የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 10.10.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ጀርመናዊው ወጣት የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ትናንት ጃፓን ላይ ተካሂዶ በነበረው እሽቅድድም ሶሥተኛ ቢወጣም በአጠቃላይ ነጥብ እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም የዓለም ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል።

default

በመጪው ዓመት በኡክራኒያና በፖላንድ የጋራ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ለመድረስ የሚደረገው የምድብ ማጣሪያ በመጠቃለል ላይ ነው። በምድብ-አንድ ጀርመን ቱርክን አስደናቂ በሆነ አጨዋወት 3-1 በመርታት እስካሁን ዘጠኝ ግጥሚያዎቿን በሙሉ በማሸነፍ ከወዲሁ ለፍጻሜ ማለፏን አረጋግጣለች። የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ጥንካሬ ከወዲሁ ለአውሮፓ ዋንጫ ባለቤትነት ዕጩ እያደረገው ነው። አሠልጣኙ ዮአኺም ሉቭም በውጤቱና በቡድኑ አጨዋወት እርካታውን መግለጹ አልቀረም።

“እርግጥ ጥቂት የጎል ዕድሎቻችንን በአግባብ ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል። ሆኖም እዚህ በ 50 ሺህ ተመልካቾች ፊት የቱርክ ቡድን በስሜት በሚታገልበት ሁኔታ ድሉ ክብደት የምሰጠው ነው’”

Bastian Schweinsteiger

ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር

በአንዲት ነጥብ ልዩነት የሚከተሉት ቤልጂግና ቱርክ ግን በሁለተኝነት ለማለፍ የነገውን ምሽት የመጨረሻ ግጥሚያ ውጤት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ቱርክ ከአዘርባይጃን የምትገናኝ ሲሆን ከባዱ ጨዋታ የሚጠብቃት እርግጥ ከጀርመን የምትጋጠመው ቤልጂግ ናት።
በምድብ ሁለትም ሩሢያ ለፍጻሜ ለማለፍ ስትቃረብ አየርላንድ በሁለተኝነት ለማለፍ ከአርሜኒያ በምታደርገው ግጥሚያ አንዲት ነጥብ ይበቃታል። በምድብ-ሶሥት ኢጣሊያ በአንደኝነት ስታልፍ ሰርቢያ ኤስቶኒያን ቀድማ በሁለተኝነት ከፍጻሜው ዙር ለመድረስ በነገው ምሽት ስሎቬኒያን መርታቷ ግድ ነው። በምድብ-አራት ማጣሪያውን የማለፍ ዕድል ያላቸው ፈረንሣይና ቦስና-ሄርሤጎቪና ሲሆኑ ፈረንሣይ የጎላ ዕድል ያላት ይመስላል። በምድብ-አምሥት ውስጥ ኔዘርላንድ አንዲት ነጥብ ሳታስነካ በዘጠኝ ግጥሚያዎች 27 ነጥቦችን በመያዝ የፍጻሜ ተሳታፊ ስትሆን ሁንጋሪያን በሶሥት ነጥብ ብልጫ የምታስከትለው ስዊድን በሁለተኝነት ለማለፍ ጥሩ ዕድል ነው ያላት። ለንጽጽር ያህል ስዊድን በነገው ምሽት የምትጋጠመው ከኔዘርላንድ ሲሆን ሁንጋሪያ የምታስተናግደው ፊንላንድን ነው።

ከምድብ-ስድሥት ግሪክ ለፍጻሜው ዙር ለመድረስ አንዲት ነጥብ ትበቃታለች። በሁለት ነጥቦች ዝቅ ብላ የምትከተለው ክሮኤሺያም ግሪክ ከተሸነፈችላት ጥሩ ዕድል ይኖራታል። ከምድብ-ሰባት እስከ ዘጠን ደግሞ ስፓኝና እንግሊዝ፤ እንዲሁም የፖርቱጋልና የዴንማርክ አሸናፊ ከመጨረሻዎቹ 16 አገሮች መካከል የሚመደቡት ናቸው።

በመጪው ዓመት በኤኩዋቶሪያል ጊኒና በጋቦን የጋራ አስተናጋጀት ለሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጽሜ ውድድር ሰንበቱን በተካሄዱት ግጥሚያዎች ላይቤሪያ ከማሊ 2-2፤ ካፕ-ቬርዴ ከዚምባብዌ 2-1፤ ኢትዮጵያ ከማዳጋስካር 4-2፤ ናይጄሪያ ከጊኒ 2-2፤ ዛምቢያ ከሊቢያ 0-0፤ ሞዛምቢክ ከኮሞሮስ 3-0፤ ጋምቢያ ከቡርኪና ፋሶ 1-1፤ ግብጽ ከኒጀር 3-0፤ ደቡብ አፍሪቃ ከሢየራሌዎን 0-0፤ ሱዳን ከጋና 0-2፤ ኡጋንዳ ከኬንያ 0-0፤ ቻድ ከማላዊ 2-2፤ ቱኒዚያ ከቶጎ 2-0 ተለያይተዋል።

ትናንትና ከትናንት በስቲያ ከተካሄዱት ግጥሚያዎች በኋላ አንጎላ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ሊቢያ፣ ማሊ፣ ኒጀር ቱኒዚያ፣ ዛምቢያ፣ ሞሮኮና ሱዳን ለፍጻሜው ዙር ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ ያለፈው የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ ደቡብ አፍሪቃ አደናጋሪ በሆነው የውድድሩ ደምብ መሠረት ከወዲሁ ተሰናክላ ቀርታለች። የደቡብ አፍሪቃ ተጫዋቾች፣ አሠልጣኝና ተመልካቾች በሜዳቸው ከሢየራሌዎን ባዶ-ለባዶ ሲለያዩ ውጤቱ የሚበቃ መስሏቸው ፈንድቀው ነበር። ሆኖም ግን ኒጀር፣ ደቡብ አፍሪቃና ሢየራሌዎን እኩል ዘጠኝ ነጥብ ቢኖራቸውም ደምቡ ትንሿን ኒጀርን አስቀድሟል። አሠልጣኙ ፒትሶ ሞሢማኔ ወሣኙ ነገር የጎል ልዩነት ነው በሚል ኒጀር በግብጽ 3-0 እንደተመራች ለእኩል ለኩል ውጤት ታክቲኩን ቀይሮ ነበር።
ይህ የደምብ ግራ አጋቢነት ነው ደቡብ አፍሪቃን ያሰናከለው። ሌላው ቀርቶ የፌደሬሺኑ ፕሬዚደንት እንኳ በቴሌቪዥን ቡድኑን እንኳን ደስ ያለህ ከማለት ወደ ኋላ አላሉም። የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን እንግዲህ ግራ ተጋብቶ ግራ ከማጋባት ለዓባል ማሕበራቱ መሪዎች እንኳ ግልጽ ያልሆነ ደምቡን ወደፊት የማያሿማ አድርጎ ማስቀመጡ ግድ ነው።

ለማንኛውም በምድብ-ሁለት ላይ እናተኩርና ኢትዮጵያ ማዳጋስካርን 4-2 አሸንፋለች። ይሄውም በአስካሁኑ ማጣሪያ በዚህችው በማዳጋስካር ላይ ሁለተኛው ድል መሆኑ ነው። የምድቡ ቀደምት በ 14 ነጥቦች ማለፏን ያረጋገጠችው ጊኒ ስትሆን ናይጄሪያ በ 11 ነጥቦች ሁለተኛና ኢትዮጵያ ደግሞ በሰባት ነጥቦች ሶሥተኛ ናት። ማዳጋስካርም በአንዲት ነጥብ የመጨረሻ ሆና ቀርታለች። ያሳዝናል፤ አጠቃላዩ የምድቡ የነጥብ ይዞታ ኢትዮጵያን የትም የሚያደርስ አይደለም።

BdT Berlin Marathon

አትሌቲክስ

የኬንያው አትሌት ሞሰስ ሞሶፕ ትናንት በቺካጎ ማራቶን ሩጫ ሁለት የአገሩን ልጆች ዌስሊይ ኮሪርንና በርናርድ ኪፕዬጎን በማስከተል አሸናፊ ሆኗል። ሞሶፕ ሩጫውን በሁለት ሰዓት ከአምሥት ደቂቃ ከ 37 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም ይህም ለቺካጎ ማራቶን አዲስ ክብረ-ወሰን መሆኑ ነው። የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ በካና ዳባ ደግሞ አራተኛ ሆኗል። በሴቶች ሩሢያዊቱ ሊሊያ ሾቡኮቫ ግሩም በሆነ 2 ሰዓት ከ 18 ደቂቃ ከ 20 ሤኮንድ ጊዜ ለተከታታይ ሶሥተኛ ጊዜ አሸናፊ ስትሆን ሩጫውን በሁለተኝነት የፈጸመችው እጅጋየሁ ዲባባ ናት። የሾቡኮቫ ጊዜ የብሪታኒያዋ ፓውላ ሬድክሊፍ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ካስመዘገበችው የዓለም ክብረ-ወሰን በአንዲት ደቂቃ ያህል ብቻ ዘግየት ያለ መሆኑ ነው።

በዚሁ የሩሢያዊቱ አትሌት ልዕልና ጠንክሮ በታየበት ሩጫ በላይነሽ ገብሬ አራተኛ ስትወጣ አስካለ ታፋም ስምንተኛ ሆናለች። የቺካጎው ማራቶን ከስፖርቱ አንጻር አስደናቂ ሆኖ ሲጠናቀቅ በሌላ በኩል የአንድ ተሳታፊ ሞት የጋረደውም ሆኖ ነው ያለፈው። ከአራት ዓመታት በፊት ደርሶ እንደነበረው ሁሉ ትናንትም አንድ የ 35 ዓመት የሰሜን ካሮላይና ነዋሪ ከግቡ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው ተዝለፍልፎ ወድቆ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ ሕይወቱ አልፏል። የሰውዬው መሞት በይፋ የተነገረው ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ነበር።
በሌላ ቦስተን ውስጥ ትናንት በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ የኢትዮጵያው አሊ አብዶሽ የኬንያ ቶፎካካሪውን ሣም ቻሌንጋን በአምሥት ሤኮንዶች ልዩነት በማስከተል አሸናፊ ሆኗል። ከሁለት እስከ ስድሥተኛው ቦታ የተከታተሉት በሙሉ ኬንያውያን ነበሩ። በሴቶቹ ግማሽ ማራቶንም የኬንያ ተወላጅ የሆነችው የአሜሪካ ዜጋ ጃኔት ቼሮቦን ለድል በቅታለች። ያለፈው ጊዜ ሻምፒዮን ኬንያዊቱ ካሮሊን ሮቲች ደግሞ በሁለተኝነት መወሰኑ ግድ ሆኖባታል። ሩጫው የተዘጋጀው የቦስተንን ማራቶን በሚያቀናብረው በቦስተን የአትሌቲክ ማሕበር ነበር።

Sebastian Vettel - Große Preis von Suzuka

ፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም

ጀርመናዊው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ባለፈው ሰንበት በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል። የ 24 ዓመቱ ወጣት ትናንት በጃፓኑ ግራንድ-ፕሪ ሶሥተኛ ሲወጣ ሻምፒዮንነቱን ገና አራት እሽቅድድሞች ቀርተው ሳለ ከወዲሁ ያረጋገጠው በአጠቃላይ ነጥብ የማይደረስበት በመሆኑ ነው። ዜባስቲያን ፌትል ከውድድሩ በኋላ በድሉ የተሰማውን ታላቅ ደስታ በመግለጽ በተለይም ደጋፊዎቹን አመስግኗል።

“በጣም ነው ደስ ያለኝ። ዓመቱን ሙሉ ብዙ ድጋፍ ነበረን። እናም መልካም ዕድል የተመኙልኝን ሁሉ በጣም ነው የማመሰግነው’

በትናንቱ እሽቅድድም የብሪታኒያው ጄሰን ባተን ሲያሸንፍ ሁለተኛ የወጣው ደግሞ የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ነበር። ሁለቱም ለዜባስቲያን ፌትል ያላቸውን አድናቆት ከውድድሩ በኋላ ገልጸዋል። እርግጥ በፌትል ጥንካሬ የተደነቁት የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ብቻ አይደሉም። የጀርመኑ የእግር ኳስ ብሄራዊ ተጫዋች ባስቲያን ሽባይንሽታይገር ሳይቀር በቡድኑ ስም እንኳን ደስ ያለህ ሳይል አላለፈም።

“ሻምፒዮንነቱን በዛሬው ዕለት እንደሚያረጋግጥ የጠበቅኩት ነገር ነበር። በእኔ ዕይታ ጀግና ነው ለማለት እወዳለሁ። በዚህ ወጣት ዕድሜ እንደዚህ ባለ የበላይነት ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን መብቃት አስደናቂ ነገር ነው። ይህ ከዚህ በፊትም አዘውትሮ የታየ ነገር አይመስለኝም። እና ሁላችንም እንደምንኮራበት በመግለጽ በመላው ቡድናችን ስም እንኳን ደስ ያለህ እላለሁ”

ዜባስቲያን ፌትል እስካሁን በተካሄዱት እሽቅድሞች ዘጠኝ ጊዜ ሲያሸንፍ፤ አራት ጊዜ ሁለተኛ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሶሥተኛና አራተኛ ነበር። በቀሪዎቹ አራት እሽቅድድሞችም ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። በወቅቱ በአጠቃላይ 324 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ጄሰን ባተን በ 210 ሁለተኛ እንዲሁም አሎንሶ በ 202 ሶሥተኛ ነው። የሚቀጥለው እሽቅድድም ሣምንት በደቡብ ኮሪያ ይካሄዳል።

Flash-Galerie Andrea Petkovic

ቴኒስ

በቴኒስ ለማጠቃለል በጃፓን ዓለምአቀፍ ፍጻሜ ግጥሚያ የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ ትናንት እጅግ ጠንካራ በሆነ አጨዋወት የስፓኙን ኮከብ ራፋኤል ናዳልን በማሽነፍ በተከታታይ ለሁለተኛ የውድድር ድሉ በቅቷል። የ 24 ዓመቱ ወጣት ባለፈው ሣምንት የታይላንድ-ኦፕን አሸናፊ እንደነበር አይዘነጋም። በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አራተኛ የሆነው መሪይ ደከም ካለ የመጀመሪያ ምድብ ጨዋታ በኋላ ሁለተኛውን ናዳልን ያሽነፈው በለየለት 3-6, 6-2, 6-0፤ ማለት በ 2-1 ውጤት ነበር። በጃፓኑ-ኦፕን በጥንድ ደግሞ ኤንዲይ መሪይና ጄሚይ መሪይ የቼክ-ስሎቫክ ተጋጣሚዎቻቸውን 6-1, 6-4 ረትተዋል። ሻገር ብሎ በቻይና-ኦፕን ፍጻሜም የቼኩ ቶማስ ብርዲች የክሮኤሺያ ተጋጣሚውን ማሪን ቺሊችን በማሽነፍ ለሶሥተኛ የውድድር ድሉ በቅቷል። በሴቶች ፍጻሜ ደግሞ የፖላንዷ አግኒየሽካ ራዶቫንስካ ጀርመናዊቱን አንድሪያ ፔትኮቪችን አሸንፋለች።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic