የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 29.08.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ደቡብ ኮሪያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር እሁድ በ 10,000 ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያ የወርቅና የነሀስ ሜዳይ አገኘች። አርሰናል በማንቸስተር ዩናይትድ አይቀጡ ቅጣት ተቀጣ። መድፈኞቹ የእሁዱን 8 ለ 2 አንገፍጋፊ የሽንፈት ፅዋ እየተናነቃቸው ሲጎነጩ ከ15 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያቸው መሆኑ ነው።

default

ኢብራሒም ጄላን ደቡብ ኮሪያ ውስጥ አሸንፎ

ተቀናቃኞቹ ሊቨርፑል እና ቸልሲ እጅ ለእጅ ተያይዘው መከረኛውን አርሰናል ቁልቁል እየተመለከቱ ደረታቸውን ገልበጥ አድርገዋል። ሁለቱን ማንቸስተሮች ግን የሚስተካከላቸው አልተገኘም።

ዝርዝሩን ከሌሎች የፕሪሚየር ሊግ ዘገባዎች ጋር አቀናጀተን ከቡንደስ ሊጋ ትንታኔ በኋላ እናቀርባለን። እሁድ የተጀመረውን የስፔን ላሊጋ ጨረፍ አድርገን ደግሞ በሜዳ ቴኒስ አጠር ያለ ዘገባ እናሳርጋለን።

በመጀመሪያም አትሌቲክስ ኢትዮጵያዊው አትሌት ኢብራሒም ጄላን ደቡብ ኮሪያ ዴጉ ውስጥ በተካሄደ የዓለም አትሌቲክ የሩጫ ውድድር ትናንት አሸናፊ ሆነ። ኢብራሒም የ10,000 ሜትር ውድድሩ ማብቂያ ዙር ላይ ቀድሞ የወጣውን እንግሊዛዊ አትሌት ተስፈንጥሮ በመቅደም ነበር የወርቅ ባለድል ሊሆን የቻለው። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ የማነ መርጋ በሶስተኝነት አጠናቆ እሱም ለሐገሩ የነሐስ ሜዳይ አስገኝቷል። በዓለም አቀፍ ውድድሩ ለአምስተኛ ግዜ ወርቅ ለማግኘት አልሞ የነበረው ጀግናው ቀነኒሳ በቀለ በህመም ውድድሩን አቋርጦ መውጣቱ ታውቋል። ይሁንና ግን የሀገሩ ልጅ ሌላኛው ወጣት ጀግና ኢብራሒም ጄላን ወርቁ ከኢትዮጵያውያን እጅ እንዳይወጣ ተፋልሞ ተሳክቶለታል።

የሚገርመው ነገር የዛሬ አስር ዓመት ግድም ለአምስተኛ ግዜ ወርቅ ለማስግኘት የተወዳደረው ጀግናው አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ በሶስተኛነት ሲያጠናቅቅ ተስፈንጥሮ በመውጣት ወርቁን ያስጠበቀ አለመኖሩ ነው። ዘንድሮ ግን ቀነኒሳ ባይሳካለት ሌላኛው ተተኪ ወጣት አትሌት ተሳክቶለታል። በረዥም ርቀት ውድድር ሀያል የነበረችው ኢትዮጵያ መሰል ወጣቶችን በብዛት እና በአስተማማኝ ማፍራት አለመቻሏ ብዙዎችን ያሳሳበ ጉዳይ ሆኗል። በእሁዱ ውድድር ኢብራሒም ጄላን ውድድሩን በአንደኛነት አጠናቆ ወርቅ ሲጎናፀፍ ሩጫውን ያገባደደው በ27 ደቂቃ ከ13.81 ሰከንድ ነበር። እንግሊዛዊው Mohamed Farah በ 27 ደቂቃ ከ14,07 ሰከንድ እንዲሂም ሌላኛው ኢትዮጵያዊ የማነ መርጋ በ 27 ደቂቃ ከ19,14 ሰከንድ በማሸነፍ የብር እና የነሀስ ሜዳይ ተሸላሚ ሊሆኑ ችለዋል። በትናንትናው ውድድር የመጨረሻ ዙር ላይ ቀድሞ የወጣው እንግሊዛዊ የወርቁ ባለቤት እንደሚሆን ፈፅሞ አልተጠራጠረም ነበር።

ድንገት ከኋላው ኢትዮጵያዊው ወጣት ጀግና እንደ አቡሸማኔ ተወርውሮ በመውጣት እንግሊዛዊውን አርዶ ጉድ አድርጎታል። ባልጠበቀው ሁኔታ የተረታው ዝንግሊዛዊ አትሌት ስለ ኢብራሒም ጄላን አስደናቂነት ሲገልፅ « ስለሰውዬው ምንም ፍንጭ አልነበረኝም። ምን ያህል ብቃት እንዳለውም አላውቅም ነበር። እውነቱን ለመናገር 300 ሜትር ሲቀረው ወርቁን ያገኘሁ መስሎኝ ነበር» ሲል ሽንፈቱን በቁጭት ገልጿል። አከል አድርጎም «በመጨረሻው ዙር ከጀርባዬ ስመለከተው ዘና ለማለት ሞከርኩ። እናም ለራሴ ዘና ብዬ ግን በፍጥነት እንድጨርስ ነገርኩት፤ ግን የሆነው ሌላ ነው። እግሮቼ ራዱ፣ ቁርጠትም ለቀቀብኝ» ሲል የተሰማውን ስሜት ሳይደብቅ ገልጿል።

በሴቶች የ10,000 ሜትር የሩጫ ውድድር ግን ኬንያውያንን የሚስተካከላቸው አልተገኘም። ከነሐስ አስቶ እስከወርቅ፤ ሜዳዩን ባጠቃላይ ኬንያውያን ጠራርገው ወስደዋል። በዚህም መሰረት እስከትላንቱ ውጤት ኬንያ በ 2 ወርቅ፣ 2 ብር እና 2 ነሐስ አንደኛነቱን ጨብጣለች። ዩናይትድ ስቴትስ በ2 ወርቅ እና 2 ብር ያለነሀስ ሜዳይ በሁለተኛነት ትከተላለች። ሩሲያ በ1 ወርቅ እና በ2 ብር ሶስተኛ ስትሆን፤ ኢትዮጵያ በ1 ወርቅ እና በ1 ነሐስ በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ጀርመን ያለምንም ወርቅ 1 የብር ሜዳይ ይዛ በስምንተኛ ደረጃ ላይ ናት። ለጀርመን ናዲኔ ሙለር ነሐስ ያስገኘችው በቅዝምዝም ውርወራ ነው። ጀርመናዊቷ ደስታዋን ስትገልፅ፥

Nadine Mueller

ጀርመናዊቷ ናዲኔ ሙለር ለሐገሯ ነሐስ አስገኝታለች

«በቃ ድንገት ልዩ ስሜቴ ውስጤን ፈንቅሎት ነበር። ትክክለኛው ሰዓት ላይ የተጮኸ የደስታ ጩኸት ነበር፤ አሁን አልፏል ግን ነሐስ ይዤ ወደቤቴ እመለሳለሁ። እጅግ በጣም በጣም ደስ ብሎኛል። የምር የማይታመን ነገር ነው።»

አሁን ወደ ጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ እናቀናል። ከዚያም የእንግሊዙን ፕሬሚየር ሊግ ትንታኔ እናስከትላለን። ከአርብ ጀምሮ በተከናወነው አራተኛው ዙር የጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ውድድር ውጤት ባየር ሙኒክ፣ ሻልካ እና ዌቬርደር ብሬመን ከአንደኛ እስከሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ባየር ሙኒክ ካይዘር ላውተርንን 3 ለ0 አሸንፏል። በእለቱ ማሪዮ ጎሜዝ ሶስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሀት ትሪክ ሰርቷል። በ55ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የፍፁም ቅጣት ምት ስቷል። ካይዘር ላውተርንኖች በ90ኛው ደቂቃ ላይ ኢቮ ሌቼቪች የተሰኘውን ተጫዋቻቸውን በቀይ ካርድ ከሜዳ አጥተዋል። ብሬመን ሆፈንሀይምን 2 ለ 1፣ ሻልካ ቦሩሲያ ሞንሼንግላድባህን 1 ለ ላባዶ አሰናብተዋል። ማሰራጫ ጣቢያችን ከሚገኝበት ከቦን ከተማ ብዙም የማይርቀው የኮሎኝ ከተማ ቡድን ኮሎኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳክቶለት ሀምቡርግን 4 ለ 3 ለማሸነፍ ችሏል። ፍራይቡርግ ዎልፍስቡርግን 3ለ 0፣ ኑረምበርግ አውስቡርግን 1 ለ ምንም እንዲሁም ሄርታ ቤርሊን ሽቱትጋርትን 1 ለዜሮ በማሸነፍ ነጥብ ይዘው ወጥተዋል። ማይንዝ ከከሀኖቨር 1ለ1፣ባየር ሌቨርኩሰን ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ባዶ ለባዶ ተለያይተዋል።

በዚህም መሰረት ባየር ሙኒክ፣ ሻልካ እና ቬርደር ብሬመን በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ባየር ሙኒክን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሻልካ ትናንት አሸናፊ ለመሆን የበቃው በስፔናዊው አጥቂ ራውል ጥረት ነበር። ራውል በ64ኛው ደቂቃ ላይ ነው ሻልካን አሸናፊ ያደረገችውን ግብ ከመረብ ያሳረፈው።

ከዛው ከእግር ኳስ ሳንወጣ አሁን የምንሸጋገረው ወደ እንግሊዝ ይሆናል። በሳምንቱ ማገባደጃ ላይ ከተከናወኑ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች መካከል ዛሬም ድረስ የብዙዎች መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ የቆየው የመድፈኞቹ ዳግም መንኮታኮት እና የማን ዩናይትዶች ፍፁም ሃያል ሆኖ መቆየት ነው። አርሰናል ከ15 ዓመታት ወዲህ አይቶት የማያውቀውን ከባድ ሽንፈት በኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም ሳይወድ ተቀብሏል። የማንቸስተሮቹ እነ ሩኒና አሽሌ ያንግ በመድፈኞቹ መድፍ አልባ የግብ ክልል እየተመላለሱ መድፈኞቹን ያለተከላካይ ሲደበድቡ ነበር ያመሹት። ለማንቸስተር የግብ ሲሳይ ለአርሰናል የመከራ ውርጅብኝ በሆነው አጋጣሚ አርሰናሎች ሩኒ አርሰናል ላይ ሶስት ግብ አግብቶ ሀትትሪክ ተሳክቶለታል። አሽሌ ያንግ ሁለት፣ ናኒ፣ ዳኒ ዌልቤክ እና ፓርክ አንድ አንድ ደርሷቸዋል። በጥቅሉ ማንቸስተር አርሰናል ላይ 8 ጎሎችን አከታትሎ በማስገባት መድፈኞቹን የፕሬሚየር ሊጉ የጎል ጎተሮች አሰኝቷል። መድፈኞቹ ተንገታግተውም ቢሆን ማንቸስተር ላይ ሁለት ግቦችን በማስገባት በዜሮ ከመውጣት ድነዋል።

የአርሰናል አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ሽንፈት እንደተፈራው ቡድኑን ለመሰናበት መልቀቂያ አላስገቡም። ይልቁንም የተዳከመ ቡድናቸውን ለማጠናከር በጀታቸውን በፍጥነት በማፍሰስ ተጫዋቾችን ለመግዛት ወደ 20 የሚሆኑ አፈላላጊዎችን አሰማርተዋል። ከሁለት ቀናት በኋላ የተጫዋች ዝውውር ማድረግ ስለማይቻል ቬንገር ቀኑ ሳያልፍባቸው እየተጣደፉ ይመስላል። «ጠንክረን እየሰራን ነው። በአሁኑ ወቅት በርካታ ተጫዋቾችን አናግረናል። እናስፈርማቸዋለን። ቡድናችንን የሚያጠናክሩ ከሆኑ ልናስፈርማቸው የሚያችለን በጀት አለን» ሲሉ ተደምጠዋል። አክለውም « አጥቂ ለማስፈረም ጫፍ ላይ ነን። ሆኖም አማካይና ተከላካይም ያስፈልገናል» ብለዋል 15 ዓመታት የቆዩበትን ቡድናቸውን ከጉድ ለማውጣት። ለጉድ የዳረጋቸው በአደባባይ ያሳጣቸው ቡድን ማንቸስተር አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርግሰን ደግሞ የሙያ አጋራቸውን ወጥረው የያዙት ተቺዎች ለቀቅ እንዲያደርጓቸው ጠይቀዋል። ፈርግሰን « እንደማስበው ትችቱ ፍትሀዊ አይደለም። ለዓመታት ለአርሰናል የሰራው፤ ፍልስፍናውን ጠብቆ ቡድኑ ድንቅ ተጫዋቾችን እንዲያፈራ አስችሏል። በተጫዋቾች ሽያጭም ለቡድኑ ከፍተኛ ገቢ ማስገኘቱን መርሳት ተገቢ አይደለም» ብለዋል።

Sport Leichtathletik Weltmeisterschaften Daegu Südkorea Usain Bolt Flash-Galerie

ዴጉ ደቡብ ኮሪያ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር

ከዋነኞቹ ተቀናቃኞች መካከል ቸልሲ ኖርዊችን 3 ለ 1 ረትቷል። የቸልሲ አጥቂ ዲዲየር ድሮግባ በደረሰበት ጉዳት ራሱን ስቶ ቆይቶ ሆስፒታል የገባ ሲሆን ራሱን እንዳወቀና እንደተሻለው ተዘግቧል። ሊቨርፑልም እንደዛው ቦልተን ወንደረርስን 3 ለ 1 አሰናብቷል። ሊቨርፑል በገዛቸው አዳዲስ ተጫዎቾቹ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ነው። ጆርዳን ሄንደርሰን፣ ማርቲን ስክሬትል እና ቻርሊ አዳም ናቸው ሊቨርፑል 3 ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ያስቻሉት። ሌኛው የቅርብ ጊዜው ሀያል ማንቸስተር ሲቲ ቶትንሀም ሆትስፑርን 5 ለ 1 በሆነ ሰፊ ልዩነት አሸንፏል።

በዚህም መሰረት ማንቸስተር ዩናይትድ እና ማነቸስተር ሲቲ በተመሳሳይ 9 ነጥብ እና በግብ ክፍያ ልዩነት የደረጃ ሰንጠረጁ ላይ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ተቀምጠዋል። ሊቨርፑል ሶስተኛ፣ ቸልሲ አራተኛ እንዲሁም ዎልቨርሀምፕተን አምስተኛ ደረጃን በተከታታይ ይዘዋል። ሁሉም ተመሳሳይ 7 ነጥብ ይዘው የሚለያዩት በግብ ልዩነት ነው። የፈረደበት አርሰናል ወራጅ ቀጣናውን ጫፍ ተጠግቶ 17ኛ ደረጃን ይዟል። በእርግጥ ቡድኖቹ ገና ሶስተኛ ውድድር ስለሆነ ያደረጉት ወደፊት የሚፈጠረውን ከወዲሁ መተንበይ አይቻልም።

እስካሁን በ6 ግቦች የማንቸስተር ሲቲው ጄኮ 1ኛ ግብ አግቢ ሲሆን፤ የማንቸስተር ዩናይትዱ ሩኒ በ5 ግቦች ይከተለዋል። ሌላኛው የማንቸስተር ሲቲ ተጫዋች አጉዌሮ እና የቦልተኑ ክላስኒች እያንዳንዳቸው 3 ግቦችን በማግባት በ3 ደረጃ ግብ አግቢነት ይገኛሉ። የሊቨርፑሉ ሱዋሬስ እና የማንቸስተር ሲቲው ሲልቫን ጨምሮ 6 ተጫዋቾች ሁለት ሁለት ግቦችን በማስቆጠር የ 4ኛ ደረጃ ግብ አግቢነትን ተቆጣጥረዋል።

አሁን አጫጭር ስፖርታዊ ዘገባዎችን እናስደምጣለን። በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ ሪያል ዛራጎዛን 6 ለ ባዶ በሆነ ውጤት እንደማይሆን አድርጎታል።የፈረንሳዩ ሊዮን ሞንፐሊየን 2 ለ 1 አሸንፏል።

ቴኒስ በሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ሰርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች አሁንም አንደኝነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ስፔናዊው ራፋኤል ናድል ከዓለም አስሩ ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተወዳዳሪዎች ሁለተኛ ሲሆን፤ ስዊዘርላንዳዊው ሮጀር ፌደረር ሶስተኛ ሆኗል። ሙዚቃ፦ አድማጮች የዕለቱ የስፖርት ዘገባችን በዚህ ይጠናቀቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ ነኝ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic