊድን ጋር የምትጋጠም ሲሆን ብቃቷን ለማስመስከር ተጨማሪ ዕድል ይጠብቃታል። ፈረንሣይ ዩ.ኤስ.አሜሪካን 1-0 ስትረታ ነገ ደግሞ ቤልጂግን ታስተናግዳለች። ኢጣሊያ የኤውሮ-2012 አብሮ አስተናጋጅ የሆነችውን ፖላንድን በአዲሱ የብሮስላቭ ስታዲዮም 2-0 ስታሸንፍ ጀርመን ደግሞ ከሌላዋ አዘጋጅ ከኡክራኒያ ኪዬቭ ላይ 3-3 ተለያይታለች።

የኡክራኒያ ቡድን በመጨረሻ ድሉን ያጣው ፈጣን በሆነ የማጥቃት አጨዋወት ሶሥት-ለአንድ ከመራ በኋላ ነው። አንዳንድ የጎል ዕድሎችም በከንቱ አምልጠውታል። የጀርመኑ አሠልጣኝ ዮዓኺም ሉቭ በበኩሉ ምንም እንኳ ተከላካዮቹ ከአንዴም ብዙ ጊዜ ሲንገዳገዱ ይታዩ እንጂ አዲስ ዘዴ ለመፈተሽ ያደረገው ሙከራ የተሳካ እንደነበር ነው የተናገረው።

“የመጣነው ለሙከራ በመሆኑ ብዙ ጠቃሚ ግንዛቤ ይዘን ነው የምንመለሰው። በዚህ በአውሮፓ ዋንጫ ውድድር ዋዜማ ሙከራ የማድረግ መብት አለን። ለነገሩ ቡድናችን የነበረውን ውጤት መልሶ በመቀልበስ ጥሩ ሞራል እንዳለው አስመስክሯል። ለነገሩ ጨዋታውን በሰፊው በመቆጣጠራችንም ያን ያህል ያልረካሁ አይደለሁም”

የሆነው ሆኖ ጀርመን በነገው ምሽት ከብርቱ ተፎካካሪዋ ከኔዘርላንድ ጋር የምትጋጠም ሲሆን ከሽንፈት ለመዳን ከኪየቩ የበለጠ ስክነት ሊኖራት እንደሚገባ አንድና ሁለት የለውም። በተቀሩት የወዳጅነት ግጥሚያዎች ሜክሲኮ ከሰርቢያ 2-0፤ ዌልስ ከኖርዌይ 4-1፤ ደቡብ አፍሪቃ ከአይቮሪ ኮስት 1-1፤ ኔዘርላንድ ከስዊስ 0-0፤ እንዲሁም ግሪክና ሩሢያ 1-1 ተለያይተዋል።

IAAF Leichtathletik Weltmeisterschaft Usain Bolt

የዓመቱ ድንቅ አትሌት ቦልት

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት ግሪክ ውስጥ በተካሄደው በዘንድሮው የአቴን ክላሢክ ማራቶን ሩጫ በወንዶች የሞሮኮው አብደልክሪም ቡብከር ሲያሸንፍ የኬንያ ተወዳዳሪዎች ሣሚይ ኪፕኮስጋይና ዳኒዬል ጋቴሩ ሁለተኛና ሶሥተኛ ሆነዋል። በሴቶች ለድል የበቃችው ደግሞ ኢትዮጵያዊቱ አትሌት እልፍነሽ መላኩ ነበረች። ሩሢያዊቱ ካሚላ ካኒፖቫ ሁለተኛ ስትወጣ ቱኒዚያዊቱ አሚራ ቤን አሞር ሩጫውን በሶሥተኘት ፈጽማለች። ኮረብታ በሚበዛው የአቴን ማራቶን ላይ ቅዝቃዜና መለስተኛ ዝናብ ታክሎ እንደተለመደው ብዙም ክብደት የሚሰጠው ፈጣን ጊዜ አልተመዘገበም። የአቴኑ ክላሢክ ማራቶን እንደሚተረከው በፋርስ ጦር ላይ የተገኘ ድልን ለአቴናውያን ለማብሰር የግሪኩ መልዕክተኛ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 490 ማራቶን ከተሰኘችው መንደር አጠገብ ተነስቶ የሮጠበትን መስመር የተከተለ ነው። በዚሁ የማራቶን ርቀት፤ እንዲሁም አጠር ባሉ የአምሥትና የአሥር ኪሎሜትር ሩጫዎች 18 ሺህ ሰዎች ተሳትፈዋል።

የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ባለፈው አርብ ሞናኮ ላይ ባደረገው ታላቅ የስፖርት ምሽት የዓመቱን የዓለም ድንቅ አትሌቶች መርጦ ሰይሟል። በወንዶች የጃማይካው መንኮራኩር ዩሤይን ቦልት ለሶሥተኛ ጊዜ ለዚህ ታላቅ ክብር ሲበቃ በሴቶች ደግሞ የመቶ ሜትር መሰናክል ሩጫ የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው አውስትራሊያዊቱ ሤሊይ ፒርሰን በአንደኝነት ተመርጣለች። ቦልት በድንቅ አትሌትነት ሊመረጥ የበቃው የቅርብ ተፎካካሪዎቹን የአገሩን ልጅ ዮሃን ብሌክንና የኬንያውን ወጣት አትሌት ዴቪድ ሩዲሻን ጠባብ በሆነ የድምጽ ልዩነት በመብለጥ ነው። ፒርሰንን በመፎካከር በዕጩነት የቀረቡት ደግሞ ኬንያዊቱ የረጅም ርቀት ኮከብ ቪቪያን ቼሩዮትና የኒውዚላንዷ አሎሎ ወርዋሪ ቫሌሪይ አዳምስ ነበሩ።

ዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ባለፉት 23 ዓመታት የዓለም ድንቅ አትሌቶችን እየመረጠ ሲሸልም ለዚህ ታላቅ ክብር ከበቁት ድንቅ የስፖርት ሰዎች መካከልም ሃይሌ ገ/ሥላሴ፣ ቀነኒሣ በቀለ (ለዚያውም ሁለቴ)፤ እንዲሁም መሠረት ደፋር ይገኙበታል። በነገራችን ላይ እንደ ዩሤይን ቦልት ሁሉ ከዚህ ቀደም ሶሥቴ ለመመረጥ የበቃው የሞሮኮው ሂሻም-ኤል-ጉዌራይ ብቻ ነበር።

Formel 1 Lewis Hamilton an der Spitze

ሉዊስ ሃሚልተን

ፎርሙላ-አንድ

በትናንትናው ዕለት አቡ ድሃቢ ላይ በተካሄደው የፍርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ጀርመናዊው የዓለም ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል ምንም እንኳ ከመጀመሪያው ረድፍ ቢነሣም እንደተለመደው ለድል ሳይበቃ ቀርቷል። ፌትል በመጀመሪያ ጎማ ሲፈነዳበትና ከዚያም ሌሎች ቴክኒካዊ እክሎች ሲገጥሙት የኋላ ኋላ እሽቅድድሙን ማቋረጡ ግድ ነው የሆነበት። በአንጻሩ የብሪታኒያው ዘዋሪ ሉዊስ ሃሚልተን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ባሳየው ግሩም አነዳድ ለአንደኝነት ሲበቃ የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ሌላው የብሪታኒያ ተወዳዳሪ ጄሰን ባተን ሶሥተኛ ሆኗል። ፌትል በትናንቱ ሽንፈት የሰባት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን ሚሻዔል ሹማኸር በአንድ የውድድር ወቅት ውስጥ 13 ጊዜ በማሽነፍ ካስመዘገበው ክብረ-ወሰን መድረሱ ሲያመልጠው በተለይም በዕለቱ ባጋጠመው ችግር ማዘኑ አልቀረም።

“እርግጥ ሁኔታው መቼም ያናድዳል። ዛሬ አውቶሞቢላችን በጥሩ ሁኔታ ላይ ነበር። ፊት ለመሽቀዳደም በሚበቃበት ሁኔታ ላይ ነበር ለማለት እችላለሁ። ግን አልሆነም። እናም ችግሩ ምን እንደነበረ መረዳት እንደምንችል ተሥፋ አደርጋለሁ”

ፌትል በዚህ ዓመት ለ 11 ድሎች ሲበቃ የዘንድሮው የውድድር ወቅት ሊያበቃ ከእንግዲህ የቀረው መጪው የብራዚል ጋራንድ-ፕሪ ብቻ ነው።

Wimbledon Roger Federer

ሮጀር ፌደረር

ቴኒስ

የስዊሱ ተወላጅ ሮጀር ፌደረር ትናንት በፓሪስ ማስተርስ ፍጻሜ ግጥሚያ ፈረንሣዊ ተጋጣሚውን ጆ-ዊልፍሪድ-ሶንጋን በሁለት ምድብ ጨዋታ ለማሽነፍ በቅቷል። ፌደረር በዚሁ የፓሪስ ቤርሢይ ማስተርስ ፍጻሜ ሲያሸንፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ይሄውም በዚህ ዓመት ከዶሃና ከትውልድ ስፍራው ከባዝል ቀጥሎ ሶሥተኛ ድሉ መሆኑ ነው። የስዊሱ ተወላጅ ሽልማቱን በተቀበለበት ወቅት ወቅቱን በታላቅ ጉጉት ሲጠብቀው እንደቆየና ሕልሙ እንደነበርም ተናግሯል። ፌደረር በፓሪሱ ሮላንድ ጋሮስና በቤርሢይ ሁለቱንም የፓሪስ ውድድሮች ሲያሸንፍ ከአንድሬ አጋሢ ቀጥሎ ሁለተኛው ተጫዋች ይሆናል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic