የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 26.09.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ሃይሌ ገ/ሥላሴ ለሶሥት ዓመታት ጠብቆ ያቆየው የማራቶን የዓለም ክብረ-ወሰን ትናንት በዚያው በተመዘገበበት በበርሊን በኬንያዊው አትሌት በፓትሪክ ማካው ተሰብሯል።

default

ፓትሪክ ማካው

የኬንያው አትሌት ፓትሪክ ማካው ትናንት በዚህ በጀርመን በተካሄደው 38ኛ የበርሊን ማራቶን ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን በማስመዝገብ ሃይሌ ገ/ሥላሤን ከዙፋኑ አውርዷል። የ 26 ዓመቱ ኬንያዊ ባለፈው ዓመትም የበርሊን ማራቶን አሸናፊ እንደነበር የሚታወስ ነው። ማካው ትናንት ሩጫውን በ 2 ሰዓት ከ 3 ደቂቃ ከ 18 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም ሃይሌ ገ/ሥላሴ ከሶሥት ዓመታት በፊት አስመዝግቦት የነበረውን የዓለም ክብረ-ወሰን ያሻሻለው በ 21 ሤኮንዶች ነው። ማካው በውድድሩ ዕለት ጧት ጥሩ ስሜት እንዳልነበረው ሲገልጽ በዚሁ የተነሣም በታላቅ ድሉ ከመጠን በላይ የተደሰተ መሆኑን ነው የተናገረው።

“ከመጠን በላይ ደስተኛ ነኝ። እናም በእግዜር ዕርዳታ እንደዛሬው ግሩሙ ሩጫ ለመሮጥ ተመልሼ እንደምመጣ ተሥፋ አድጋለሁ”
ኬንያውያን የማራቶኑን ድል በሙሉ ሲጠቀልሉ በተለይም በወንዶች ከአንድ እስከ አራት ተከታትለው መግባታቸው በወቅቱ በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫ ሃያላኑ ለመሆናቸው ከቅርቡ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወዲህ እንደገና ተጨማሪ ማረጋገጫ መሆኑ ነው። በነገራችን ላይ በሴቶች አንደኛ የወጣችውም ቀደም ሲል በግማሽ ማራቶን ታዋቂ የነበረችው ኬንያዊት ፍሎሬንስ ኪፕላጋት ናት። የጀርመኗ ተወዳዳሪ ኢሪና ሚቲቼንኮ ሁለተኛ፣ የእንግሊዟ ፓውላ ሬድክሊፍ ሶሥተኛ፤ እንዲሁም አጸደ ሃብታሙ ከኢትዮጵያ አራተኛ ሆናለች።

የዘንድሮው የበርሊን ማራቶን ለሃይሌ ገ/ሥላሴ አሳዛኝ ትውስትን ጥሎ ያለፈ ነው። የአስማ ችግር ያለው ታላቁ አትሌት መተንፈስ ተስኖት ሩጫውን ከ 35 ኪሎሜትር በኋላ ሲያቋርጥ ውድድሩን ለታዘበ ምነው ቀደም ሲል በክብር ተሰናብቶ በነበር ማሰኘቱ አልቀረም። የ 38 ዓመቱ ሃይሌ በዓለምአቀፍ ውድድሮች ያልተጎናጸፈው ድልና ያላገኘው ክብር አይገኝም። በመሆኑም በመሠረቱ ከእንግዲህ የሚያስመሰክረው ምንም ነገር አይኖርም። የትናንቱ የበርሊን ማራቶን ሩጫ ጉልህ አድርጎ ያሳየው ነገር ካለ ድንቁ አትሌት እየጠነከረ ለሄደው ፉክክር ጊዜው ያለፈበት መሆኑን ነው። እርግጥ ማኔጀሩ ጆስ ሄርማንስ በበኩሉ ለጋዜጠኞች እንደገለጸው የሃይሌ ዘመን አላበቃም ባይ ናቸው።
“የምትጠይቁኝ የሃይሌ መጨረሻ ነወይ ብላችሁ ከሆነ፤ የለም መጨረሻው አይደለም። ምናልባት የአዲስ ክብረ-ወሰን ማስመዝገብ ዘመኑ ማብቂያ ይሆናል። ይህ ነው እኔ የሚሰማኝ”

ያም ሆነ ይህ ሃይሌ ገ/ሥላሴ በማራቶን ሩጫ የነ አበበ ቢቂላን ክብር ለማስመለስ ለነበረው ሕልም ትልቁ ዕድል በቤይጂንግ ኦሎምፒክ ወቅት አምልጦታል። ያኔ በአየር ብክለት የተነሣ የመተንፈስ ችግር እንዳይገጥመው ባደረበት ስጋት ከተሳትፎ መቆጠቡን ነበር የመረጠው። አልሆነም። በጥቅሉ ለሃይሌ ከትናንቱ ውድድር ከተገኘው ግንዛቤ በኋላ ስንብት ከማድረግ ሌላ የተሻለ ምርጫ ይኖራል ብሎ መናገር በጣሙን ያዳግታል። በትክክለኛው ሰዓት በቃ ማለት ብልህነት ነው።

Fussball Bundesliga Werder Bremen gegen Hertha BSC Tor Pizarro

ክላውዲዮ ፒሣሮ

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ማንቼስተር ዩናይትድ በስድሥተኛ ግጥሚያው ለመጀመሪያ ጊዜ እኩል ለእኩል በመለያየት የመጀመሪያዋን አንዲት ነጥብ አጥቷል። ሆኖም ማኒዩ ከትናንት በስቲያ ከስቶክ ሢቲይ ጋር 1-1 ይለያይ እንጂ በጎል ብልጫ ማንቼስተር ሢቲይን አስከትሉ ፕሬሚየር ሊጉን መምራቱን እንደቀጠለ ነው። ማንቼስተር ሢቲይ በበኩሉ ግጥሚያ ኤቨርተንን 2-0 አሸንፎ ነበር። ቼልሢይ ደግሞ ስዋንሢ ሢቲይን 4-1 ሲረታ ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ በሶሥተኝነት ይከተላል። አራተኛ ኒውካስል ዩናይትድ፤ አምሥተኛ ሊቨርፑል ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ሰንበቱ የሬያል ማድሪድና የባርሣ እንዲሁም የከዋክብቶቻቸው የክሪስቲያኖ ሮናልዶና የሊዮኔል ሜሢ ነበር ለማለት ይቻላል። ሁለቱም ድንቅ ተጫዋቾች በየፊናቸው ሶሥት ጎሎች በማስቆጠር የድል ዋስትና ነበሩ። ሬያል ማድሪድ ቫሌካኖን 6-2 ሲያሸንፍ ከሮናልዶ ሶሥት ግቦች ባሻገር የተቀሩትን ጎሎች ያስቆጠሩት ጎንዛሎ ሂጉዌይን፣ ካሪም ቤንዜማና ራፋኤል ቫራኔ ናቸው። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ባርሤሎናም አትሌቲኮ ማርዲድን 5-0 ሲሸኝ ክለቡ በአምሥት ግጥሚያዎች 11 ነጥቦችን በመሰብሰብ አሁን ከሬያል ቤቲስ አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። እርግጥ ቤቲስ አንድ ጨዋታ ይጎለዋል። ይሄው ማንም ያልጠበቀው ክለብ ዛሬ ማምሻውን ጌታፌን ካሽነፈ አመራሩን ወደ አራት ነጥቦች ከፍ ሊያደርግም ይችላል። ሬያል ማድርሪድ በበኩሉ አምሥተኛ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ቀደምቱን ክለብ ባየርን ሙንሺንን የሚያቆም ተፎካካሪ አሁንም አልተገኝም። ክለቡ ባለፈው ሰንበት ግጥሚያውም ሌቭርኩዝንን በቀላሉ 3-0 ሲረታ በስድሥት ግጥሚያዎች አንዴም ሳይሸነፍ በበላይነቱ እንደቀጠለ ነው። ጎሎቹን ያስቆጠሩት ቶማስ ሙለር፣ ዳኒየል-ፋን-ቡይተንና አሪየን ሩበን ነበሩ። በተለይም ሆላንዳዊው አርየን ሩበን ከረጅም ጊዜ የመቁሰል እረፍት በኋላ ተመልሶ በመጀመሪያ ጨዋታው ጎል በማግባቱና በተመልካቾቹ በመወደሱ ደስታው ወደር አልነበውም።

“በጣም ነው የተደነቅኩት። እና ደጋፊዎቻችንን በጣም ማመስገን አለብኝ። በዕውነቱ አስደናቂ ነበር። የደጋፊዎቼን ድምጽ ስሰማ መላ ሰውነቴን እንደመንዘር ነው ያደረገኝ”

ባየርን ከስድሥት ግጥሚያዎች በኋላ ሙሉ 18 ነጥቦችን ይዞ የሚመራ ሲሆን ብሬመንና መንሸንግላድባህ ሁለት ነጥቦች ዝቅ ብለው ይከተላሉ። ግላድባህ ኑርንበርግን 1-0 ሲረታ ቬርደር ብሬመን ሁለተኛ ቦታውን መልሶ የያዘው ትናንት ሄርታ በርሊንን 2-1 በማሽነፍ ነው። የድሉ ዋስትና ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ክላውዲዮ ፒሣሮ ነበር። ፒሣሮ የዘንድሮ ሕልሙ ባየርንን መፈታተን እንደሆነ ነው ያመለከተው።

“ጥሩ ነው የምንጫወተው። ፊት ነው ያለነውም። ባየርን ሙንሺን አንዴ እስከሚደናቀፍ እንጠብቃለን። እርግጥ የራሳችንን ስራ መሥራትና በማሸነፍ መቀጠል አለብን። እና ከዚያ በኋላ በመጨረሻ ማን ግንባር ቀደም እንደሚሆን እናያለን”

በሌሎቹ የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች ኮሎኝ ሆፈንሃይምን 2-0፤ ሻልከ ፍራይቡርግን 4-2፤ እንዲሁም ዶትሙንድ ማይንስን 2-1 ሲያሸንፉ አውግስቡርግና ሃኖቨር ደግሞ ባዶ-ለባዶ ተለያይተዋል። በፊታችን ሰንበት ሶሥቱም ቀደምት ክለቦች የሚጫወቱት ከሜዳቸው ውጭ ሲሆን ጠንከር ያለ ትግል ነው የሚጠብቃቸው።

የጀርመን ቡንደስሊጋ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ይህን የመሰለ ሲሆን በዚህ በያዝነው ሣምንት አጋማሽ ላይ ነገና ረቡዕ ደግሞ በከፊል ማራኪ የሆኑ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የምድብ ዙር ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ከነዚሁ መካከል ዋነኞቹ ባየርን ሙንሺን ከማንቼስተር ሢቲይ፣ ሢ.ኤስ.ኬ.ኤ ሞስኮ ከኢንተር ሚላን፣ ሬያል ማድሪድ ከአያክስ አምስተርዳም፣ ቫሌንሢያ ከቼልሢይ፣ እንዲሁም አርሰናል ከኦሊምፒያሎስ ፒሬውስ ናቸው።

Formel 1 Singapur 2011 Sieger Sebastian Vettel

ዜባስቲያን ፌትል

ፎርሙላ-አንድ/ቴኒስ/የቢስክሌት እሽቅድድም

በፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ወጣቱ ጀርመናዊ የሬድ-ቡል ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ጨርሶ የሚበገር ሆኖ አልተገኘም። ፌትል ትናንት በሢንጋፑር ግራንድ-ፕሪ እሽቅድድም እንደገና በፍጹም የበላይነት ሲያሸንፍ ከውድድሩ ፍጻሜ ቀድሞ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን አሁን የምትጎለው አንዲት ነጥብ ብቻ ናት። ዜባስቲያን ፌትል ከባድ በሆነው የውድድር ቦታ እሽቅድድሙን በስኬት በመፈጸሙ ታላቅ ዕፎይታ እንደተሰማው ነው የገለጸው።

“ለዚህ ድል ትልቅ ግምት ነው የምሰጠው። ቦታውን እወደዋለሁ። እርግጥ ውድድሩ ከባድ ከሚባሉት አንዱ ነው። ስህተት የመስራት አንዳች ጊዜ የለም። እናም ታዲያ ከግብ ሲደረስ ትልቅ ሸክም ነው የሚቃለለው”
የ 24 ዓመቱ ወጣት በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ በጃፓን በሚካሄደው እሽቅድድም ጠቅላላ ድሉን እንደሚያረጋግጥ የሚጠራጠር የለም።

በፈረንሣይ-ሜትስ የቴኒስ ኤ.ቲፒ. ውድድር ፍጻሜ ግጥሚያ የአገሪቱ ተወላጅ ጆ-ዊልፍሪድ-ትሶንጋ የክሮኤሺያ ተጋጣሚውን ኢቫን ሉቢቺችን በሶሥት ምድብ ጨዋታ ሁለት-ለአንድ በማሸነፍ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ የውድድር ድሉ በቅቷል። ትሶንጋ በዚህ ዓመት ለሮተርዳምና ለኩዊንስ ፍጻሜ ደርሶ ሲሸነፍ የመጨረሻ ድሉን ያስመዘገበው በ 2009 ዓ.ም. በቶኪዮ ነበር። በቡካሬስት ዓለምአቀፍ የወንዶች ፍጻሜ ግጥሚያ ጀርመናዊው ፍሎሪያን ማየር የስፓኝኙን ፓብሎ አንዲሃርን 6-3, 6-1 አሸንፏል። በደቡብ ኮሪያ በሆንሶል-ኦፕን ደግሞ የስፓኟ ማሪያ-ሆሴ-ማርቲኔዝ-ሣንቼዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜ የደረሰች የካዛክስታን ተጋጣሚዋን ጋሊና ቮሽኮቦየቫን በማሸነፍ የ 220 ሺህ ኤውሮ ተሸላሚ ሆናለች።

መሥፍን መኮንን


Audios and videos on the topic